አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
የስታር አሊያንስ ግሩፕ አባል የሆነውና በስካይትራክስ ባለአራት ኮከብ ደረጃ የተሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈጣን ዕድገት ላይ ይገኛል፡፡ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን አረጋግጦ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አየር መንገዶች በኪሳራ በተዘፈቁበት ወቅት ብሔራዊ አየር መንገዱ ትርፋማ ሆኖ መቀጠል ችሏል፡፡ ይህ ማለት መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የገጠመው አሳዛኝ የአውሮፕላን አደጋ ትልቅ ፈተና ደቅኖበታል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ በተለይ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋና ዋና ተጠቃሽ የገጠሙት ፈተናዎች ናቸው፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ቃለየሱስ በቀለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የ2011 በጀት ዓመት እንዴት ገመገማችሁት?
አቶ ተወልደ፡- እንደሚታወቀው የ2011 በጀት ዓመት በጣም ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡ ምናልባትም በታሪካችን እጅግ ፈታኝ ወቅት ነበር ብለን እናምናለን፡፡ ዋነኛውና ከባዱ የገጠመን ችግር በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ነበር፡፡ አደጋው ክፉኛ ጎድቶናል፡፡ በአደጋው የተከሰተውን ቀውስ ሙያዊ በሆነ አሠራር ተወጥተነዋል፡፡ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሚዲያው ረድቶናል፡፡ ተጓዥ ደንበኞቻችን ከአጠገባችን ቆመዋል፡፡ በሰበሰብነው ግብረ መልስ ቀውሱን በሙያዊ አሠራር እንደተወጣነው ገልጸውልናል፡፡ ችግሩን በብልሃት ተወጥተነዋል፡፡ ነገር ግን አደጋው በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ የምንወዳቸውን ባልደረቦቻችንን፣ የምናከብራቸውን መንገደኞቻችንን በአደጋው አጥተናል፡፡ እስካሁን ድረስ በየዕለቱ እናስባቸዋለን፡፡ እንደሚታወቀው አደጋው ከደረሰ በኋላ ከዓለም ቀድመን የነበሩንን የማክስ አውሮፕላኖች በሙሉ እንዲቆሙ አድርገናል፡፡ እኛን ተከትሎ ቻይና፣ ካናዳ፣ ኢንዶኔዥያ፣ አውሮፓ በስተመጨረሻ አሜሪካ የማክስ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ከሥራ ውጪ አድርገዋል፡፡
የማክስ አውሮፕላኖች ከሥራ እንዲወጡ ከተደረገ ሰባት ወራት ሊሆን ነው፡፡ እኛ 30 ማክስ አውሮፕላኖች አዘን አምስት ተረክበን ነበር፡፡ በአደጋው አንድ አውሮፕላን ያጣን ሲሆን፣ በአጠቃላይ አምስት አውሮፕላኖች ከሥራ ውጪ ሆነውብናል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የአውሮፕላን እጥረት ፈጥሮብናል፡፡ በተጨማሪም የሮልስ ሮይስ ሞተር የተገጠመላቸው ቦይንግ 787 አውሮፕላኖች የቴክኒክ እንከን የገጠማቸው በመሆኑ የአውሮፕላን እጥረቱን አባብሶታል፡፡ ምንም እንኳ የሮልስ ሮይስ ኩባንያ ካሳ እየከፈለን ቢሆንም፣ የአውሮፕላን እጥረቱ በሥራችን ላይ ጫና አሳድሯል፡፡
ሌላው የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ በ21 በመቶ ጨምሯል፡፡ በማንኛውም ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ከተቀረው ዓለም በ35 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ በተለይ የአፍሪካ አገሮች የገጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስ በገበያችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በቻይናና በአሜሪካ መካከል የተከፈተው የንግድ ጦርነት በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህን ሁሉ ችግር ተቋቁመን ትርፋማ በመሆናችን ደስተኞች ነን፡፡
ሪፖርተር፡- አፈጻጸማችሁን በአኃዝ አስደግፈው ቢገልጹልን?
አቶ ተወልደ፡- ዕድገታችን እንደቀጠለ ነው፡፡ ገቢያችን በ2011 ዓ.ም. በዶላር በ17 በመቶ፣ በብር በ25 በመቶ አድጓል፡፡ የመንገደኛ ቁጥር በ17 በመቶ በማደግ 12.1 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም በታሪካችን ያጓጓዝነው ትልቁ የመንገደኛ ቁጥር ነው፡፡ በጭነት በኩል 432,000 ቶን አጓጉዘናል፡፡ አጠቃላይ ገቢያችን አራት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ 260 ሚሊዮን ዶላር አትርፈናል፡፡ ከታክስ በኋላ የተጣራ ትርፋችን 189 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
የምንዛሪ ለውጥ ትርፋችንን ቀንሶታል፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች በተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በአገሬው ገንዘብ የሸጥነውን ሽያጭ በዶላር ቀይረን ወደ አገራችን ለማስገባት ተቸግረናል፡፡ እንደ አንጎላ፣ ሱዳን፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዚምባቡዌ፣ በቅርቡ ደግሞ ኤርትራ ካሉ አገሮች ገንዘባችንን ለማውጣት ችግር እየገጠመን ነው፡፡ በአንጎላ 40 ሚሊዮን ዶላር፣ በሱዳን 30 ሚሊዮን ዶላር፣ በዚምባቡዌ 15 ሚሊዮን ዶላር፣ በኤርትራ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ተይዞብናል፡፡
በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በየአገሩ የተያዘብን ገንዘብ ብዙ ችግር እየፈጠረብን ነው፡፡ አንደኛ ገንዘቡን ልንጠቀምበት አንችልም፡፡ ሁለተኛ የምንዛሪ ለውጥ በሚደርግበት ጊዜ የምናወጣው ገንዘብ መጠን ይቀንስብናል፡፡ ከሚመለከታቸው መንግሥታት ጋር ውይይቶች ብናደርግም፣ እስካሁን ተጨባጭ መፍትሔ አላገኘንም፡፡ እነዚህን ችግሮች ሁሉ ተቋቁመን የአየር መንገዱን ዕድገት ማስቀጠል በመቻላችንንና ትርፋማ በመሆናችን ደስተኞች ነን፡፡ ባገኘነው ውጤት ተበረታትናል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተፈጠው የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ በሥራችሁ ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም?
አቶ ተወልደ፡- የወጪ ንግድ ቀንሷል፡፡ ይህም በጭነት ሥራችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይሁን እንጂ የጭነት አውሮፕላኖቻችንን ወደ አውሮፓና ቻይና መስመሮች በማሰማራት ጥሩ ሥራ ሠርተናል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ የካርጎ አየር መንገድ ነው፡፡ አሥር ግዙፍና ዘመናዊ የሆኑ የቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖች አሉን፡፡ ሁለት ቦይንግ 737 የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖችም አሉን፡፡ አብዛኞቹ ቦይንግ 777 አውሮፕላኖች በቻይናና አፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓና አፍሪካ የበረራ መስመር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ደቡብ አሜሪካ ገበያ ገብተናል፡፡ ወደ ማያሚ፣ ሜክሲኮ፣ ቦጐታ፣ ኪዩቶ፣ ሊማ፣ ሳኦፖሎና ፔሩ እንበራለን፡፡ የኢትዮጵያ የጭነት በረራ ፍላጎት ሲዳከም ወደ ሌሎች ሥራ ወዳለባቸው መስመሮች አውሮፕላኖቻችንን በማሰማራት እናካክሳለን፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዲኤችኤል ጋር የሽርክና ኩባንያ መሥርቷል፡፡ ከዲኤችኤል ጋር ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ተወልደ፡- የካርጎ ክፍላችንን ወደ ካርጎና ሎጂስቲክስ ሥራ እያሰፋን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከነደፈው የኢንዱስትሪያሊያዜሽን ፖሊሲ ጋር በተያያዘ የመልቲሞዳል የተሟላ የሎጂስትክስ አገልግሎት ለመስጠት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሐዋሳ፣ በአዳማ፣ በመቐለ፣ በኮምቦልቻ፣ በድሬዳዋና በጅማ ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ወደ እነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ሥራ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማግኘት ሲችሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ወደኋላ የቀረች ናት፡፡ እንደ ብሔራዊ አየር መንገድ ይህን ችግር ለመቅረፍ በዓለም ቀዳሚ ከሆነው የሎጂስቲክስ ኩባንያ ጋር ጥምረት በመፈጠር የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት ሥራ ጀምረናል፡፡ ኩባንያው በሐዋሳና በአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከፈተ ሲሆን፣ በቀጣይ በድሬዳዋ፣ በኮምቦልቻና በመቐለ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትጵያ አየር መንገድ ትርፋማ እንደመሆኑ መጠን ለሠራተኞቹ ምን ዓይነት ማበረታቻዎች እያደረገ ነው?
አቶ ተወልደ፡- በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሰው ኃይል ፍልሰት ከፍተኛ ነው፡፡ የሠለጠኑ ሠራተኞች ከኩባንያ ወደ ኩባንያ ይፈልሳሉ፡፡ ስለዚህ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማቆየት ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ አቪዬሽን አካዳሚ አለው፡፡ ባለሙያዎቹን በጥሩ ሁኔታ ያሠለጥናል፡፡ እነዚህ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ከአየር መንገዱ ጋር እንዲቆዩ እንፈልጋለን፡፡ ሠራተኛው ከአየር መንገዱ ጋር እንዲቆይ በተቻለ መጠን ደስተኛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከደመወዝ ማሻሻያ በተጨማሪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አቅም በፈቀደ መጠን ለመስጠት እንጥራለን፡፡ ከዓመታት በፊት በሠራተኛው የኑሮ ሁኔታ ላይ ባካሄድነው ጥናት የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት እጥረት ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ለይተናል፡፡ ሠራተኛውን የቤት ባለቤት ለማድረግ የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ከአሥር ዓመት በፊት ጀምረናል፡፡ የዘገየም ቢሆን 1,200 መኖሪያ ቤቶችን ገንብተን ለሠራተኞቻችን አስረክበናል፡፡ ዛሬ ካሉን 14,000 ቋሚና 3,000 የኮንትራት ሠራተኞች አንፃር ሲታይ 1,200 ቤት አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹የኢትዮጵያ መንደር›› ብለን በሰየምነው የመኖሪያ ስፍራ ቦታ ያለን በመሆኑ 11,000 አፓርትመንት መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን፡፡ በቅርቡ ዝግጅቱ ተጠናቆ ግንባታ ይጀመራል፡፡ በተቻለ ፍጥነት ግንባታውን አጠናቀን የሠራተኞቻችንን የቤት ችግር እናቃልላለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 550 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የማክስ አውሮፕላን ጉዳይ ትልቅ ችግር ፈጥሮባችኋል፡፡ አውሮፕላኑን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የአሜሪካው ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽንና የቦይንግ ኩባንያ የሚያደርጉትን ጥረት ምን ያህል በቅርበት እየተከታተላችሁት ነው?
አቶ ተወልደ፡- የተካሄዱትን ስብሰባዎች በሙሉ ተሳትፈናል ማለት አይቻልም፡፡ እኛ አቋማችንን ከመጀመሪያ ጀምሮ በግልጽ አስቀምጠናል፡፡ በእጃችን ብዙ መረጃዎች ስላሉን በግልጽ ተናግረናል፡፡ መጀመርያ አካባቢ በእኛና በቦይንግ ኩባንያ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በኋላ ግን ቦይንግ ዘግይቶ ቢሆንም እውነታዎቹን ተቀብሏል፡፡ እኛ በአደጋው የተፈጠረውን ቀውስ በመቆጣጠር፣ የአደጋ ምርመራ ሥራውን በማገዝ ሥራ ተጠምደን ስለነበርን በአሜሪካ በሚካሄደው የማክስ አውሮፕላን ብቃት እንደገና የማረጋገጥ ሒደት ላይ ብዙም አልተሳተፍንም፡፡ ዝርዝር መረጃ ባይኖረንም የብቃት ማረጋገጫ ሥራው ጫፍ ላይ መድረሱን የቦይንግ ኩባንያ አሳውቆናል፡፡ እኛ የአደጋው ተጎጂ በመሆናችን ከፊት ለፊት መሆን አንፈልግም፡፡ ከኋላ ሆነን የብቃት ማረጋገጫ ሥራው በተገቢው መንገድ መካሄዱን፣ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት መሳተፋቸውን ማረጋገጥ መርጠናል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኩባንያችሁ የአደጋ ተጎጂዎች ቤተሰቦችን ካሳ እየከፈለ ነው? ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ተወልደ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የቅድሚያ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ የተጎጂ ቤተሰቦች በአግባቡ መያዛቸውንና ተገቢው ካሳ እንዲያገኙ ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ ሥራውን ጀመርነው እንጂ አላጠናቀቅንም፡፡ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ጉዳዩ የተወሳሰበ ነው፡፡ አንዳንድ የተጎጂ ቤተሰቦች የቦይንግ ኩባንያን በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ከሰዋል፡፡ የእኛ ኢንሹራንስ ኩባንያና የቦይንግ ኢንሹራንስ ኩባንያ እየተነጋገሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ማለት ቦይንግን የከሰሱ ቤተሰቦች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሳ ማግኘት አይችሉም?
አቶ ተወልደ፡- ጉዳዩ ውስብስብ ነው፡፡ እኛ የራሳችን የመድን ዋስትና የሰጡን ኩባንያዎች አሉ፡፡ የቦይንግ ኩባንያ እንዲሁ የራሱ የመድን ኩባንያዎች አሉት፡፡ ሁለቱ የመድን ኩባንያዎች የካሳ አከፋፈሉ ላይ ይነጋገራሉ፡፡ የማክስ አውሮፕላን የዲዛይን ችግር እንዳለበት ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ተደራድረው የካሳ አከፋፈሉ እንዴት መሆን እንዳለበት ይወስናሉ፡፡ በእኛና በቦይንግ የመድን ኩባንያዎች መካከል በጋራ የሚሠሩት የማካካስ ሥራ ይኖራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱ ቤተሰቦች አሉ፡፡ እነርሱ የፍርድ ሒደቱን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የቦይንግ ኩባንያ በቅርቡ በማክስ አውሮፕላን ለደረሱ አደጋዎች ለተጎዱ ቤተሰቦች የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደመደበ አስታውቋል፡፡
አቶ ተወልደ፡- አንዳንድ የዜና ዘገባዎች ትክክል ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቦይንግ ለኢትዮጵያና ለኢንዶኔዥያ 100 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል፡፡ ሁለት ቦታ ሊከፍሉት ይችላሉ፡፡ የቦይንግ ኩባንያ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ተያያዥ ወጪዎች 100 ሚሊዮን ዶላር እንደመደበ ገልጾልናል፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ በቅርቡ በአየር መንገዱ ላይ ክሶች አቅርቧል፡፡ አየር መንገዱ ለማደግ በሚያደርገው ጥረት የበረራ ደኅንነትን ጥያቄ ውስጥ ከቷል የሚል ወቀሳ አቅርቧል፡፡ ይህ ዜና በአሶሺየትድ ፕሬስ በወጣ በማግስቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ከሴኔጋል ወደ አዲስ አበባ ለመብረር ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በገጠመው የቴክኒክ እክል ምክንያት ተመልሶ ለማረፍ ተገዷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደኅንነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል?
አቶ ተወልደ፡- ለአሶሺየትድ ፕሬስ ደጋግመን እንደገለጽነው የቀረበው ወቀሳ የውሸትና መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው፡፡ ቅሬታ ያለው፣ በተወሰደበት ዕርምጃ ቂም የቋጠረ የቀድሞ ሠራተኛ በአሜሪካን አገር ጥገኝነት ለማግኘት ሲባል የተቀነባበረ ውንጀላ ነው፡፡ ግለሰቡ በአሜሪካ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ የፈጠረው ልብ ወለድ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍታም ቢሆን የበረራ ደኅንነትን ጥያቄ ውስጥ አይከትም፡፡ አየር መንገዱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ቡድን እንደመሆኑ የጥገና ሥራውንም የሚያከናውነው ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ተቋም እንደመሆኑ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተቋማት ኦዲት ይደረጋል፡፡ የአሜሪካው ፌዴራል የአቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን (FAA)፣ የአውሮፓ ኅብረት የአቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ (EASA)፣ የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) እና አያታ ኦፕሬሽናል ሴፍቲ ኦዲት (IOSA) ምርመራ ይካሄድበታል፡፡ በተጨማሪም በምንበርባቸው አገሮች በሙሉ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የበረራ ደኅንነት መስፈርት እናሟላለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሺያኖች ለረዥም ጊዜ የሠለጠኑ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የጥገና ደኅንነት መመርያዎችን ተከትለው የሚሠሩ፣ ይህም በበላይ አለቆች የሚረጋገጥበት አሠራር ነው ያለን፡፡ ከሴኔጋል በባማኮ በኩል ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በመነሳት ላይ የነበረው አውሮፕላናችን የቴክኒክ ችግር ስለገጠመው አብራሪዎቻችን የቴክኒክ ችግር ሲፈጠር የሚደረገውን የተለመደ የበረራ አሠራር በመከተል አውሮፕላኑን መልሰው በሰላም አሳርፈውታል፡፡ ተሳፋሪዎቻችንንም በሌሎች በረራዎች አሳፍረናል፡፡ ይህ የተለመደ አሠራር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ መደበኛ ሥራችሁ እንመለስና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሆቴል ሥራ ገብቷል፡፡ ባለአምስት ኮከብ የሆነውን ኢትዮጵያን ስካይላይት ሆቴል ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ የሁለተኛውን ሆቴል ግንባታ ጀምሯል፡፡ የሆቴል ሥራ እንዴት ነው?
አቶ ተወልደ፡- የሆቴል ሥራ ለእኛ አዲስ ነው፡፡ የሆቴል ሥራ የተካንበት አይደለም፡፡ እኛ አየር መንገድ ነን፡፡ ወደ ሆቴል ሥራ የገባነው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንዱ እንደ ብሔራዊ አየር መንገድ ለአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፉን መደገፍ እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛው የትራንዚት መንገደኞቻችን የሚያርፉበት ምቹ ሆቴል ለማዘጋጀት ከማሰብ ነው፡፡ 373 ምቹ የመኝታ ክፍሎች ያሉት፣ የቻይና፣ የአውሮፓና የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤቶች ያሉት ግዙፍ ሆቴል በተሳካ ሁኔታ ገንብተን ሥራ አስጀምረናል፡፡ ሆቴሉ በጥሩ ሁኔታ ዲዛይን የተደረገ ዘመናዊ ሆቴል ነው፡፡ ከ2000 በላይ ሰዎች የሚይዝ የተሟላ የስብሰባ አዳራሽ አለው፡፡ ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አጠገብ በመገንባቱ ለገቢና ወጪ እንግዶች ምቹ ነው፡፡ ሆቴሉ ሥራ በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ለስብሰባ፣ ለሠርግና ለሌሎች ዝግጅቶች ተመራጭ ቦታ መሆን ችሏል፡፡ አዲስ አበባን ተመራጭ የቱሪዝምና የስብሰባ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡ በሆቴሉ ሥራ ደስተኞች ነን፡፡ የሽያጭ ሠራተኞቻችን የአየር ቲኬትና የሆቴል አገልግሎት በአንድ ላይ ለመሸጥ ችለዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ እንግዳ የአየር ቲኬትና የሆቴል አገልግሎት ከአንድ ቦታ መግዛት የሚያስችል አሠራር ዘርግተናል፡፡ በዚህም ለቱሪዝም ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው፡፡ የኢትዮጵያን የቱሪስት መስዕቦችን በስፋት እያስተዋወቅን ነው፡፡ የኢሌክትሮኒክ ቪዛ አገልግሎትም በመጀመራችን አዲስ አበባ ለኮንፈረንስ ተመራጭ ከተማ እንደሆነች እያስተዋወቅን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ሥራ በከፊል ተጠናቆ ለመንገደኞች ክፍት ተደርጓል፡፡ ሰፊ የሆነ ተጨማሪ ቦታ በመዘጋጀቱ የነበረውን መጨናነቅ አቃሎታል፡፡ ይሁን እንጂ የማስፋፊያው ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሥራ ቢጀመምርም እንኳ፣ ከአየር መንገዱ ፈጣን ዕድገትና የመንገደኞች ፍሰት ጋር ሲተያይ ኤርፖርቱ በቅርብ ዓመታት የሚሞላ ይመስላል፡፡ አዲስ ለመገንባት የታሰበው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጉዳይ ምን ላይ ደርሷል?
አቶ ተወልደ፡- ትክክል ነው፡፡ አሁን ያለው ኤርፖርት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይሞላል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ሊገነባ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ተመርጧል፡፡ በአዲስ አበባና አዳማ መካከል የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ውይይቶች አካሂደናል፡፡ የኦሮሚያ ባለሥልጣናት እየተባበሩን ነው፡፡ መሬቱን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው፡፡ ኤዲፒአይ የተባለው የፈረንሳይ ኩባንያ የኤርፖርት ማስተር ፕላኑን ሥራ እንዲሠራ ተሰጥቶታል፡፡ ሥራውን ጀምሯል፡፡ የንፋስ አቅጣጫ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ንድፍ ለመሥራት የንፋስ አቅጣጫውን ለረዥም ጊዜ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር የነበሩ ጉዳዮችንም ጨርሰናል፡፡ ቀጣዩ ሥራ መሬቱን ለግንባታ ማዘጋጀትና የፕሮጀክት ፋይናንስ ማፈላለግ ሥራ መሥራት ነው፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከፍተናል፡፡ በያዝነው ዓመት ተጨባጭ ዕርምጃ እንራመዳለን ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የብድር ጫና ስላለ ተጨማሪ ብድር የመውሰድ ፍላጎት የለውም፡፡ ይህ በአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክቱ ላይ ተፅዕኖ አያሳድርባችሁም?
አቶ ተወልደ፡- ዋናው ነገር የአየር መንገዱ ብድርን የመክፈል ብቃት ነው፡፡ ጥሩ ተበዳሪ ከሆንክ፣ ጠንካራ የሒሳብ መዝገብ ካለህ ብድር በራሱ ችግር አይደለም፡፡ በቅርቡ ለአንድ ኤርባስ 350 ግዥ የሚውል ብድር ለማግኘት ጨረታ አውጥተን ነበር፡፡ 23 ባንኮች ብድር ለማቅረብ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚበደረው ያለ መንግሥት ዋስትና በራሱ ነው፡፡ ታማኝ ከፋይ በመሆኑ ችግር አይገጥመውም፡፡ እንደ ጄፒሞርጋን፣ ሲቲና በርክሌይ ያሉ ግዙፍ ባንኮች ደንበኞቻችን ናቸው፡፡ የቻይና ኤግዚም ባንክም ሊያበድረን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ራዕይ 2035 የተባለ የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር አዘጋጅታችሁ ለቦርድ አቅርባችኋል፡፡ ስለ ዕቅዱ ሊነግሩን ይችላሉ?
አቶ ተወልደ፡- ራዕይ 2035 በመጪው 15 ዓመታት አየር መንገዱ የሚመራበት የዕድገት መርሐ ግብር ነው፡፡ ይህን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት ቀደም ሲል ተግባራዊ ያደረግነው ራዕይ 2025 ስኬታማ በመሆኑ ነው፡፡ በራዕይ 2025 የተቀመጡትን አብዛኞቹን ግቦች በማሳካታችን አዲስ መርሐ ግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው መርሐ ግብር አሁንም ቢሆን አዋጭ ነው፡፡ ቢዝነስ ሞዴሉ አይቀየርም፡፡ የራዕይ 2035 ዓላማ የአየር መንገዱን ዕድገት ማስቀጠል ነው፡፡ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ከዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር በመነጋገር ላይ ነን፡፡ ምናልባትም በመጪው ጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ይፋ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደሰማነው አየር መንገዱን 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ያለው ኩባንያ ለማድረግ፣ የአውሮፕላኖች ብዛት ወደ 200 ለማሳደግ አቅዳችኋል?
አቶ ተወልደ፡- እነዚህ ቁጥሮች ተከልሰዋል፡፡ ምናልባትም ከዚያም ከፍ ሊል ይችላል፡፡ መጨረሻ የደረስንበት ቁጥር አሁን እጄ ላይ የለም፡፡ ከጠቀስከው ቁጥሮች ትንሽ ከፍ ይላል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድን በ2035 የት ደርሶ ማየት ይፈልጋሉ?
አቶ ተወልደ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ መድረክ ቀዳሚ ሆኖ ማየት እንፈልጋለን፡፡ ዛሬ ከዓለም 46ኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በ2035 በ20ኛ ተራ ቁጥር ላይ እንዲሠለፍ የማድረግ ራዕይ ሰንቀናል፡፡