Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክክለሳ የሚሻው የሆቴል ሥራ ውል

ክለሳ የሚሻው የሆቴል ሥራ ውል

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የሆቴል ኢንዱስትሪው በታወቀ ደንብ፣ በሥርዓት እንዲመራና እንዲተዳደር ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሠማሩትንና የመንግሥትን ግንኙነት የሚወስን ሕግ በአንድ በኩል፣ የባለሆቴሎቹንና የተገልጋዩን ግንኙነት ደግሞ በሌላ በኩል በማድረግ የሚያስተዳድሩ ሁለት ዓይነት ሕግጋት አሉ፡፡ የመጀመሪያውን ሁኔታ የሚወስኑና ደንብ የሚያስይዙት ሕግጋት፣ የዚህ ጽሑፍ አካል አይሆኑም፡፡ ትኩረቱ፣ የባለሆቴልና የደንበኞችን ወይም ተስተናጋጆችን ግንኙነት የሚመለከተውን የሕግ ክፍል ጽሑፍ ይዳስሳል፡፡ ጥቂት ከውል ውጭ ኃላፊነትን መሠረት ያደረጉ ሐሳቦች ቢኖሩም የበለጠ የሚያደላው ወደ ውል ነው፡፡

ስለ ሆቴል አገልግሎት ውል ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ ዋና የሕግ ምንጩ፣ በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ ከአንቀጽ 2653 እስከ 2671 ድረስ ስለ ሆቴል ሥራ ውል መሆን ያለባቸውን፣ የተፈቀዱትንና የተከለከሉትን ድርጊቶች ለማሳወቅ ሞክሯል፡፡ ምንም እንኳ በ19 አንቀጾች የተቀነበበ ቢመስልም፣ ካለፋቸው አንቀጾች እያስታወሰ፣ ወደ ፊት ከተደረደሩት እየጠቆመ በማዛመድና በማስተሳሰር ባመለከተው እንኳ ሲታይ ከእነዚህ አንቀጾች የማያንሱ ሌሎች አንቀጾችን በጋራ ስለሚጠቀም በዚህ ጽሑፍም መለስ ቀለስ እያልን እንደሁኔታው መጠቃቀሳችን አይቀርም፡፡

የሆቴል አገልግሎት ውል በጠቅላላው

በፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለ ሆቴል አገልግሎት የውል ሕግ ወደተደነገጉት ከመግባታችን አስቀደመን ‘ሆቴልን የሚመለከቱ ሕግጋትን የማውጣት ሥልጣኑ የፌዴራል ነው ወይስ የክልል?’ የሚለውን መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ የወጣው ኢትዮጵያ አሐዳዊ የመንግሥት አስተዳደር ትከተል በነበረበት ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ በሚሆንበት ጊዜ ሕግ የማውጣት ሥልጣኑ ሊቀየር ይችላል፡፡ የማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን መሆኑ ቀርቶ የክልሎች ሊሆንም ይችላል፡፡

የሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ ተፈጻሚነት ያላቸው በርካታ ሕግጋት መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የንግድ ሕግ፣ የኢንቨስትመንት፣ የታክስ፣ የአሠሪና ሠራተኛና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የባለ ሆቴሉንና የደንበኞችን ወይም ተስተናጋጆችን ግንኙነት የሚወስኑት የውልም ይሁን ከውል ውጭ ኃላፊነትን የሚመለከቱትን ሕግጋት የማውጣት ሥልጣን የተተወው ለክልል መንግሥታት ነው፡፡ የሆቴል አገልግሎት ውልም ቢሆን የክልሎች ነው ማለት ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ወይም 55 ለፌዴራል መንግሥት ተለይቶ አልተሰጠም፡፡ በመሆኑም የክልል ሥልጣን ነው ማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ እንደ ብዙዎቹ የሕግ ዓይነቶች የሆቴል አግልግሎት ውልን በሚመለከት ክልሎች አዲስ ሕግ አላወጡም፡፡ ስለሆነም የፍትሐ ብሔር ሕጉን እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በአበባና በድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች ላይ ተፈጻሚነት የሚኖረውን የማሻሻልም ይሁን እንደ አዲስ ሕግ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ከዚያ በስተቀር ክልሎች በራሳቸው ግዛት ተግባራዊ የሚሆን ሌላ ሕግ የማውጣት ሥልጣን አላቸው፡፡

የሆቴል ሥራ ውል ምንነት

አንቀጽ 2653 (1) በሚከተለው መልኩ የሆቴል ሥራ ውልን ይተረጉመዋል፡፡ ‹‹የሆቴል ሥራ ውል ማለት አንድ ሰው የሆቴልን ሥራ የሙያ ተግባሩ በማድረግ ሰውን ለአንድ ሌሊት ወይም ለብዙ ሌሊት ለማኖር የሚደረግ ውል ማለት ነው›› ይላል፡፡ በአማርኛ ‘የሆቴል ሥራ ውል’ የሚለው በእንግሊዝኛው “Contracts of Innkeepers” የሚለውን ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው የሆቴል ሥራ ብያኔ፣ የመኝታ አገልግሎት መስጠትን ነው እንደ ዋና ሥራ አድርጎ የወሰደው፡፡ ሌሎች ሕግጋትን ስናይ ግን ሆቴል ለሚለው የተሰጠው ብያኔ የመኝታ አገልግሎት በመስጠት ብቻ አለመታጠሩን እንረዳለን፡፡ አንድ ምሳሌ ብቻ እናንሳ፡፡ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ደረጃ ምደባ ለመወሰን የወጣው ደንብ ቁጥር 173/2002 አንቀጽ 2 (4) ‹‹ሆቴል ማለት የመኝታ፣ የምግብና የመጠጥ እንደ አስፈላጊነቱም የመዝናኛ የስብሰባና መሰል አገልግሎቶችን ለቱሪስቶችና ለሌሎች ተጠቃሚዎች የሚያቀርብ ድርጅት ነው›› ይላል፡፡

በደንቡ ለሆቴል የተሰጠው ብያኔ፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ከተገለጸው የሰፋ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2671 ላይ ሆቴል ባይሆኑም እንደሆቴል የሚወሰዱት በዚሁ ሕግ እንዲተዳደሩ ወስኗል፡፡ በመሆኑም፣ በአንቀጽ 2653 የተሰጠው ትርጉም ጠባብ ቢሆንም፣ ወረድ ብሎ ሌሎች አገልግሎቶችንም ተመልሶ አጠቃሏቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመሥሪያ ቤት ክበቦች፣ ሻይ ቤቶች፣ የሕዝብ መደሰቻ ቤቶች፣ መታጠቢያ ቤቶች፣ አልጋ ባላቸው የማደሪያ ቤቶችና የመሳሰሉትን አካትቷል፡፡ የመኝታ ሥራ ባይኖራቸውም የመብል፣ የመጠጥና ሌሎች አገልግሎቶችን ለደንበኞች ስለሚያቀርቡ ከደንበኞቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት እንደሚወሰን በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 2653 እስከ 2671 ድረስ የተዘረዘሩት ተፈጻሚ ናቸው፡፡

የሆቴል ሥራ ውል የራሱ የተለዩ ባሕርያት ቢኖሩትም በመሠረታዊው የውል ሕግ መርሆች የሚመራና የሚገዛ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ስለ ችሎታ፣ ስምምነት፣ የውል አደራረግ ሁኔታ (ፎርም) እና የውል ጉዳይ ስለ ውል በጠቅላላው በተገለጸው ይገዛል፡፡ የሆቴል አገልግሎት ለማግኘት ማለትም የሚጸና ውል ለማድረግ ችሎታ ያለው ሰው መሆንን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ 18 ዓመት መሙላት (ወይም ከችሎታ ማጣት ነፃ መውጣትን) ታሳቢ ያደርጋል፡፡ የሆቴል አገልግሎት ውል በጽሑፍ ይሆን ዘንድ የሚያስገድድ ድንጋጌ ስለሌለ፣ በጽሑፍም፣ በቃልም፣ በምልክትም መዋዋል ይቻላል፡፡ ውል ስለመኖሩ በማናቸውም የማስረጃ ዓይነት ማስረዳት የተፈቀደ ነው ማለት ነው፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ የሆቴል ሥራ በማለት ዕውቅና የሰጠው ለአንድ ሌሊት ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት ደንበኛን የማሳደር አገልግሎት መስጠትን ነው፡፡ በሌሊት መቁጠሩ የብያኔው ጉድለት ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ላያድሩበት ነገር ግን ሊውሉበት ብቻም የመኝታ ቤትን ይከራይዋልና፡፡ እንዲህም ሆኖ ከአንድ ሌሊት ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ሰው ከሆቴሉ ጋር ያለው ግንኙነት በዚሁ ሕግ ይተዳደራል፡፡ ከአንድ ወር ከበለጠ ግን በኪራይ ሕግ መሠረት እንደሚሆን አንቀጽ 2653 (2) ይናገራል፡፡ በእርግጥ አንድ ወር ማለትስ በራሱ እንዴት ነው የሚወሰነው? የሚለው ግርታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆቴል ከኖረ ተከራይ እንጂ ‹‹ደንበኛ›› አይደለም፡፡ ስለዚህ የተከራይና አከራይ መብት ግዴታ ይኖራቸዋል፡፡ በምን መሥፈርት ተከራይ፣ በምን መሥፈርት ደንበኛ ብሎ መለያየት ይቻላል? አንድ ወርና ከዚያ በላይ ካሳለፈ ወይም አስቀድሞ ከአንድ ወር በላይ እንደሚቆይ ካሳወቀና ውል ካደረጉ? በየዕለቱ የሚያድስ ተከራይ ይባላልን? አንድ ወር ስላለፈው ብቻ? ፍርድ ቤት ምን ምን ማስረጃዎችን በማየት ተከራይ ወይም ደንበኛ ብሎ ይወስን? በየዕለቱ ክፍያ መፈጸምን ወይም በየሳምንቱ አልያም በየወሩ መክፈሉን ወይም ሆቴል ላይ የሚሞላውን ቅጽ?

የፍትሐ ብሔር ሕጉ ለአንድ ወር ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በውል የተሰጠ  ስለሚል የመኝታ አገልግሎት ለማገኘት አስቀድሞ በዚሁ መልክ የጊዜው መጠን መታወቅ ያለበት ይመስላል፡፡ አስቀድሞ ካልተቆረጠ በስተቀር፣ በየዕለቱ በሚታደስና እስከ መቼ የሚለው እስካልታወቀ ድረስ እንደ ሆቴል አገልግሎት መቆጠሩ ሚዛን ይደፋል፡፡ ካልሆነ፣ ወር ሲሞላው ቀድሞ ለተኖረበት ተመልሶ በኪራይ ሕግ መሠረት ነው ግንኙነት የሚወሰነው የሚል ወለፈንዳዊ አሠራር ይመጣል፡፡

ከሆቴል ሥራ የውል ጊዜ ጋር የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ‘ለምን ያህል ጊዜ ጸንቶ ይቆያል?’ የሚለው ነው፡፡ አንቀጽ 2654 ላይ እንደተገለጸው፣ የሆቴል ክፍለ ቤትን (Room) ለመገልገል ለአንድ ቀን የሚደረግ ውል ከእኩለ ቀን ጀምሮ መልሶ በማግሥቱ እስከ እኩለ ቀን ድረስ የጸና ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ተቃራኒ ውል ከሌለ በቀር የሚል ተዋዋዮች እንዳሻቸው እንዲወስኑ የሚፈቅድ ሐረግ ስለተቀመጠ፣ ከእኩለ ቀን እስከ እኩለ ቀን የሚለው መርህ ሊለወጥ ይችላል፡፡ ይኼ ሁኔታ፣ ውል በሚደረግበት ጊዜ ማሳወቅን መስማማትን ታሳቢ ያደረገ አንቀጽ ነው፡፡ ውሉ በሚደረግበት ጊዜ (አልጋ በሚያዝበት ጊዜ ወይም በክፍሉ ውስጥ በተለጠፉ ወይም በተቀመጡ ማስታወቂያዎች)  ካልተገለጸ በቀር ተፈጻሚ የሚሆነው ይኼው የጊዜ ገደብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስከ እኩለ ቀን ደንበኛው ካላራዘመ፣ ባለ ሆቴሉ እንዲለቅ የማድረግ ካልሆነም ለተጨማሪ አንድ ቀን እንደተራዘመ ሕጉ ግምት ስለወሰደ፣ የአንድ ቀን ተጨማሪ ክፍያ የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ደንበኛው አስቀድሞ አልጋ ተከራይቶ፣ በተስማማበት ቀን ቢቀር እንኳ አልጋ የያዘባቸው ቀናት ብዛት ከግምት ሳይገባ የአንድ ቀን ክፍያ የማስከፈል መብትን ለባለ ሆቴሉ ይሰጣል፡፡ ባለ ሆቴሉ ካከራየው ደንበኛውን መጠየቅ አይችልም፡፡ ደንበኛው ቀድሞ የከፈለው ገንዘብ ካለ፣ ገንዘቡ እስከሚያልቅ ድረስ ለተከራዩ ጠብቆ ማቆየት ግዴታው ነው፡፡

ሆቴል ስለሚያሟላቸው ቁሶች

በሆቴሉ ክፍለ ቤት መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ዘርፉ ባዳበራቸው ልማዶች መሠረት እንዲወሰን ሕጉ በአንቀጽ 2656 ላይ ጠቅሶ አልፎታል፡፡ የሆቴሎችን ደረጃ ለመወሰን በወጣው መመርያ የቱሪስት ደረጃና ባለኮኮብ ሆቴሎች ማሟላት ያለባቸው ዝቅተኛ መሥፈርት ተገልጿል፡፡ ያም ሆኖ፣ ደንበኛው ባለሆቴሉን በመብትነት ሊጠይቀው በሚችልበት መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚስችል መነሻ ሊሆን የሚችለው፣ ውላቸው እንጂ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ እምብዛም አያግዝም፡፡

የባለ ሆቴልና ደንበኛ የሚባሉትና የማይባሉት

የሆቴል አገልግሎት የሚሰጠው ሰው ሙያዬ ብሎ የሚይዘውን የሚለከት እንጂ፣ ቤት የፈጣሪ ነው ብሎ እንግዳ ተቀብሎ ያሳደረውን ሁሉ አይመለከትም፡፡ ባለ ሆቴሉ ለትርፍ ብሎ የሚሠራ ነጋዴ መሆን አለበት፡፡

‘ደንበኛ’ የሚባለውም ረግቶ የሚቆይ ኗሪን ሳይሆን አልፎ ሒያጅ  (Transient Guest) ሊባሉ የሚችሉትን የሚመለከት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 2653 ጀምሮ የተገለጹት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት እንዲህ ዓይነት ዓደንበኞች ላይ እንጂ ከወር በላይ ለሚቆዩ ተከራዮች አይደለም፡፡ የተከራይ (Tenant) መብትና ግዴታዎች የሚተዳደሩት በሌላ ሕግ ነው፡፡

ሌላው፣ ደንበኛ በሚባልበት ጊዜ የደንበኛውን እንግዳስ (የእንግዳ እንግዳ) ያካትታልን የሚለው ነው? በተለይ በሕግ መነፅር ሲታይ አጀንዳ የሚሆነው የእንግዳ እንግዳው በሆቴሉ ውስጥ ጉዳት በሚያጋጥመው ጊዜ ነው፡፡ ለእንግዳ እንግዳ፣ ባለሆቴሉ ኃላፊነት ይኖርበታልን? ምናልባትም በሆቴሉ ዕውቅናና አሠራር የተፈቀደ ከሆነ ኃላፊነትም ሊከተል ይችላል የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ይቻላል፡፡

የተስተናጋጅ ንብረትና የባለ ሆቴል ኃላፊነት

የባለ ሆቴልና የደንበኛው ንብረትን በሚመለከት ግንኙነታቸው የሚተዳደረው በአደራ ውል መሠረት እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ከሆቴል አገልግሎት የሚያገኝ ሰው፣ የአልጋ፣ የዋና፣ የልብስ ማሳጠብ አገልግሎትም ሆነ ሌሎች የመደሰቻ ተግባራትን ማድረግም ቢሆን ዕቃን ተረክቦ መጠበቅ የባለ ሆቴል ግዴታ ነው፡፡ በዋጋ በአደራ ዕቃ የማስቀመጥ ውል እንዳደረጉ ተቆጥሮ በዚህ ሕግ መሠረት ግንኙነታቸው ይወሰናል፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሆነው አንቀጽ 2663 ነው፡፡

የአደራ ውል (Bailment Contract) ምን እንደሆነ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2779 ላይ እንደሚከተለው ብያኔ ሰጥቷል፡፡ ‹‹አደራ ማለት አደራ ተቀባይ የተባለው አደራ አስቀማጭ የተባለውን ሌላ ሰው ዕቃ ተቀብሎ በአደራ ጠባቂነት እንዲያስቀምጥለት የሚገባበት የውል ግዴታ ማለት ነው፡፡›› በዚህ ትርጉም መሠረት ደንበኛው አደራ አስቀማጭ (በአደራ ዕቃውን የሚያስቀምጥ)፣ ባለ ሆቴሉ ደግሞ አደራ ተቀባይ ይሆናሉ፡፡ ባለ ሆቴሉ የደንበኛውን ዕቃ በአደራ የማስቀመጥ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የአደራ ውል በክፍያም ወይም ያለ ክፍያም ሊሆን ይችላል፡፡ በአደራ የማስቀመጥ ግንኙነት ወቅት የአደራ አስቀማጩና ተቀባዩ በአደራ የተቀመጠውን ንብረት በሚመለከት እንደ ዕቃው ዓይነት (በቶሎ የሚበላሽ፣ የሚቆይ፣ ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጣ ወዘተ) ሊለዋወጥ ይችላል፡፡

በኮመን ሎው (Common Law)፣ ባለ ሆቴል ስለ ደንበኛው ደኅንነት ኃላፊነት አለበት፡፡  ደንበኛው (እንግዳው) ወደ ሆቴሉ ይዞት ለመጣው ንብረት ቢጠፋ (ቢሠረቅ)፣ ባለ ሆቴሉ ቢያውቅም ባያውቅም በመርህ ደረጃ ኃላፊ ነው፡፡ ወደ ክፍል የገባም ይሁን በፓርኪንግ ለተቀመጠ መኪና ወይም ሌላ ንብረት፣ ባለ ሆቴሉ ኃላፊነነት አለበት፡፡ ከዘራፊ ወንበዴዎች የመከላከል ግዴታ ነው፡፡ ቃጠሎ፣ ጎርፍ፣ ስርቆት፣ ግዴለሻዊ አያያዝ ወዘተ የደንበኛውን ንብረት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶችም ቢሆን በኮመን ሎው ሥርዓት ባለ ሆቴሉ ለደንበኛው ንብረት ኃላፊነት አለበት፡፡

ስለ ንብረቱ ጉዳት በገንዘብ መካስ አሊያም መተካት ፍትሕ ማድረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በኮመን ሎውም ቢሆን የፈጣሪ ቁጣ (Acts of Nature) ማለትም መሬት መንቀጥቀጥ፣መብረቅ፣ በከባድ ዝናብ ምክንያት ጎርፍና መሰል የተፈጥሮ እንጂ በባለ ሆቴሉ ጥንቃቄ የማይቀሩ፣ በቸልተኝነቱ የማይፈጠሩ ድርጊቶችን የሚመለከት ሲሆን፣ በሕዝባዊ ብጥብጥና ሁከት ምክንያትም ንብረት ቢጠፋ ባለ ሆቴሉ ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡

ይሁን እንጂ፣ ይህ የኮመን ሎው አሠራርን በእንደገና በሕግ እያረቁ የባለ ሆቴሉን የኃላፊነት መጠን የመገደብ አዝማሚያ ተንሰራፍቷል፡፡ አሜሪካን በምሳሌነት ብንወስድ፣ ክፍለ ግዛቶቹ (States) የራሳቸውን ሕግ በማውጣት የኃላፊነትን መጠን ወስነዋል፡፡ የኃላፊነትን መጠን ብቻ ሳይሆን፣ በሆቴል ክፍለ ቤቶች ውስጥ መኖር ስላለባቸው ካዝናዎች፣ የደንበኛ ዕቃ፣ የገንዘብ መጠንና ለባለ ሆቴሉ የማስታወቅ ግዴታ፣ ማስታወቂያ በክፍለ ቤቶች የመለጠፍ ግዴታና የሚኖራቸውን ሕጋዊ ውጤት መወሰን ተለምዷል፡፡ የኃላፊነትን መጠን ለመወሰን ደንበኞች አስቀድመው እንዲያውቁት ማድረግን ግዴታ ያደረጉ ክፍለ ግዛቶች አሉ፡፡ ካዝና ማዘጋጀት፣ የበርና የመስኮት ቁልፎች አስተማማኝነት፣ የዋጋ መጠን ጣሪያ መወሰንና ከዚያ በላይ ከሆነ ኃላፊነት እንደማይኖርበት መወሰን (ለምሳሌ 500 ዶላር በማለት)፣ ሻንጣ በሚጠፋበት ጊዜ በሻንጣው ውስጥ ምን ምን እንዳለ ስለማይታወቅ፣ በቁርጥ አስቀድሞ በሕግ መወሰን፣ ብሎም በባለ ሆቴል ቸልተኝነት ወይም ንዝህላልነት ለሚጠፋ ንብረት የቅጣት መጠን በሕግ መቁረጥ አስፈላጊ ነው፡፡

በካናዳ የኃላፊነቱ መጠን እንደየክፍለ አገሩ ሕግ ይለያያል፡፡ ኃላፊ የሚሆንበትና የማይሆንበት ሁኔታዎች የተወሰኑ ልዩነቶች አሉ፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ደንበኞች የክፍለ አገሮቹን ሕግጋት በማወቅ ነው ለጠፋ ንብረታቸው ካሳ መጠየቅ የሚችሉት፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ የተገለጸው የኃላፊነት መጠን 500 ብር ነው፡፡ ደንበኛው በሆቴሉ ውስጥ ለጠፋበት ንብረት በመርህ ደረጃ የሚጠይቀው ከእዚህ ገንዘብ አይበልጥም፡፡ በኢትዮጵያ ክልሎች ያወጧቸው ሕግጋት ስለሌሉ በደንበኞች ላይ መደናገርን አይፈጥርም፡፡

የደንበኛ ጥፋት በሚኖርበት ጊዜ የሆቴሉ ኃላፊነት መኖር ወይም አለመኖር ለምሳሌ ወደ መጸዳጃ ቤት ገባሁ ብሎ ዕቃ መጋዘን ክፍቶ ሲገባ (ጨለምለም ብሏል ብንል) ተንሸራትቶ ቢወድቅና ዕቃ ቢመታው፣ ዕቃዎች ተደረማምሰው ቢጎዳ፣ የደንበኛው ጥፋት ነው ማለት ይቻላል ወይ?

በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ካልተወጣ ወይም ካላደረገ ለሚጠፋ ንብረት፣ የዋጋው መጠን ከግምት ሳይገባ ባለሆቴሉ ኃላፊነት እንዲኖርበት ሕጉ ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የ500 ብር የካሳ ጣሪያ ይቀርና በዕቃው ዋጋ ልክ ኃላፊ ይሆናል፡፡ ጉዳት የደረሰው በአደራ የተሰጠው ዕቃ ላይ ከሆነ፣ ጉዳት አድራሹ ባለሆቴሉ ወይም ሠራተኞቹ ወይም የቤተሰቡ አባል ከሆነ፣ ባለሆቴሉ ንብረቱን በአደራ አላስቀምጥም ባለበት ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ እንደሆነ፣ በንብረቱ ዋጋ መጠን ባለሆቴሉ የመክፈል ግዴታ እንደሚኖርበት አንቀጽ 2665 እና 2666 ላይ ተገልጿል፡፡

ያም ሆኖ ግን ለጉዳቱ ምክንያት የሆነው በደንበኛው ጥፋት፣ በዕቃው ሥሪት ወይም ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች በሚሆንበት ጊዜ፣ የባለሆቴሉ ኃላፊ መሆን ይቀራል፡፡ ባለሆቴሉን ከኃላፊነት ነፃ ለማድረግ የሚፈጸሙ ውሎች አስገዳጅነት እንደማይኖራቸው የፍትሐ ብሔር ሕጉ ግልጽ አድርጓል፡፡

ባለሆቴሉ፣ የደንበኛው ውል ከእኩለ ቀን የሚጀሚር ቢሆንም ከጧት ጀምሮ፣ የመልቀቂያ ጊዜውም በእኩለ ቀን የሚጠናቀቅ ቢሆንም እስከ ማታ ድረስ ያለ ክፍያ በአደራ ንብረቱን የማስቀመጥ ግዴታ እንዳለበት አንቀጽ 2657 ላይ ተደንግጓል፡፡

በሆቴሉ ውስጥ እንደተፈጸሙ ከሚቆጠሩት መሃል ተሽከርካሪዎችና ሕይወት ያላቸው እንሰሳትም ይካተታሉ፡፡ አንድ መኪና ወይም ፈረስ ያለው ሰው ፈረሱን አልያም መኪናውን ለሆቴሉ ወይም ለተሽከርካሪም ይሁን ለእንስሳት ጥበቃ አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች ከሰጠ፣ ሕጉ በእዚህ ሁኔታም ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን አንቀጽ 2670 (2) ላይ ተደንግጓል፡፡

ተሽከርካሪን በሆቴል መቆሚያ ቦታ አቁሞ ቁልፉን ደንበኛው ከያዘው፣ የአደራ ውል አለ ማለት ይቻላል፡፡  በፓርኪንግ መኪና አቁሞ ከሆቴል አገልግሎት ማገኘት የአደራ ውል እንዳለ መቆጠር እንዳለበት የብዙ አገሮች ሕግ አሊያም የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ያሳያሉ፡፡ የፓርኪንግ ክፍያም ቢፈጸም በዋጋ የተደረገ የአደራ ውል ይሆናል፡፡ 

የደንበኛን ንብረት መያዝ

ደንበኛው ለተጠቀመበት አገልግሎት ክፍያ ካልፈጸመ፣ ባለ ሆቴሉ የደንበኛውን ንብረት ሊይዝ ይችላል፡፡ በአንቀጽ 2662 ላይ ይኼው ሁኔታ ተገልጿል፡፡ የማይያዙ ንብረቶች አሉን? ለምሳሌ ልብስ የጋብቻ ቀለበት አንዳንድ አገሮች ልብስና የጋብቻ ቀለበትን በማሰገደድ ማስያዣ እንዳይሆኑ በሕግ ተከልክሏል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ያመጣቸውን ዕቃዎች ይዞ ይቆያል ከማለት ውጪ ተጨማሪ የለውም፡፡ ይዟቸው የመጣው ዕቃዎች የሚለው የጋብቻ ቀለበትና ልብስን ይጨምራል ወይ የሚለው ለትርጉም የተተወ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚወስኑት፡፡ የደንበኛውና የባለ ሆቴሉ ግንኙነት ልክ ተንቀሳቃሽ ንብረት አስይዞ ገንዘብ እንደመበደር ስለሚሆን ለዚሁ በሚሆነት ሕግጋት ይተዳደራል፡፡

ስለ ተረሳ ንብረት

የተረሳ ዕቃን በሚመለከት የባለ ሆቴሉ ኃላፊነት ምን ይሆን? ለምን ያህል ጊዜስ ባለሆቴሉ ይዞ መጠበቅ ይኖርበታል? ባለቤቱ ባይመለስስ ንብረትነቱ ለማን ይተላለፋል? ላገኘው ሰው? በንብረት ሕግ መሠረት ነው የሚገዛው ወይስ በምን ሕግ?  ‹‹የአንዱ ውዳቂ፣ ለሌላው ገንዘብ ነው›› (One man’s trash is another man’s treasure) እንዲል ጥንታዊው የኮመን ሎው ወድቆ የተገኘ ዕቃን የሚመለከተው የንብረት ሕግ መርህ፡፡ በመሆኑም ያገኘው ሰው ባለቤት ይሆናል፡፡ የባለቤትነት ሁኔታው የሚወሰነው በንብረት ሕግ አማካይነት ካለሆነ በስተቀር ስለ ሆቴል ሥራ በተገለጸው ክፍል ስለዚህ ጉዳይ ፍንጭ የለውም፡፡

ደንበኛን ስለ ማባረር

ደንበኛን ከያዘው ሆቴል ማስለቀቅ የሚቻልባቸው ምክንያቶች ምን ምን ናቸው? ተከራይ ሲሆንስ ይለያልን? ሒሳብ ባይከፍልስ የት ፍርድ ቤት ይቅረብ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት አነስተኛ ጉዳዮችን የሚያዩ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን እንዲኖራቸው ማደረግ  በአንዳንድ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ለማስለቀቅ ምክንያቶቹ አለመክፈል፣ መታመም፣ ሞት፣ ከተዋዋለው ጊዜ በላይ መቆየት፣ ያልተገባ ባሕርይ በማሳየት ማወክ ወዘተ ሊሆኑ እንደሚችሉ በተለያዩ አገሮች ሕግጋት ላይ ተገልጿል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለዚህ ጉዳይ ዝምታን መርጧል፡፡

መብልና መጠጥ አቅራቢ ኃላፊነት

አንቀጽ 2658 (2) እና 2659 ላይ ከሠፈረው እንደተገለጸው ባለ ሆቴሉ ለተከራዩትም ይሁን ለሌሎች ደንበኞች የመብልና የመጠጥ የሚያቀርብ ከሆነ፣ “ስለ ጤናማ ፀባያቸውና መርዛም ላለመሆናቸው ኃላፊ ነው::” ጤናማ ፀባይ (Sound) እና መርዛማ አለመሆን (Harmless) ማለት ምን ማለት እንደሆኑ በተለይም ጤናማ ፀባይ የሌለው ምግብ ወይም መጠጥ ነው ለማለት በመለኪያነት የሚያገለግለውን መሥፈርት በሕጉ ባይመላከትም በሳይንሳዊ መንገድ ሊታወቅና ሊረጋገጥ የሚችል ነው፡፡

የባለ ሆቴሉን ኃላፊነት ሊያስቀሩ የሚችሉት የተፈጥሮ ቁጣ የሚመስሉ ከባለ ሆቴሉ አቅም በላይ የሆኑ አልበለዚያም የደንበኛው ስህተት ሲኖር ነው፡፡ የባለ ሆቴሉን ኃላፊነት የሚስቀሩ ከእዚህ ውጭ የሆነ ምክንያቶችን ዕውቅና አልሰጠም፡፡ 

አንድ ምግብ ውስጥ የሚኖር መደበኛ የምግቡ አካል ለምሳሌ አጥንት ጥርስን ቢሰብርና በወጥ ውስጥ ድንጋይ (አሸዋ) ተገኝቶ ጥርስን ቢሰብር በአጥንቱ አልፊነት ባይኖርም በአሸዋው ግን መኖር እንዳለበት  “Foreign/Natural Test” (ከምግብ ውጭ የሆነ ባዕድ ነገር) ንድፈ ሐሳብ ይባላል፡፡ ሌላውና አሁን አሁን የተሻለ ተቀባይነት እያገኘ የሄደው ‘’ምክንያታዊ ግምት ወይም ጥበቃ’’ (Reasonable Expectation Test) መለኪያን የመጠቀም ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ የምስር ክክ ወጥ ውስጥ አሸዋ ሊገኝ እንደሚችል ደንበኛውም ሊገምት ይገባል፡፡ በአሳ ወጥ ውስጥ አሳ አጥንት ሊገኝ እንደሚችል ተመጋቢው መጠበቅ አለበት፡፡ ግን ደግሞ ከአሳ የተዘጋጀ ሳንዱች ወይም ኮተሌትና የተጠበሰ አሳን ሁለቱንም እኩል አጥንት ሊኖር ይችላል ብሎ ደንበኛ እንዲገምት ይጠበቃል ወይ ለሚለው እንደ ጉዳዩ እየታዬ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲሰጡ ሥልጣን አላቸው፡፡

የፍትሐ ብሔር ሕጉ ከላይ የተጠቀሱትን መለኪያዎች አይቀበልም፡፡ የምግቡና መጠጡ አካልም ይሁን ከዚያ ውጭ፣ ባለ ሆቴሉን ምክንያታዊ ጥበቃና ግምትም በመለከያነት ሊነሱ አይችሉም፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያትና የተጎጂው ስህተት መኖር ብቻ ናቸው በባለ ሆቴሉ በኩል ሊነሱ እንዲችሉ ሕጉ የፈቀደው፡፡

የ’ሜኑ’ ሕግ

በ’’ሜኑ’’(የምግብ ዓይነትና ዋጋ ዝርዝር መግለጫ) ላይ የተገለጸው ሒሳብም የምግብ አሠራርና ይዘትም እውነት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንዳነድ አገሮች “Truth in Menu Laws” የተሰኙ ሕግጋት አውጥተዋል፡፡ ሥያሜያቸውም ዓላማቸው በሜኑ ላይ የተገለጸውና ለደንበኛው የሚቀርበው ተመሳሳይ መሆን፣ ትክክለኛነትን የሚያመለክት ነው፡፡ በተለያዩ ሕግጋት ያሉትን በማጠቃለል ለመግለጫነት የዋለ አገላለጽ ነው፡፡ ምግቡ የሚይዛቸው አላባውያን፣ የእያንዳንዳቸው መጠን፣ ለጤና ያላቸው ጠቀሜታ፣ የአዘገጃጀት ሒደት፣ ተፈጥሯዊ ወይም ኬሜካል በመጠቀም የተገኙ ስለመሆናቸው (ኦርጋኒክ ስለመሆን አለመሆናቸው) ወዘተ በትክክል ደንበኞች መረጃ መስጠትን አስገዳጅ አድርገዋል ይገባል፡፡ ደንበኛው ከጤናው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ስለመሆን አለመሆኑ የሚያሳውቅ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ አንድ የምግብ ሜኑ ምን ምን መያዝ እንደሚገባው የሚወስኑ ሕግጋት ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት የሚኑ ሕግ መኖራቸው በለተለይ ለቱሪስት ምቾት ለጠቃሚዎችም የጤና ሁኔታ ጥበቃ ለማድረግ ያግዛል፡፡

ይህን ጽሑፍ ለመቋጨት፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው የሆቴል ሥራ የውል ሕግ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ማስተዳደር ቢችልም፣ በዚህ ዘርፍ እየታየ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግን ጎደሎው ብዙ ነው፡፡ ከላይ የቀረበው ያለውንና የጎደለውን በወፍ በረር ለመቃኘት እንጂ በጥልቀት ለመዳሰስ በማሰብ አይደለም፡፡ በተለይ የሚጎድሉትን አጥንቶ ዘመኑን የዋጀ ሕግ ማውጣት በቱሪዝም ዘርፍ አገሪቱ ልታገኝ የምትችለውን ገቢ ለማሳደግ፣ የተገልጋዮችና በሆቴል ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን ግንኙነት ለማሳመር ያግዛል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...