Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ኃላፊነት አለባቸው!

በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ አገር መሠረታዊ ለውጥ ውስጥ ስትገባ፣ ከየአቅጣጫው የተለያዩ ፍላጎቶችና ስሜቶች መንፀባረቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ፍላጎቶችና ስሜቶች እርስ በርስ ከመደጋገፍ በተጨማሪ፣ የእርስ በርስ ጉሽሚያና ፍትጊያም ስለሚያስከትሉ ለውጡ በወጀብ ሊናጥ ይችላል፡፡ የተለያዩ ክስተቶችም የሚያስከትሉት ወጀብ መደናገጥን፣ ሥጋትን፣ ግራ መጋባትንና ተስፋ መቁረጥን ጭምር ሊያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወጀቡን በፅናት በመቋቋም የተስፋ ጭላንጭል የመፍጠር ኃላፊነት፣ ለአገራቸው የሚያስቡ ዜጎች ግዴታ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያም ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ የተጓዘችበት ለውጥ በርካታ ተስፋ ሰጪ ጅማሬዎች ቢኖሩትም፣ በእየፈፋውና በእየገመገሙ የሚሰሙ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች አልተለዩትም፡፡ ነገር ግን የአገር ጉዳይ ተስፋ ስለማይቆረጥበት፣ ለማንም አደራ ስለማይባልበትና ስለማይዘናጉበት ሁሌም ንቁ መሆን የግድ ይላል፡፡ ለሥልጣን፣ ለግል ጥቅም፣ ዝና፣ ክብርና ስም ሲባል የሚፈጸሙ አላስፈላጊ ድርጊቶችን መታገል ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና ለዜጎች ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ በእኩልነት ተደራሽ እንዲሆኑ ተባብሮ መሥራት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥታዊ ሥልጣንም ሆነ የአገር ሀብት ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ሳይሆን፣ ብዙኃን በነፃነት የሚኖሩበት ሥርዓት ማረጋገጥ የኢትዮጵያዊያን የማይታለፍ ግዴታም ኃላፊነትም ነው፡፡

ከአገር ህልውና በላይ የሚቀድም ስለማይኖር የግለሰቦችና የቡድኖች ጩኸት አገር ማደንቆር የለበትም፡፡ ጥቂቶች መድረኩን ተቆጣጥረው አጀንዳ እየፈበረኩ ብዙኃኑን ማስጨነቅ አይኖርባቸውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥቂቶች ይጮሃሉ፣ ብዙኃን ግን በዝምታ ተውጠዋል፡፡ አጋጣሚው የተመቻቸላቸው እንዳሻቸው አገርን ሲያምሱ፣ የብዙኃን በአርምሞ ውስጥ መሆን ያሳስባል፡፡ ያለችን አንድ አገር ናትና ለህልውናዋ በፅናት መቆም የግድ መሆን አለበት፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች፣ ምሁራንም ሆኑ የቤተ እምነቶች መሪዎች፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል መጨነቅና መጠበብ አለባቸው፡፡ ጥግ ይዞ ማጉረምረም ወይም በሐሳብ መብሰልሰል ፋይዳ የለውም፡፡ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በዘመናት አብሮነቱ የሚጋራቸው በርካታ የጋራ ጉዳዮች አሉት፡፡ ሥነ ልቦናው በጣም የተቀራረበ በመሆኑም አንዱ ያለ ሌላው ሕይወት ይከብደዋል፡፡ ይህንን የቤተሰብ ያህል የተዛመደ ሕዝብ ለማበጣበጥና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚሞክሩ ኃይሎችን፣ በተባበረ ክንድ የማስቆም ኃላፊነት የሁሉም መሆን አለበት፡፡ የጋራ ኃላፊነት ነውና፡፡

ጥቅማቸውና ክብራቸው የተነካ የሚመስላቸው ‹አገር ልትፈርስ ነው፣ ልትበተን ነው…› እያሉ ሲያላዝኑ እነሱ እንደሚያስቡት ሳይሆን፣ የተሻለ ተስፋና ብሩህ ዘመን እንዳለ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ አገር የምትለካው በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት አለመሆኑን ተግባራዊ ትምህርት መኖር አለበት፡፡ ማንም እየተነሳ የአገርን ክብርና ሞገስ ሲያንኳስስ ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ በበርካታ ትውልዶች መስዋዕትነት እዚህ የደረሰች ታሪካዊት አገር መሆኗን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ህልውና በላይ የምንደራደርበት ምንም ዓይነት ጉዳይ እንደሌለ መገንዘብም ማስገንዘብም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በትውልዶች ቅብብሎሽ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየተከፈለላት ለዚህ ትውልድ ስትተላለፍ፣ ይህም ትውልድ ታሪካዊ አደራውን ተረክቦ የሚፈለግበትን ግዴታ ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህ ኃላፊነት ተጠያቂነት እንዳለበትም መገንዘብ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ ከችግሮቹ የሚያላቅቃት ሁነኛ መፍትሔም ያስፈልጋታል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው ችግሮቿን ከማቃለል ይልቅ፣ በችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮችን መደራረብ ተለምዷል፡፡ በእዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ድርጊት ላይ የሚሳተፉት ደግሞ ለአገር ምንም ደንታ የሌላቸው ናቸው፡፡ የእነሱ የሥልጣንና የጥቅም ጥማት እስካልረካ ድረስ አገር ከማተራመስ አይመለሱም፡፡ እነዚህን በቸልታ ማየት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም ከሌለ ማንም ካሰበው ቦታ ሊደርስ አይችልም፡፡ ሰላምን እያናጉ ዓላማን ማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች ካሉም፣ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ትርምስ ውስጥ ነው የሚገቡት፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ግጭት በመቀስቀስ ሰላማዊ ዜጎችን መግደል፣ ማፈናቀል፣ መዝረፍና የሁሉም ነገር የበላይ ለመሆን መሞከር ውጤቱ ቀውስ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ባለመገዛት ሥርዓተ አልበኝነት መፍጠርም የማይወጡት አረንቋ ውስጥ ይከታል፡፡ ከትናንት ጉልበተኞች አወዳደቅ ያልተማሩ አዳዲስ ጉልበተኞችም መረዳት ያለባቸው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ የፈለጉትን መፈጸም እንደማይቻል ነው፡፡ የጉልበት መንገድ የሚወስደው ወደ አምባገነንነት ነው፡፡ አምባገነንነት ደግሞ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ኋላቀርነት ነው፡፡ ኋላቀርነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ዛሬም ከእነ ክፋቱና ውርደቱ በጉልህ ይታያል፡፡ አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን መገንዘብ ያለባቸው፣ ተመራጩና የሚያዋጣው መንገድ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መሠረት ጥብቅና አስተማማኝ እንዲሆን፣ አስፈላጊዎቹን ነገሮች ሁሉ ለሟሟላት መረባረብ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧ በኩራትና በነፃነት የሚኖሩበት ሥርዓት መገንባት የኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በተለይ አገር ለመምራት ኃላፊነት የወሰዱም ሆኑ ነገ ሥልጣን ለመረከብ የሚያስቡ ከጥቅም ይልቅ ለፍትሕ፣ ከሥልጣን ይልቅ ለሰብዓዊነት ዋጋ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፁ መደመጥ አለበት፡፡ በሕዝብ ድምፅ ብቻ ሥልጣን መያዝ መለመድ ይኖርበታል፡፡ በአሻጥርና በክፋት የተተበተበው ኋላቀሩ የፖለቲካ ምኅዳር መሠልጠን ይጠበቅበታል፡፡ የፖለቲካ ተዋናዮቹም ሆኑ ተከታዮቻቸው ለዴሞክራሲያዊ ሕግጋት መገዛት አለባቸው፡፡ የጨዋታ ሕጉን ሳያውቁ ፖለቲከኛ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ እያወቁ እየጠፉ ማደናገርም እንዲሁ፡፡ ሕዝብ የአገሩ ሉዓላዊ ባለቤት ስለሆነ መከበር አለበት፡፡ ሕዝብን የማያከብር ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቪስት ስለሕዝባዊነት የመናገር የሞራል ብቃቱ የለውም፡፡ ሕግ የማያከብሩ፣ ጨዋነት የጎደላቸው፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የማይገዙና በአጠቃላይ ከሥልጡን አስተሳሰብ የተጣሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ራሳቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ለአገር ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ ያላቸው ደግሞ፣ በቁርጠኝነት ኃላፊነታቸውን መወጣት ግዴታቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት በተግባር ሊረጋገጡ የሚችሉት ሕጋዊነት በሕገወጥነት ላይ የበላይ መሆን ሲችል ብቻ ነው፡፡ ነጋ ጠባ አገር ለማፍረስ የሚያሴሩና የእነሱ ፍላጎት እስካልተሟላ ድረስ ሕዝብ የሚያተራምሱ ከንቱዎች አደብ የሚገዙት፣ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው በተግባር ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...