በአንድ ጊዜ ከ10 ሺሕ ሰው በላይ ማስተናገድ የሚችለውን የአዲስ አበባ ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት ግንባታ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በበይፋ አስጀምረውታል፡፡ አራት ኪሎ ከፓርላማ ፊት ለፊት ከአርበኞች ሕንፃ ጎን የሚገነባው ቤተ መጻሕፍት በ38,687 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ከሚኖሩት ልዩ ልዩ አካላት መካከል ለሕፃናትና አዋቂዎች የሚሆን ለየብቻ የማንበቢያና የአረንጓዴ ስፍራ፣ ከ100 ሰው በላይ የመያዝ አቅም ያላቸው ሦስት የስብሰባ አዳራሾች፣ ለደራስያን፣ ከያንያን የሚሆን የመለማመጃና የቴአትር ማዕከላት ይገኙበታል፡፡ በተያያዘ ዜናም ከንቲባው የዓድዋ ማዕከል ግንባታንም በዕለቱ አስጀምረዋል፡፡ እንደ ከንቲባው ጽሕፈት ቤት መግለጫ፣የዓድዋ ማዕከል በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚድሮክ ተመላሽ በተደረገው ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን በውስጡም ከሚኖሩት አገልግሎቶች መካከል የዓድዋ ሙዚየም፣ ከ2000 ሰው በላይ የሚይዝ የዓድዋ አዳራሽ፣ የሲኒማ አዳራሽ፣ ቤተ መጻሕፍት የስፖርት ማዘውተርያዎችና ጂሞች፣ የሕፃናት መጫወቻና የማቆያ ስፍራ ይገኙበታል፡፡ ማዕከሉ የውስጥም ሆነ የውጪ ይዞታው ለመዝናኛ የተመቸ ሲሆን በውስጡም “ሁሉም ከዚህ ይጀምራል!” የሚል የአዲስ አበባ ከተማ ‘ዜሮ (0.00) ኪ.ሜ‘ በአንድ ኪሎግራም ወርቅ ምልክት ይቀመጥበታል ተብሏል፡፡ ፎቶዎቹ ከንቲባው የመሠረት ድንጋይ በመጣል ግንባታዎቹን ሲያስጀምሩ የነበረውን ገጽታ በከፊል ያሳያሉ፡፡