Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቁጥጥር የሚደረግበትና በተጠያቂነት የሚሠራ ተቋም ሆኖ በአዲስ መልክ ሊደራጅ...

ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቁጥጥር የሚደረግበትና በተጠያቂነት የሚሠራ ተቋም ሆኖ በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው

ቀን:

በፖለቲካ እንቅስቃሴና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ክትትል እንዳያደርግ ይገደባል

የፖሊስ ተግባር ማከናወንና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አይችልም

ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና ወገንተኝነት እንዲሁም ከደኅንነት ሥጋት ነፃ የሆኑ ሠራተኞችን በማጣራት ይደራጃል

የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም የሆነው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሕገንግሥቱ የተደነገጉ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የአገሪቷን ሕጎችና ድንጋጌዎችን በማክበር፣ ከፖለቲካ ተሳትፎና ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ በገለልተኝነት ተግባርና ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣና ለዚህም ሲባል በዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት መርህ ተቋማዊ ቁጥጥር የሚደረግበት አድርጎ በድጋሚ ለማደራጀት መንግሥት ዝግጅቶችን እያገባደደ መሆኑ ተሰማ፡፡

ሪፖርተር ከምንጮቹ ያገኘው ታማኝ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ መንግሥት ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎትን በተገለጸው መልኩ በድጋሚ ለማደራጀት አስፈላጊ የሆነውን የሕግ ማዕቀፍማርቀቅ ሥራ አገባዷል፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ በይቅርታና በመደመር እሳቤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ የልማትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖረው እያደረገ ይገኛል ያሉት ምንጮች፣ ሁሉም ዜጋ በአገሪቱ ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ባለቤት እንዲሆን በማድረግ መግባባት የተሞላው ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር የተጀመረውን የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ ሁለንተናዊ የሪፎርም ዕርምጃዎችን መንግሥት በመውሰድ ላይ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋምም በድጋሚ እንዲደራጅ የሚደረገው በዚሁ መርህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ ነፃና ዴሞክራሲዊ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲፈጠር በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ትርጉም ያለውና የማይተካ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ቢታወቅም፣ ኃላፊነቱን በሥውር የሚሠራና በሚስጥር የሚወጣ፣ ከሰው ልጆች መሠረታዊ መብትና ነፃነት በሆኑት የግል ንብረትና ግላዊ ግንኙነት ላይ ጣልቃ የመግባት ልዩልጣን የሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ተግባሩም ከዘመኑ ግልጽ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ጋር እንደሚቃረን ያስረዱት ምንጮቹ፣ ከዚህ ልዩ የሥራ ባህሪይ በሚመነጭ ምክንያት ሚስጥራዊ ሥራቸውን ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ ከሌሎች የሲቪል ተቋማትተለየ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግባቸው እንደሚገባ ታምኖበት ተቋሙን መልሶ ለማደራጀት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም አኳያ ፓርላማው በተቋሙ ላይ ከሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል በተጨማሪ፣ የከፊል ነፃ (quasi-independent) ቁጥጥር እንዲደረግበት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ከፊል ነፃ ኢንስፔክተር ጄኔራል በመሾም የተቋሙ አሠራር ግድፈትን በተመለከተ በዜጎች የሚነሱ ከመብት ጥሰት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን እንዲጣራ ለማድረግ መታቀዱንና ይህም በማሻሻያ ሕጉ አስገዳጅ ሆኖ እንደሚቀመጥ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ በአዲስ መልክ እንደገና ከተደራጀ በኋላ ኃላፊነቱን የሚወጣው ከብሔራዊ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም፣ ከዜጎች ደኅንነትና ሰላማዊ ሕይወት፣ ከአገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ደኅንነት እንዲሁም ከአገሪቷ የውጭ ግንኙነት መርህ አንፃር ብቻ እንደሚሆን ከምንጮቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተቋሙ በድጋሚ ሲደራጅም ሦስት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች እንደሚኖሩት፣ እነዚህም የውስጥ የመረጃ ሥራዎችን የሚያከናውን የውስጥ ደኅንነትና መረጃ ዘርፍ፣ የውጭ የመረጃ ሥራዎችን የሚያከናውን የውጭ ደኅንነትና መረጃ ዘርፍና የፀረ ስለላና የፀረ መረጃ ሥራዎችን የሚያከናውን የፀረ መረጃ ዘርፍ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ማንኛውም አገልግሎቱ አባል በማንኛውም ሰው ላይ ቶርቸር፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት፣ ስቃይና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መፈጸም አይችልም ያት ምንጮች ይህንን ተግባር የፈጸመ ማንኛውም የተቋሙ አባል አግባብነት ባላቸው ሕጎች ተጠያቂ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙም ሆነ የተቋሙ አባላት የፖሊስ ተግባራትን ማከናወን፣ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደማይችሉ በሚወጣው ሕግ ክልከላ እንደሚጣልባቸው አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ምልክት ሊሆን የሚችለው በተቋሙ ላይ የሚጣለው ፖለቲካ ነክ ክልከላዎች መሆናቸውን የገለጹት ምንጮቹማንኛውም የተቋሙ አባል የፖለቲካ ፓርቲ አባልም ሆነ ወገንተኛ መሆን እንደማይችሉ በሚወጣው ሕግ የሚደነገግ ከመሆኑ በተጨማሪ በቅጥር ወቅትም ሆነ በኋላ በማንኛውም ወቅት ጥብቅ ማጣራት የሚደረግባቸው እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ተቋሙም ሆነ አባላቱ በአገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ፖለቲካዊ ዓላማ በመደገፍ፣ በማስፋፋት ወይም ተፅዕኖ ለማሳደር በማናቸውም ሁኔታ እንቅስቃሴ እንዳያደርግና ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ በማናቸውም ሁኔታ የመከታተልና የማጣራት ተግባር እንዳያከናውን ክልከላ እንደሚጣል አመልክተዋል፡፡

 በማንኛውም ሁኔታ ተቋሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ተግባር ተክቶ እንዳይሠራሚከለከል ቢሆንም፣ አባላቱ የጦር መሣሪያ ለመያዝ፣ ስለጦር መሣሪያ አጠቃቀም ሥልጠና ለመስጠት ወይም የጦር መሣሪያ ለመጠቀም እንደማይከለከሉ ገልጸዋል፡፡

ለመረጃና ደኅንነት የተለየ ተግባር ሲባል ሰብዓዊ ክብርን በጠበቀ መንገድ በመብቶችናነፃነቶች ላይ ገደብ ሊጣል እንደሚችል የገለጹት ምንጮቹ፣ የሚሆነው በሕግ መሠረትና ብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ፣ ለመከላከልና ለማሳደግ፣ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ከአደጋ ለመከላከል፣ የአገልግሎቱን ሠራተኞች ደኅንነት ለመጠበቅ፣ አንድ ሰው መሠረታዊ መብቶቹንና ነፃነቶቹን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የሌሎችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እንዳይጋፋ ለማድረግ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

 የሕግ ማዕቀፉን አጠናቆ በዚህ ዓመት በፓርላማ ለማፅደቅና በዚሁ አግባብም ተቋሙን መልሶ ለማደራጀት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...