Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስደትና ጣጣው!

ሰላም! ሰላም! ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ‘ብዙ ተባዙ አዲስ አበባንም ሙሉዋት’ ነው እንዴ የተባለው?›› እያልኩ ባሻዬን ሳስቃቸው ሰነበትኩ። ኑሮ ተወደደ እንላለን ለካስ ሰው በዝቶ ነው? ረክሶ ነው ለማለት አፌን ይከብደዋል፡፡ ምንም እንኳን ሌሎች ቢሉትም፡፡ የዛሬን አያድርገውና ሰው ብርቅ በነበረበት ዘመን የኖሩት እነባሻዬ ከመንገድ አንድ የሚያውቁት ሰው ሲያገኙ እንዴት ተፍነክንከው እንደሚጠመጠሙበት ሲያስታውሱ እንባ እንባ ይላቸዋል። አለላችሁ አይደል የዛሬው ‹‹ኤጭ! መጣ ደግሞ ይኼ…›› ብለን ሳንጨርስ በጀርባችን ሌላው ቀድሞት ኖሮ፣ ‹‹ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ፤›› ብሎን ቁጭ። ይገርማችኋል ከመብዛታችን የተነሳ ቤት እንኳ የምንሠራው ተደራጅተን ያውም ወደ ላይ ሆኗል። አንድ ወዳጄ ይኼን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ነገር ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር አያይዤ ሳነሳበት፣ ‹‹እኔስ የባቢሎን ግንብ ጉዳይ ተመልሶ ሳይመጣ አልቀረም ባይ ነኝ፤›› ይለኛል። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹አንተ የምታየው የዛሬን ብቻ ነው። የሕዝብ ቁጥር እኮ ከትውልድ ትውልድ የሚጨምረው በእጥፍ ነው። በፊት በአራት ፎቅ የሚሠራው የጋራ መኖሪያ 8፣ 16፣ 32 እያለ መቀጠሉ መቼ ይቀራል?›› ይለኛል። እሱ እንዲህ ሲያወራኝ እኔ የማስበው ስለ ‘ፕራይቬሲ’ እና ስለ ‘ፕራይቬት ፕሮፐርቲ’ ነው። ከኢንተርኔት እስከ መሬት የራስ ብለን የምንተማመንበት ጥሪት ብሎም አካውንት እየተነፈግን እንዴት እንዘልቀው ይሆን? ተነስተን የምንወድቅለት ሁሉ የ ‘ሊዝና የፌዝ’ እየሆነ ሞራላችንን ባይገለው ምን ነበረበት?  ‘እናት መሬት’ መግባን ያልጠገብነው አልበቃን ብሎ ኑሯችን በቆጥ ላይ ቆጥ እየሆነ ሲሄድ ወደየት ይሆን መሸሸጊያው? ምስጢር በርባሪው፣ ይዞታ ነጣቂውና ስውር ቀማኛ በበዛበት ዓለም መኖር እየሰለቸኝ አልጋዬ ላይ ስገላበጥ የማንጠግቦሽ ድምፅ ከደጅ ጮክ ብሎ ይሰማል። ‘ነጋ ደግሞ ጎህ ቀደደ አዲስ ተስፋ ተወለደ’ ያለው ገጣሚ ትዝ እያለኝ ካልጋዬ ዱብ ብዬ ወረድኩ። መቼም ተስፋ ባይኖር ምን እንሆን ነበር ግን?

 ጣጣዬን ጨራርሼ ከቤት ስወጣ የእኔዋ ማንጠግቦሽ ከአንድ ነዝናዛ ጎረቤታችን ጋር ወገቧን ይዛ ታስነካዋለች። ‹‹ኧረ ምንድን ነው?›› ብዬ ብጠይቅ ማንጠግቦሽ ላይ የቀረበው ክስ በጦር ጠማኝ ጎረቤታችን አንደበት ተብራራልኝ። ክሱን ስሰማ በአገሪቱ በሕግ የሚያላግጠው ሰው ቁጥር ከኢኮኖሚ አኃዙ በላይ እንዳየለ ገባኝ። ክሱ ምን መሰላችሁ? ውዷ ማንጠግበሽ መቼም ለቤቷ ታታሪ ሠራተኛ ነች። የሙያዋን ጉዳይ ደጋግሜ የነገርኳችሁ ስለሆነ አሁን ስለሱ ምንም ማለት አልፈለግም። ታዲያላችሁ ጓዳዋ ተቀምጣ የምታነጥረው ቅቤ ሽታው ጎረቤት ዘምቶ አምሮት ቀስቅሶ ኖሯል። ‹‹ጉድ አፍልቷል አትለኝም?›› ያለኝ ኋላ ላይ ተገናኝተን የነገርኩት የባሻዬ ልጅ ነው። ‘ብበላ ብበላ አልጠረቃም ምነው እንዲያው፣ ይኼ ሆዴ ምን ነገር አምሮት ነው?’ ሆነና ጉዳዩ ጎረቤታችን፣ ‹‹ቅቤ ማንጠሩን አንጥሪ ሽታውን መቆጣጠር ግን ግዴታሽ ነው›› ብላ ማንጠግቦሽን ሰቅዛ ያዘቻት። ይኼ የኑሮ ውድነት የት ያደርሰን ይሆን? ‘ከጎረቤት ምቀኛ ከባልቴት ቀማኛ ይሰውራችሁ’ ብዬ ልለፈው እንጂ ስንቱ የፍሳሽና መፀዳጃ ቤት ቱቦ ሽታ 12 ወራት ሙሉ ጉንፋን በጉንፋን እያደረገን ቅቤ ሸተተኝ ተብሎ ቡራ ከረዩ የሚያስኬድ አልመሰለኝም። ያው የኑሮ ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ፡፡ በድምፅ፣ በመኪና ጭስ፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ብክለት አገሩ እየታመሰ ኪሎው ከ100 ብር በላይ የሆነው ቅቤ ሽታ አገር ያምስ? በኋላማ ቢጨንቀኝ ማንጠግቦሽን ጠጋ አልኩና፣ ‹‹በቃ ምን ቸገረሽ ምሳ ሲደርስ ጠርተሽ አቅምሻቸው! ወደው መሰለሽ? ግድ የለሽም ለእኔ ስትይ፤›› ስል ለመንኳት። እግዜር ይስጣት እሷም ተለምናኝ እንዳልኳት ማድረጓን በሌሊት የልፊያ ጨዋታችን መሀል አበሰረችኝ። ‘መልካም ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት’ ልበል ወይስ ተቀይሯል? ምን እኮ እውነታው ላይቀየር ሥርዓትና ቋንቋው እየተለዋወጠ አስቸገረን እኮ፡፡

እናላችሁ ገና ከደጅ ብቅ ከማለቴ ስልኮቼ ይንጫጩ ጀመር። የደላላ ስልክ ብዛቱን መናገር ቀባሪን ማርዳት ነው። አንዱን ስለው አንዱ አንዱን ከቀልቤ ሆኘ ሳላናገር ሌላው ጥልቅ እያለ ድንግርግር አለኝ። አታስዋሹኝና ‘በኔትወርኩ’ መገኘት ደስታው ፈንቅሎ ሊጥለኝ ነበር። በዚህ ዓይነትማ እንደ ገዢው ፓርቲ ዕቅድ አገራችን በቅርብ ዓመታት ልታሳካው ከምትባዝንለት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሠለፍ ጎን ለጎን መሠረተ ልማቱም በሁለት እግሩ ከቆመ እውነትም ተሃድሶ ሆነ ማለት ነው። ዳሩ የእኛ አገር ዕድገት እንደ ገመድ ጉተታ ከዚያ ሲስቡት ወዲህ ያለውን እያሽቆለቆለ አስቸግሯል። ከሚቀርቡልኝ የሥራ ዕድሎች አንዱን መርጬ ጊዜዬን መሰዋት ነበረብኝ። ለስንምት ወራት የሚከራይ ‘ገስት ሃውስ’ አስስ ስባል ግን ሳላመነታ ሩጫ ጀመርኩ። ያላደለው ያልፍልኛል ብሎ የሰው አገር ሄዶ እየተደበደበ ‘ተጠርዞ’ ይመለሳል ያደለው እንዲህ ዶላር ጠርዞ መጥቶ ‘ገስት ሃውስ’ ስምንት ወራት ይንፈላሰላል። ወጪውን አስባችሁታል? ሌላው ቢቀር ለፋብሪካ የሚሆን ቦታ ዙሪያውን አጥር ማጠሪያ መሆን ይችላል። ዳሩ የእኛ ሰው ወላ ካሜሪካ ወላ ከዱባይ በሰላም አሊያም በፀብ ተመልሶ ሲመጣ ባጠራቀማት ረብጣ ትከሻውን ማክበድ እንጂ ለአገር የሚበጅ ሥራ ማሰብ ሲያልፍም አይነካው። ታዲያ አገራችን ኢትዮጵያ በጥቂቶች ራዕይ በብዙኃኑ ስለራስ ብቻ እያሰቡ ኑሮ እንዴት ብላ ነው የምዕተ ዓመቱን ግብ የምትመታው? አትሉልኝም። ወዲያው ዋኖቻችን እንኳ ከስንት አንዴ የማይቆረቁራቸውን ጉዳይ እኔ ሥራ ፈትቼ እያሰብኩት መሆኑ ሲገባኝ ወደ ሥራዬ ሮጥኩ። አጥብቆ መጠየቅና መመርመር ‘ቻፓ’ ከማስመለጥ ውጪ ምንም አልፈይድ አለ። የቸገረ ነገር!

የተባልኩትን ዓይነት ቤት ሦስት ሰንጋ በሬ በሚገዛ ዋጋ እንዳገኘሁ ለደንበኞቼ ደውዬ ነገርኩ። አንድ ሰንጋ በሬ እስከ 60 ሺሕ ብር የሚሸጥበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ‘ገስት ሃውሱን’ ለማየት እንደ ቸኮሉና እዚያው ያለሁበት ሆኜ እንድጠብቃቸው ነግረውኝ መምጣት ጀመሩ። እነሱን እየጠበቅኩ በአንድ በኩል የእንግዳ ማረፊያው ቤት (ምንም እንኳ እስከእነ ሙሉ የቤት ዕቃው ቢሆንም) ይከራያል የተባለበትን ዋጋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በበሬ ከማረስ ያልተላቀቀው ምስኪኑ ገበሬ ሥቃይ ለምን እንደሆነ ሳላውቅ ተዛምዶ ያስጨንቀኝ ጀመር። ቆይቼ ሌላ የማዋየው ሰው የለኝምና የባሻን ልጅ ስነግረው፣ ‹‹ሞኝ! ዕድሜ ለለውጡ መንግሥታችን። ዛሬ ገበሬው ሁሉ ሀብታም ሆኖ መስሎኝ? ምነው አንበርብር ጤፍ የምንሸምትበትን ዋጋ ረሳኸው?›› ብሎኛል። ወይ ከተሜና ገጠሬ! እንዳመሉ ኑሮ እንደ ወንዙ ጉዞ የሰው ልጅ የተካነበት ባህሪው ነው። ቆላና ደጋ የማይግባቡበትን ሁሉ እያቻቻለና እያግባባ ይህ ጉደኛ ምድር ችሎናል። እንዲህ ተመስጬ ሳለሁ መሬቱ እስኪንቀጠቀጥ አቧራው እስኪጎን ከፍተኛ ፍንዳታ ሰማሁ። ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ደገመ። ‹‹አለቅን ዛሬ! ወይኔ ሳይደላኝ! ወይኔ ጠላቴን ሳላፍረው! ወይኔ ዘለዓለም የሰው እጅ እንዳየሁ!›› ምን ያላልነው አለ? ብቻ ሰው ሁሉ በራሱ ዙሪያ በሆኑ ነገሮች ቁጭቱን እየገለፀ ይጯጯህ ነበር። ምንም ተባለ ምን ይህቺን አገር እለውጣታለሁ በማለት እየታገለ ያለው መንግሥታችን እኔ የሰማሁትን ቢሰማ ይደነግጥ ነበር፡፡ ‹‹እንዴት የአገሬን መጨረሻ ሳላይ የሚል አንድ ሰው ይጠፋል?›› ብዬ ባሻዬን ስለሁኔታው ነግሬያቸው ሳበቃ ጥያቄ ባቀርብላቸው፣ ‹‹አንተ ደግሞ ታበዛዋለህ። አገር እኮ የምትኖረው መጀመሪያ እኛ በሕይወት ስንኖር ነው። ይኼን አጣኸውና ነው?›› አሉኝ። ኋላ የፈነዳው የከባድ መኪና ጎማ መሆኑን ስነግራቸው ከት ብለው እየሳቁ እንዲህ ነበር ያሉት። ‹‹እንኳንም ቴዎድሮስ አሸለበ! እንኳንም ምንሊክ አንቀላፋ!›› አሉ፡፡ ‘ቴረሪዝም’ በሌለበት ዘመን የነበረ ጀግና ዓለም ራሷ ‘ቴረር’ በሆነችበት ዘመን ከሚኖረው ሰው ጋር አንድ እንደሆነ ሁሉ፡፡

በሉ እንሰነባበት። ሀብታም ያውም በዶላር ኪሱ ያበጠ ሲከፍል ዓይን የለውም። ያልኳችሁን ቤት ያለምንም ክርክር በቅድሚያ ከፍለው ደንበኞቼ የኪራይ ውሉን ተፈራረሙ። እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት ጊዜ አልነበረኝም። ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሰዓት ደርሶ ነበርና ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ ከነፍኩ። ግሮሰሪያችን ጢቅ ብላ ሞልታለች። የባሻዬ ልጅ ከሩቅ አይቶኝ ኖሮ ጠራኝና ከያዘልኝ ቦታ ላይ ጉብ አልኩ። ‹‹አንበርብር ዛሬ ይለይልናል!›› አለኝ ከቢራው ጎንጨት እያደረገ። ይኼን ጊዜ አብሮት የተማረ የብዙ ዘመን ወዳጁ፣ ‹‹ይለይላቸዋል ብለህ አስተካክለው። እኛ ከለየልን ቆይተናል!›› ሲል ተናገረ። የባሻዬ ልጅ ደነገጠ። ‹‹እንዲህ ባለው ሰዓት እኛና እነሱን ምን ለያየንና?›› ሲል ኮስተር ብሎ ጠየቀው። ‹‹ኳሷ!›› አለ ጮሌነት የሚታይበት አስተያየቱን ጠበብ እያደረገ። ቀጠለና፣ ‹‹እነሱና እኛ ጨዋታውን የምንጫወትበት ኳስ አንድ መሰለህ? እኛ የምንጫወተው ዓለም በምትባል ሜዳ፣ ሕይወት በምትባል ኳስ ነፍስ አስይዘን ነው። እንደነሱ ‘ፌር ፕለይ’ ብሎ ነገር የማያውቀው ጨዋታ፤›› ብሎ ሲነካካለት የባሻዬ ልጅ ገባው። ነገርን ነገር ስላነሳው የባሻዬ ልጅ በተራው፣ ‹‹ካነሳኸው ላይቀር በደንብ እናውራው። የእኛና የእነሱ ጨዋታ አንተ ባልከው መንገድ ከሆነ የት ተገናኝቶ? የዛሬ ዘመን ሰው ሐሳቡ ሁሉ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው። እንዴት እንደሚያገኘው በጥልቀት ማሰብ ትቷል። እነሱ ቢሸነፉ ቢያንስ  ሞክረው ነው። እኛ በሕይወት መድረክ ላይ ስንረታ ሰው የመሆንን ትርጉም ረስተን ለዛ ያለው ኑሮ ርቆን ነው። ይኼው ሌብነት፣ ስግብግብነት፣ ምቀኝነት፣ አስመሳይነት የተሸነፈው ኑሯችን ውጤት ናቸው፤›› ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። የባሻዬ ልጅ ተናግሮ ሲጨርስ ጨዋታው እየጀመረ ነበር። ያለፈው ሁሉ ቢያልፍም መጪው ጊዜ ሁሌም አዲስ ነው። ድል የናፈቀው ደጋፊ ዓይኑን የቴሌቪዥን ‘ስክሪኑ’ ላይ ጥዷል። ጉጉትና ድል ሲፋጠጡ ያስፈነድቃሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በስደት ዓለም መከራቸውን እየበሉ ያሉ ወገኖቻችን ጉዳይ ሲታሰበን እንባ እንባ ይለናል፡፡ ስደትና ጣጣው የሐበሻን ናላ እስከ መቼ ያዞራል? ሕገወጥ ስደት የሚያስከትለው አደጋ ታስቦበት መፍትሔ ካልተበጀ ብዙ ዋጋ ያስፍላል፡፡ ስደትና ጣጣው ይታሰብበት፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት