ከብሔራዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ብቻ የተለያዩ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች ሲረከብ የቆየው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገር ውስጥ አምራቾች ተወዳድረው ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ጋበዘ፡፡
ሜቴክ ያለ ምንም ተወዳዳሪ በብቸኝነት የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ የኤሌክትሪክ ቆጣሪና ትራንስፎርመሮች ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ሜቴክ በምርት ጥራትና ምርቶቹን በሚፈለገው ብዛት በወቅቱ ካለማቅረብ ጋር በተያያዘ፣ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር የታየበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የድርጅቱን የ2011 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎች ድርጅቱ አንድ አቅራቢ ብቻ እንደነበረው አስታውሰው፣ ይህ አሠራር እንዲቀር ተደርጎ የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሣርያዎች አምራቾች ተወዳድረው ምርታቸውን እንዲያቀርቡ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደተናገሩት፣ ሁሉም አምራቾች እኩል ዕድል ተሰጥቷቸው ምርታቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ አምራቾች ድርጅቱ በሚፈልገው መጠን አምርቶ የማቅረብ አቅም እንደሚያንሳቸውና የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ አምራቾቹ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ራሱ የሚያስፈልጉትን መሣርያዎች ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደገጠመው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2011 በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ሽያጭ 7.3 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚተላለፍ አስታውቋል፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ለመሰብሰብ አቅዶ 799.3 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደቻለ፣ 513.8 ሚሊዮን ብር ቀሪ ተሰብሳቢ ሒሳብ እንዳለ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ኅብረተሰቡን ያማረረውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአራት ዓመታት የሚፈጸም የታሪፍ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው፣ ሁለተኛ ዙር የዋጋ ጭማሪ ከመጪው ታኅሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ድርጅቱ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገልጸው፣ ከኅብረተሰቡ የሚሰበሰበው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ የኦፕሬሽኑን ወጪ እንኳ የሚሸፍን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር የገለጹት አቶ እሱባለው፣ ሥራውን ከማቋረጡ በፊት መንግሥት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያውን እንዳፀደቀ አስረድተዋል፡፡ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም፣ የኑሮ ውድነቱን ከግምት በማስገባት የታሪፍ ማሻሻያው በአራት ዓመታት እንዲተገበር መደረጉን ገልጸው፣ የመኖሪያ ቤቶች በተለይ እስከ 50 ኪሎ ዋት አወር የሚጠቀሙ ደንበኞች ቀድሞ በነበረው ታሪፍ እንደሚከፍሉ አክለዋል፡፡ ደንበኞች የሚጠቀሙት የኃይል መጠን በጨመረ ቁጥር የሚከፍሉበትን ሥሌት እያደረገ እንደሚሄድ ገልጸው፣ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል በቁጠባ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሦስት ሚሊዮን ያህል ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ 80 በመቶ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ናቸው፡፡ በ2012 ዓ.ም. ለአንድ ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ማቀዱን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይልና መሣርያዎች ስርቆት ድርጅቱ እየገጠመው ያለ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ከኃላፊዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በንግድና በአነስተኛ ማምረቻ ሥራዎች የተሰማሩ አንዳንድ ግለሰቦች በኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አቶ እሱባለው ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ ምሰሶዎችና ትራንስፎርመሮች ላይ ዝርፊያ እየተፈጸመ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በተለይ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በክሬንና በጭነት ተሽከርካሪዎች የታገዘ የትራንስፎርመር ዘረፋ እየተፈጸመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባና ዙሪያው በሚገኙ ከተሞች 156 የስርቆት ወንጀሎች መፈጸማቸው፣ በዚህም በድርጅቱ ላይ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰ አቶ እሱባለው አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት 31 ትራንስፎርመሮች በአዲስ አበባና አካባቢዋ መሰረቃቸውን፣ ስርቆቱ በአብዛኛው የሚፈጸመው በበዓላት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን በመጠቀም አገልግሎቱን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡