[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቤት ምሳ እየበሉ ነው]
- ደስታው እኮ ሊለቀኝ አልቻለም፡፡
- የትኛው ደስታ?
- የሽልማቱ ደስታ ነው፡፡
- የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሽልማት ነው የምትይኝ?
- ምን ጥያቄ አለው?
- እኛም እኮ ተሰባስበን ሌላ ሽልማት ሰጠናቸው፡፡
- የምን ሽልማት?
- የወርቅ ሽልማት ነዋ፡፡
- ከየት መጥቶ?
- ምን ማለት ነው?
- ያው ወርቁ በኮንትሮባንድ ነው የሚጓዘው ብዬ ነዋ፡፡
- ለእሳቸው የሚሆን እናጣለን ብለሽ ነው?
- መቼም የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ የለህበትም?
- ምኑን አመጣሽብኝ?
- አሁን ሁሉ ነገር ኮንትሮባንድ ስለሆነ ብዬ ነው፡፡
- ኧረ ሰው እንዳይሰማሽ?
- ትንሽ ግን የፈዘዝን አይመስልህም?
- እንዴት?
- ጠዋት ከሰዎች ጋር ተገናኝቼ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- ምን እየሠራችሁ ነው ብለው ጠየቁኝ?
- አልገባኝም?
- እንዳይቆጫችሁ አላሉኝም መሰለህ?
- ምኑ ነው የሚቆጨን?
- ሥልጣናችሁን ተጠቀሙበት እንጂ ብለው ነዋ፡፡
- ምን ማድረግ እንችላለን ብለሽ ነው?
- ኧረ ብዙ ሐሳብ ሲነግሩኝ ነበር፡፡
- እኮ ምን?
- ለምሳሌ ከሽልማቱ ብዙ ነገር ልናገኝ እንችላለን፡፡
- ምን ዓይነት ነገር?
- ሽልማቱ እኮ አገራዊ ይዘት እንዳለው አትርሳ፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ከአገርም አልፎ ዓለም አቀፋዊ አንደምታ አለው፡፡
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- ስለዚህ ሽልማቱን አስታከን ብዙ ልናተርፍባቸው የሚችሉ ነገሮችን ማዘጋጀት እንችላለን፡፡
- ምን ዓይነት ነገር?
- ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ ብዕር፣ ኧረ ብዙ ነገር ማዘጋጀት እንችላለን፡፡
- ብለሽ ነው?
- የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሳይቀሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምስል በየሕንፃዎቻቸው ሲያበሩ አልነበር እንዴ?
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- ታዲያ የውጭዎቹ እንደዚህ ሲያሞጋግሱን እኛ እንዴት ወደኋላ እንላለን፡፡
- ሐሳብሽ ጥሩ ነው፡፡
- ስለዚህ ይኼን ሐሳብ ለማንም ብታቀርበው ተቀባይነት ያገኛል፡፡
- ታዲያ ምን እያልሽኝ ነው?
- ሐሳቡን ሳንቀደም እንቅደም፡፡
- ያዋጣናል ግን?
- ስነግርህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት እኛም ራሳችንን እንሸልማለን፡፡
- ምንድነው የምንሸልመው?
- ቪላ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ተቃዋሚ ስልክ ደወለላቸው]
- እንኳን ደስ ያለህ ለማለት ነው የደወልከው?
- ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ለሽልማቱ ነዋ፡፡
- የምን ሽልማት?
- የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ነዋ፡፡
- እርስዎ እኮ አይደለም የተሸለሙት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሽልማቱማ የሁላችንም ነው፡፡
- ይህቺ ጎንበስ ጎንበስ ዕቃ ለማንሳት ነው አሉ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ያው ሽልማቱ የሁላችንም ነው ካሉ ገንዘቧንም እንካፈል እንዳይሉ ብዬ ነዋ፡፡
- ለቀልድማ ማን ብሎህ?
- በጣም አፍሬያለሁ ግን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምኑ?
- በሁሉም ነገር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ለውጡን እኮ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እያስኬዳችሁት ነው፡፡
- ከአንተ ድሮስ ምን ይጠበቃል?
- እውነቴን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- እንዴት ብላችሁ ነው የከለከላችሁት?
- ምኑን?
- ሰላማዊ ሠልፉን ነዋ፡፡
- እ…
- ታዲያ በምን ተሻላችሁ?
- ከምኑ?
- ከበፊቶቹ ነዋ፡፡
- በል በል ከእነሱ ጋር እንዳታወዳድረን፡፡
- ለምን?
- ይኸው ዓለም ሳይቀር ለውጡን አድንቆ አይደለም እንዴ የሸለመን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ እንዳትሆኑ እፈራለሁ፡፡
- እ…
- ለእናንተም እኮ ጥሩ ነበር፡፡
- ምኑ?
- ሠልፉ ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- የሕዝቡን ትርታ ትሰሙበት ነበራ፡፡
- እ…
- እሱን ለነገሩ የሚሰማ ጆሮ የላችሁም፡፡
- ምን አልክ?
- ለመሆኑ ይኼን ያህል ምንድነው የሚያስፈራችሁ?
- እ…
- ቁጣው ከገነፈለ ግን የማትወጡት ነገር ውስጥ ትገባላችሁ፡፡
- የማን ቁጣ?
- የሕዝቡ ነዋ፡፡
- ለምን ይቆጣናል?
- ስለምታፍኑት ነዋ፡፡
- በለውጡማ ነፃነት እንጂ ማፈን የለም፡፡
- በተግባር ካላሳያችሁ ማንም አይሰማችሁም፡፡
- ይኸው ዓለም ሰምቶን አይደል የሸለመን፡፡
- በአገር ውስጥም መሸለም አለባችኋ፡፡
- እሱስ መቼ ይቀራል?
- በዚህ አካሄዳችሁ የምትሸለሙትን አውቀዋለሁ፡፡
- ምንድነው የምንሸለመው?
- ውርደት!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ተዋችሁት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን?
- ኢኮኖሚውን ነዋ፡፡
- እንዴት ይተዋል?
- ምን እያደረጋችሁት ነው ታዲያ?
- እ…
- የኢኮኖሚው ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው እኮ፡፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ምን አስባችሁ ነው?
- ስለምኑ?
- ስለኢኮኖሚው አልኩዎት እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን እናድርግ?
- ወደው አይስቁ አሉ፡፡
- እንዴት?
- መልሰው እኔኑ ይጠይቁኛል እንዴ?
- ምን ላድርግ?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ልትቆም እኮ ነው፡፡
- እ…
- የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በጣም እየተዳከመ ነው፡፡
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- የኢኮኖሚ ፕሮግራም የላችሁም እንዴ?
- ምን አልከኝ?
- የፈጣሪ ያለህ፡፡
- ምነው?
- አገሪቷ ውስጥ ገንዘብ ጠፍቷል፡፡
- አሁን ትንሽ ታገሱን፡፡
- እንዴት?
- የመንግሥት ድርጅቶችን ልንሸጣቸው ነዋ፡፡
- እሱ መፍትሔ ነው ብለው ነው?
- ዛሬ በልተን ማደር ከቻልን ስለነገው እግዚአብሔር ያውቃል፡፡
- ለነገሩ እናንተ በዚህ ከቀጠላችሁ አዲሱ የሚመሠረተው ፓርቲ ውስጥ እግዚአብሔርም አለበት ትላላችሁ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር አየር ላይ መንሳፈፉን ትታችሁ ወደ ምድር ውረዱ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አገሪቷ እየተንኮታኮተች ነው፡፡
- እ…
- የኢኮኖሚውን ጥያቄ መልሱ፡፡
- መመለሱማ አይቀርም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በኋላ ኢኮኖሚው ከተበላሸ ከፖለቲካው በላይ የራስ ምታት ነው የሚሆንባችሁ፡፡
- እሱ መቼ ጠፋን?
- ታዲያ መፍትሔ ስጡታ?
- ግራ ገብቶን ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገር እኮ ነው እየመራችሁ ያላችሁት?
- ታዲያ ሕዝቡ ካለተባበረን ምን እናድርግ?
- ምን ሕዝቡ ገንዘብ ያዋጣ እያላችሁ ነው?
- ግብር እኮ በሥርዓት የሚከፍል ጠፍቷል፡፡
- ምን ተሠርቶ ግብር ይከፈል?
- እ…
- ለነገሩ እኛ አልሰማ ብለናችሁ እንጂ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁንማ ነግራችሁን ነበር፡፡
- ምንድነው?
- ልመና!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞው ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- ኪኪኪ…
- ምን ያስገለፍጥሃል?
- ገርማችሁኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አድርገን?
- በቃ መላቅጡ ጠፍቶባችኋል እኮ፡፡
- የእናንተ ሥራ ነዋ፡፡
- ምን አጠፋን እኛ?
- አገሪቷን ለዚህ መከፋፈል ያበቃችኋት እናንተ አይደላችሁ እንዴ?
- በእውነት እኛም ተገርመናል፡፡
- በምኑ?
- ላለፉት ዓመታት ያስተማርናቸው አካላት በእውነት አስገርመውናል፡፡
- እ…
- እኛ ካሰብነው በላይ ነው እኮ የብሔር ፖለቲካውን ያጦዙት፡፡
- የሥራችሁን ይስጣችሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ የብሔር ፖለቲካው እኛ ከገባን በላይ ነው የገባው ስልዎት፡፡
- እያንዳንዷን ሒሳብ ማወራረዳችሁ አይቀርም፡፡
- ሕዝቡ ግን እንደሚወደን ያውቃሉ ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተን?
- ባይወደን ኖሮ ለዓመታት የሰበክነውን የብሔር ፖለቲካ እንዴት እንደዚህ ያጦዘዋል፡፡
- ግድ የለም የእጃችሁን ታገኙታላችሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገር መምራቱን የቻላችሁት ስላልመሰለን ብትመልሱልን ይሻላችኋል፡፡
- ምኑን?
- ሥልጣኑን፡፡
- እሱንማ አታስቡት፡፡
- ለማንኛውም ለሽልማቱ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
- መቼም ዓይናችሁ ቀልቷል?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ሽልማት ብርቃችን አይደለም፡፡
- ለነገሩ እኛም እናንተን እንሸልማችኋለን፡፡
- በምን?
- በሴራ!