Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና ከግዕዝ ወደ አማርኛና ትግርኛ የተተረጎሙ ሥራዎች ዳሰሳ

የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና ከግዕዝ ወደ አማርኛና ትግርኛ የተተረጎሙ ሥራዎች ዳሰሳ

ቀን:

ተሾመ ብርሃኑ ከማል

በአሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብና ተማሪው ወልደ ሕይወት ‹‹ሐተታ›› በሚል መጠርያ የሚታወቁትና በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉት ሥራዎቻቸው በተለያዩ የአውሮፓና የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ተተርጉመው ታትመዋል፡፡

የዘርዐ ያዕቆብን ሐተታ ብቻ አቶ አበበ ረታ ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመው በእንግሊዝ “ኒውስ ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያን ኒውስ” በሚባለው ጋዜጣ ላይ ያወጡ መሆናቸውን አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ፣ ‹‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብን በ1936 ዓ.ም. ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ተረጉሙት፤›› በማለት በመጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡ ፕሮፌሰር ክላውድ ሳምነር (በፈረንሣይኛና በእንግሊዝኛ 1977 ዓ.ም.)፣ አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ በ1948 ዓ.ም. ወደ አማርኛ ተርጉመው ያሳተሙትን፣ አቶ ዳንኤል ወርቁ ካሳ ዳግመኛ በ1995 ዓ.ም. አሳትመውታል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (በአማርኛ 2006 ዓ.ም.) አለቃ ያሬድ ፈንታ (በአማርኛ 2007 ዓ.ም.) የመቐለ ዩኒቨርሲቲው ብሩህ ዓለምነህ የአቶ ዘመንፈስን ትርጉም በአለቃ ያሬድና በፕሮፌሰር ጌታቸው ትርጉሞች በመታገዝ ትርጉሙን ያሻሻሉትና ያሳተሙት (2010 ዓ.ም.) ዶ/ር ሓጎስ አብርሃ (በትግርኛ፣ በ2011 ዓ.ም.) የተረጎሙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አቶ ብሩህ ዓለምነህ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና የዘርዐ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች (ከነሐተታቸው)›› በሚል 320 ገጾች ተንትነውታል፡፡ የተማሪዎች መማሪያ እንዲሆን ታስቦም የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በአንድ ዓመት ውስጥ አራት ጊዜ ታትሟል፡፡

በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሱ መጻሕፍት ሁሉ የየራሳቸው የሆነ የፊት ሽፋን ሥዕል አላቸው፡፡ ቀደም ብሎ ከተጠቀሱት ሊቃውንት በተጨማሪ አቤል ቸርነት (1985 ዓ.ም.) በላይ ጊደይ (1983 ዓ.ም.) ጣሰው አስፋው (1996 ዓ.ም.) በዶ/ር ሓጎስ አብርሃ ሲጠቀሱ፣ በፕሮፌሰር ጌታቸው ሥራም ዓለማየሁ ሞገስ (1960) ካርሎ ኮንቲ ሮዚኒ (1912 ዓ.ም.) ዳዊት ወርቁ ኪዳኔ (2004 ዓ.ም.) ኢኖ ሊትማን (1908 ዓ.ም.) ልዋም ተስፋ ልደት (1999 ዓ.ም.) ቦሪስ ቱርጊዬቭ (1997 ዓ.ም.) እና ክላውድ ሳምነር (1974 ዓ.ም.) ስለሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ መጻፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ብሩህ ዓለምነህ በተለምዶ ዋቢ መጻሕፍት በሚቀመጡበት የመጨረሻ ገጾች ባይጽፉም በግርጌ ማስታወሻ ላይ በነፕሮፌሰር ጌታቸው ከተጠቀሱት ጸሐፊያን በተጨማሪ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃን፣ ቴዎድሮስ ኪሮስ (1997 ዓ.ም.) ጠቅሰዋል፡፡ ከዳንኤል ወርቁ በስተቀር ሁሉም መቅድም፣ መግቢያ፣ ሰፋ አድርገው የጻፉ ሲሆን፣ አለቃ ያሬድ ፈንታና ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ምስጋና ጭምር አስፍረዋል፡፡ ዳንኤል ወርቁ ደግሞ እንደ መቅድምና መግቢያ ሆኖ ሊያገለግል ይችል የነበረውን አስተያየት ከትርጉሙ መጨረሻ ላይ እነ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒን፣ አባ ጁሰፔ ዳኡርቢኖን ተችቶበታል፡፡ እነ ዓለማየሁ ሞገስን አድንቆበታል፡፡

ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ማነው? የፈላስፋውን ማንነት የሚነግረን ራሱ ነው፡፡ እርሱ ራሱ የሚነግረንን የሕይወት ታሪክ በተመለከተ ከላይ ከተጠቀሱት መጻሕፍት መካከል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይል የተረጎሙት ቀጥተኛ በመሆኑ ለአንባቢ ከበድ ስለሚል አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ከተረጎሙት መውሰድ ቀለል የሚል ሆኖ ስለሚያገኘው ጸሐፊው እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡

‹‹የእኔ ትውልድ ሥር መሠረትም ከአክሱም ካህናት ወገን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኔ ክርስቶስ በተወለደ 1592 ዓ.ም. ያዕቆብ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነሐሴ 25 ቀን በአክሱም አውራጃ ከአንድ ደሃ ገበሬ ተወለድሁ፡፡ በተጠመቅሁ ጊዜም የክርስትና ስሜ ዘርዐ ያዕቆብ ተባለ፡፡ ሰዎች ግን ወርቄ ብለው ይጠሩኝ ነበር፡፡›› (ገጽ ሁለትና ሦስት)

በዓለም ስሙ ወርቄ በክርስትና ስሙ ዘርዐ ያዕቆብ የሚባለው አክሱማዊ ከሕፃንነት ዕድሜው ጀምሮ አስተዋይ እንደነበረና ከመሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት እስከ መጻሕፍት ትርጓሜ እንደተማረና በተለይም ከፍተኛ ትምርት ላይ ሲደርስ ከታወቁ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትና ከፈረንጆች መማሩንና ከተማሪነት ዕድሜው ጀምሮ በትርጓሜዎቹ ላይ ቅሬታ እንደነበረው ይነግረናል፡፡ ሆኖም ቅሬታውን እስኪያድግ በልቡ ያዘ እንጂ ለማንም አልተናገረም ነበር፡፡ ተምሮ ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀል ግን ወልደ ዮሐንስ የሚባል ምቀኛ ተነሳበት፡፡ ይህም ሰው ከአፄ ሱስንዮስ ጋር አጣላው፡፡ በመጣላቱም አገሩን (የትውልድ ሥፍራውን) ጥሎ ወደ ሸዋ መጣ፡፡ ዋሻም ውስጥ ሆኖ ሐተታውን ጻፈ፡፡ የዘርዐ ያዕቆብን አስደናቂና አስደማሚ ፍልስፍና በግል አንብቦ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህም ሆኖ ደግሞ ‹‹ይህ ፈላስፋ አንድም ታሪኩን ሰርቆ፣ ካልሆነም በብዕር ስም የጻፈ ፈረንጅ እንጂ እንዲህ ያለ ፈላስፋ ኢትዮጵያ ሊኖራት አይችልም፤›› የሚሉ ፈረንጆች አሉ፡፡ የፈረንጁን ማንነት የሚገምቱም አይጠፉም፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱ ታሪካችንን ሲሰርቁ፣ የራሳችንን ሥራዎች እንደ ቅርጫ ሥጋ መድበው ለሌሎች ሲከፋፍሉ፣ ቁጥራችንን፣ ፊደላችንን፣ እስከ ዓረብ አገር የዘለቁትን ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶቻችንን ‹‹ይህ የእዚህ ነው፣ ይኼኛው ደግሞ የእዚህ፤›› እያሉ በማን አለብኝነት ሲመድቡ፣ እያየን ደግሞ በመናኛ ልዩነቶች እየከፋፈሉ ወደ መሠረታዊ ጉዳያችን እንዳናተኩር ሲያደርጉ፣ እኛን ተመሪ፣ ራሳቸውን መሪ ሲያደርጉ፣ እኛን ለተረጅነት፣ እነሱን ለረጅነት ሲያደርሱ በእርግጥስ ዘርዐ ያዕቆብ ፈረንጅ ነው ቢሉ ማን አለባቸው? ‹‹ታዝቦ ተራራ ሸበቶ ራሱ፣

ቢስቅ ያምርበታል በረዶ ነው ጥርሱ፤›› በማለት አቶ መንግሥቱ ለማ በግጥም ጉባዔ እንደገለጹት በእኛ ድክመት ቢስቁስ ማን ሃይ ሊላቸው ይችላል? የእኛው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ በነበረበት ዘመን (እ.ኤ.አ. 1592 እስከ 1685) በአውሮፓ፣ በእስያና በአሜሪካ ዝነኛ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ ከነዚህም ፈላስፎች መካከል ከዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን ለማውሳት ብንሞክር እንኳንስ በሥራቸው ለስማቸው ቦታ ይጠበናል፡፡ ሁሉም ፈላስፎች ግን 16ኛውና 17ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩና እንደኛው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ በጭፍን ማመንን ሽረው ምክንያት ባለው መንገድ ማመንን ያስተማሩ ናቸው፡፡ 1694 እስከ 1778 የነበረው ፈረንሣዊው ቮልቴር፣ 1711 እስከ 1776 የነበረው ዴቪድ ሂዩም፣ 1737 እስከ 1809 የነበረው ቶማስ ፔን የመሳሰሉት ሊቃውንት የኒያን ፈላስፎችን ጽንሰ ሐሳብ ያዳበሩ ናቸው፡፡ ከነቮልቴር ቀጥሎም እነሄግልና ካንት ከነሄግል በኋላም እነ ካርል ማርክስ ሳይንሳዊ ይዘት ሰጥተውታል፡፡

‹‹ሰው በልማድ ሳይሆን በመመራመር መኖር አለበት›› ብሎ ዘርዐ ያዕቆብ እንዳስተማረው ሁሉ ምክንያታውያን 16ኛው እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የሃይማኖት ሰዎች እውነትን ለማግኘት የምንችለው በምክንያት ብቻ ነው፡፡ እነዚህም የሃይማኖት ሊቃውንት ማንኛውም ነገር እምነትም ሆነ ልምድም መታየት ያለባቸው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ በወቅቱ ተራማጅ የነበሩት ፈላስፎች በአክራሪዎቹ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም (አንደኛው ዘርዐ ያዕቆብ) ‹‹መኃይማን እምነታቸው በማወቅ ላይ ሳይሆን ባለማወቅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በፈጣሪና በባዕድ አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት አያውቁም፤›› በማለት ሽንጣቸውን ገትረው በማስተማራቸውና ይህም አስተሳሰባቸው ተቀባይነትን እያገኘ በመሄዱ ሰዎች ስለተፈጥሮ በይፋ ማወቅ ጀመሩ፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ መሠረታዊ ነጥቦች ዛሬም አከራካሪ ቢሆኑም፣ ብዙዎቹ ጥያቄዎች መንስዔያቸው (ምክንያታቸው) ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየታወቀ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ የእኛው ፈላስፋ በኖረበት አካባቢ በተለይም 16ኛውና 17ኛው ክፍለ ዘመን ጆርጅ በርክሌይ ስለሰው ልጅ ዕውቀት፣ ስለሰው ልጅ የመረዳት ችሎታ የጻፈ ሲሆን ይህ ሰው ከቁስ አካል ይልቅ አዕምሮን ያስቀደመ ፈላስፋ ነበር፡፡ ይህ አየርላንዳዊ ፈላስፋ ምንም ሐሳባዊ ቢሆን በጣሊያን፣ በፈረንሣይ፣ በአሜሪካ እየተዘዋወረ ስለተፈጥሮ ሳይንስና የሒሳብ ሥሌት አስተምሯል፡፡ ..አ. 1596 እስከ 1650 የነበረው ሬኔ ዲካርት የተባለው ፈረንሣዊ ፈላስፋም በዘመኑ የነበሩት ጣሊያናዊው ጆን ኪንሰር በፍልስፍናው መዳበር በእጅጉ የረዱት ሲሆን፣ እንደ ..አ. 1637 ‹‹ሥልት›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ ማንኛውንም ነገር ያለ ጥያቄ መቀበል አግባብ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ለዘመኑ ሳይንስ መስፋፋትም አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ስለደም መዘዋወር (ስለሥርዓተ ደም ልብ) ጥልቅ ጥናት ያደረገውና ..አ. 1578 እስከ 1657 የነበረው እንግሊዛዊው ዊልያም ሃርቬ ስለተፈጥሮ ሳይንስ ጠባብ አመለካከት የነበራቸው ሰዎች ተቃውሞ ቢያቀርቡበትም ግኝቱን ለማስረዳት በቂ ዕውቀት ነበረው፡፡

በወቅቱ የነበሩት የእንግሊዝ መሪዎች ስለተቀበሉት የተነሱበትን ጠላቶች ለማኮሰስ ችሏል፡፡ ..አ. 1588 እስከ 1679 የነበረው እንግሊዛዊ ፈላስፋ ቆማስ ሆብስ የነቤከን፣ ሞንታኝ፣ ዴካርት፣ ጋሊሊዮ ጋሊሊና ኪፕዝና በወቅቱ የነበረውን ፍልስፍና ለመቀየር አነሳሳው፡፡ ይህም ፈላስፋ እንደኛው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ ደቀመዝሙር (ወልደ ሕይወት ወይም ምትኩ ሀብቱ) ስለተፈጥሮ ሕግ፣ ስለዕውቀት፣ ምክንያት ፍላጎት፣ ባህሪይ፣ መንግሥትና መስተዳድር የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ አስተምሯል፡፡ ..አ. 1651 ያሳተመው መጽሐፍም ‹‹መንግሥትን ሰዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ የፈጠሩት ማስፈራሪያ ነው፤›› በማለት አሥፍሯል፡፡

ዘርዐ ያዕቆብ በነበረበት ዘመን የሚታወቁትን ፈላስፎች ስናነሳ ..አ. 1632 እስከ 1677 የነበረውን ቤኔዲክተስዴ ስፒኖዛን ልንረሳው አንችልም፡፡ የእሱና የዴካርትስ ደቀ መዝሙር የነበረውንና ..አ. ከ1646 እስከ 1717 የነበረውን ጀርመናዊውን ጎትፍሬት ቪልሃም ሌይብኒስ ከእሱም ጋር ታላቁን የእነግሊዝ ፈላስፋ ጆን ሎክ (..አ. 1632 እስከ 1704) መጥቀስና ታሪካቸውንም ማያያዝ አስፈላጊነት ይኖረዋል፡፡ እስካሁን ስለተወሱት ፈላስፎች የተጠቀሰው ግን ወደ ፊት በዚህ መስክ ለሚደረገው ጥናት አትኩሮትን አቅጣጫ ለማስፋት እንጂ፣ አንዱ ከሌላው የሚመሳሰሉበት ብቻ ሳይሆን የሚለዩበትን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ጊዜው በሦስትና በሁለት መቶ ዓመት ቀደም አለ እንጂ ከእኛው ዘርዐ ያዕቆብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ ያለው የጆርጅ ቤከንን የሕይወት ታሪክ እንኳን ብንመለከት እንደ ሚከተለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ጆርጅ ቤከን ..አ. 1214 እስከ 1294 የነበረ እንግሊዛዊ ሲሆን የዚህም ሰው ታሪክ የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ሥራው እስኪታወቅ ድረስ ለሳይንስና ለፍልስፍና መሠረት የጣለ መሆኑ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ተረስቶ ኖሯል፡፡ ይህ ሰው በዘመኑ በነበረው አስተሳሰብ በመቶ ዓመታት የቀደመ ሲሆን፣ የሰው ልጅ የመጓጓዣ አገልግሎት በፈረሶች መጎተቻቸው ቀርቶ ራሳቸውን የሚችሉ ይሆናሉ፡፡ እንዲያውም በአየር ላይ መብረሩ አይቀርም፡፡ በማለት ግንዛቤውን አስተምሯል፡፡ ስለመስታወት ነክ ነገሮች ያደረገው ጥናት አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ለመሥራት ያስቻለው ከመሆኑም በላይ በንጥረ ነገሮች ላይ ባደረገው ምርምርም (በኬሚስትሪ) ስለፈንጂዎች አሠራር ለማወቅ በቅቶ ነበር፡፡ እንደዚህም ያለው በወቅቱ ከነበሩት ሰዎች አስተሳሰብ የራቀ ዕውቀት ጆርጅ ቤከንንሰይጣን ምክር ተካፋይ የሆነ አስመስሎታል፡፡

በወቅቱ በአካባቢው በነበሩት ትምህርት ቤቶችም የሃይማኖት ሰዎች ተፅዕኖ በጣም የላቀ ስለነበርና እነዚያ ሊቃውንት ከሚያውቁት በላይ ሊቅ የሆነው ጆርጅ ቤከን ብቅ ማለት ክፉኛ ስላስፈራቸው አሥር ዓመት ሙሉ ከማንኛውም መጻሕፍትና መሣሪያ እንዲገለል አደረጉትና በግዞት ተቀመጠ፡፡ ቤከንን ያውቀው የነበረ አንድ የቤተ ክህነቱ ሰው ጳጳስ ሆኖ ሲመረጥም አስፈታውና አሥር እስከ አሥራ ሁለት ዓመታት ምርምሩን ነፃ ሆኖ እንዲሠራ አስቻለው፡፡ ሆኖም ተቃዋሚዎቹ በመብዛታቸውና ..አ. 1278 በዋለው ችሎት ተከሶ እንደገና እስር ቤት እንዲወርድ ተደረገ፡፡

የቤከን አዕምሮ ሳይንሳዊ በሆነ ዕውቀት የታነፀ ስለነበረ እውነትን ለማግኘት ማስረጃዎችን መፈለግና መመርመር በተለይም ስለተፈጥሮአዊ ዓለም ተጨባጭነት ከሌላው አመለካከት መራቅ እንደሚገባ፣ እምነት በሃይማኖት ሰዎች ተፅዕኖ ሳይሆን፣ በማወቅ እንደሆነ አስተማረ፡፡ ‹‹ታላቅ ሥራ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉም በእምነትና በሳይንስ መካከል የሚቃረን ነገር እንደሌለ ገለጸ፡፡ የጆርጅ ቤከን ፍልስፍና ..አ. 1561 እስከ 1626 ከነበረው ሰር ፍራንሲስ ቤከን ጋር ይመሳሰላል ተብሎ ይዘከራል፡፡

በዚህ ንዑስ ርዕስ የቀረበው የንፅፅር ሐተታ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ታሪካችንን ስንመለከተው አንድ ዓይነት ፍልስፍና በሌሎች በአውሮፓና በእስያ ሲከሰት በኢትዮጵያም ጭምር የሚከሰት መሆኑን ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ማብራራት ያስቸግራል፡፡ ምናልባት የሥልጣኔ ነፋስ ሲነፍስ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ሊሠራጭ እንደሚችል መገመት ይቻል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዓይን አብራዎቹ›› በሚል ርዕስ ባሳተምኩት መጽሐፌ (2011 205) እንደገለጽኩት ሁሉ 20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ሸኽ ዘካሪያ በኋላ አለቃ ንዋየ ክርስቶስ በታሪክ ገጽ መከሰታቸውን እንመለከታለን፡፡

ከአለቃ ንዋየ ክርስቶስ የሕይወት ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የኖሩት 1837 እስከ 1912 ዓ.ም. ሲሆን ይህም እ.ኤ.አ. ከ1845 እስከ 1920 መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ማለትም 1844 እስከ 1921 ታኦይዝምን፣ ይሑዲነትን፣ ዞሮአስተርን፣ ክርስትናን፣ እስልምና አጣጥሞ ለመምራት ሐሳብ የነበረው ኢራቃዊው ዓብዱል በሃ ተነስቶ ነበር፡፡ ዛሬ «በሃኢ» እየተባለ የሚጠራው ሃይማኖትም የእሱ ነው፡፡

ከዚህ ዘመን ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ማለትም እ.ኤ.አ. 1839 እስከ 1908 ደግሞ ህንዳዊው ሱፊ ሚራዝ ጉላም አህመድ ክርስትናን ከእስልምና ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ተነስቶ ነበር፡፡ የዚህም ሰው ሃይማኖት «አህመዲያ» እየተባለ ሲጠራ በህንድ ውስጥ ዛሬም ብዙ ተከታዮች አሉት፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በመጠኑ ከላይ እንደተጠቀሰው አለቃ ንዋየ ክርስቶስም ክርስትናንና እስልምናን አንድ አድርጎ ለማራመድ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ እኚህ ሰው በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በሩቅ ምሥራቅ ስለነበረው ሒደት ዕውቀቱ አልነበራቸውም፡፡ ወይም እንደ ነበራቸው የሚያመለክት መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን የትም መሄድ ሳያስፈልጋቸው የኦርቶዶክስ ተዋዶ አመለካከትን በፕሮቴስታንት (በኢትዮጵያ ሰባተኛው ቀን አክባሪ ዕውን እንዲሆን መሠረት እንደሆኑ ይነገራል) አመለካከት ለመቃኘትም ሐሳብ እንደ ነበራቸው በደቀ መዛሙርታቸው የተጻፉት ሥራዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአለቃ ንዋየ ክርስቶስ እስልምናና ኦርቶቶክስ ተዋሕዶን ለመከለስ ምክንያትሆኗቸው መጻሕፍት ነበሩ ቢባል በተለይም ስዊድናውያን ሚሽኖች ቁርዓንን በራሳቸው መንገድ (ህዳጉ ላይ) በዓረብኛ ማብራሪያ የሰጡትን ተመርኩዘው እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ ከእርሳቸው 500 ዓመት ያህል ቀደም ብለው የነበሩት አፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ አፄ ልብነ ድንግል ከእነ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ የላቀ እንጂ ያነሰ ሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዳልነበራቸው በታሪክ የተረጋገጠ ነው፡፡

ከእርሳቸው 400 ዓመታት ቀደም ብለው የነበሩት እጨጌ ዕንባቆም በርካታ መጻሕፍትን ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ የመለሱ ሲሆን ከቁርዓንና ከሃዲስ በመውሰድ ክርስቲያናዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ የመን ከሚኖሩ ይሁዲ ቤተሰብ የሚወለዱትና እ.ኤ.አ. 1470 እስከ 1560 የኖሩት እጨጌ ዕንባቆም በተለይም ‹‹አንቀጸ አሚን›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ቁርዓንን እየጠቀሱ ክርስትናን ያስተምሩ እንደነበር ሲታወቅ በዚህም የተነሳ ኢማም አህመድ ኢብራሂም (ግራኝ) ከቦታ ቦታ እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል፡፡ በረመዳን መጨረሻ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠበቀው ‹‹ለይለቱል ቀድር›› በልደት ሌሊት ከሚፈጠር ተዓምር ጋር አያይዘውታል፡፡ እንደ አለቃ ንዋየ ክርስቶስና እጨጌ ዕንባቆም ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት እየመጡ ስለክርስትና በራሳቸው መንገድ የጻፉ ሲሆን፣ የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊነት ግን መቀበል እንደተሳናቸው እንረዳለን፡፡ ተሳናቸውም አልተሳናቸውም ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ስሜቱን በነካ ሰው ለመታወቅ ቻሉ እንጂ ከእርሱ የላቁ ሊቃውንትና ሊቀ ሊቃውንት በሁሉም ሃይማኖትና ርዕዮት መስኮች ሊኖሩን እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ ሌሎቹን ታሪካቸውንና ማንነታቸውን አጥብቀው ለሚመረምሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ለጊዜው ከግዕዝ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ስለተተረጎመው የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ሥራ እናተኩር፡፡

የጸሐፍቱ ትርጉም አንድነትና ልዩነት እንደሚታወቀው ሁሉ የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ሥራ በአገራችንና በውጭ አገር ሊቃውንት የተተረጎመ ሲሆን ቀደም ሲል በንፅፅር እንደቀረበው ሁሉ ‹‹ይህ ሰው ፈረንጅ ቢሆን እንጂ፣ ጥቁር አፍሪካዊ አይጽፈውም›› ያስባለ ሰው ነው፡፡ ዳሩ ግን፣ የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብን ፍልስፍና ወደ ተረጎሙት ሊቃውንት ሥራ ከመግባታችን በፊት አንባቢያን ስለትርጉም የተወሰነ ሐሳብ ይጨብጡ ዘንድ በጥቂቱ እናውሳ፡፡ በመሠረቱ ትርጉም ማለት ከተጻፈበት ቋንቋ ተርጓሚው ወደ ሚያውቀው ቋንቋ በመመለስ መልዕክቱን ማስተላለፍ ማለት ሲሆን፣ ትርጉሙ ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላው ቋንቋ ሲተረጎም ግን የሰዋስው አለመመሳሰል፣ ትርጓሜ ሊያስለውጡ የሚያስችሉ ቃላትና የመሳሰሉት ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ትርጉም ቢባልም መቶ በመቶ የተዋጣለት ላይሆን፣ ከመቻሉም በላይ የአገላለጽ ልዩነትንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም የመገኛ ቋንቋ ቃላትና ሐረጎች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ቀጥተኛ ትርጉም ላይኖራቸው ስለሚችል በማብራራት መጠቀም ግዴታ ሊሆን ይችላል፡፡ ይልቁንም ተርጓሚው ወደ ሚፈለገው ቋንቋ ሲተረጉም አንድም መገኛ ቋንቋውን ወይም መተርጎሚያ ቋንቋውን በሚገባ ካላወቀ የተፈለገው መልዕክት በሚገባ ላይተላለፍ ይችላል፡፡

የፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ሥራን የተረጎሙት የእኛ ሊቃውንት በአተረጓጎም አንድ ወይም ልዩ ይሆኑ እንደሆነ ለመረዳት ጥቂት ምሳሌዎችን እጅ እንዳመጣ (ረንደምሊ) እንመልከት፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ሐተታ ዘዘርዐ ያዕቆብ›› በሚል ርዕስ በተረጎሙትና ማብራሪያ በሰጡበት መጽሐፍ ክፍል ሦስት (ገጽ 24) ‹‹ከፀሎት በኋላ ሥራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ቁጭ ብዬ ስለሰው ጭቅጭቅ፣ ስለክፋታቸውም፣ ሰዎች በስሙ እያመፁ ጓደኞቻቸውን ሲያሳድዱ፣ ወንድሞቻቸውን ሲገድሉ ዝም ስለሚለው ፈጣሪያቸው ስለእግዚአብሔር ጥበብ ማስብ ጀመርኩ፣ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ፈረንጆች ኃይል አግኝተው ነበር፡፡ ግን ፈረንጆቹ ብቻ ሳይሆኑ የአገር ሰዎችም ከእነሱ የባሰ ከፍተዋል፤›› በማለት የተረጎሙትን፤ አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ደግሞ ‹‹ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ ወሐተታ ወልደ ሕይወት›› በሚል ርዕስ በምዕራፍ ሦስት ገጽ 6 እንደሚከተለው ተርጉመውታል፡፡

‹‹ከፀሎት በኋላም ሥራ ስላልነበረኝ ስለሰዎች ሁከትና ክፋታቸውን ሁል ጊዜ ተቀምጬ አስብ ነበር፡፡ ሰዎች በስሙ በሚነግዱበት፣ ባልንጀሮቻቸውን በሚያሳድዱበት፣ ወንድሞቻቸውን በሚገድሉበት ጊዜ ዝም ስለሚለው ፈጣሪያቸውእግዚአብሔርን ጥበብ ሁል ጊዜ ተቀምጬ አስብ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ፈረንጆች አይለው ነበርና ነገር ግን ፈረንጆች ብቻ አልነበሩም፡፡ የአገሩ ሰዎችም ከእነሱ ይልቅ ይከፉ ነበር››፡፡

ዳንኤል ወርቁ ካሳ ዘመንፈስ ቅዱስ የተረጐሙትን (19480) ‹‹መጽሐፈ ፍልስፍና›› በሚል ርዕስ ምዕራፍም ክፍል ሳይሰጥ ‹‹ስለአምላክ መኖርና ሃይማኖት መለያየት›› የሚል ንዑስ ርዕስ ሰጥቶ ገጽ 7 እንዳሰፈረው ደግሞ ‹‹ከፀሎትም በኋላ ሥራ ስለሌለኝ ሁል ጊዜ ስለሰዎች ክፋትና ሰዎች በእርሱ ስም ሲበድሉ፣ ወንድሞቻቸውን ጓደኞቻቸውን ሲያባርሩና ሲገድሉም ዝም በማለቱ ስለፈጣሪ ጥበብ አስብ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ፈረንጆቹ አየሉ፡፡ ነገር ግን ያገሩ ሰዎችም ከእነሱ የባሰ ክፋት ሠሩ እንጅ ፈረንጆቹ ብቻቸውን አልነበረም የከፉት፤›› ይለዋል፡፡

ዶ/ር ሓጎስ አብርሃ ‹‹ፍልስፍና ዘርዐ ያዕቆብን ወልደ ሕይወትን›› ማለትም የዘርዐ ያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍና በሚል ርዕስ ከግዕዝ ወደ ትግርኛ የተረጎሙትን እኔ ወደ አማርኛ ስመልሰው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ ‹‹ከፀሎት በኋላ ሥራ ስላልነበረኝ፣ ሁል ጊዜ ቁጭ ብዬ ስለሰው ልጆች ጭቅጭቅና ክፋታቸው፣ ሰዎች በስሙ (እግዚአብሔርን) እያመፁ ጓደኞቻቸውን እያሳደዱ፣ ወንድሞቻቸውን ሲገድሉ ዝም ስለሚለው የእግዚአብሔር ጥበብ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ፈረንጆች ኃይል አግኝተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፈረንጆች ብቻ ሳይሆኑ እነዚያ ያገሩ ልጆችም ከእነሱ የባሰ ይከፉ ነበር፡፡

ቀደም ሲል የቀረቡት ትርጉሞች በሦስት ሊቃውንት የተተረጎሙ ቢሆኑም የአለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስና የዶ/ር ሓጎስ አብርሃ፣ አማርኛና ትግርኛ ከመሆናቸው በስተቀር በጣም ተቀራራቢ ሲሆኑ፣ ሌሎቹን መጠነኛ ልዩነት እናይባቸዋለን፡፡

‹‹የዘርዐ ያዕቆብ ዋነኛ ጥረት በዕውቀት ላይ የተገነባ ማኅበረሰብ መፍጠር ነበር፤›› በማለት የሚያብራራልን ወጣቱ የፍልስፍና መምህር ግን ቀጥታ ትርጉም ስላልሆነ በዚህ ረገድ ላነፃፅረው አልቻልኩም፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተጠቀሰው ሥራቸው በክፍል አምስት ‹‹ለተመራማሪ እውነት ፈጥና ትገለጻለች፣ ምክንያቱም ፈጣሪ በሰው ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ንፁህ ልቦና የሚመረምር ሥርዓትና ሕጎች አይቶ እውነትን ያገኛል፤›› ሲሉ በገጽ 33 የተረጎሙትን፤ አለቃ ያሬድ ፈንታም ‹‹ለሚመራመር ግን እውነት ፈጥኖ ይገለጻል፡፡ የተፈጥሮ ሥርዓትና ሕግጋትን አይቶ ፈጣሪ በሰው ልብ ባሳደረው ንፁህ ልቦና የሚመራመር እርሱ እውነትን ያገኛል፤›› በማለት ይተረጉሙታል፡፡ የሁለቱ ሊቃውንት ትርጉም እውነትን አንስታይና ተባዕታይ ከማድረጋቸው በስተቀር ተመሳሳይነት ይታይበታል፡፡ እውነት ግን ፆታ ስለሌለው/ስለሌላት በሁለቱም ቢቀርብ ቅር የሚያሰኝ አይደለም፡፡

 አስቀመጠና አሳደረ የሚለውም ተቀራራቢ ትርጉም አለው፡፡ ዳንኤል ወርቁ ያሳተመው የዘመንፈስ ቅዱስ ሥራ ደግሞ ይህንኑ መሠረተ ሐሳብ በገጽ 13 ‹‹ለሚመረምር ግን እውነት ቶሎ ይገለጻል፡፡ ፈጣሪ በሰው ልብ ያስገባውን ንፁህ ልቦና የፍጥረት ሕግጋትና ሥርዓትን ተመልክቶ የሚመረምር እርሱ እውነትን ያገኛል፤›› ይላል፡፡ በዚህ ትርጉም የመጀመርያው ዓረፍተ ነገር ከሁለቱ ተርጓሚዎች ጋር ተቀራራቢ ቢሆንም፣ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ግን ይለያል፡፡ ከሁሉ አስቀድመን የምንጠይቀው ፈጣሪ በሰው ልቦና አስቀመጠው? አሳደረው ወይስ አስገባው? ሁለተኛው ግዕዙ ‹‹የተፈጥሮ ሕግጋትን ተመልክቶ ለሚመራመር ይላል?›› የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ ዶ/ር ሓጎስ አብርሃ በትግርኛ በተረጎሙት መጽሐፍ ገጽ 32 ‹‹ንዝመራመር ሰብ ግና ሀቂ ፈጢና እያ ትግለጽ፡፡ ምኽንያቱ ፈጣሪ ኣብ ውሽጢ ልቢ ብዛቕመጦ ንፁህ ልቦና ዝመራመር ኩሉ ናይ ተፈጥሮ ሥርዓትን ሕግጋትን ርዕዩ ሓቂ ይረክብ፤›› በማለት ተርጉመውታል፡፡ ይህን ወደ አማርኛ ስመልስው ‹‹ለሚመራመር ሰው ግን ሀቅ ፈጥና ነው የምትገልጸው፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ በሰው ልብ ባስቀመጠው ንፁህ ልቦና የሚመራመር ሁሉ የተፈጥሮ ሥርዓትን፣ ሕግጋትን አይቶ ሀቅን ይረዳል፤›› የሚል ነው፡፡ የዶ/ር ሓጎስ ትርጉም ከአለቃ ያሬድ ፈንታ ትርጉም ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም የሚመራመርና የሚመረምር የሚለው ቃል ግን አጠያያቂ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት የሚመረምር የሚለው ከመንፈሳዊ ኃይል ጋር የተያያዘ ሲሆን ተመራማሪ የሚለው ግን ያለመንፈሳዊ ኃይልም ሊከናወን ስለሚችል ነው፡፡

ይልቁንም ቅን የመረዳት ጉዳይ ስለሆነ ዘርዐ ያዕቆብ በንፁህ ልቦና የተፈጥሮ ሥርዓትን መርማሪ እንጂ ተመራማሪ ነበረ ብሎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰር ጌታቸው እንዳስቀመጡት ‹‹የተፈጥሮ ሥርዓትን ለሚመረምር ተመራማሪ ሀቅን ያገኛል፤›› ወይም አለቃ ያሬድ እንዳሉት ‹‹እውነትን ያገኛል፡፡›› እዚህ ላይ ግን ፕሮፌሰር ጌታቸውና ዶ/ር ሓጎስ ‹‹ስለሀቅ መገኘት›› ሲገልጹ አለቃ ያሬድናአቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ሥራ ግን ስለእውነት መገኘት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሀቅና እውነት አንድ ናቸው ወይ?›› ብለን ስንጠይቅ አንድ የማይሆኑበትን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ‹‹የሰውን ሀቅ አልፈልግም›› ማለት ‹‹የሰውን እውነት እፈልጋለሁ›› ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱ ‹‹የሰውን ሀቅ አልፈልግም ማለት የሰውን ዕቃ፣ ሀብት፣ ንብረት›› ማለት ሲሆን የሰውን እውነት ማለት ግን እውነት ከመናገር ወይም ከማድረግ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
መደምደሚያ

በዚህ ዓይነት ትርጉሙን እያነፃፀርን ማየት እንችላለን፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ብዙ ጊዜና ገጽ ይጠይቃል፡፡ የጋዜጣውም ባህሪ አይደለም፡፡ ዋናው ቁም ነገር መጽሐፍ ሲተረጎም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በትርጉም ረገድ ከፍተኛ የሆነ ቸልታ ያሳያሉ፡፡ በዓውዱ መሠረት መፍታት ሲገባቸው በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ሲያደርጉ አይስተዋሉም፡፡ ብሩህ ዓለምነህ የተባሉት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር 330 ገጽ የተነተኑት ፍልስፍናው ባህር ስለሆነ ነው፡፡ የወደፊቱ በቅርቡም 1,000 ገጽ የሚተነትኑ የነብሩህ ዓለምነህ ተማሪዎች ይመጣሉ፡፡

መታወቅ ያለበት ዓብይ ጉዳይ ግን በኦሪታውያን፣ በክርስቲያንና በሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተጻፉ በርካታ ፍልስፍናዎች መኖራቸው አለማጠያየቁ ነው፡፡ እነዚህ ፍስፍናዎች ተፈልፍለው ለመውጣት የሚችሉትም ከብዙ ጭጋጋማ ሁኔታና አመለካከት ነው፡፡ ይህን በሚመለከት ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ‹‹ሕዝባችን በብዙ የሐሰት ነገር ያምናል፡፡ እምነታቸውም መርምረውና እውነትን አግኝተውበት ሳይሆን፣ ከቀደሙ አባቶች ስለሰሙ እንጂ፡፡ እነዚያ የቀደሙ አባቶችስ ይኼንን ያደረጉት ገንዘብና ክብር ለማግኘት ካልሆነ በስተቀር ስለምን ዋሹ? እንደዚሁም ሁሉ ሕዝብን ሊገዙ (ሥልጣን) የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ‹‹እውነትን እንድንነግራችሁ እግዚአብሔር ወደናንተ ልኮናል›› ይላሉ፣ ሕዝቡም አመነ፡፡ ከእነሱ በኋላ የሚመጣውም ትውልድ ያለ ምርመራ የአባቶቻቸውን እምነት ተቀበለ፡፡ እንዲያውም የአባቶቻቸውን እውነተኛነት ለማስረዳት ምልክቶችን፣ ታሪኮችንና ተዓምራትን እየጨመሩ ይብስ አፀኑት፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ይህን ሠራ፤ እግዚአብሔርን የሐሰተኞች ተካፋይና የሐሰት ምስክር አደረጉት፤›› ማለታቸውን ብሩህ ዓለምነህ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ከገጽ 51 እስከ 52 አሥፍረዋል፡፡ በእርግጥም፣ የአገራችን ሰላም በአንድነታችን ካሰፈንን እነዚህ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ፍልስፍናዎች ሩቅ ባልሆነ ጊዜ፣ እንደ ዘርዐ ያዕቆብ ፍስፍና ሁሉ፣ በብዙ በብዙ ሊቃውንት ይተረጎማሉ፡፡ በፍልፍስናችን በተመሠረተ አመለካከትም አገራችን ወደ ላቀ ደረጃ ትደርሳለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡
 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢዜማ ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በፀጥታ አካላት ተወስደው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታወቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣...

ኢሰመጉ የቀረበበትን የገለልተኝነት ጥያቄ አስተባበለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...