Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰላማዊ ሠልፉ ስለአዲስ አበባ ወይም ባልደራሱ ሳይሆን ስለአገር ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ሰላማዊ ሠልፉ ስለአዲስ አበባ ወይም ባልደራሱ ሳይሆን ስለአገር ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ሠልፉ ከተከለከለ ወደ መጨረሻው አማራጭ ‹‹እንቢተኝነት›› ይኬዳል ተብሏል

ራሱን የ‹‹አዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት›› በማለት የሚጠራው የሰላማዊ ሠልፍ አደራጅ ኮሚቴ፣ ለዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ስለአንድ ከተማ አዲስ አበባ ወይም ባልደራሱ ጉዳይ ሳይሆን፣ ስለአገር መሆኑን የሠልፉ አደራጆች ገለጹ፡፡

የሠልፉ አደራጆች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፊት ለፊት 50 ሜትር ገባ ብሎ በሚገኘው ጌጅ ኮሌጅ ባለበት ሕንፃ አንደኛ ፎቅ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፣ ሰላማዊ ሠልፉ ስለታፈኑት የዴሞክራሲ መብቶች ተቃውሞ ለማሰማት ነው፡፡ ስለአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራሱ) ወይም ስለአዲስ አበባ ከተማ አይደለም፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ድምፅን ለማሰማት ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ስለአዲስ አበባ ብቻ ከሆነ ሕዝቡ ሠልፍ መውጣት እንደሌለበት አስረድቷል፡፡

በአገሪቱ ሰላምና አንድነት ላይ ትልቅ አደጋ ማንዣበቡን የጠቆመው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ የፈነጠቀውን የዴሞክራሲ ተስፋ ታሳቢ አድርገው፣ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪል ተቋማትና ዜጎች፣ የተለያዩ ተግዳሮቶችና የመብት አፈናዎች እንደደረሰባቸው ተናግሯል፡፡ በመሆኑም በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የሚገኘው ሕዝብ፣ የአገሩ ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ እያሳሰበና እያሠጋ በመምጣቱ፣ ባለአደራ ምክር ቤቱ በሕዝብ የተሰጠውን አደራ በማክበር፣ ለዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ መጥራቱን አብራርቷል፡፡ ሰላማዊ ሠልፉ ዋና ዋና ስድስት ዓላማዎች እንዳሉትም አክሏል፡፡

ብዙ ሕዝብ ዋጋ የከፈለባቸው የዴሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄዎች፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥና ከገዥው ፓርቲ ውጪ ባሉ ጽንፈኞች እየደረሰባቸው ያለውን አፈና መቃወምና የገዥውም ፓርቲ አካሄድ በአፋጣኝ እንዲስተካከል ማሳሰብ የመጀመርያው ዓላማ መሆኑን ጋዜጠኛ እስክንድር ገልጿል፡፡ በሐሳባቸውና በፖለቲካ ልዩነታቸው ምክንያት ብቻ በአስፈጻሚው አካልና በሕግ ተርጓሚው ትዕዛዝ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በአዲስ አበባ ታስረው የሚገኙ የህሊና እስረኞች፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁም ለመጠየቅ መሆኑን አክሏል፡፡ ምክር ቤቱ በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው የሰላማዊ ሠልፉ ዓላማ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሕገወጥ እንደሆነ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 654/2001 በአስቸኳይ እንዲሰረዝም መሆኑን ገልጿል፡፡ መንግሥት ጽንፈኛ ኃይሎችና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሃማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው፣ እንዲሁም መንግሥት ለሁሉም ሃይማኖቶችና ቤተ እምነቶች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግም ለማሳሰብ መሆኑን አብራርቷል፡፡ በመጨረሻ የሠልፉ ዓላማ እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ‹‹ልዩ መብትና ጥቅም አለን›› በሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተካሄደ ያለውን የመብት ጥሰት ለመቃወምና መላው ኢትዮጵያውያን እኩል መብት ያላቸው መሆኑን ለማሳሰብ ሰላማዊ ሠልፉ አስፈላጊ መሆኑን አስረድቷል፡፡

መንግሥት የሰላማዊ ሠልፉን ዓላማ ተረድቶ ስለዴሞክራሲና ሽግግሩ መሥራት ከጀመረ ደስ እያላቸው በቀጣይ ስለምርጫው እንደሚሠሩም ጋዜጠኛ እስክንድር አውስቷል፡፡ ባለአደራ ምክር ቤቱ ሕዝብ እንዲያነቁና እንዲያደራጁ ተልዕኮ እንደሰጣቸው ጠቁሞ፣ ያንን ለማድረግ ባለመቻላቸው ሁሉንም ዓይነት ትግል እያደረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ሰላማዊ ሠልፉ በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የእምነት አባቶች፣ የባህል መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ መንግሥትን በመገሰጽና ወጣቱን በመምከር ትውልዳዊ አደራቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሰላማዊ ሠልፉ ተሳታፊዎችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በቀጥታ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲያመሩ፣ የሰላማዊ ሠልፉ ዓላማ ከግቡ የሚደርሰው ሰላማዊ መንገድን በመከተል ሲቻል ብቻ መሆኑን ጠቁሞ፣ ማንኛውንም ሐሳብን የመግለጽ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያዊነትን በተከተለ መንገድና በሠለጠነ አግባብ እንዲሆን አሳስቧል፡፡

ሰላማዊ ሠልፉ የተለየ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ቋንቋና እምነት ያላቸውን እህት ወንድም ኢትዮጵያውያንን ከማብሸቅ፣ ለፀብ ከመጋበዝና ለፉክክር በማይጠራ መልኩ መደረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ሰላማዊ ስብሰባውን በማንኛውም ሁኔታ የሚያውክ ቢኖር መረጃ በመያዝ ለመገናኛ አካላትና ለፀጥታ አስከባሪዎች እንዲደርስ እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋጋ የከፈለበት የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ጥያቄዎቹ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ የሚጠየቅበት መሆኑን በመረዳት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ርዕዮት ዓለም ወይም የፖለቲካ መስመር መለያየት ሳይኖር፣ ሁሉም አንድ ላይ ሆነው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጠይቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም ሕዝባዊነታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ሕዝቡ ሐሳቡን የመግለጽ መብቱን በማይገድብ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ፣ የመገናኛ ብዙኃንም አግባብነት ያለው ዘገባ እንዲሠሩም ጠይቋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፉ ከአስተዳደሩ ይሁንታን ስለማግኘቱ ለጋዜጠኛ እስክንድር ለቀረበለት ጥያቄ እንደገጸለው፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ጽሕፈት ቤት መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ሕዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል፡፡ አስተዳደሩ ግን ምንም የሰጠው ምላሽ የለም፡፡ ይህ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 3/1983 አንቀጽ 6(1) መሠረት በ12 ሰዓታት ውስጥ ፀጥታን ከማስጠበቅና የሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ አንፃር የማይችል ከሆነ ለጠያቂው ማሳወቅ እንዳለበት ከመደንገጉ አንፃር፣ ያንን ባለማድረጉ ጥያቄያቸውን ፈቃድ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ (10) ድንጋጌ መሠረትም የፀጥታ አስከባሪዎች የሕዝብን መብት፣ ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት አንዳባቸው በመደንገጉ፣ ያንኑ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ጋዜጠኛ እስክንድር ገልጿል፡፡

ነገር ግን መንግሥት ወይም የከተማ አስተዳደሩ በባለአደራ ምክር ቤቱ ላይ ጥላቻ ስላለው፣ ሕዝቡ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ እንዲወጣ እንደማይፈልግ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የተጠለፈውን የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ለመታደግ፣ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ግድ ቢሆንም፣ መንግሥት ወይም የፀጥታ አካሉ በአደባባይ ወጥቶ ሰላማዊ ሠልፉን ማድረግ እንደማይቻል ከገለጹ፣ ጠብመንጃ ከያዘ አካል ጋር በባዶ እጁ ወጥቶ አንድም ሰው ጉዳት እንዲደርስበት ስለማፈልጉ፣ ሰላማዊ ሠልፉን እንደማያደርጉም ጋዜጠኛ እስክንድር ገልጿል፡፡

ነገር ግን ሰላማዊ ሠልፉ ታገደ ማለት ትግል ቆመ ማለት አለመሆኑንና በሳይንሳዊ መንገድ ሰላማዊ ትግል ሦስት ደረጃዎች እንዳሉት ጠቁሞ፣ ወደ መጨረሻው ደረጃ እንደሚሸጋገሩ ገልጿል፡፡ በሕዝብ ግንኙነት ደረጃ በጋዜጣዊ መግለጫ የመጀመርያው ትግልና በአደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ሁለተኛው ዓይነት የትግል ሥልት መሆኑን የጠቆመው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ እነዚህ ከተከለከሉ ሦስተኛውን ‹‹እንቢተኛነት›› ማለትም ወደ ሥራ ማቆምና ትምህርት ማቆም አድማ እንደሚሸጋገሩ አስታውቋል፡፡ ስለባልደራሱ ሕጋዊነት የተጠየቀው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ እንደ ማንኛውም ድርጅት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ ሰርተፍኬት እየጠበቀ ነው፡፡ ይኼን ያደረጉት ሕጋዊነት ለማግኘት ሳይሆን ለመመዝገብ መሆኑንና ፈቃድ ሰጪም ሆነ ነሺም ሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ፈቃድ የሚገኘው ከተፈጥሮ እንጂ ከመንግሥት አለመሆኑን፣ የሚያስገድድ ሕግም ባለመኖሩ አንድ ግለሰብም ሰላማዊ ሠልፍ መጥራት እንደሚቻል ገልጿል፡፡ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ግጭት ቢፈጠር ኃላፊነት ስለመውሰዳቸው ተጠይቀው፣ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ ግጭት ቢነሳ ኃላፊነት እንደማይወስዱ ገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርጉ ሲያሳውቁ፣ በዝምታ ውስጥ በመፈቀዱ መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰዱ እንደሆነ አብራርቷል፡፡

ምክር ቤቱ ሕጉን ጠብቆ ማሳወቁን አስታውሶ፣ አስተዳደሩም ሆነ መንግሥት ምንም ዓይነት ክልከላ እስካላደረገ ድረስ ኃላፊነቱ የመንግሥት መሆኑን አክሏል፡፡ በፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ ያላግባብ ታስረውብናል ስለሚሏቸው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላትና ሌሎች የህሊና እስረኞች በሚመለከት ምላሽ የሰጡት ደግሞ የምክር ቤቱ አባልና የሕግ ባለሙያው አቶ ሔኖክ አክሊሉ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደገለጹት፣ አባሎቻቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ በሰዓታት ልዩነት በተገደሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ ግድያውን በሚመለከት መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ሲል፣ ፖሊስ ደግሞ፣ ‹‹የሽብር ተግባር ነው›› በማለት፣ አባላቱን አስሯቸው እንደሚገኝና ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የነበረውን የፍትሕ አሰጣጥ ሒደት በመከተል፣ ፍትሕ የተራበውን ሕዝብ ፍትሕ እንዲያገኝ እያደረገው አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት በወንጀል ሕግ የተደነገገ ራሱን የቻለ ወንጀልና ቅጣት ያለው ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቶች ሁለቱን ሳይለዩ ወይም ምንም ሳይሉ እንዳስቀጠሉት አክለዋል፡፡ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ቢያመላክቱም፣ ምንም ፍትሕ ሳይሰጥ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫውን በሚሰጥበት ወቅት፣ ጥቂት ወጣቶች የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት፣ መግለጫው እንዳይሰጥ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡

ከፍተኛ ጩኸት እያሰሙ መግለጫው ወደሚሰጥበት ቢሮ ለመግባት ሲሞክሩ፣ የውጭ በር ተዘግቶባቸው ሳይገቡ ተቃውሞአቸውን በውጭ አሰምተዋል፡፡ ተቃውሞ የቀረበው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለበት አካባቢ ወይም መቶ ሜትር ርቀት ላይ ቢሆንም፣ አድማ በታኝ ፖሊሶች ዝግጁ ሆነው በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ከመቆም ባለፈ ወደ ተቃውሞው ተጠግተው ለመበተን ያደረጉት እንቅስቃሴም አልነበረም፡፡

በርካታ የፖሊስ መኮንኖችም የመገናኛ ሬዲዮ ይዘው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከመታየት በስተቀር፣ በጩኸት ተቃውሞ ያቀርቡ የነበሩትን ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞአቸውን እንዲያሰሙ አላደረጉም፡፡ በአካባቢው ራቅ ራቅ ብለው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዘው በተጠንቀቅ ከቆሙ የፖሊስ አባላት በተጨማሪ፣ የአካባቢው ነዋሪና አላፊ አግዳሚው ግርግር ፈጥሮ ለጊዜውም ቢሆን ሰላምን የሚነሳ እንቅስቃሴ ተስተውሏል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...