Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ጎን ለጎን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከግብፁ...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ጎን ለጎን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከግብፁ አቻቸው ጋር ሊመክሩ ነው

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሞስኮ እንደሚያቀኑና ከጉባዔው ጎን ለጎንም በታላቁ የህዳሴ ግድብ አለመግባባቶች ዙሪያ እንደሚመክሩ ተሰማ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉዞና ከግብፅ ጋር ያደርጉታል የተባለውን የጎንዮሽ ውይይት በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለው አመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. አንስቶ በሩሲያ የሚካሔደውን ጉባዔ ለመታደም ወደ ሥፍራው እንደሚያቀኑ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

የጉዞው ዓላማ ሩሲያ ከአፍሪካ አገሮች ጋር የሚኖራት ትብብርን በተመለከተ የሚደረገውን ስብስባ መታደም ቢሆንም፣ ከዚሁ ስብሰባ ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሩሲያ አቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግብፁ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር በታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከሰሞኑ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ውይይት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቅን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ በውኃ ሚኒስትሮቻቸውና በቴክኒክ ባለሙያዎቻቸው አማካኝነት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት፣ ከሳምንት በፊት ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ግብፅ ሦስተኛ አደራዳሪ ወገን እንዲገባ መጠየቋና ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበውን ጥያቄ እንደማትቀበለውና ያለ ሦስተኛ ወገን ልዩነቶች ላይ መስማማት እንደሚቻል  መግለጿ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባለፈ ግብፅ ሳይንሳዊ አመክንዮችን ላለመቀበል ስትል የድርድሩን መንፈስ ማስተጓጎል የተለመደ ተግባሯ እንደሆነ በመግለጽ ኢትዮጵያ መተቸቷ ይታወሳል፡፡

በቅርቡ በካይሮ ተካሂዶ በነበረው የሚኒስትሮቹ ስብስባ ላይ ግብፅ በተናጠል ካቀረበችው ሰነድ ይዘቶች መካከል በኢትዮጵያ መንግሥት በእጅጉ ከተተቹት ነጥቦች ዋነኛው፣ ግብፅ የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆንና ኢትዮጵያም በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ እንድትለቅ የሚለው ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ 165 ሜትር መሆኑን ማረጋገጥና የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ እንድትለቅ ባቀረበችው የተናጥል የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ሰነድ መጠየቋ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ባለፈም የህዳሴ ግድቡ የኃይል ማመንጨት ተግባር የግብፅ ባለሙያዎች በሚወከሉበት የጋራ ቡድን መመራት አለበት የሚል ሐሳብም ተካቷል፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ሉአላዊነትን የሚዳፈር፣ በትብብር ላይ ተመሥርቶ ከተጀመረው ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት መንገድ ያፈነገጠ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርገዋለች፡፡ የሱዳን ስብሰባ ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ጉዳዩ ቡድን ዘጠኝ በመባል ለሚታወቀው፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ዋና የደኅንነት ኃላፊዎች አባል ለሆኑበት ቡድን እንደሚመራ ቢጠበቅም፣ ግብፅ የሦስተኛ ወገን አማራጭን አንስታለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...