Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእስረኞች ደመወዝ እየተከፈላቸው በግብርና ኢንዱስትሪዎች እንዲሠሩና ለሰብዓዊ መብቶቻቸውም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው የሚፈቅድ...

እስረኞች ደመወዝ እየተከፈላቸው በግብርና ኢንዱስትሪዎች እንዲሠሩና ለሰብዓዊ መብቶቻቸውም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው የሚፈቅድ አወጅ ሊወጣ ነው

ቀን:

እስረኞችን ወርኃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው በግብርና ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ መብት የሚሰጥና ለሰብዓዊ መብቶቻቸውም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውሚደንግገው ረቂቅ አዋጅ ላይ ፓርላማው ተወያይቶ በዝርዝር እንዲታይ ወሰነ፡፡

ሪፖርተር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባወጣው ዘገባ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች እንደማንኛውም ዜጋ ከሚዲያ አካላት ጋር ቃለ መጠይቅ የማድረግ፣ ሰብዓዊ ክብርን ከሚያዋርድ፣ ጭካኔ ከተሞላበትና ጤንነታቸውን አደጋ ላይ ከሚጥል አያያዝ የመጠበቅ መብታቸውን የሚያረጋግጥ አዋጅ ሊወጣ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይህ አዋጅ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርየማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ ለማቋቋም የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዚህ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት ኮሚሽኑ ሲደራጅ ከሚሰጡት አዲስ ኃላፊነቶች መካከል የግብርና ኢንዱስትሪዎችን በሥሩ ማደራጀት ይገኝበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ማዕከላት የሚገኙ እስረኞች በተወሰኑ ቋሚና የጓሮ አትክልት የማምረት ሥራዎች ቢሳተፉም አብዛኛውን ታራሚ የሚያሳትፉ አለመሆናቸውን የሚያስረዳው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፣ በየማዕከላቱ የሚገኙ እስረኞች ጉልበትና እውቀትን ወደ ኢኮኖሚው ለመመንዘርና እስረኞችም ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ በቀጥታ ወደ ሥራና ራሳቸውን ብሎም ቤተሰቦቻውንጥቀም እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት የእስረኞች ማረሚያ ማዕከላት የግብርና ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙና እስረኞች በእንሰሳት ማድለብ፣ በወተት ከብት ዕርባታ፣ በዶሮ ዕርባታ፣ በእንቁላልና ወተት ምርትና የመሳሰሉ አዳዲስ የአግሮ ኢንዱስትሪ ሥራዎች በስፋት እንዲሳተፉ የሚያስችል ድንጋጌ አካቷል፡፡

ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የኢንዱስትሪ ሽግግር ሥራዎችን ለመሥራት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶችም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና የሙያ ሥልጠና ማዕከል እንዲሆኑ ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዞ የግንባታ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን የረቂቁ አባሪ የሆነው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ባለፈ ረቂቅ አዋጁ የታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞችን ሰብዓዊ ክብሮችና መብቶች በአስገዳጅነት ለማስከበር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

የሚቋቋመው ኮሚሽን የአሠራር ሥርዓቶች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ወይም የሚፈጽማቸው ተግባሮች ዋና ዓላማ እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ታርመውና በመልካም ሥነ ምግባር ታንጸው ሕግ አክባሪ፣ ሰላማዊና አምራች ዜጎች ሆነው ወደብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሚሆን ያስቀምጣል፡፡

በመሆኑምየታራሚዎች አያያዝ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በዜግነት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በታሠረበት ምክንያት፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ወይም በሌሎች ማናቸውም መሰል ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ልዩነት ማድረግ የተከለከለ ነው፤ሲል ረቂቅ የሕግ ሰነዱስቀምጣል፡፡ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ እስረኞች በሁለት የሚከፈሉ መሆኑን እነዚህም በፍርድ ቤት የእስር ቅጣት የተወሰነባቸው ታራሚዎችና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ የተወሰነባቸው እስረኞች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ማረሚያ ቤት በሕግ ሥልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ መኖሩን ሳያረጋግጥ ማንኛውንም ሰው መቀበል እንደማይችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

እስረኛን በቂ ስፋት በሌለው፣ የተፈጥሮ ብርሃንን ለማስገባት በማይስችሉ መስኮቶች ማስቀመጥና እንዲሁም የጤና ሁኔታን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መያዝና ማታ ላይ የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌላቸውና የአልጋ፣ ፍራሽና የመኝታ አልባሳት በሌላቸው ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ በክልከላነት እንዲቀመጡና ይህንንም ማረሚያ ቤቶች የማክበር ግዴታ እንደሚኖርባቸው በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

ይህ ቢሆንም ከማረሚያ ቤት ለማምለጥ የሞከረ፣ ዝግጅት ያደረገ፣ በሌሎች እስረኞች ወይም በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረ ወይም ያደረሰ፣ ወይም የማረሚያ ቤቱን ደንብና ሥርዓት ለማክበር ፍቃደኛ ያልሆነ፣ ወይም የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎችና ፖሊሶች ትዕዛዝ ለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆነ ወይም በራሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረ እስረኛ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የተለየ የእስር ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ሊደረግ እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

ነገር ግን እነዚህን እስረኞች ለይቶ የመያዝ ተግባር 15 ተከታታይ ቀናት በላይ በተለየ የእስር ክፍል ውስጥ ማቆየትን፣ በጨለማ የእስር ክፍል ውስጥ ማሰርን እንዲሁም በቀን ውስጥ ቢያንስ ሦስት ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ከታሰረበት ክፍል ውስጥ ወጥቶ በክፍት ቦታ ላይ የተፈጥሮ ብርሃን እንዳያይ መከልከል እንደማይቻል ተካቷል፡፡

እስረኞች ከውጭ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከሚፈቅደው ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸውና የመሳሰሉት ጋር የመገናኘት መብት በተጨማሪሚስጥራዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ እስረኛው በደብዳቤ ወይም በጽሑፍ የመገኛኘት እንዲሁም በማረሚያ ቤት ቆይታው የሕትመት፣ የምስልና ድምፅ የሚተላለፉ መረጃዎች የማግኘት፣ ከሚዲያ አካላት ጋር ቃለ ምልልስ የመስጠት መብት ይጠበቅለታል፤የሚል አንቀጽ በረቂቁ ተካቷል፡፡

በተጨማሪም ታራሚዎች ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮቻቸው ማቃለያ ፍቃድ እንደሚያገኙ ረቂቅ የሚደነግግ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል የታመሙ ቤተሰቦቹን በአጃቢ ፖሊስ ወጥቶ የሚጎበኝበት እንዲሁም በቅርብ ዘመዶች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የመገኘት መብት እንዲኖራቸውና ማረሚያ ቤት ኮሚሽኑም ይህንን አሠራር ማመቻቸት እንደሚገባው በሰነዱ ተረቅቋል፡፡

 የሕግ ሰነዱ ሴት ታራሚዎች፣ እስረኞችን በተመለከተና 18 ወራት ያላለፈው ሕፃን ያላቸው በሚሆኑበት ጊዜ ልዩ መብቶች እንደሚኖራቸው አካቷል፡፡ ከነዚህም መካከል፣ 18 ወራት ያላለፈው ሕፃን አስፈላጊ እንክብካቤ እንዲያገኝ ከእናቱ ጋር አንዲቆይ እንደሚደረግና ማረሚያ ቤት ኮሚሽኑም ለዚህ የሚያስፈልገውን በጀት የማሟላት ግዴታ ያለበት መሆኑ ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ሴት እስረኞች ከማረሚያ ቤት ውጭ የሚኖር ሕፃን ካላቸው በተቻለ መጠን በየጊዜው በአጃቢ ፖሊስ በመውጣት ሕፃኑን የሚጎበኙበትን ሁኔታ ወይም በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ለዚሁ ዓላማ ተለይቶ በሚዘጋጅ ቦታ እንዲገናኙ እንደሚደረግ ተካቷል፡፡

 ሴት እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ወቅት ከጾታቸውና የግል ንጽህና አጠባበቃቸው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶች ኮሚሽኑ እንዲያቀርብ በረቂቁ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በሌላ በኩል ሴት እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የሚወልዱ ከሆነ ወደ ሆስፒታል ሄደው እንዲወልዱ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ መደበኛ የሕክምና ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያገኙም ተካቷል፡፡

ማረሚያ ቤቶች የማረም፣ የማነፅና መልሶ ወደ ኅብረተሰቡ የመቀላቀል ዓላማቸውን ለማሳካት እንዲችሉ መልካም ሥነ ምግባር ለተላበሱለኅብረተሰቡ አደገኝነት የሌላቸውና አርዓያ ለሆኑ እስረኞች እንደነገሩ ሁኔታ የማበረታቻ ጥቅም የመስጠት መብት በረቂቁ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት እስረኞችን ከፍተኛ ጥበቃ ካለው ማረሚያ ቤት ወደ ዝቅተኛ ጥበቃ ያለው ማረሚያ ቤት የማዘዋወር፣ የተጠቀሱትን ባህርይ የተላበሱ እስረኞች ከማረሚያ ቤት ውጭ ሄዶ የመሥራትና ለሠራውም ሥራ የተሻለ ክፍያ እንዲከፈለው የማድረግ፣ የፍርድ ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ያሉ በመልካም ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁና ከእስር ቤት የማምለጥ ሥጋት የላቸውም ብሎ ኮሚሽኑ የለያቸውን እስረኞች ያለ አጃቢ ፖሊስ ከማረሚያ ቤት ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው እንዲመለሱ የመፍቀድ ሥልጣን ለኮሚሽኑ ተፈቅዶለታል፡፡

የማረሚያ ቤት ኮሚሽኑ የእስረኞችን ሰብዓዊ መብቶች በጠበቀ ሁኔታ መያዙን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንዲቻል የተለያዩ ስልቶች ተቀምጠዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የውጭ ቁጥጥር ስልት አንዱ ሲሆንየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና አባላትና የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ እንዲሁም በሕግ የማረሚያ ቤትን የመቆጣጠርና የመጎብኘት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ ያለቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማረሚያ ቤቶችን የመጎብኘት፣ ቅሬታ ያላቸውን እስረኞች የማነጋገር፣ የእስረኞችን መዝገብ የመመርመር፣ የማረሚያ ቤት ሠራተኞችን፣ ፖሊሶችን እንዲሁም ኃላፊዎችን የማናገርና ውጤቱን ከማሻሻያ ሐሳብና ዕርምጃ ጋር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለሕዝብ የማሳወቅ ሥልጣን በረቂቁ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፓርላማው በረቂቁ ላይ የመጀመሪያ ውይይት አድርጎ በዝርዝር እንዲታይ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...