Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪዎች ባደረጉት ረሃብ አድማ አንዳንዶቹ ሆስፒታል መግባታቸው ተጠቆመ

በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪዎች ባደረጉት ረሃብ አድማ አንዳንዶቹ ሆስፒታል መግባታቸው ተጠቆመ

ቀን:

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ከተፈጠረው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ፣ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችና አባላት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ለአራት ቀናት ባደረጉት የረሃብ አድማ፣ አንዳንዶቹ ሆስፒታል መግባታቸው ተጠቆመ፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ በአግባቡ እያስተናገዳቸው እንዳልሆነና ፍትሕ እንደተነፈጉ የሚናገሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችና አባላት፣ የአሥራት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጋዜጠኛ ጌታቸው አምባዬ፣ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራሱ) አባልና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ ከመስከረም 30 ቀን እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በረሃብ አድማ ማሳለፋቸው ተገልጿል፡፡

የአብን ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ስለፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች እስረኞች የረሃብ አድማ በሚመለከት ሪፖርተር አነጋግሯቸው እንደገለጹት፣ አመራራቸው አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በርካታ አባሎቻቸው ላለፉት አራት ቀናት ረሃብ አድማ አድርገዋል፡፡ አራት ቀናት ከውጭም ሆነ ከውስጥ ምንም ዓይነት ምግብ አላገኙም፡፡ ይኼ በመሆኑ በተለይ አቶ ክርስቲያን ተጎድቷል፡፡ በጣም በመድከሙም ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ገብቶ ሕክምና ተደርጎለት መውጣቱን ተናግረዋል፡፡

ከሰኔ 15ቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ፣ ላለፉት አራት ወራት አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በእስር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ የባለአደራው ምክር ቤት (ባልደራሱ) አባላት፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም እስረኞች፣ ‹‹ፍትሕ አላገኘንም›› በማለት የረሃብ አድማውን ቢያደርጉም፣ አቶ ክርስቲያን ግን በጤናው ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠመው ገልጸዋል፡፡

አብን ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ እየተከታተለው ቢሆንም፣ የንቅናቄው አባላት፣ ደጋፊዎቻቸው፣ የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከታሰሩት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ሊቀመንበሩ እንደገለጹት ከዛሬ ጥቅምት 5 ቀን እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሦስት ተከታታይ ቀናት የማኅበራዊ ድረ ገጾች ዘመቻ ይጀመራል፡፡ ‹‹መንግሥት ሳናጣራ አናስርም›› ቢልም አባሎቻቸው፣ አመራሮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ላለፉት አራት ወራት በተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተጉላሉ በመሆኑ፣ የሚፈጸምባቸውን ግፍ የታሰሩትን ሰዎች ምሥል በማድረግ እንደሚያጋልጡ ተናግረዋል፡፡ ስለታሳሪዎቹ መረጃ መጻፍና እነሱን የሚያስታውሱ መጣጥፎችን በመጻፍና እንዲፈቱ በመንግሥት ላይ ግፊት የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በታሰሩና የረሃብ አድማ ያደረጉት የባልደራሱ አባላት፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በቁጥር 59 መሆናቸውን የጠቆመው፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው፡፡

ከባህር ዳሩና ከአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በአግባቡ እያስተናገዳቸው ባለመሆኑ፣ የረሃብ አድማ ማድረጋቸውንና ከ59 እስረኞች ሦስቱ ብቻ ጠያቂ እንዳላቸው አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የረሃብ አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ከመንግሥት አካል የተሰጣቸው ምላሽ እንዳለ የተጠየቁት የአብን ሊቀመንበር፣ የተለያየ ጥረት ቢደርጉም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምናልባት በባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ ጉዳይ ታስረው እንደነበሩትና በዋስ እንደተለቀቁት፣ የእነሱም ጉዳይ በተመሳሳይ ሁኔታ ይቋጫል የሚል ተስፋ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በተመሳሳይ ጉዳይ ፍርድ ቤት በሚቀርቡት በእነ አስጠራው ከበደና ሲያምር ጌቱ የምርመራ መዝገብ ያሉ፣ ከ20 በላይ ተጠርጣሪዎች ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውና የሌሎቹንም ሁኔታ የሚገምቱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአዴፓ ጋር ስለመዋሃዳቸው እየተነገረ ስለመሆኑ ተጠይቀው፣ በአሁኑ ጊዜ ዕቅድም፣ ሐሳብም ሆነ ውይይት እንደሌላቸው ጠቁመው፣ የሚነገረው ሁሉ ሐሰትና በሬ ወለደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...