Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተገነባው አንድነት ፓርክ በቀን 1,500 ጎብኚዎችን ያስተናግዳል

  በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተገነባው አንድነት ፓርክ በቀን 1,500 ጎብኚዎችን ያስተናግዳል

  ቀን:

  የተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች በተገኙበት መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የታላቁ ቤተ መንግሥት አንድነት ፓርክ በቀን 1,500 ጎብኚዎችን ያስተናግዳል፡፡

  በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዳብ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፋርማጆ)፣ እንዲሁም በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

  በተለያዩ ጊዜያት ዕድሳት ሲደረጉላቸው ቢቆዩም ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት ሳይሆኑ የቆዩ ሰባት ታሪካዊና ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ሕንፃዎችን ጨምሮ ስድስት መስህቦችን የያዘው አንድነት ፓርክ፣ ለመደበኛ የመጎብኛ ክፍያ 200 ብር፣ ለልዩ የመጎብኛ ክፍያ (ቪአይፒ) ደግሞ 1,000 ብር ይጠይቃል፡፡ የውጭ ዜጎች ለመደበኛ የመጎብኛ ክፍያ 20 ዶላር፣ ለልዩ የመጎብኛ ክፍያ ደግሞ 50 ዶላር እንደሚጠየቁ ታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያን ሎጎና አሳዛኝ ታሪካችን በአንድ ላይ ለማየትና ለመረዳት ያስችላል የተባለው ይህ ፓርክ፣ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አንስቶ እስከ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመነ መንግሥት ድረስ የተሠሩ ሥራዎች በዓውደ ርዕይ ቀርበውበታል፡፡ ሕንፃዎቹን ጨምሮ በዓውደ ርዕይነት የቀረበው ይህ ታሪካዊ ሥፍራ የፓርኩ ዋና መስህብ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የአንድነት ፓርክ ግቢ የ130 ዓመታት ታሪክ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡

  ስድስት የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈውበት የተገነባው ይህ ፓርክ፣ በውስጡ የተለያዩ እንስሳት ማሳያ፣ የባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ ዋሻ፣ የአገር በቀል ዕፅዋት ማሳያና የዘጠኙ እልቂት እልፍ ቆዳን በመስህብነት ይዟል፡፡ በግቢው ለተሠራው የአረንጓዴ ሥፍራና የመሬት አቀማመጥ ማስተካከያ ስድስት ሺሕ የጭነት መኪና አፈር ጥቅም ላይ መዋሉ ተነግሯል፡፡

  ፓርኩ ከመከፈቱ ቀደም ብሎ የመጎብኘት ዕድል የነበራቸው የተለያዩ ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ለአብነትም ህል በአገሪቱ ረዥም ታሪክ እንዳለውና ከቀደምት ታክሲዎች ለማሳያ ቢቀመጥ በሚል በታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር በተሰጠ አስተያየት የዳግማዊ ምኒልክ ሦስተኛ መኪና ለዕይታ እንድትቀርብ መደረጉ ተጠቁመዋል፡፡ ሆኖም የዳግማዊ ምኒልክ ቤንትሌይ መኪና ሊገኝ እንዳልተቻለ ተነግሯል፡፡

  ፓርኩን ለመጎብኘት የሚቻለው ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለክፍያ የተዘጋጁ አራቱም መንገዶች ከወረቀት ገንዘብ ንክኪ ውጪ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሰዎች ወደ 6030 የጽሑፍ መልዕክት በመላክ፣ በአንድነት ፓርክ ድረ ገጽ (Unitypark.et) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ የፓርኩ የሒሳብ ቁጥር አሊያም የፓርኩ በር ላይ በፓስ ማሽን ካርድ ተጠቅሞ መክፈል ብቻ ነው የሚቻለው፡፡

  በተያያዘ እጅ ምሥል የአፍሪካ ካርታን ምልክቱ ያደረገው ይህ ፓርክ፣ የአፍሪካን ሰላም እንዲገልጽ ተደርጎ እንደተሠራ ተገልጿል፡፡ በፓርኩ ግቢ ለጉብኝት የገባ ሰው በጉብኝቱ ላይ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ አልተበጀለትም፡፡

  የአንድነት ፓርክ ስያሜ ከመደመር እሳቤ አንፃር ተሰጠ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ከቋሚና አግድም አንድነት ያሳያልም ተብሏል፡፡ ቋሚ አንድነት አገሪቱ የመጣችበት ታሪክ እንደሆነና አግድም አንድነቱ ደግሞ ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለን አንድነት ያሳያል ተብሏል፡፡

  ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ስድስቱም መስህቦች ሥራ ሲጀምሩ ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፣ ፓርኩ ዕውን እንዲሆን ከሠራተኞች ጥረት በዘለለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀን ሦስቴ ሲደረግ የነበረው ጥብቅ ክትትል ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img