Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕወሓት የሚያወጣቸው መግለጫዎች በሕዝቡ ውስጥ መደናገርን እየፈጠሩ መሆናቸውን ኢሕአዴግ አስታወቀ

ሕወሓት የሚያወጣቸው መግለጫዎች በሕዝቡ ውስጥ መደናገርን እየፈጠሩ መሆናቸውን ኢሕአዴግ አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የግንባሩ አባል የሆነው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰሞኑን የሚያወጣቸው መግለጫዎች፣ የተሳሳቱና በሕዝብ ውስጥ መደናገር እየፈጠሩ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ማምሻው ላይ የወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በሕወሓት የኢሕአዴግን ውህደት አስመልክቶ የሚሰጡ መግለጫዎች የተሳሳቱና አደናጋሪ በመሆናቸው ለሕዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈልጓል፡፡

ኢሕአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ኅብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ ለማሸጋገር በ1996 ዓ.ም. ከተካሄደው አምስተኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ መቆየቱን የሚገልጸው የኢሕአዴግ ምክር ቤት፣ በተለይ ባለፈው ዓመት በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የጥናት ሥራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህድ ፈጥረው ጠንካራ አገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር መወሰኑን ገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ሕወሓት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውህደቱ ላይ አሉታዊ ገጽታ ያላቸውን ተደጋጋሚ መግለጫዎች እያወጣ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ‹‹ሕወሓት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በሁለት መሠረታዊ  ምክንያቶች ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን፤›› ያለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት፣ የመጀመርያው ስህተት ከድርጅት አሠራርና ዲሲፕሊን ጋር ሲያያዝ ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ይዘቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ሕወሓትን ጨምሮ ሌሎች አጋርና አባል ድርጅቶች ኢሕአዴግን ወደ ውህደት የሚያሸጋግረው ጥናት በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ያለ ልዩነት መወሰኑን መግለጫው አስታውሶ፣ ሁሉም ድርጅቶች በጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተው ጥናቱ እንዲዳብር የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ከውሳኔ በፊት ጥናቱን የሚያዳብሩ ሐሳቦችን የማሰባሰብ ናቸው ያለው መግለጫው፣ በዚህ ደረጃ የተካሄዱ የአመራር ውይይቶች ላይ ሕወሓትና ሌሎች አባልና አጋር ድርጅቶች መሳተፋቸውንና አስተያየታቸውን መስጠታቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹የተሰጡ አስተያየቶች ጥናቱን ለማዳበር ወይም ያልታዩ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲዳሰሱ ለማድረግ እንጂ የውሳኔ ወይም የአቋም ጉዳይ ሆነው የቀረቡ አልነበሩም፤›› በማለት፣ የመጨረሻው የውህደት ውሳኔ አሠራሩን ጠብቆ ወደፊትም የሚታይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ደረጃና የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ሳይገለጽበት፣ ሕወሓት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅቱን አሠራርና ዲሲፕሊን የጣሰ መሆኑን የገለጸው የኢሕአዴግ ምክር ቤት፣ መግለጫው ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ሊታረም ይገባል ብሏል፡፡

ምክር ቤቱ የሕወሓት ሌላኛው ስህተት ያለው ደግሞ፣ ውህደቱን አሃዳዊ መንግሥት ለመመሥረት የታቀደ አስመስሎ ማቅረቡ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ‹‹ፓርቲው ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ በሚቀየርበት ወቅት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር መብታቸው እንደሚገፈፍና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ፈርሶ አሃዳዊ መንግሥት እንደሚመሠረት አድርጎ የሚያቀርበው ሐሳብ ለማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር፣ ለመከራከሪያ የሚሆን ተጨባጭ ነገር የለውም፤›› ብሏል፡፡ የኢሕአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውኃ የሚቋጥር መከራከሪ አይደለም ያለው ምክር ቤቱ፣ ኢሕአዴግ ወደ ውህደት መጥቶ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ቢሆን ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን ዕውን በማድረግ እኩልነትና ፍትሕ የነገሠባት፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ይቻላል እንጂ የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን መብት የሚሸራርፍበት ምንም ምክንያት የለውም ብሏል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ ቆይቶ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ ችግሮች የተከበበው የኢሕአዴግ አደረጃጀት የኦሮሞ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥያቄን ለመመለስ የማይመች መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢሕአዴግ አደረጃጀትን በዘመናዊ አሠራር የሚመራ ፓርቲ ለመመሥረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሐሳብን በመደመር ሐሳብ ለመተካት ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን ፓርቲው ገልጾ፣ የመደመር ሐሳብ ከዚህ ቀደም የነበሩ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከርና የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት የአዲሱን ትውልድ መብትና ጥቅም ያስከብራል ብሏል፡፡

እስካሁን ምላሽ ያገኙ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ምላሽ ላላገኙ የሕዝብ ጥያቄዎች ትኩረት በመስጠት፣ በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት አቅጣጫ መቀመጡንም ፓርቲው ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...