‹‹ዋተር ፎል›› በሚል መጠሪያ ሥራ የጀመረው አገር በቀል ሆቴል፣ ከአንድ ዓመት ተኩል ቆይታ በኋላ ‹‹ቱሊፕ ኢን›› በሚል ስያሜ ወደ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴልነት መሸጋገሩን አስታወቀ፡፡
ባለ ሦስት ኮከብ ደረጃ ያለው ይኸው ሆቴል፣ ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ለማግኘት አሥር ወራት የፈጀበት ሲሆን፣ በውስጡም ደረጃቸውን የጠበቁ ፈጣን የኢንተርኔት፣ የመኝታ አገልግሎት እንዲሁም የመሰብሰቢያና የመመገቢያ አዳራሾችን እንዳሟላ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ኦሎምፒያ አካባቢ የሚገኘው ‹‹ቱሊፕ ኢን›› ሆቴል ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማደግ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረግ እንዳስፈለው ገልጿል፡፡
ከ120 በላይ የሥራ ዕድል እንደፈጠረና ለሠራተኞቹም ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንደገባ የገለጹት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ አየለ የቱሊፕ ኢን ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሆቴሉ መስከረም መጀመርያ ላይ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገለጻ ከአገር በቀል ሆቴልነት ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ሆቴልነት በሚቀየርበት ጊዜ ሆቴሉ ሥራ አላቋረጠም ነበር፡፡
‹‹የብራንዱ ዋናው መሠረታዊ ነገር ንፅህና ነው›› ያሉት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ፣ ለሠራተኞችም ንፅህና ላይ ትኩረት በማድረግ ሥልጠና መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ሬስቶራንት፣ የእንግዳ መቀበያ፣ ፈርኒቸር እንዲሁም የማረፊያ ክፍሎች በቅየራው ወቅት ከተስተካከሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዲሁም የዚህ ፕሮጀክት አማካሪ አቶ ቁምነገር ተከተል በበኩላቸው፣ ሆቴሉ ባለ ሦስት ኮከብ ዓለም አቀፍ ደረጃን ለማግኘት መሠረታዊ መሥፈርቶችን እንዳሟላ ገልጸው፣ መሥፈርቶቹም ከምግብና መጠጥ ጋር፣ ከመኝታ አቅርቦት ጋር፣ እንዲሁም ከእንግዳ መስተንግዶና አቀባበል ጋር እንደሚያያዙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴሎች ሊያሟላቸው ከሚገቡ መሥፈርቶች መካከል፣ እንግዳው ለምሳሌ የቢዝነስ ተጓዥ ከሆነ ሊፈልጋቸው የሚችሉ ውድ ያልሆኑ ነገር ግን መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች ተሟልተው መቅረባቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹ይህ ሆቴልም እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች አሟልቷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከዲዛይን ጀምሮ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመሥራት ይቀላሉ፡፡ ነገር ግን ነባር ሆቴሎችን የመቀየር ፕሮጀክት በሚሆንበት ጊዜ ከባድ ሥራን ይጠይቃል፤›› በማለት አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፋቸውንም አቶ ቁምነገር ገልጸዋል፡፡
እንደ ምሳሌ ያነሱትም የሆቴሉ ሕንፃ በሚገነባበት ወቅት ያልተሟሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ሲሆን፣ በዚህ ፕሮጀክም ከኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከኃይል አቅርቦት ጋር የሚነሱ ችግሮች ፈታኝ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዲዛይን በጥንቃቄ አለመሠራቱ ትልቅ ፈተና ሆኖብን ነበር፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን ለማሻሻል ሞክረናል፤›› በማለት ሲገልጹ፣ የኃይል አቅርቦቱን በሚመለከትም፣ ‹‹ሆቴሉ በፊት ይጠቀም የነበረው የኃይል አቅርቦትና አሁን ወደሚገኝበት ደረጃ ሲያድግ የሚጠቀመው የኃይል መጠን የተለያየ በመሆኑ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከ80 በመቶ በላይ መሥፈርቶቹን ማሟላት በመቻሉም የብራንዱን ፈቃድ እንዳገኘ ጠቅሰዋል፡፡
በመጪዎቹ ሁለት ወራት የሙከራ ጊዜውን እንደሚያገባድድ የሚገልጹት አማካሪው፣ ሆቴሉ የሚሰጠውን አገልግሎት፣ ሕንፃውን እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የምንገመግምበት ጊዜ ይሆናል ብለዋል፡፡ ‹‹አገር በቀል ሆቴሎች በሚሠሩበት ወቅት ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቀው ከተሠሩ ወደፊት ለውጦችን ለማድረግ አስቸጋሪ አይሆንባቸውም፡፡ በቀላሉ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ መሄድ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ሆቴል በሉፍ (በሉቨር) ሆቴል ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩ በርካታ ብራንዶች አንዱ ሲሆን፣ ቱሊፕ ኢን፣ ሮያል ቱሊፕ እንዲሁም ጎልደን ቱሊፕን በማካተት በዘጠኝ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሃያ ስድስት ሆቴሎችን በሥሩ በማካተት እንዲሁም በ54 አገሮች ውስጥ በድምሩ ከ1,500 በላይ ሆቴሎች ያሉት መነሻው ከፈረንሳይ የነበረና ለቻይና የተሸጠ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡