Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን ተባብረን ከችግር አዙሪት እናውጣት!

ኢትዮጵያ ከየአቅጣጫው በተለያዩ ችግሮች ተወጣጥራለች፡፡ ለአንዱ ችግር መፍትሔ ሳንሰጠው ሌላው በላዩ ይደረብብናል፡፡ አንዱን ቀዳዳ ሳንደፍነው ሌላ ቦታ ቀዳዳ ይፈጠራል፡፡ ለፖለቲካችን መፍትሔ ሳንሰጠው በሌላ በኩል ኢኮኖሚያችን ማፍሰስ ይጀምራል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት እናድርግ ብለን ዞር ከማለታችን፣ ፖለቲካችን ይዝረከረክና የሚሰበስበው ያጣል፡፡ ብቻ ሁሉ ነገር እያፈሰሰብን ተቸግረናል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ላለፉት ዘመናት ስናንከባልላቸው የመጡ የቤት ሥራዎቻችንን ሳናገባድድ፣ በየጊዜው አዳዲስ የቤት ሥራዎችን እየጨመርን ጉዟችን ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ተቸግረናል፡፡ ኢትዮጵያም በአዲስ ተስፋ ወደፊት ከማስኬድ ይልቅ አስቸጋሪ ወደሆነ የችግር አዙሪት ውስጥ ከተናት ከዕለት ወደ ዕለት አካሄዳችን አስጊ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁሉም በየፊናው መስከን ተስኖት በዘፈቀደና በማንአለብኝነት የፈለገውን እየተናገረና እያደረገ ይኸው አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ አሉን የምንላቸው ውድ እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ፣ ሰብዓዊነትና ተቻችሎ መኖር ቦታ ሳይሰጣቸው አገር ላይ አደጋ እየተደቀነ ነው፡፡ ችግሮች በራሳቸው መፍትሔ ስለማያመጡ፣ ሁሉም ረጋ ብሎ ቢያስብ መልካም ነው፡፡

አገር ሥጋት ላይ መሆኗን ሁሌም ከመናገር ወደኋላ አላልንም፡፡ ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው፣ አሁን የምንሄድበት የእውር ድንብር አካሄድ የት እንደሚያደርሰን ስለሚታወቅ መስከን አዋጪ ነው፡፡ ምንም እንኳን አሁን ያለንበት ችግር እያሳሳቀ ሳይሆን እያስለቀሰ የሚወስደን በመሆኑ፣ በኋላ ላይ መመለስ የማንችለው ችግር ውስጥ ገብተን ኪሳራ ውስጥ ከመዘፈቃችን በፊት ልናስብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም በመሆኗ ሁላችንም ይመለከተናል፡፡ አሁን አሁን አገራችን ላይ አጉራ ዘለልና ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ግለሰቦች አብዛኛውን መድረክ ተቆጣጥረው አገሪቷን የኋላ ሲወስዷት፣ እንዳላየና እንዳልሰማ መቀመጥም አዋጭ መንገድ አይደለም፡፡ እንደውም በርካቶች በአጉራ ዘለልነትና በጥራዝ ነጠቅነት ከሚያጠፉት ጥፋት ባልተናነሰ፣ በአገራችን ጉዳይ ተመልካች ሆነን ነገሮች ሲበላሹ ቁጭ ብለን የምንመለከተው የባሰ ጥፋት ማስከተላችን አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም የመከራው ዝናብ ሲመጣ ሁላችን ላይ መውረዱ ስለማይቀር ነው፡፡ ለዚህ ነው አገሬን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ አገር ወዳድ መሆኑን በተግባር ማሳየት ያለበት፡፡ እርግጥ ነው ማንም አገሩን ለማገልገል ሲነሳ፣ መንገዱ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አገሩ ሁሉ በጭፍን ብሔርተኝነትና በዘር ፖለቲካ ተመርዞ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሆኖም አገሪቷ ወዳልተፈለገ መንገድ ስትሄድ ቁጭ ብሎ መመልከት ከትርፉ ኪሳራው ይልቃል፡፡

ለዓመታት አገራችንን ከችግርና ከመከራ ተላቃ ባናያትም፣ በርካታ መቀየር የምንችልባቸውን ዕድሎች ማክሸፋችን ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ በቅርቡ በአገራችን የመጣው ለውጥ ተስፋ ያለመቁረጣችን ውጤት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም የምናገኘውን ዕድል እያባከንን፣ አገራችንን በችግር መጥበስ ተገቢ አካሄድ አይደለም፡፡ አሁን በአገራችን የመጣው ለውጥ ሁላችንም በውስጣችን አገራችን ወደ ተሻለ የዕድገትና የብልፅግና መንገድ ገብታ እንድትለወጥ ባለን መሻት የመጣ ነው፡፡ አሁን የተሰጠንን ዕድል መጠቀም ካልቻልን ግን ነገሮች ጭራሽ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ አምርተው እንዳያከስሩን ያሳስባል፡፡ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንደሚባለውም ለሁላችን ተስፋ የነበረው ለውጥ ተቀልብሶ ችግር ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን የመጣው ለውጥ በአንድ ወገን የመጣ እንዳልሆነ ሁሉ፣ በቀጣይ ስለምንጓዝበትም መንገድ ከአንድ ወገን ከመጠበቅ ይልቅ ሁላችንም የድርሻችንን እናዋጣ፡፡ ያለበለዚያ የችግሩ ዳፋ ለሁላችንም ይተርፋል፡፡

ለውጡ የተወለደው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ኢሕአዴግ የፓርላማውን ሙሉ መቀመጫ በተረከበ ማግስት ከሕዝብ በተነሳው ከፍተኛ ተቃውሞ ነው፡፡ በወቅቱ ለዓመታት ተጠራቅመው የመጡ ጭቆናዎችና ብሶቶች በሕዝቡ ፊት አውራሪነት እንዲመለሱ ጥያቄዎች በመቅረባቸው፣ ኢሕአዴግ ሳይወድ በግዱ ለውጥ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ነገሮች እንደነበሩ መቀጠል ስላልቻሉም፣ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ኢሕአዴግ አዳዲስ ሰዎችን ወደ ሥልጣን አምጥቶ የለውጥ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ለውጡ ከአጀማመሩ በርካቶች ተስፋ እንዲሰንቁ ቢያደርግም፣ አሁን አሁን ያለው አካሄድ ግን አስፈሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዓመታት ታፍነው የነበሩ ድምፆች በአደባባይ መሰማታቸው፣ ሁሉን አቃፊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጅማሮ ተደርጎ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ማንም ያለምንም መከልከል ሐሳቡን የማንፀባረቅ ተፈጥሮአዊ መብት አለው፡፡ ሆኖም በለውጥ ስም እንደፈለጉና እንደልብ የመሆን አባዜ፣ ኋላ ላይ ሥርዓተ አልበኝነትንና ማን አለበኝነትን ወልዷል፡፡ በዚሁ የለውጥ እሳቤ መንግሥት ዋነኛ የሆነውን ሕግ የማስከበር ሥራውን መወጣት እየተሳነው መጥቷል፡፡ ወትሮውንም ቢሆን ጠንካራ የሚባል ተቋም በሌለበት አገር ሕግ ማስከበር ከባድ መሆኑ ቢታወቅም፣ ከለውጡ ጋር የመጡ ነፃነቶችን በሕግና በሥርዓት መቆጣጠር አቅቶን በርካታ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ በፊት የነበሩን መልካም እሴቶች ላይ ከመጨመርና ከማከማቸት ይልቅ፣ እነሱን እያፈራረስን የሚከፋፍሉንና የሚለያዩን ሐሳቦች ላይ ማተኮራችን እየጎዳን ነው፡፡ ወትሮንም ቢሆን እዚህ ያደረሰን አንድነታችንና መተባበራችን መሆኑን እያወቅነው፣ በመቃቃርና በግጭት የኋልዮሽ ጉዞውን ከተያያዝነው ሰነባበትን፡፡

ከፊታችን በርካታ ፈተናዎች ይጠብቁናል፡፡ ለአብነት አገራዊ ምርጫ ለማድረግ የወራት ዕድሜዎች ብቻ ይቀሩናል፡፡ እንኳን እንደዚህ በተከፋፈለ አገር ይቅርና በሰላማዊ አገርም ምርጫ ማድረግ የራሱ የሆኑ ፈተናዎች አሉት፡፡ ለአብነት ምርጫን አነሳን እንጂ ኢኮኖሚው በራሱ አደገኛ ሕመም ውስጥ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ፖለቲካችን እንደዚህ ታሞ፣ ኢኮኖሚያችን ደግሞ ክፉኛ ስቃይ ውስጥ እያለ ፈታኝ የሆነውን ምርጫ ማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከማንም አይሰወርም፡፡ ለዚህ ነው ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ ቆም ብለን እናስብ የምንለው፡፡ የተሳፈርንበት የለውጥ ባቡር የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ያሳፈረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአንዳችን ፍላጎት ከሌላችን ይለያል፡፡ በዚህ ወቅት ግን የራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮር እንጓዝ ብንል፣ በፍላጎቶቻችን ፍትጊያ የተሳፈርንበትን የለውጥ ባቡር ወዳልሆነ አቅጣጫ ልንወስደው እንችላለን፡፡ ስለዚህ ሁላችንንም የሚያዋጣንና የሚያጠናክረን፣ የጋራ የሆኑ ነገሮቻችን ላይ ማተኮራችን ነው፡፡ ለጊዜው ቢያንስ የተሳፈርንበት ባቡር አንድ በመሆኑ፣ የምንሄድበትን አቅጣጫ እንድናውቅ በሰከነና በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መደማመጥ እንጀምር፡፡ ያለበለዚያ ባቡሩን እኔ ልምራ፣ እኔ ልምራ በሚል አላስፈላጊ ፉክክር መስማማት አቅቶን የባቡሩን ጉዞ እናስተጓጉለዋለን፡፡ ባቡሩ ውስጥ እስካለን ድረስ ለሁላችንም የሚጠቅመውን መንገድ መከተል እንጂ፣ የራሴን ፉርጎ ይዤ እንዳሻኝ እሆናለሁ ማለት አያዋጣንም፡፡ በመሆኑም አሁን የተገኘውን የለውጥ አጋጣሚ ተጠቅመን፣ ሁላችንም የምንኮራባት ኢትዮጵያን እንገንባ፡፡ ኢትዮጵያንም ተባብረን ከችግር አዙሪት እናውጣት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...