Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርለወሳኝ ችግሮቻችን የመፍትሔ ሐሳቦች!

ለወሳኝ ችግሮቻችን የመፍትሔ ሐሳቦች!

ቀን:

በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር አመቺ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ በአዲሱ አመራር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ቢሆኑም፣ አገራችን ያሉባት ውስብስብ ችግሮች በቀላሉ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ በአገራችን ብዙ ትኩረት የተነፈጋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ፡፡  ከእነዚህ መካከል ይበልጡን አንገብጋቢ ያልኳቸውን አምስት ጉዳዮች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡  

1. የሥነ ሕዝብ ጉዳይ

ኢትዮጵያ ወደ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላት ግዙፍ አገር ነች፡፡ በሕዝብ ብዛትም ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች፡፡ በየዓመቱ በ2.5 በመቶ የሚድገው የአገራችን የሕዝብ ቁጥር፣ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ጭማሪ እንደሚያሳይ ያመለክታል፡፡ የውልደት ቁጥር በሚፈለገው መጠን አለመቀነሱና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትም በሚፈለገው መጠን አለመዳረሱ፣ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ለሚገኘው የሕዝብ ቁጥር መብዛት ከአፍሪካ ባሻገር በዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦናል፡፡

በመጪዎቹ 30 ዓመታት ውስጥ የዓለም የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛውንና ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ከሚይዙት ዘጠኝ አገሮች አምስቱ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት ሲሆኑ፣ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2050 ዓ.ም. የዓለም የሕዝብ ብዛት 9.8 ቢሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡

 የአገራችን ሕዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2050 168.8 ሚሊዮን እንደሚሆን ስለሚታመን፣ ከዓለም አገሮች አሥረኛዋ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ያሰኛታል፡፡ በተለይ በደቡቡ የአገሪቱ ክፍል በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ በመሆኑ፣ የሕዝብ ጥግግቱ ወደ አሳሳቢነት ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ከሚባሉት አገሮች ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለሚገኘው ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት እጅግ አዳጋች ይሆንባታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመመደብ ያወጣችው ዕቅድም ገቢራዊ የመሆኑ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡ የግብርና ምርት መቀነስና የመሬት ለምነት መቀነስ ብሎም የመሬት ጥበት በሚያስከትለው የምርት መዳከም ምክንያት ከገጠሩ ክፍል የሚሰደደው ሕዝብ ለከተሞች ፈታኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ 70 በመቶው የሕዝቡ ክፍልም ከ30 ዓመታት በታች የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝና በአብዛኛው ሥራ ፈላጊ ነው፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራውም በሚፈለገው መጠን ባለማደጉ ሥራ አጥ የሆነው የሕዝብ ክፍል ለፀጥታ ችግር፣ ለወንጀልና ለስደት ይዳረጋል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መብዛቱ ከኢኮኖሚው ዕድገትና ከምርታማነት ጋር ካልተጣጣመ፣ የአገሪቱ ነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ማኅበራዊ ቀውሶች ይበረክታሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች መንግሥት በሥነ ሕዝብ ላይ አተኩሮ መሥራትና ራሱን የቻለ የሥነ ሕዝብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቋቁሞ የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱ እንዲረጋጋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

2. የማኅበራዊ ጉዳዮች ነገር

ኅበራዊ ችግሮች ለሌሎች ችግሮች መንስዔዎች ናቸው፡፡ የበርካታ አገራዊ ችግሮች መሠረታቸው የማኅበራዊ ችግር መንሰራፋት ነው፡፡ ማኅበራዊ ዘርፉ ተዘንግቶ ቁንጮ ላይ ባሉ ሌሎች ችግሮች ላይ በማተኮራችን፣ ዋና ዋናዎቹን ችግሮች ከሥር መሠረታቸው መቅረፍ አልቻልንም፡፡ ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉ ሲቀሩ የጤና፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የአከባቢያዊ ችግሮች ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ወጣቱ  ክፍል ሥራ በማጣቱ ምክንያት ሥራ አጥነት የሚባል ማኅበራዊ ችግር ይፈጠራል፡፡ ሥራ አጥ የሆነው ይህ ወጣት በተለያዩ ወንጀሎችና ጥፋቶች ላይ ይሰማራና የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ሱሰኝነት፣ ስደት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ተባብሮ ወንጀል መፈጸም፣ የፀጥታ አለመረጋጋትና ሥራ አጥነት ማኅበራዊ ችግሮች ሆነው ይከሰታሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሲቀሩ ሌላ ዓይነት ችግር ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡ መንግሥት ወይም በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት የተሰጠው መሥሪያ ቤት በአብዛኛው ሁሉን አቀፍ በሆኑ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በተወሰኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ላይ በተለይም በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋዊያን፣ በጎዳና ተዳዳሪዎችና የደሃ ደሃዎች ተብለው በተለዩት ላይ በማተኮሩ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚያስችል ቁመና ላይ አይገኝም፡፡ በዚህ ምክንያት ማኅበራዊ ችግሮችን አንድ በአንድ ነቅሶ መፍታት የሚችልና ወደፊት እየተበራከቱ የሚሄዱትን ማኅበራዊ ችግሮች  መቅረፍ  የሚያስችል ጊዜውን ያሳለጠ ቁመና ያስፈልገዋል፡፡                                                                                                                                                                                          3. ልዩ ክህሎትና ተሰጥኦን የማሳደግ ጉዳይ

ከሰላሳ በላይ ልዩ ክህሎቶች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከአሥር እስከ 15 በመቶ የሚሆነው የሕዝብ ክፍል ክህሎትና ተሰጥኦ አለው፡፡ ልዩ ክህሎት ያላቸው ዜጎች ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የተለያየ ትምህርት ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ልዩ ክህሎትን መሠረት ያደረገ ትምህርት አይሰጥም፡፡ ጠቅላላ ትምህርትን መሠረት ያደረገው የትምህርት ሥርዓታችን ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች አመቺ አይደለም፡፡ ሁሉም ትውልድ በአንድ ዓይነት የትምህርት መስመር እንዲያልፍ ስለሚገደድ፣ ለኮሌጅና ለዩኒቨርሲቲ ደርሶ ባመጣው ነጥብ ተወዳድሮ ባገኘው የትምህርት ቤት መስክ ላይ ይመደባል፡፡ የትምህርት መስኩ በውድድር እንጂ በክህሎት አይደለም፡፡ ወጣቶች በአብዛኛው በቶሎ ሥራ የሚያስገኝ የትምህርት መስክ ላይ ስለሚሠማሩ፣ በውስጣቸው ያለው ልዩ ክህሎትና ተሰጥኦ ይሟሽሻል፡፡ ለአገር የሚኖራቸው ልዩ አበርክቶ ገደል ይገባል፡፡ አገርም ከየትውልዱ ማግኘት የሚገባትን ልዩ አበርክቶት ታጣለች፡፡ ስለዚህ ልዩ ክህሎትና ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች ለአገራቸው ልዩ አበርክቶ እንዲያደርጉ የሚያስችል፣ ከመደበኛው በተጨማሪ የተለየ የትምህርት ሥርዓት ሊቀረፅና ሊተገበር ይገባል፡፡                                                                                                                                                                                         4. የምግብ ዋስትና ጉዳይ

ለሰው ልጅ ምግብ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ያለ ምግብ ለ15 ቀናት ያህል እንደሚቆይ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተዘርግቶ ከውጭም ድጋፍ እየተገኘበት ነው፡፡ 22 በመቶ የሚሆነው የሕዝባችን ክፍል በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ወይም ከድህነት ወለል በታች ባለው መደብ ውስጥ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የተባበሩት መንግሥታት ባደረገው ጥናት፣ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች 70 በመቶ ገቢያቸውን ለምግብ ፍጆታ ያውላሉ፡፡ አብዛኛውን ገቢያቸውን ምግብ ላይ አውለውም ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡ ናቸው፡፡ አገራችን የምግብ ዋስትናን ማስጠበቅ ፈተና ሆኖባታል፡፡ በገጠሩ የአገራችን ክፍል የመሬት ለምነት መቀነስና የይዞታው መጥበብም የምግብ ዋስትናን ማስጠበቅ ፈታኝ ካደረጉት መካከል አንዱ ችግር ነው፡፡

በአብዛኛው የሚራበው ምግብ አምራች የሆነው የአገሪቱ ዜጋ ነው፡፡ ችግሩ ግን ቀጥሏል፡፡ የዕርዳታ ጥገኝነታችንም ማብቂያ አጥቷል፡፡ሥጋት ከቦናል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማስጠበቅ ምርትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ልዩና ዘመናዊ አደረጃጀት ተዘርግቶ ከምግብ አመራረት፣ አዘገጃጀት፣ ግብይት፣ ሥርጭት፣ ድህንነትና ጤንነት አጠባበቅ፣ ከቦታ ወደ ቦታ የማጓጓዝና አጠቃቀም አኳያ የሚተገበር ሥርዓት በመፍጠር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ችግር ግን ምርታማነትና የምርት ብክነት በመሆኑ፣ የግብርናው ዘርፍ ትኩረት ይፈልጋል፡፡

5. የደረቅ ቆሻሻ ጉዳይ

በኢትዮጵያ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ደረቅ ቆሻሻ በራሱ ጊዜ የሚበሰብስ ነው፡፡ አንድ ሰው በየቀኑ በአማካይ 0.45 ኪሎ ግራም ቆሻሻ ያመነጫል፡፡ በዚህም ከ45 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ቆሻሻ በየቀኑ ከየግለሰቡ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል ብዛት ያለው ቆሻሻ በአግባቡ በአግባቡ ካልተወገደ ለአካባቢ ብክለት፣ ለአየር ንብረት መለወጥ፣ ለጤና ችግር፣ ለተፈጥሮ ውድመት፣ ለመኖሪያ አካባቢ አለመመቸትና ለመሳሰሉት ችግሮች ይዳርጋል፡፡ ሳይንሳዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በመከተል ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድና መልሶ መጠቀም መቻል ለአካባቢ ጠንቅነቱን ለማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡

አበስብስቦ ማቃጠል፣ መልሶ መጠቀም፣ መቅበርና ወደ ማዳበሪያነት መቀየር ለቆሻሻ አወጋገድ መፍትሔዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ግን ዘመናዊና ምቹ የሆነው ቆሻሻን መልሶ መጠቀም ነው፡፡ ደረቅ ቆሻሻን በማቀነባበር እንደ ሀብት መጠቀም የዘመኑ ፈጠራ ነው፡፡ ለዚህም የደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀሚያ ማዕከል በማዘጋጀት ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ፣ በመለየት፣ በማጠራቀም፣ በማሽን ፕሮሰስ ማድረግና መልሶ ሀብት አድርጎ ዋጋ ማሠራጨት ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች በመንግሥት በኩል ጊዜው በፈቀደ ወቅት መሠራት የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ጉዳዮች ትግራ የሚረዳ የተሟላ ሰነድ በእጄ ስለሚገኝ፣ መንግሥት ጠቀሚነቱን ካመነበት ሰነዱን ለማስረከብ ፈቃደኛ ነኝ፡፡

(በላይ አበራ፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡና ባንኮች በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች እንዳይጭበረበሩ አሳሰበ

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተምና በማሠራጨት ግብይት ላይ ለማዋል ጥረት...

ዕዳውን መክፈል ያቃተው ሶደሬ ሪዞርት በሐራጅ እንዲሸጥ ፍርድ ቤት ወሰነ

ከዓመታት በፊት ሶደሬ ሪዞርትና መዝናኛን ከመንግሥት የገዙት ባለሀብቶች  ገንዘቡን...

የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በትብብር ለመሥራት በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ እየገቡ ነው

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከእስራኤልና ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች...

የኢዜማ ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በፀጥታ አካላት ተወስደው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታወቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣...