Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጊፋታ ስንቁና ትሩፋቱ

ጊፋታ ስንቁና ትሩፋቱ

ቀን:

ትዳር በባልና ሚስት መካከል ያለው የግንኙነት ሚዛን የሚጠበቅበት ትስስር ነው፡፡ ትዳር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በመባባል ባሎች ለሚስቶቻቸው የሚኖሩበት እንዲሁም ሚስቶች ለባሎቻቸው አለሁ የሚሉበትም ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን እንኳን ሁለት ሰዎች ይቅርና እግርና እግርም ይጋጫል እንደሚባለው በትዳር ላይ ግጭት አይጠፋም፡፡

በወላይታ ላይ የሆነውም ይህ ነው፡፡ በ1970 ዓ.ም. እንደተጋቡ የሚናገሩት ወ/ሮ ዘነበች ገለቶና አቶ በቀለ ባልቻ እንደልማዱ በጠለፋ የተዋሀዱ ናቸው፡፡ የወ/ሮ ዘነበች ጓደኛ እንዲሁም የአቶ በቀለ እህት የሆኑት ወ/ሮ በላይ ባልቻ፣ ለጥልፊያ ሁኔታውን እንዳመቻቹት፣ ይህም የሆነው ወ/ሮ ዘነበችን በመውደዳቸውና ከቤተሰቡ አንድ አካል እንዲሆኑ በመፈለጋቸው መሆኑን ያወሳሉ፡፡

የወንድማቸውን ጓደኞች በማሠማራትም እንዳስጠለፏቸውና ወ/ሮ ዘነበችም ከተጠለፉ በኋላ በሽማግሌ ሥርዓቱን ጠብቀው እንደተዳሩ ወ/ሮ በላይ ከዛሬ 42 ዓመት በፊት የሆነውን፤ ዛሬ ላይ እየተደረገ እስኪመስል ድረስ ነበር በሐሳብ ጭልጥ ብለው ያወጉን፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የሁለቱ ፍቅር ግን ከተጋቡ ከ23 ዓመት በኋላ ተበተነ፡፡ ሁሉም ጥፋት ያለው ወንድሜ ላይ ነው፡፡ እሷ ለእኛ በጣም ጥሩ ነበረች፤›› በማለት ሳግ ተናነቃቸው፡፡ በ1970 ዓ.ም. የተመሠረተው ትዳር በ1993 ዓ.ም. ፈረሰ፡፡ እንደ ወ/ሮ ዘነበች፣ ባልና ሚስት በንግድ ተሠማርተው በሚኖሩበት ወቅት ባል ቀድሞ ወደ ቤት ሲገባ፣ እሳቸው በመኪና ማጣት ምክንያት ከሳቸው ኋላ ይገባሉ፡፡ በዚህም ባል የቅናት መንፈስ እያደረባቸው ይመጣል፡፡ አንድ ሁለት ሲባባሉ ቅራኔ ተፈጠረ፡፡ በዚህም የተነሳ ትዳሩ ከ23 ዓመት በላይ መቀጠል አልቻለም፡፡

ጊፋታ ስንቁና ትሩፋቱ

 

ወ/ሮ ዘነበች ልጆቻቸውን እዛው በመተው ሌላ አካባቢ በመሄድ ኑሯቸውን ይጀምራሉ፡፡ ልጆቹ ታዳጊ ሕፃናት ነበሩና እናታቸውን ወደ ቤት መመለስ አልቻሉም፡፡ እንደ አቶ በቀለ ገለጻ ወ/ሮ ዘነበችን ወደ ቤት ለመመለስ ስምንቴ መሞከራቸውን ሆኖም እንዳልተሳካላቸው ነገር ግን ዘንድሮ የጊፋታን በዓል አስታኮ ታሪክ መለወጡን አስረድተዋል፡፡ ከ19 ዓመት ፍቺ በኋላ ጊፋታን አስመልክተው ሽማግሌዎች በሁለቱ መሀል ሽምግልና ቆሙ፡፡ ባለትዳሮቹም አላሳፈሯቸውም፤ እሺታቸውን ቸሯቸው፡፡

እኚህ ባለትዳሮች ከሁለት አሠርታት ያህል የመለያየት ቆይታ ሁለቱም አግብተው እያንዳንዳቸው አንድ ልጅ ሲወልዱ ወ/ሮ ዘነበች ከአዲሱ ትዳራቸው ወዲያው መፋታታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ዘነበች 19 ዓመት የፍቺ ጊዜ በሕይወታቸው ከባድ ጊዜ እንደነበረ፣ ነገር ግን ኑሮ አሸንፏቸው እንደማያውቅ ገልጸው፣ ‹‹ከልጆች ተለይቶ መኖር ምንም ያክል ከባድ ቢሆንም እየሠራሁ ለልጆቼ እናት መሆን ችያለሁ›› ብለዋል፡፡

አቶ በቀለ ከአዲሷ ሚስታቸው ጋር እስካሁን ያልተፋቱ ቢሆንም፣ በባህላቸው መሠረት ከአንድ በላይ ሚስት ቢኖራቸው ችግር ስለሌለው ወ/ሮ ዘነበች ተቻችሎ ለመኖር ፈቃደኛ መሆናቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጊፋታን ምክንያት በማድረግ ሽማግሌ ዕርቅ ጠይቆ እንቢ አይባልም፡፡ በዚህች በምንኖራት አጭር ዕድሜ ከፀብ ይልቅ ዕርቅ እንደሚሻልም ዕድሜ አስተምሮኛል፤›› ብለዋል፡፡

ከምንም ነገር በላይ በሽምግልና መታረቅ እንደሚያስመርቅ የገለጹት ወ/ሮ ዘነበች፣ ለቀጣይ ሕይወትም መሠረት እንደሆነና ምርቃቱ ስንቅ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁንም ድረስ እወደዋለሁ፣ ከዚህ በኋላም የሚያጣላንን ነገር በመቅረፍ ሰላማዊ ኑሮን ለመኖር ዝግጁ ነኝ፤›› በማለት ቀጣይ ምዕራፋቸውን ለማሳመር መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡

አቶ በቀለ በበኩላቸው፣ ‹‹ከዚህ ቀደምም ብዙ ሞክሬ እንቢ ያለችኝ እሷ ነች፣ አሁን ላይ ዕርቅ በመውረዱ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡ 1,000 ብር በማይሞላ ጥሎሽና ከ3,000 ብር ባልበለጠ ዘመድ አዝማድ በታደመበት የሠርግ ድግስ የተጀመረው ፍቅር ከ19 ዓመት በኋላ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡

እነዚህን ጥንዶች ያስታረቀው በዓመት አንዴ የሚመጣው የጊፋታ በዓልም ዘንድሮ በደማቁ ተከብሮ ውሏል፡፡ የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል፣ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ሲከበር የነበረ፣ በብሔሩ ዘንድ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረና ከብሔሩ ማንነት ጋር ትስስር ያለው ታላቅ ክብረ በዓል ነው፡፡ የወላይታ ብሔር ማንነት የሚገለጽባቸው በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሉት ሲሆን፣ ከብሔሩ የማይዳሰሱ ሀብቶች መካከል የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ይህ ክብረ በዓል በብሔሩ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ ነው፡፡ ጊፋታ ማለት (ባየራ) ታላቅ ወይም የመጀመርያ ማለት ነው፡፡

የወላይታ ብሔር አባላት የጨረቃን ዑደት በማስተዋልና በማሥላት ዘመን ይቆጥራሉ፡፡ ከመስከረም 14 እስከ 20 መካከል በሚውለው እሑድ ጠዋትም የጊፋታ በዓል ይከናወናል፡፡ በዚህ ቀንም ጠዋት ላይ ‹‹አሹዋ ዋጋ›› ወይም የጊፋታ ማብሰሪያ እርድ ይከናወናል፡፡ ጊፋታ ከ‹‹ሹሁሃ ዋጋ›› ጀምሮ ለቀጣይ 18 ቀናት ማለትም እስከ ‹‹ጎልዋ አቄታ›› ማለትም በዓሉን በይፋ ማሳረግ ሥርዓት ድረስ በምሥጋና፣ በመልካም ምኞት መግለጫና በምግብ፣ በአለባበስ፣ በአጋጌጥ እንዲሁም የዜማ ሥርዓቶች ታጅቦ ይከበራል፡፡

በዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት እንዲሁም የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ የመቻቻል፣ የይቅር ባይነትና የመተሳሰብ ተምሳሌት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ከዕዳ ነፃ ሆነው እንዲቀበሉትና ለብልፅግና ተግተው እንዲሠሩ የሚያበረታታ በዓል እንደሆነም ይነገራል፡፡ ከሁሉም በላይ ዓመቱን ሙሉ በሥራ የደከመ፣ የዛለና የተሰላቸ አካልና አዕምሮ የሚዝናናበት በዓልም ነው፡፡

‹‹ጊፋታ ሲመጣ ሰው አንድነቱን ያጠናክራል፣ ተጣልቶ የነበረ ሰው ይታረቃል፣ የይቅርታ ትልቁ እሴት ጊፋታ ውስጥ አለ፤›› ሲሉም የጊፋታን እሴቶች ለትውልድ ለማስተላለፍ ዕቅዳቸው እንደሆነ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳገቱ ኩምቢ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የጊፋታ በዓል አከባበር ላይ ሦስት መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ የመጀመርያው የቋንቋና የባህል ሲምፓዚየም ተካሂዷል፡፡ በዚህም የወላይታ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም የአመራር አካላት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ሁለተኛው የወይዘሪት ጊፋታ 2012 ዓ.ም. የቁንጅና ውድድር ሲሆን፣ የመጨረሻው “ለጊፋታ እንሮጣለን” በሚል የጊፋታ 2012 ዓ.ም. ታላቁ ሩጫ የተካሄደበት መርሐ ግብር ነበር፡፡ ሩጫው 3.5 ኪሎ ሜትር የሸፈነና ከ20,000 በላይ ተሳታፊዎች የሮጡበት ነበር፡፡

አቶ ፀጋዬ ስምዖን የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ኃላፊ፣ ዘንድሮ የወላይታ ሕዝብ የጊፋታን በዓል በሰፊው እንዳከበረ አውስተው፣ በዓሉ ከዘመን መለወጫነት ባሻገር ይዘቱ ለየት ያለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ ከአባወራ ጀምሮ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ልጃገረዶች እንዲሁም ሕፃናት ሁሉም የራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት አባቶች ልክ በዓሉ እንዳለቀ ለቀጣዩ ዓመት በዓል ተቀማጭ የዕርድ ዕቁብ ይጀምራሉ፡፡ ለጊፋታ የሚታረድ በሬም ሌላ ሥራ አይሠራም፡፡ በዓሉ እስኪደርስ ይቀለባል፡፡ በተመሳሳይ እናቶች የቅቤ ዕቁብ ይገባሉ፡፡ ወጣቶችም በዓሉ ከመድረሱ ከሦስት ወር በፊት የደመራ እንጨት ይሰበስባሉ፣ ለበዓሉ የሚሆን እንጨት ይፈልጣሉ፡፡ ልጃገረዶች እናቶቻቸውን ከማገዝ በተጨማሪ እንሾሽላን በመጠቀም ራሳቸውን ያስውባሉ፤ በዚህም መሠረት ዓመት በዓሉን ሁሉም በየፊናው በጉጉት ይጠብቀዋል፡፡

የምግብ ሥነ ሥርዓቱ አንዱ የጊፋታ በዓል መገለጫ ነው፡፡ እሑድ በዓሉ ሊሆን ከሐሙስ ጀምሮ ኮሴታ ሀሙሳ የሚሉት ምግብና መጠጥ ይዘጋጃል፡፡ ቅዳሜም ባጭራ ቅየሯ የሚል ስያሜ ያለው የተለያዩ የምግብ ፌስቲቫሎች ይካሄዳል፡፡ ይህ በየዓመቱ ጊፋታ ሲከበር የሚከናወን ተግባር ነው፡፡

አቶ ፀጋው፣ በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን፣ ከሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የቴክኒክ ቡድን መዋቀሩንና ዘንድሮ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለመሥራት መንገድ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥ ተፅዕኖ ላይ ወድቆ እንደነበር አውስተው፣ ለተከታታይ 12 ዓመታት ከዚህ ተፅዕኖ ሥር ለመውጣት ትልቅ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ የመስቀል በዓልን ከጊፋታ ጋር አንድ የማድረግ ነገር እንዳለ፣ ሆኖም ፍፁም እንደማይገናኙ፣ መስቀል ሃይማኖታዊ በዓል ሲሆን፣ ጊፋታ ባህላዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የጊፋታ አከባበር ላይ ከዘጠኙም ክልሎች የተወከሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል፡፡ ከበዓሉ ባሻገር የወላይታ ሕዝብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አለው፡፡ ይህ ሕዝብ የጨረቃ፣ የፀሐይ እንዲሁም የነፋስ እንቅስቃሴን በማየትና በማጥናት የተፈጥሯዊ ሥርዓቶችን እንቅስቃሴና ውጤት የመረዳት ዕውቀት አለው፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ፓኡዋ፣ ጡማ፣ ጤሯ እንዲሁም ሳባና በማለት ወቅቶችን ይከፍላል፡፡

ከወቅቶቹ በተጨማሪም የራሱ የሆነ የቀናት፣ ሳምንታትና ወራት አቆጣጠር ሥልት አለው፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ሙሉ ቀን “ኢሲ ወንታ” በማለት ሲጠሩት፣ ሰባቱን ቀናት ናኡ ዎንታ፣ ሄዙ ዎንታ፣ ኦይዱ ዎንታ፣ ኢቺቻሹ ዎንታ፣ ሀስፑን ዎንታ እንዲሁም ናኡ ጊያ ሁለት የገበያ ቀን እንደማለት ነው በማለት ይጠሩታል፡፡

ወላይታዎች ሳምንታትን የሚቆጥሩት በአካባቢያቸው የሚውለውን ትልቅ ገበያ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ናኡ ጊያ፣ ሄዙ ጊያ፣ አይዳ ጊያ እንዲሁም ኢቺቻሹ ጊያ በማለት አራቱን ሳምንታት ከቆጠሩ በኋላ ኢሲ አጊና ይላሉ፡፡ ይህም አንድ ጨረቃ እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ 12 ጨረቃዎችን ከቆጠሩ በኋላ ኢሲ ላይታ ይላሉ፡፡ ይህም አንድ ዓመት ማለት ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ አሮጌው ዓመት አልቆ አዲስ ዓመት የሚጀምርበትን ቀን ለይተው በማወቅ በአዲሱ ዓመት በመጀመርያ ወር፣ በወሩም የመጀመርያው ቀን የዘመን መለወጫ በዓላቸውን ያከብራሉ፡፡

የቤት አሠራር

ከዘመን አቆጣጠር ባሻገር የወላይታ ሕዝብ በቤት አሠራራቸው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በራሳቸው አገር በቀል ምህንድስና ዕውቀቶች በመመራት የሚሠሯቸው አራት የቤት አሠራር ጥበቦች አሏቸው፡፡ እነርሱም ዙፋ ኬታ፣ ሜሹዋ፣ ጉላንታና ቡራሪያ ይባላሉ፡፡

ዙፋ ኬታ የሚባለው የቤት አሠራር በጥራትና በጥንካሬ በመጀመርያ ደረጃ ሲመደብ፣ በግማሽ ጨረቃ ቅርፅ ሆኖ ከታች ከወለሉ ጀምሮ እስከ ጣሪያው ማዋቀሪያ ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ በሐረግ ይማገራል፡፡ የሰንበሌጥ ክዳኑ ግን ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ ቅርፅ አለው፡፡ ሁለተኛው ሜሹዋ የሚባለው የቤት አሠራር ሲሆን፣ በጥራትና በጥንካሬ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደብ ነው፡፡ አመጋገሩም ከታች እስከ ላይ ጣሪያ ውቅር ድረስ ጥቅጥቅ ተደርጎ የሚሠራ ነው፡፡

ግድግዳው በወፍራም ፍልጥ እንጨትና ወራጅ የሚሠራ ሲሆን ውስጣዊ አመጋገሩ ሰንሰለታማ ዛጎል አስተሳሰር ሥልትን በመከተል ከላይ እስከ ታች መሬት ድረስ በቀጥታ መስመር ይወርዳል፡፡

ጉላንታ የሚባለው የቤት አሠራር ሦስተኛ ደረጃ የሚሰጠው የቤት ዓይነት ነው፡፡ ይህ አሠራር ከውስጥ በኩል አመጋገሩ በዘጠኝ ዙር ክፍተት የሚሠራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዙር ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ዙር ያህል ጥቅጥቅ ያለ ማገር ይዞርበታል፡፡

ከየጉላንታው መሀል በግምት ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ካሬ ሜትር ያህል ክፍተት ይኖረዋል፡፡ ከአንዱ መዋቅር ከሌላው መዋቅር መሀል ሞጋ የሚባል ከቀጫጭን የማገር እንጨቶችና ከነጭ ወፊቾ ተጠምጥሞ የሚሠራ ጌጥ እንደ አምባር ዙሪያው ላይ ይታሰርበታል፡፡ የመጨረሻው የቤት አሠራር ቡራሪያ የሚባለው የጎጆ ቤት ዓይነት ነው፡፡ ይህ ማንኛውም ሰው አቅም የሌለውም ቢሆን ሊሠራው የሚችለው የቤት ዓይነት ነው፡፡ በማንኛውም አካባቢ በሚገኝ የግድግዳ እንጨት ወይም ወራጅና አጠና እንዲሁም ደግሞ ከቀርከሃና ከሽምበቆ ሊሠራ ይችላል፡፡

የመከላከያ ካብ

ከወላይታ ጋር አብሮ የሚነሳው የመከላከያ ካቡ ነው፡፡ ካቡ ከ1767 ዓ.ም. እስከ 1807 ዓ.ም. በወላይታ እንደነገሡ በሚነገርላቸው በንጉሥ አማዶ ዘመን እንደተገነባ ይነገራል፡፡ ከዱጉና ፋንጎ ተነስቶ ሁምቦ፣ ኦፋ፣ ኪንዶ ዲዳዬን፣ ኪንዶ ኮይሳን እንዲሁም ቦሎሶ ቦንቤ ወረዳዎችን የሚካፈለው የንጉሥ አማዶ የመከላከያ ካብ (Keelaa) ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በኪንዶ ኮይሻ የሚገኘው ካብ በጊዜው የድንበር ገዢ በነበሩት አኮ ኢጃጆ አስተባባሪነት እንደተሠራ ይነገራል፡፡

የዚህ ካብ ቁመት በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ሲሆን፣ ካቡን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከ17 እስከ 20 ዓመት እንደፈጀ ይገመታል፡፡ የድንጋይ ካቡ የሕዝቡ ጠንካራ ሠራተኛ፣ ለጋራ ጥቅም ሲባል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ፣ ፅናትና የአገር ፍቅር ስሜት ያለው መሆኑን በተግባር ያሳየበት፣ የጥንካሬ መገለጫው ህያው ቅርስ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...