Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአዲስ አበባ መንገዶች

የአዲስ አበባ መንገዶች

ቀን:

በያሬድ በላይ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በአንድ የአገር ውስጥ ቴሌቪዥን የተመለከትኩት ነገር ነው፡፡ ከአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ኃላፊ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅና እኔም እንደ አንድ የመንገድ ተጠቃሚ አሽከርካሪ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ የታዘብኳቸው፣ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚባክንባቸውና በሕዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ሥራዎች ናቸው፡፡

በቃለ መጠይቁ የሰማነው ኤጀንሲው ብዙ ሚሊዮን ብር የተከፈለባቸውን እንደ ዘመናዊ የመኪና ፓርኪንግ ዓይነት ግንባታዎችን ያለግልጽ ጨረታ ለተመሳሳይ ሥራ ተቋራጭ ሲሰጥ መቆየቱን ነበር፡፡ ይህንን የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ተግባር ለሕዝብና ለመንግሥት ጆሮ እንዲበቃ ያደረጉትን ዜጎች እያመሰገንኩ፣ እኔም እንደ አንድ አሽከርካሪና የትራንስፖርት ምህንድስና ባለሙያ፣ በአዲስ አባባ መንገዶች ላይ የታዘብኳቸውን ፈጽሞ አላስፈላጊ ግን ደግሞ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ የባከነባቸውንና የሚባክንባቸውን ተግባሮች እንደሚከተለው ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

በመንገድ አካፋይና ዳርና ዳር የተሠራና በመሠራት ላይ ያለ የብረት አጥር

ይህ በመንገድ አካፋይና ዳርና ዳር የተሠራና በመሠራት ላይ ያለ የብረት አጥር ፈጽሞ አላስፈላጊና ከመንገድ ትራንስፖርት ምህንድስና ሙያ ውጭ የሆነ (unnecessary & unprofessional) ሥራ ከመሆኑም በላይ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ባክኖበታል፣ እየባከነበትም ይገኛል፡፡ አጥሩ ለከፍተኛ ገንዘብ ብክነት ምክንያት ከመሆኑም በተጨማሪ የዛፍ መትከያ ቦታዎችን ይዟል፣ ነባር ዛፎች እንዲነቀሉ አድርጓል፣ እንደዚሁም መንገዶችን አቆሽሿል፡፡

ይህ ቀድሞውንም አላስፈላጊ የሆነ የብረት አጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነቃቅሎና ተሰባብሮ እንደሚጠፋ ራሳቸው አሠሪዎቹም እንደሚያውቁት አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የመንገድ ማዞሪያዎችንና መታጠፊያዎችን እንደዚሁ በብረት አጥር አዘግተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብረቱ ብዙም ሳይቆይ ተነቃቅሎ ጠፍቶ በአሁኑ ወቅት የተተከለበት ኮንክሪት ብቻ ነው የቀረው፡፡ የአሁንም እንደዚሁ እንደሚጠፋ እያወቁ ነው ሌላ የብረት አጥር የሚያሠሩት፡፡ ምንድን ነው ምክንያታቸው? ምክንያቱንና መልሱን ታታሪ ጋዜጠኞች እንዲያጣሩና እውነታውን ለሕዝብና ለመንግሥት ጆሮ እንዲያደርሱ እንደ አንድ ዜጋ በዚህ አጋጣሚ አደራ ልላቸው እወዳለሁ፡፡

የመንገድ ማዞሪያዎችንና መታጠፊያዎችን መዝጋት

የመንገድ ማዞሪያዎችንና መታጠፊያዎችን (U-Turns & Junctions) መዝጋት ሌላው የማይገባና ከመንገድ ትራንስፖርት ምህንድስና ሙያ ውጭ የሆነ ሥራ ሲሆን፣ ፈጽሞ አላስፈላጊ ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ጉዳቶች በአገርና በሕዝብ ላይ ያደረሰና እያደረሰም የሚገኝ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ጉዳቶች መጥቀስ ይቻላል፡-

  • በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎችና በተሸከርካሪ ተጓዦች ማዞሪያዎች/መታጠፊያዎች በመዘጋታቸው ምክንያት በየዕለቱ ተጨማሪ መንገድ እንዲጓዙ ተጨማሪ ሰዓት በመንገድ ላይ እንዲያጠፉ ስለሚገደዱ ጊዜአቸውና ገንዘባቸው ይባክናል፣ ከፍተኛ የሕዝብና የአገር ሀብት በየቀኑ ይጠፋል፣ የአገር ኢኮኖሚ ይጎዳል፡፡
  • ማዞሪያዎቹ/መታጠፊያዎቹ በመዘጋታቸው ምክንያት አሽከርካሪዎች ወዳልተዘጉት በሚሄዱበት ወቅት ተጨማሪ ሰዓት በመንገድ ላይ እንዲቆዩ ስለሚገደዱ፣ የመንገድ  የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጠራል ወይም ይባባሳል፡፡
  • በአጥሩ ግንባታ ሰበብ ከፍተኛ የመንግሥትና የሕዝብ (የግብር ከፋዩ) ገንዘብ ባክኗል፣ እየባከነም ይገኛል፡፡

መንገዶች ሲገነቡ ማዞሪያዎችና መታጠፊያዎች የሚደረጉላቸው ተገቢው ጥናት ተደርጎና አስፈላጊ ሥፍራዎች ተለይተው ነው እንጂ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የአንድ መንገድ ግንባታ ዲዛይን ሲዘጋጅ፣ ከሚካሄዱት ጥናቶች መካከል አንዱ መንገዱ እያስተናገደ ያለው ትራፊክ ዓይነትና መጠን (classified traffic count)፤ መነሻና መዳረሻ (Origin & Destination) ተጠንቶና ከትራፊክ ዕድገት መጠኑ (growth rate) ጋር ተገናዝቦ በአገልግሎት ዘመኑ ወቅት ሊያስተናግድ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ትራፊክ (forecasted traffic) ዓይነት መጠንና አቅጣጫ /መዳረሻ ይወሰናሉ፡፡ ከዚያም በጥናቱ ውጤት መሠረት መንገዱ በተለያዩ ቦታዎች አስፈላጊ የሆኑ ማዞሪዎችና መታጠፊያዎች እንዲኖሩት ይደረጋል፡፡

በዚህ አግባብ የከተማዋ መንገዶች ተገንብተውና አስፈላጊ ማዞሪያዎችና መታጠፊያዎች ተደርገውላቸው ሳለ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ማዞሪያዎቹና መታጠፊያዎቹ ተዘግተው መንገዶቹ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በመደረጉ ከፍተኛ ጉዳት በአገርና በሕዝብ ላይ ደርሷል እየደረሰም ይገኛል፡፡ የሚገርመው ነገር ማዞሪያዎቹንና መታጠፊያዎቹን የሚዘጋቸው መሥሪያ ቤት የገነባቸው መሥሪያ ቤት አይደለም፡፡ መንገዶቹን/ማዞሪያዎቹን የሚገነባው ወይም የሚያስገነባው ከሙያው ዘንድ አግባብ ያለውና የሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን፣ የሚዘጋቸው ወይም ከአገልግሎት ውጭ የሚያደርጋቸው ደግሞ ‹‹የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ›› የተባለ መሥሪያ ቤት ነው፡፡

ይህ አላስፈላጊና ከመንገድ ትራንስፖርት ምህንድስና ሙያ ውጭ የሆነና ከፍተኛ ገንዘብ የባከነበትና የሚባክንበት ሥራ እንዲሠራ የተፈለገበትን ትክክለኛ ምክንያት እንዲያጣሩና ለሕዝብና ለመንግሥት ይፋ እንዲያደርጉ አሁንም ታታሪ ጋዜጠኞችን አደራ ልል እወዳለሁ፡፡

ስለ አዲስ አበባ መንገዶች ካነሳሁ ዘንድ ሌሎች የታዘብኳቸውን ጉዳዮችንም የሚመለከተው መሥሪያ ቤት (የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን) ተገቢውን ትኩረት ይሰጣቸው ዘንድ በማሰብ በዚሁ ጽሑፌ ለመጠቃቀስ ወይም ለመጠቆም ወደድሁ፡-  

በጅምር የሚቀሩና የሚዘገዩ ግንባታዎች

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ተጀምሮ እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ከተከናወነ በኋላ ይቋረጥና ለዓመታት ከፊሉ ሳይገነባ ሲቀር እናያለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ ከገርጂ መብራት ኃይል እስከ እግዚአብሔር አብ ድረስ ያለው መንገድ ከፊሉ ሳይሠራ ለብዙ ዓመታት ቆሞ ቀርቷል፡፡ እንደዚሁም ከገርጂ መብራት ኃይል እስከ ሮባ ዳቦ ያለው መንገድ በከፊል ከተሠራ በኋላ ሳይጠናቀቅ ግንባታው ቆሟል፡፡ የዚህ ዓይነት ችግር ዋነኛው መንስዔ፣ በመንገድ ሥራዎች ዕቅድ፣ ዲዛይንና ግንባታ ወቅቶች (planning, design & construction stages) የተቀናጀና የተሟላ የሥራ ክንውን ዘዴ (organized & comprehensive methodology) አለመኖሩ ወይም አለመተግበሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የግንባታ ጥራት ችግር

አብዛኞቹ የአዲስ አበባ መንገዶች የግንባታ ጥራት ችግር ይታይባቸዋል፡፡ በተለይ የፍሳሽ መውረጃዎችና የማጽጃ ጉድጓዶች (drainage ditches & manholes) ከፍተኛ የጥራት ችግርና ጉድለት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የእግረኛ መንገዶችም ሳይጠናቀቁ የመቅረትና የጥራት ችግር ይታይባቸዋል፡፡

የፍሳሽ መውረጃዎች ጽዳት ችግር

የፍሳሽ መውረጃዎች በአግባቡና በወቅቱ ሲጸዱ አይታይም፡፡ በሚጸዱበትም ወቅት ቆሻሻው ከማጽጃ ጉድጓዶቹ ውስጥ ይወጣና መንገድ ዳር ተደፍቶ ለብዙ ወራት ሳይነሳ ይቆያል፣ ከአካባቢው ላይ መጥፎ ሽታን በመፍጠር በተለይም በእግረኞች ላይ ለጉንፋንና ተመሳሳይ በሽታዎች ምክንያት ይሆናል፡፡ አልፎ አልፎም ከነጭራሹ ሳይነሳ ይቀርና ሳር ሲበቅልበት ይታያል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት እየፈሰሰባቸው የሚገነቡና የሚጠገኑ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ ተገቢውን የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ከዚህ በላይ ለጠቀስኳቸው ጉዳዮች/ችግሮች የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው፣ አስፈላጊውን ተግባር እንደሚያከናውኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው <[email protected]> ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...