Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ሪፎርሙን አስመልክቶ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ አካላትን አስጠነቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የጀመረውን የቴሌኮም ሪፎርም ፖሊሲ አስመልክቶ የተሳሳተ መግለጫ ሰጥተዋል ያላቸውን መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች፣ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ኢትዮ ቴሌኮም አስጠነቀቀ፡፡

የቴሌኮም ሪፎርም እንዲሳካ ትክክለኛና ወቅታዊ የሆነ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማድረስ ወሳኝ እንደሆነ የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም ጉዳዩ የማይመለከታቸው፣ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ያልሆኑ ተቋማት የሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ሠራተኞቹንና አጋሮቹን ግራ እያጋባ በመሆኑ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

የድርጅቱን የመጀመርያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው ሐሙስ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞችና ማኔጅመንት ተረጋግተውና ተናበው ሥራቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙ ቢሆንም ጉዳዩ የማይመለከታቸውና ስለቴሌኮም ዘርፍ ግንዛቤ የሌላቸው ኃላፊዎች የሚሰጡት የተሳሳተ ማብራርያ በኩባንያው ሠራተኞች ላይ ውዥንብር እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

‹‹ለውጥ ይኖራል ሲባል ሠራተኛው ሥጋት ውስጥ ይገባል፡፡ ማኔጅመንትም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ የዕለት ተዕለት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ይበደላል፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ይህ እንዳይሆን ማኔጅመንቱ ለሠራተኛው የቴሌኮም ሪፎርም ምን ማለት እንደሆነና ለምን እንዳስፈለገ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲሠራ አመራር በመስጠት ላይ እንደሆነ፣ በዚህም ኩባንያው አመርቂ ውጤት እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ያለበትን የውጭ ብድር በአግባቡ መክፈል በመጀመሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ባሻሻለበት ወቅት፣ ስለፕራይቬታይዜሽንና ሊበራላይዜሽን የሚሰጡዋቸው የተሳሳቱ መረጃዎች አጋሮቹን ውዥንብር ውስጥ እየከተታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ስንገነባ ሌላው የሚያፈርስ ከሆነ ለቴሌኮም ሪፎርም አይጠቅምም፣ አገርም ይጎዳልና ይህ ድርጊት እንዲታረም አሳስበናል፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት ኢትዮ ቴሌኮም መንግሥት የቀረፀውን የቴሌኮም ሪፎርም ፕሮግራም መሠረት አድርጎ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን የሚያስችለውን ‹‹ብሪጅ›› የተሰኘ የንግድ መርሐ ግብር ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን፣ በዚህም አመርቂ ውጤት በማግኘት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን የማፍረስ ዓላማ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ለውጥ ሊደረግ ነው ተብሎ ኢትዮ ቴሌኮም የሚፈራርስበት ሁኔታ አይፈጠርም፣ አናደርግም፣ ይህ እንዲደረግ አንፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡

የቴሌኮም ፕራይቬታይዜሽን አስመልክቶ ለውጡን በዋነኛነት የሚመራው የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሆነ ጠቁመው፣ ማንኛውንም መግለጫ መስጠት የሚችለው ሚኒስቴሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የፕራይቬታይዜሽኑን ሥራ በአማካሪዎች ለማሠራት ኩባንያዎች እንዲጫረቱ መጋበዙን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ሁለት ኩባንያዎች ድርድር ጀምረዋል የሚባለውን ዘገባ አስተባብለዋል፡፡

መንግሥት ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ ገበያው እንዲገቡ መወሰኑን አስታውሰው፣ ፈቃድ የሚሰጠው አዲስ የተቋቋመው የኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ፈቃድ መስጠቱ የራሱ ሒደት እንዳለው ጠቁመው፣ ፈቃድ የሚያገኙት ኩባንያዎች ገብተው ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ ጊዜ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ውድድር ገበያ የሚገባ በመሆኑ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን አደረጃጀቱንና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በማሻሻል ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ያለውን ንብረት ዋጋ ለማወቅ ኬፒአምጂ KPMG የተሰኘ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር የንብረት ትመና ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የመጀመርያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለመገናኛ ብዙኃን አቅርቧል፡፡ ኩባንያው 10.1 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘና የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የሩብ ዓመቱ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ21 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡

ከውጭ አገልግሎት 41.15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም የ129 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በሩብ ዓመቱ ኩባንያው 141.5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ብድር እንደከፈለ የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ቀደም ሲል ብድሩን ለመክፈል አዳግቶት እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ብድሩን በአግባቡ መክፈል በመጀመሩ ከንግድ አጋሮቹ ጋር ያለው ግንኙነት እንደተሻሻለ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች ቁጥር ወደ 44.4 ሚሊዮን እንዳሳደገ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 42.9 ሚሊዮን የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ናቸው፡፡ 21.6 ሚሊዮን የዳታና ኢንተርኔት፣ አንድ ሚሊዮን የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ደንበኞች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ የቴሌኮም ስርፀት ከ41.1 በመቶ ወደ 45 በመቶ እንዳደገ ተገልጿል፡፡

እያደገ የመጣውን የሞባይል፣ የዳታና የኢንተርኔት ፍላጎት ለማሟላት ኩባንያው የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

የመሬት አቅርቦት መዘግየት፣ የቴሌኮም ማጭበርበርና የመሣርያዎች ስርቆት ኩባንያውን የገጠሙት ዋና ዋና ፈተናዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች