Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ዐደይ አበባ የያዘውን ቀኝ እጃችንን እናንሳና ከመፀው ጋር ወደፊት! እንኳን ለመፀው ወቅት አደረሰን፣ አደረሳችሁ! ሰኔ 26 የገባውን ክረምት እነሆ መስከረም 25 ሸኝተነዋል። ደስም ይበለን። ወዳጆቻችን ሆይ! በወራቱ ጌታ በመስከረም 26 ቀን የባተው፣ እጅ ነሥተን ስለተቀበልነው የመፀው ወቅት በዕውቀት ላይ ተመሥርተን፣ በትውፊታችን ላይ ተንተርሰን እስቲ እናውጋ።አረፍ በልና እናውጋአይደለም እንዴ የሚለው ብሂሉ!
መጀመርያ መፀው ምን ማለት እንደሆነ እንፍታ፣ እናፍታታ። እንደሌሎቹ ስሁታን እንዳንፋታ፣ ከፀደይ ጋር እንዳንጋባ የሊቃውንቱን ጓዳ እናንኳኳ።

እንዲህ ይሉናል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ:- መፀው ትርጉሙ አበባ ማለት ነው፡፡ መገኛው ግስ ‹‹መፀወ›› አበበ፣ አበባ ያዘ፣ ዘረዘረ፣ ሊያፈራ ማለት ነው፡፡ ጸገየ (አበበ) ብሎ ጽጌ (አበባ) ይጠቅሳል፡፡ መስከረም 26 ገብቶ ታኅሣሥ 25 ይወጣል ይለናል። እንደ አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ አገላለጽም፣ የክረምት ተረካቢው መፀው የተባለው ክፍለ ዘመን እንደ ክረምት የውኃ ባሕርይ ያፈላል፡፡ ይገናል፡፡ እንቡር እንቡር ይላል፤ ይዘላል፤ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይመላሉ፡፡ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው ይነሣሉ፡፡ ይበቅላሉ ይለመልማሉ፡፡ አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣እንቡጥና ፍሬ ማሳየት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ታዲያ መሠረቱ ይሄ ሆኖ ሳለ በመፀው መንበር ላይ ከመስከረምና ጥቅምት፣ ከኅዳርና ታኅሣሥ ጋር የማይተዋወቀው ፀደይን ማስገባት ለምን? እስቲ ስለ ፀደይ ደግሞ እናውጋ። ታኅሣሥ 26 ገብቶ መጋቢት 25 ከሚያበቃው በጋ ቀጥሎ የሚመጣልን ወቅት ፀደይ ነው፡፡ ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ፀደይን ዘመነ በልግ ይለዋል፡፡ በልግ የሚደርስበት የሚታጨድበት ወዲያውም የሚዘራበት ወርኃ ዘርዕ (የዘር ወር) ሲልም ያክልበታል፡፡ ከመቐለ እስከ አሥመራ በበልግ/ ፀደይ የሚያገኙትን የጤፍ አዝመራፅዳይ ጣፍይሉታል።
በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት የሚዘንበው ዝናብም የበልግ ዝናብ በመባልም ይጠራል፡፡ ይታወቃል።

‹‹ፀደይ በመስከረም? ወይስ በመጋቢት? በፈረንጅ ወይስ በአበሻ?›› በሚልርዕስ ሐተታ የጻፉት አፈ ሊቅ አክሊሉ እንደገለጹት፣ ዛሬ ግን አንዳንድ ሰዎች በአውሮፓ ክፍለ ዘመን እየተመሩ ፀደይ፣ በመስከረም 26 ቀን የሚገባው ክፍለዘመን ስም ነው እያሉ ያቀርባሉ፡፡
መምህራን ፀደይ በጥቅምት በኅዳር ነው አይሉም፤ የባሕረ ሐሳብ፣ የአቡሻሕርና የመርሐ ዕዉር ቁጥር መምህራን፣ ድጓ ነጋሪዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ፀደይ በመስከረም መጨረሻ ይገባል አይሉም፡፡ አይከራከሩበትም አይለያዩበትም፡፡ ፀደይ የሚገባው በመጋቢት 26 ቀን ነው ማለትን አይክዱም አያስተባብሉም፡፡ ክፍለ ዘመናችንም ከፈረንጆች ክፍለ ዘመን መለየቱን ገልጠው ያስረዳሉ፡፡ እኛ መፀው ስንል ፈረንጆች ፀደይ ገባ ይላሉ እያሉ የክፍለ ዘመናችንን ልዩነት ሐተታ ያብራራሉ፡፡ መጻሕፍቱም ይኼንኑ ይመሰክራሉ፡፡

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ክፍለ ዘመናችንን ለምን ያዘዋውሩታል? ፀደይ ማለት በልግ ማለት እንደሆነ እየታወቀ፣ የበልግ ዝናብ ዘንቦ ገብስ ዘንጋዳ ማሽላ በቆሎ የሚዘራበት ወራት ከፊታችን ቁሞ ነገሩን ቀምሞ እየመሰከረ አደናጋሪ ነገር ማምጣት ምን ይጠቅመናል? ይልቅስ ‹‹ወረጎ መሬት›› ማለት መሬት የሚሰባበት የሚወፈርበት የሚዳብርበት ወራት መሆኑን መገንዘብ መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ አስረግጠው ያሳስባሉ፡፡

የዘመን አቆጣጠራችን መነሻና መድረሻ የወቅት አከፋፈልና ስያሜ ተጠንቅቆ ባለመያዙና በቅጡ ባለመተላለፉ ይኸው ዘመን በተለወጠ ቁጥር አገሪቱ የስህተት ጭፍራ እየሆነች ነው። ብዙዎች ከክረምት በኋላ የመጣልን ወቅትፀደይነው እያሉ ነው። ልክ ክረምታችንን በድፍረት በስህተትሰመርእንደሚሉት። ነገ ደግሞ ፀሓይ በምዕራብ ወጥታ በምሥራቅ ትጠልቃለች ይሉን ይሆናል።

ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍ የሚጠበቅባቸው ሚዲያዎች ትኩረት እየሰጡት አይደለም። የፀደይ አጋፋሪዎች ሆነው ተገኝተዋል። እንዴት ቀዳሚውና አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የቀድሞ ባልደረባው፣ ለኤዲቶሪያልርእሰ አንቀጽየሚለውን ስያሜ የፈጠሩለት አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ ዓርማን ማንሣት አቃተው? ኢዜአም እንዲሁ። ነው ወይስእንደ ንጉሡ አጎንብሱሆኖ ነው። ርእሰ መንግሥታችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓምና የኢሬቻ በዓል ሲከበር የመልካም ምኞት መልዕክት ያስተላለፉት እንዲህ በማለት ነበር:- ‹‹የክረምቱን ዶፍና ጨለማ ያሸጋገረን አምላክ ይመስገን፤ ኢሬቻ የፀደይ በረከት የምንቋደስበት››ያሉትን
ዘንድሮም እንዲህ ደገሙት። ለዚያውም ሦስት ጊዜ።

ክረምት አልፎ ፀደይ ዞሮ መምጣቱን፣ ጭለማ አልፎ የብርሃን ሸማ መተካቱንየመሻገር በዓል ነው። ከክረምት ወደ ቢራ (ፀደይ)”ኢሬቻ የፀደይ በረከት የምንቋደስበት
ዓምና እንዴት ነው ነገሩ ብለን ማሳሰቢያ ሰጥተን ነበር። ርእሰ መንግሥቱ የቅርስና የትውፊት፣ የባህልም አማካሪ የላቸውም እንዴ?

እኛ እንደ መምህርነታችን ማሳሰባችንን ማስተማራችንን አንተውም፣ ቅዱስ ያሬድ አስተምሮናልና፤ ዑቅ ወጤይቅ (እወቅ ጠይቅም) ብሎናልና። ለማንኛውምከትናንት በስቲያ መስከረም 26 ቀን የተጀመረው መፀው የአበባ ወቅት፣ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን ድረስ ዘጠና ቀናት የሚቆይ ይሆናል። የወቅትን ጥንተ ነገር እንደ ሌሎች ደራስያን ያልሳተው ዕውቁና ተወዳጁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ የመፀውን፣ ጥቅምትነት ኅዳርነትና ታኅሣሥነት ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት ተቀኝቶበታል፡፡ ከውበት ጋር በማያያዝ ጭምር፡፡ ርዕሱ ‹‹ይሰለቻል ወይ?›› የሚል ነው፡፡

ይሰለቻል ወይ?
የመፀው ምሽቱ አብራጃው ሲነፍስ
የኅዳር የጥቅምት የትሣሥ አየር
ጨረቃ አጸድላ ተወርዋሪ ኮከብ ሲነጉድ ሲበር
ይሰለቻል ወይ?
በክንድ ላይ ሁና
ብላ ዘንጠፍ ዘና
ሶባ ቀዘባዋ የሚያፈቅሯት ልጅ
ፍቅር ሲፈነድቅ ሲሠራ ሲያበጅ
ይሰለቻል ወይ?
የውበት የፍቅር የሐሴት ሲሳይ፡፡

እንደግመዋለን መስከረም 26 ቀን 2012 .. የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው ‹‹መፀው›› (Ethiopian Spring season) ገብቶልናልና በዕልልታና በሆታ በሃሌታ ይታጀብ፡፡ የሚያስደስት የአበባና ነፋስ ወቅት ይሁንልን፡፡ የስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንደጻፈው፣ ‹‹ኀለፈ ክረምቱ፤ ጸገዩ ጽጌያት፤›› (ክረምቱ አለፈ፤ አበቦችም ፈኩ)፡፡ እንደ ቀድሞው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦልናልና ደስ ይበለን፤ እልልም እንበል፡፡ አውድማዎቻችን እህልን ይምሉ! መጥመቂያዎቻችንም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፍስሱልን!! ሠናይ ዘመነ መፀው! ለከርሞ ከዕውቀት ጋር ያድርሰን።

(ሔኖክ ያሬድ ፈንታ፣ ከራስ ሙሉጌታ ሠፈር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...