Tuesday, October 3, 2023

የሰላማዊ ሠልፉ ክልከላ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ሲደረጉ ከነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበሩን ከ18 ወራት በፊት ቀይሯል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር በመሆን የተመረጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ያደረጉት ንግግር የበርካቶችን ቀልብ የሳበና ልብን ያሞቀ ነበር፡፡

ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖርላማው ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ለዓመታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረው የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሚቀረፍ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንደሚሰፋና ሁሉንም አካታች እንደሚሆን ተናግረው፣ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲስፋፉ አበክረው እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት ያህል የቆየው ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት የሻከረ ግንኙነት እንዲሻሻልና የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች  ሰላማዊ ግንኙነት እንዲጀምሩ ጥረት እንደሚያደርጉ በማስታወቅ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት የሰላም ጥሪ አስተላልፈው ነበር፡፡

ይህን ጥሪ ተከትሎም ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ለማደስና ለማሻሻል የሰላም ስምምነት ፊርማ በመፈረም፣ ለ20 ዓመታት ዘልቆ የነበረው የሻከረ ግንኙነት እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለዚህ ላደረጉት አስተዋጽኦም የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በወቅቱ ከገቡት ቃል አንፃር የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጀመረበት ፍጥነት መጓዝ ባይችልም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም መውረድ በመቻሉ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በተለይ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስፋትና የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ፣ በፖለቲካ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡት ቃል ተፈጻሚ እንዳልሆነ በመግለጽ የሚተቿቸው በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተቋቋመው የባለአደራ ምክር ቤት እየደረሰበት ያለውን ክልከላና የተለያዩ ጫናዎች በመጥቀስ፣ ሐሳባቸውን ለማጠናከሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡

በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋትን የሚደቅኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ምንም ለማለት ያልደፈረው መንግሥት፣ በባለአደራው ምክር ቤት ላይ ያለው አቋም በበርካቶች ይተቻል፡፡ በተለይ ምክር ቤቱን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠሰውን አስተያየት በምሳሌነት በመጥቀስ፣ ከዴሞክራሲ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ተግባራዊ አላደረጉም በሚል ወቀሳ የሚሰነዝሩም አሉ፡፡

ከአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄና የፖለቲካ ውክልና ጋር ተያይዞ የመጣው የከተማዋ ችግር ዋነኛ የአገሪቱ የፖለቲካ ጡዘት፣ ባስ ሲልም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደርን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ አገራዊ ክስተት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጋዜጠኛ እስክንድር የሚጠሩ ሰላማዊ ሠልፎችም ሆኑ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት የሚጠሩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች መከልከልና መተጓጎል፣ በማኅበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ከመሆን ባለፈ የተቃውሞ ምንጭም እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የጥሪ መልዕክቶች ሲተላለፍለት የነበረውና እሑድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ የታሰበው በባለአደራው ምክር ቤት የተጠራው ሠልፍ፣ በአሥራ አንደኛው ሰዓት በአዲስ አበባ ፖሊስ መከልከሉ በርካቶችን ያሳዘነ እንዲሁም ያስቆጣ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ የአገሪቱ ዴሞክራሲ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት መሄዱን የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ በመግለጽም፣ ይህም ለአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ህልውና ከፍተኛ አደጋ እንደሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

 እሑድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ከመሰረዙ በተጨማሪ፣ በዚያኑ ቀን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ሌሎች አካባቢዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት የደስታ መግለጫ ሠልፍ መከናወኑ፣ በአገሪቱ የአድልዎ ፖለቲካ እየመጣ ነው በማለት በማኅበራዊ ሚዲያው ብዙኃን ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ከግለሰቦች ባለፈ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በትዊተር ገጹ ላይ የእሑዱ ሠልፍ መቅረቱን በመቃወም መግለጫ ከማውጣቱ ባለፈ፣ ክልከላው ለምን እንደተደረገ በአስቸኳይ ለሕዝብ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተሰጠው መብት ሆኖ ሳለ የተከለከለበት መንገድ ፍፁም ትክክል አይደለም በማለት ተቃውሞውን የገለጸው ኢዜማ፣ ፓርቲው እንዲህ ዓይነት የመብት ጥሰትን አጥብቆ እንደሚቃወምም አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ለሠልፉ ዕውቅና የከለከለበት በቂ ምክንያት ካለው ቀደም ብሎ ለጠያቂዎቹና ለሕዝብ ማሳወቅ ነበረበት ያለው ኢዜማ፣ አሁንም ሠልፉ ያልተካሄደበትን ምክንያት በአስቸኳይ ለሕዝብ  ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ከሰላማዊ ሠልፉ መከልከል ጋር ተያይዞ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ ጉዳዩ ከእስክንድር ጋር ብቻ መያያዝ የሌለበትና እንዲያውም ክስተቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ለዜጎች መሠረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ምን ያህል ቁርጠኝነት እንደሚጎድለው ማሳያ ነው፡፡

በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፣ ‹‹በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ከሳይንሱ አንፃር ማብራሪያና አስተያየት መስጠት ለእኔ ይርቅብኛል ወይም ስስ ይሆንብኛል፡፡ ምክንያቱም የአዲስ አበባ ጉዳይ የህልውናዬም የሕይወቴም አካል ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ጉዳዩን ከእስክንድር ጋር ማያያዝና ጥያቄውም የእስክንድር ብቻ ማስመሰል የችግሩ ዋነኛ መገለጫ ከመሆኑም በላይ፣ በሰላማዊ መንገድ ሐሳቡን መግለጽ የሚፈልገውን የአዲስ አበባ ነዋሪ መናቅ ነው፤›› በማለት ጉዳዩ ሰፋ ባለ ዓውድ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ተቃውሞአቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን) ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ‹‹ሕዝባዊ የተቃውሞ ድምፆችን ማፈን ወደነበርንበት መመለሳችን ማሳያ ነው፤›› በማለት፣ በተለይ የእሑዱ ሠልፍ ክልከላ ሁለት ነገሮችን በመሠረታዊነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹የአምባገነንነት ባህሪ መጀመርያ ምልክቶች እንዲሁም ምን ታመጣላችሁ የሚል አስተሳሰብ መንሰራፋቱን ያሳያል፤›› በማለት፣ አሁን ላይ ከዜጎች መሠረታዊ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ እንዲሁም ከሌሎች ሰብዓዊ መብቶች መጣስ ጋር ክስተቶችን ጠቅልለው ይገልጿቸ  ዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲ መሠረታዊያንን ተረድቶ ዜጎች መብታቸውን እንዲጠቀሙና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማክበር የመሪዎች ቁርጠኝነትና አቅም ወሳኝ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ከዚህ አንፃር የአቅም ውስንነት አለበት፤›› በማለት ይተቻሉ፡፡

እንደ እሳቸው አረዳድና ትንታኔ ከዚህ የአቅምና የብቃት ውስንነት የተነሳ፣ ‹‹እንኳን ዴሞክራሲ ኢትዮጵያም ራሷ አደጋ ውስጥ ነች፤›› የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳደረሳቸው ይገልጻሉ፡፡

አሁን ያለው የዜጎችን ሰላማዊ ሠልፍ መከልከል እንቅስቃሴ ጦሱ ለአገር ህልውናም አደጋ እንደሆነ የሚገልጹት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በበኩላቸው፣ ‹‹አዲስ አበባ ላይ የሚደረግ ማንኛውም አሉታዊ ውጤት ያለው እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳራድራል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት አዲስ አበባ ላይ እየተከተለው ያለው አካሄድ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ይችላል፤›› በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከእሑድ ሰላማዊ ሠልፍ ክልከላ በኋላ በርካቶች በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሳባቸውን በመሰንዘር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የእስክንድርንም ሆነ የባለአደራው ምክር ቤትን ባይደግፉም እንዲህ ዓይነቱን አሠራርን እንደሚቃወሙ በመግለጽ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት ጥቂቶች አይደሉም፡፡

የአዲስ አበባ ሕዝብ ፖለቲካዊ መብቱ ይከበር፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከአገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲገለል ተደርጓል፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቱ ይከበር የሚሉት አስተያየቶች ደግሞ በተደጋጋሚ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡

ሰላማዊ ሠልፉ በተከለከለበት ዕለት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተደረጉት ሠልፎች፣ አድሎአዊ አሠራር መኖሩን ያመላክታል በማለት የሚገልጹት በርካቶች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር በበኩላቸው፣ ‹‹የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባን ጉዳይ እንደመስዋዕት አድርጎ ማቅረብ ይፈልጋል፤›› በማለት፣ በከተማዋ ያለውን የኃይል አሠላለፍ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

ከ1997 ምርጫ ወዲህ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎች እንደተከሰቱ መምህሩ ገልጸው፣ ‹‹አዲስ አበባ ከተማ ከ97 ምርጫ በኋላ ከሕዝቧ የተነጠለች ከተማ ነች፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የአዲስ አበባው የመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ መከልከል፣ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስተዳዳር በጉዳዩ ላይ ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከጥያቄ ውስጥ ያስገባ በመሆን አልፏል፡፡

ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቱ የሚከበርለት መቼ ነው? በማለት የሚጠይቁ በርካቶች ሲሆኑ፣ በዚህ መንገድ እየታፈነ ያለው የከተማው ነዋሪ የመጨረሻው አማራጭስ ምን ይሆን? በማለት በሥጋት ይጠይቃሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -