ከሦስት ሳምንት በፊት በሜዳውና በደጋፊው ፊት፣ የሩዋንዳ አቻውን በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ገጥሞ ሽንፈትን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ኪጋሊ ላይ ወሳኙን የመልስ ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ውጤቱ ለቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የቆይታ ጊዜ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡
በቅድመ ማጣሪያው የጅቡቲ አቻውን በጠባብ ውጤት አሸንፎ ወደ ዋናው ማጣሪያ ያለፈው የኢትዮጵያ ቡድን፣ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ሁለት ጨዋታዎችን ማለትም የማጣሪያውንና የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጎ በሁለቱም አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት መሸነፉ በብዙዎች ያልጠበቀ ነበር፡፡ ውጤቱም በምዕራብ አፍሪካዊቷ ካሜሩን አስተናጋጅነት በመጪው ዓመት ለሚከናወነው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ኢትዮጵያ ያላትን ተስፋ አጨልሞባታል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሁለት ዓመት ኮንትራት ተሰጥቷቸው ቡድኑን ሲያሠለጥኑ የቆዩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ቆይታቸውን በሚመለከት በኮንትራት ስምምነታቸው ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያን በቻን ተሳታፊ ማድረግ›› የሚል ግዴታ የተካተተ በመሆኑ በቅዳሜው የመልስ ጨዋታ የሚመዘገበው ውጤት ለአሠልጣኝ አብርሃም የቆይታ ጊዜን ሊያሳጥር አልያም ሊያስቀጥል የሚችል እንደሚሆን የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ቡድኑ ሐሙስ ጥቅምት 6 ቀን ወደ ሩዋንዳ ያመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ፣ አሠልጣኝ አብርሃምና ቡድናቸው ከሜዳው ውጭ ባላቸው ጠባብ ዕድል የሚጠቀሙ ከሆነ እሰየው፣ ካልሆነ ግን ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸው ኮንትራት እንደሚቋረጥ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኙ በሩዋንዳ አቻቸው ተሸንፈው ከማጣሪያው ውጪ የሚሆኑ ከሆነ በዚህ የውድድር ዓመት ከታዳጊው እስከ ዋናው የሴቶቹን ጨምሮ ዓለም አቀፋዊም አህጉራዊም ተሳትፎ አይኖራቸውም፡፡
በመቐለና በባህር ዳር ስታድየሞች ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገዱት አሠልጣኝ አብርሃምና ቡድናቸው ላይ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ትችትና ወቀሳ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቀድሞ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኙ የነበሩት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ቢኖረውም፣ የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ቡድን እስካሁን በነበረው ቆይታ ጠንካራና ደካማ ጎን ምን እንደሚመስል ገምግሞ ውጤቱንም ለኅብረተሰቡ አሳውቆ እንደማያውቅ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከኮሚቴው አባላት አንዳንዶቹ ‹‹አይመለከተኝም›› በሚል ዝምታን የመረጡ እንዳሉና በተለይም የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በዚህ ጉዳይ አንድ ነገር ለማለት መቆጠባቸው ግርምት የፈጠረባቸው አልታጡም፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ የቀድሞ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ፌዴሬሽኑን በአመራርነት ለማስተዳደር ሲመረጡ ለእግር ኳሱ ዕድገት የራሱ ድርሻ ይኖረዋል የሚል ተስፋ የነበራቸው ነበሩ፡፡ ምክንያቱም አቶ ሰውነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2005 ዓ.ም. ከሦስት አሠርታት በኋላ ላስመዘገበው ውጤት የአንበሳውን ድርሻ ስለሚወስዱ ልምድና ክህሎታቸው ለተተኪዎቹ አሠልጣኞች ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆናል ከሚል መነሻ የተወሰደ ስለመሆኑ ጭምር ይታመናል፡፡