Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በልውጠ ህያዋንና በዘረ መል ምሕንድስና አንቱታ ያተረፉ ባለሙያ ሙግት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ50 ዓመታት በላይ በውጭ ኖረዋል፡፡ አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ክፍል በሳይንስ ምርምር መስክ አሳልፈዋል፡፡ በተለይም በልውጠ ህዋያን፣ እንዲሁም በዘረ መል ምሕንድስና መስክ አንቱታ ያተረፉ፣ በአሜሪካ ባካሄዷቸው ምርምሮች፣ ባስገኟቸው የፈጠራ ውጤቶችና ግኝቶች ስማቸው በደማቁ ይጠቀሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤችአይቪ/ኤድስ በሽታን የሚፈውስ ክትባት ለመሥራት እየተመራመሩ የሚገኙት ኢትዮጵያዊው ምሁር ጥላሁን ይልማ (የተከበሩ ፕሮፌሰር)፣ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምናና የቫይሮሎጂ ሳይንስ ፕሮፈሰር በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲም በምርምር ሥራዎቻቸው የገዘፈ ስም ገንብተዋል፡፡ በአሜሪካ ብሔራዊ ሳይንስ አካዴሚ ብቸኛው አፍሪካዊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ ከዚህም የላቁ በርካታ ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎችን ተጎናጽፈዋል፡፡

ከበርካታ ዓመታት የውጭ አገር ኑሯቸው ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ያሉት እኚህ ሳይንቲስት፣ አንድም የቻይና ኩባንያ በአፍሪካ ደረጃ የልውጥ ህያዋን ምርምር ሥራዎችን የሚካሄድበትን ተቋም በኢትዮጵያ ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል መምጣታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣት ተመራማሪዎችና መምህራን በምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጡ፣ ዕውቀታቸውን እንዲጠቀሙ ለማበረታታት፣ ተተኪ ሳይንቲስቶች እንዲበራከቱ ለማገዝ በዩኒቨርሲቲዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ አስታከው ቁጭታቸውን ከፖለቲካዊ ችግሮች እያዋዙ አሰምተዋል፡፡ ሞግተዋል፡፡

በካሊፎኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ የዓለም አቀፉ የሞሎኪውላር ባዮሎጂ ምርምር ላቦራቶሪ ተቋም ኃላፊ በመሆን እየሠሩ የሚገኙት ሳይንቲስቱ በአንድ ወቅት የቁም እንስሳትን በአጣዳፊ ወረርሽኝነት ሲጨርስ የነበረውን የደስታ በሽታ በክትባት ማጥፋት ስለተቻለባቸው ዘመቻዎች ከትዝታቸው እያዋዙ ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ ፀረ ደስታ በሽታ ክትባት እንዳሁኑ ባልተሻሻለበት፣ በ1970ዎቹ ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ከብት ብቻ መከተብ እንደተቻለ፣ ክትባቱ ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በተሠራበት ወቅትም 124 ሺሕ ከብት በመከተብ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት እንደተሞከረ አስታውሰዋል፡፡

ቀስ በቀስ እንዲህ ያሉ የምርምር ሥራዎቹ እያደጉ፣ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በተለይም በአፍና በእግር ላይ ቁስለት እያስከተሉ በርካቶችን ለሞት የሚዳርጉ በሽታዎችን ለመወፈስ ያስቻሉ የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ረገድ ከስደት ወደ አሜሪካ ሄደው በእሳቸው ሥር ምርምር ሲያካሂዱ የነበሩ የአፍሪካ ተመራማሪዎች ውጤቶች ለዓለም መትረፋቸውን አውስተዋል፡፡ የስምጥ ሸለቆ ንዳድ እየተባለ የሚጠራውን በሽታ አምጪ ቫይረስ ለመቋቋም የሚያስችል ክትባትም እሳቸው የምርምር ማዕከል ማበልፀጉን ከትውስታቸው አካፍለዋል፡፡

‹‹እንዲህ ያለውን ዕውቀትና ችሎታ የታደሉ ኢትዮጵያውያንና የሌሎችም አገሮች ዜጎች በገዛ አገራቸው ለምን መሥራት አቃታቸው? ለምንስ በችግርና በልመና ስማችን ይነሳል?›› በማለት የሚጠይቁት ፕሮፌሰሩ፣ ይልቁንም የምዕራባውያኑ ተንኮልና ተፅዕኖ የፈጠረው ችግር እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ ‹‹በአፍሪካ የሳይንስ ግኝት እንዳይስፋፋ ያስቸገረው ለምንድን ነው?›› በማለት ይጠይቁና፣ ‹‹የአንጎልና የማሰብ እጥረት ነው እንዳልል፣ በብዙ መገለልና የዘር መድልኦ ጫና ውስጥም ሆነን ችሎታችንን አሳይተናል፡፡ ነጮቹን በልጠናቸዋል፤›› በማለት ሙግታቸውን በምዕራባውያኑ ሴራ ላይ አድርገዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምዕራቡን ዓለም ጫናና የተንኮል ሴራ ቻይና እያከሸፈችው ነው ያሉት ጥላሁን (ፕሮፌሰር)፣ ዋቢ ያደረጉትም ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቅ የምርምር ማዕከሉን በአዲስ አበባ ለመትከል ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ጋር ስምምነት ያደረገውን ቢጂአይ የተሰኘውን የቻይና ግዙፍ የምርምር ተቋም ነው፡፡

ይህ ተቋም በዘረመል ምሕንድስና እንዲሁም በዲኤንኤ ምርምር የታወቀ ኩባንያ ሲሆን፣ ይህንኑ ሥራም በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የማስፋፋት ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ተቋሙን የሚያማክሩት ፕሮፌሰሩ፣ የቢጂአይ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሳይንሳዊ ምርምር መስክ ለአፍሪካ ትልቅ ተስፋ የሚሰንቅ ሲሉ ገልጸውታል፡፡

እንዲህ ያለውን ተልዕኮ ይዞ ብቅ ያለው ይህ ተቋም፣ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ላይ የተጣባውን ብልሹ አመለካከት ለማረቅ እንደሚያግዝ ባስገነዘቡበት ገለጻቸው፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን ዘር ተኮር የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የሥርዓተ ትምርህቱን ችግር፣ እንዲሁም እንግሊዞች በዘመነ አፓርታይድ ለዓለም ያስተዋወቁት ሥርዓት እንደሆነ የገለጹትን ‹‹ሆም ላንድስ›› የተሰኘ ሥርዓት እሳቸው፣ ‹‹ክልል›› በማለት ተርጉመውታል፡፡ ይህ ክልል ተኮር የአስተዳደር ሥርዓት የአፍሪካን ጠንካራ ባህልና የኢኮኖሚ ምኅዋር በመሸርሸር ለውድቀትና ግጭት የዳረገ ሲሉ ኮንነውታል፡፡ ኢትዮጵያም ከክልል አስተዳደራዊ ሥርዓት መላቀቅ እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በመተቸት በዓለም አቀፍ ጋዜጦች ሒስ ይጽፉ እንደነበር ያወጉት ፕሮፌሰሩ፣ በተለይም የኢትዮ-ኤርትራን ደም አፋሳሽ ዕልቂት የኮነኑትም፣ የጦር መሣሪያ አምራቾች ከሁለቱ አገሮች ግጭት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያጋበሱበት፣ በአንፃሩ እስከ 100 ሺሕ የሚገመቱ ዜጎች ያለቁበት ጦርነት ምዕራባውያኑ አፍሪካን የጦር ንግድ መዳረሻቸው ያደረጉበት ሥልታቸው መገለጫ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ያደፈ ታሪክ ለመቀየር በታዳጊዎችና ወጣቶች ሥልጠና ላይ ማተኮር እንደሚገባ፣ ሳይንስና ምርምር ላይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ተማራማሪዎችን ማፍለቅ እንደሚያስፈልግ ሞግተዋል፡፡

ምንም እንኳ ፕሮፌሰሩ በምርምር መስክ በተለይም በዘረ መል ምሕንድስናና በልውጠ ህያዋን ሳይንስ ላይ ያተኮረው የቻይና ኩባንያ ወደ አፍሪካ መምጣቱ ከወዲሁ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ተቃውሞ ያሰሙትም በአካባቢ ጥበቃና በብዝኃ ሕይወት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የልውጠ ህያዋን ምርምር ሥራዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን በመከራከር ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች