Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሸገር ፓርክ ይዞታ ውስጥ ለተጠቃለለው የፓርላማ ሕንፃ መገንቢያ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጥ አስተዳደሩ...

በሸገር ፓርክ ይዞታ ውስጥ ለተጠቃለለው የፓርላማ ሕንፃ መገንቢያ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጥ አስተዳደሩ ወሰነ

ቀን:

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ለአዲሱ የፓርላማ ሕንፃ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል መግባቱ ተገለጸ

የበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚያስገነባው ግዙፉ የሸገር መናፈሻ ልማት ይዞታ ውስጥ እንዲካተት ለተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ የሕንፃ ማስገንቢያ፣ ምትክ ቦታ በአቅራቢያው እንዲሰጥ አስተዳደሩ መወሰኑ ታወቀ፡፡

ሪፖርተር ከከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽፈት ቤት ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ምክር ቤቱ ሊያስገነባ ላቀደው አዲስ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ቢሮዎችን የሚያካትት ግዙፍ ሕንፃ አራት ኪሎ አካባቢ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ 69 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥጦት የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ግንባታው የሚጠይቀውን ወጪ ማግኘት ባለመቻሉ ቦታው ለዓመታት ሳይለማ ታጥሮ በመክረሙ የከተማ አስተዳደሩ በ2011 ዓ.ም. መልሶ ወስዶታል፡፡

ይኸው ለምክር ቤቱ ሕንፃ ማሠሪያ ተሰጥቶ የነበረው ቦታ ሰሞኑን የከተማ አስተዳደደሩ ባስጀመረውና ሸገር ፓርክ በተሰኘው ተፋሰስ ተኮር የመናፈሻ ልማት ይዞታ ውስጥ ተካቷል፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የተጠቀሰውን ቦታ በመናፈሻ ልማት ይዞታ ውስጥ እንዳይካተትና ለምክር ቤቱ እንዲመለስ በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም. ለከተማ አስተዳደሩ ማሳሰቢያ ደብዳቤ ጽፈው የነበረ ቢሆንም፣ የከተማ አስተዳደሩ ግን ለመናፈሻ ልማቱ ቅድሚያ በመስጠት ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ለመገንባት ላቀደው ሕንፃ የሚሆን ተመሳሳይ መጠን ያለው ቦታ በቅርብ ርቀት ውስጥ ተፈልጎ ለምክር ቤቱ እንዲሰጥ መወሰኑን ከከንቲባው ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በምትክነት በቀረቡት የቦታ ምርጫዎች ላይ ምክር ቤቱና አስተዳደሩ መስማማት አለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምክር ቤቱ በተነጠቀው ቦታ ላይ ግንባታውን በፍጥነት ለማከናወን ያልቻለው ለታቀደው የሕንፃ ግንባታ የሚያስፈልገውን አጠቃላይ 2.7 ቢሊዮን ብር ወጪ በወቅቱ ማግኘት ባለመቻሉ ቢሆንም፣ ለሕንፃው ዲዛይንና የአፈር ምርመራ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳወጣበት ሪፖርተር ያገኘው የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

ምክር ቤቱ ለማስገንባት ያቀደው ግዙፍ ሕንፃ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከፌዴራል መንግሥት ካዝና ወጪ ለማድረግ በወቅቱ ፍላጎት አልነበረም፡፡

የግንባታ ውጥኑን ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳም ግንባታው የሚጠይቀውን ወጪ ከመንግሥት ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን በመገንዘብ ከውጭ አጋሮች በዕርዳታ ለማግኘት በማሰብ ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይሳካላቸው በ2011 ዓ.ም. ከአፈ ጉባዔነታቸው ለቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎ የአቶ አባዱላን ፈለግ በመከተል ሰሞኑን ባደረጉት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ፣ የምክር ቤቱን ሕንፃ ለማስገንባት ቀደም ሲል ተገምቶ ከነበረው አጠቃላይ ወጪ በእጅጉ የላቀ ገንዘብ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት በስጦታ ለማበርከት ቃል እንደገባላቸው ታውቋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬስት መንግሥት ለምክር ቤቱ አዲስ የሕንፃ ግንባታ በስጦታ ለማበርከት ቃል የገባው ገንዘብ መጠን 370 ሚሊዮን ዶላር ወይም አሁን ባለው የብር ምንዛሪ ተመን መሠረት 10.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

የሕንፃ ግንባታውን ወጪ ለመሸፈን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ቃል የገባው በአፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የልዑካን ቡድን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሥራ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

የሕንፃ ግንባታውን ወጪ ለመሸፈን ከተገባው ቃል በተጨማሪ፣ በሁለቱ መንግሥታት ምክር ቤቶች መካከል ትብብርን ለማሳደግና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ታውቋል፡፡

በቅርቡ በታላቁ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተመረቀውን አንድነት ፓርክ ለማልማት የወጣውን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በስጦታ መልክ የሸፈነውም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ኢንቨስተመንት የለገሀር አካባቢ የሪል ስቴት ልማት ላማከናወን በመስማማት የቅድመ ግንባታ እንቅስቃሴ የጀመረውም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...