በተመስገን ተጋፋው
በሰው ልጅ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምግቦችን በመሸጥ ኅብረተሰቡን ለችግር የሚያጋልጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች መኖራቸው፣ ከእነዚህም የተወሰኑት ተይዘው ምርታቸው እንዲወገድ፣ እንዲታሸግ ብሎም ግለሰቦቹም ሆኑ ድርጅቶቹ በሕግ ስለመጠየቃቸው በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ለገበያ ከማዋል ባለፈ ባዕድ ነገርን ከምግብና መጠጥ ጋር ቀላቅሎ መሸጡ የአደባባይ ሚስጢር ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሥር የሰደደውን ችግር ለመታደግና ጤናማ የሆኑ ምግቦች እንዲቀርቡ ለማስቻል የተለያዩ ፖሊሲዎች ተነድፈው ትግበራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ክፍተቶች በመኖራቸው አሁንም በዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ችግር ከሚታይባቸው ምግቦች አንዱ ሁሉም ሕዝብ የሚጠቀመው ጨው ተጠቃሽ ነው፡፡
ጥራቱን የጠበቀና በአዮዲን የበለፀገ ጨው በተለይ ለሕፃናት የአዕምሮ ዕድገትም ሆነ ጤና ወሳኝ ነው፡፡ ለእናቶችም ሆነ ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡም እንዲሁ፡፡ በመሆኑ መንግሥት በአዮዲን የበለፀገ ጨው ብቻ ገበያ ላይ እንዲውል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም ይህን ተፈጻሚ ማድረግ ቀላል አልሆነም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የጨው ምርት ደኅንነትን በተመለከተ መንግሥታዊ ከሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያካሄደው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሲስተር ሕይወት ገብረ ሚካኤል እንደተናገሩት፣ በፖታሺየምና በአዮዲን ያልበለፀገ ጨው መጠቀም ለጤና ጠንቅ ስለሆነ መንግሥት ይህንን ለመከላከል እየሠራ ይገኛል፡፡ ለኩላሊት፣ ለዕንቅርት፣ ለደም ካንሰር እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች የሚያጋልጠው በንጥረ ነገር ያልበለፀገ ጨው፣ በእርግዝና ወቅትም በልጆች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላል፡፡
ሕፃናት አዮዲን የሌለው ምግብ ሲመገቡ፣ የአዕምሮ ችግር፣ የደም ካንሰርና የአካል ጉድለት ሊገጥማቸው እንደሚችል ሲስተር ሕይወት ተናግረዋል፡፡
አዮዲን ከተለያዩ ምግቦች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ ከዋጋም ሆነ ጥቅም ላይ በስፋት ከመዋሉ አንፃር ጨውን በአዮዲን ማበልፀግ ተመራጭ በመሆኑ፣ መንግሥት የጨው አምራቾች በአዮዲን የበለፀገ ጨው ብቻ እንዲያቀርቡ ሕግ አውጥቷል፡፡ ሆኖም ይህን የማይፈጽሙ ስላሉ ጥራቱን የጠበቀ የገበታ ጨው የማይሸጡ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማጋለጥና ለሕግ በማቅረብ ከጤና ሚኒስቴርና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ጨውን በልኩ መጠቀም እንዳለበት፣ በተፈጥሮም አዮዲን ያላቸውን እንደ ወተት፣ እርጎ፣ ዕንቁላል፣ ዓሳ የመሳሰሉ ምግቦችን መመገብ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በወጣቶች ሰውነት ውስጥ ከ150 ማይክሮ ኦርጋን ያላነሰ በሕፃናት ላይ ደግሞ ከ50 እስከ 80 ማይክሮ ኦርጋን አዮዲን መገኘት አለበት፡፡
የሰው ልጅ ጤናው እንዲጠበቅ በአዮዲን የበለፀገ ጨው መመገብ ቢኖርበትም፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ጨውን ለምግብነት በማዋል ላይ የሚገኙ ድርጅቶችም በአገሪቷ ላይ ትልቅ የጤና መቃወስን እየፈጠሩ እንደሚገኙ፣ በአሁኑ ሰዓትም እንደዚህ ዓይነት ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝና ማኅበረሰቡም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ከአምራች ድርጅቶች ጋር በመሆንም መመርያና ሕጎችን ላይ በመወያየትና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር የምግብ ተቋማት ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡ በላቦራቶሪ ደረጃም ጨው ተመርቶ ካለቀ በኋላ አዮዲን እንዳለውና እንደሌለው ለማወቅ የተለያዩ ቁጥጥሮችን እያደረጉ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የትኛውም የጨው አምራች ድርጅት የሚያመርትበት ማሽንም ሆነ ማሸጊያ ፕላስቲኮች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ክትትሎችን እያደረገ ቢሆንም፣ በተናጠል ችግሩን መቅረፍ ስለማይቻል ኅብረተሰቡ እንዲያግዝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አገሪቷ ላይ ጥራቱን የጠበቀ አዮዲን ያለው ጨው አምራች ድርጅቶች ጥቂቶች እንደሆኑ፣ ከጥራት አኳያ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግና መንግሥትም ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው ተነግሯል፡፡
ለምግብነትም ሆነ ለኬሚካል ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ለጨርቃጨርቅና ተዛማጁ ኢንዱስትሪዎች የሚውል የጨው አቅርቦት አነስተኛ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በኢትዮጵያ ጨው ከሚመረትባቸው መካከል አፋርና ሶማሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአፋር ክልል የሚገኘው የአፍዴራ ሐይቅ 70 በመቶ ያክል የምግብ ጨውን እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡ በአፍዴራ ሐይቅ ላይ ያለው የጨው ክምችት እስከ 310 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስና በዓመት 500 ሺሕ ቶን ኩንታል እንደሚመረት ተገልጿል፡፡
በአፍዴራ ሐይቅ የሚኖረውን የአካባቢው ኅብረተሰብ ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አምራቾች የሚገኙ ቢሆንም፣ የምርት ሒደቱን ጨርሰው ለገበያ የሚያቀርቡት ከ40 በመቶ እንደማይበልጡና አብዛኛው ምርትም ክምችት ላይ እንደሚገኝ በውይይቱ ላይ ተነግሯል፡፡