Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ከፖለቲከኞችና ከፖለቲካ በላይ እንደ ቀለበት ሁሉንም ያቆራኘች አገር ትቀድማለች››

‹‹ከፖለቲከኞችና ከፖለቲካ በላይ እንደ ቀለበት ሁሉንም ያቆራኘች አገር ትቀድማለች››

ቀን:

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የሰላም ሚኒስትር

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ጥሩና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቀላቅለው የሚገኙ በመሆናቸው በግልጽ መነጋገር ቅድሚያ የሚሰጠው ከመሆኑም ባሻገር፣ ከፖለቲከኞችና ከፖለቲካ በላይ እንደ ቀለበት ሁሉንም ያቆራኘች አገር እንደምትቀድም የሰላም ሚኒስትሯ ተናገሩ፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ይህንን የተናገሩት ዓርብ ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ብሔራዊ የአገር ሽማግሌዎች ምክክር መድረክ፣ ‹‹ለአገራዊ ችግር አገራዊ መፍትሔ›› በሚል መሪ ቃል በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ ፖለቲከኞች በአገር ጉዳይ ላይ ያላቸው ቦታና ሚና እንዳለ ሆኖ፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣትና ቀጣይነት ያለው ሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለማካሄድ፣ ሁሉንም አቆራኝታ የያዘችን አገር መጠበቅ ግድ የሚል መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የድንቅና ረቂቅ ባለቤት የሆኑት ለማንም የማይወግኑ፣ ለማንም የማይቆሙ፣ አገርንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ብቻ የሚወዱ የአገር ሽማግሌዎች ሚና ትልቅና መተኪያ የሌለው የፈውስ መንገድ እንደሚሆኑ እምነታቸው መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት ጥሩና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቀላቅለው የሚገኙበት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ሁሉንም ነገር በግልጽ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዱ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ ሲያስብ፣ ሌላው ደግሞ ሁሉም ነገር ጨለማ እንደሆነ ካሰበ ለማቀራረብ አስቸጋሪና አዳጋች እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

በማንኛውም የሽግግር ሒደት ውስጥ እንደሚያጋጥመው ተግዳሮት ኢትዮጵያም የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟት የጠቆሙት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ይኼ ሊስተባበል የማይችል ሀቅ ቢሆንም ድሉንም ሆነ ችግሩን በልክ በልኩ ከማየት አንፃር ትልቅ ጎዶሎ ያለ በመሆኑ፣ ይኼንን ጎዶሎ ለመሙላት ወይም ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎችን ያህል ሚና ያለው አካል አለ ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ምን ያህል ሚናውን እንደተወጣና ምን ያህል እንደቀረው ከመከረና ከተመካከረ፣ ፊት ለፊት ያለው ተግዳሮት ከኢትዮጵያውያን በተለይም ከአገር ሽማግሌዎች የማያልፍ መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ኢትዮጵያውያን በችግራቸውና በባህሪያቸው ልክ መግባባት ከቻሉ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ አሸማጋይና አስታራቂ ሳያስፈልግ፣ ሸምጋይም ሆነ አስታራቂ ራሳቸው መሆን እንደሚችሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በርትተን፣ ተደጋግፈንና ተጋግዘን ከሠራን አልጨለመም፣ ሩቅም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አገር ወዳድና ብዙ ዕውቀት ያላቸው አባቶች በጋራ በመሆን፣ የአገርን ሰላም ለመጠበቅ ተደራጅተው ማየት ትልቅ ተስፋ እንደሚያጭር የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ስለአገር ለመማርም ሆነ በርትቶ ለመሥራት መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የለውጥ ሒደት ጥሪ የባህላዊ እሴቶችን መመለስና አዲሱ ትውልድ ወርሶ እንዲተገብራቸው ማድረግን፣ እንዲሁም የዘላቂ ሰላም መገንቢያ እንዲሆን ማድረግን እንደሚያካትትም ሚኒስትሯ አክለዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎች ሳይሰለቹና ደከመን ሳይሉ እስካሁን ያሳረፉት አሻራ ተጠናክሮና ጎልብቶ መቀጠል ያለበት ወቅት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ሳይታክቱ ከሁሉም ኢትጵያውያን ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቱን በዘላቂ ሰላምና በአገር ግንባታ ሒደት ላይ በማሳተፍ ባህልንና አገርን እንዲቀበል፣ እንዲሁም አገር በቀል ሥርዓትን በእጅ አዙር ሳይሆን በቀጥታ ከአገር ሽማግሌዎች እንዲማር ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ የፀጥታ ዕክሎችን በብልኃት ለመፍታትም የአገር ሽማግሌዎች ሚና መተኪያ የሌለው አማራጭ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ የፍትሕ አገልግሎትን የሚገኘው ከአባቶችና ከተቋማት መሆኑን ጠቁመው፣ ሽማግሌዎች እያደረጉት ያለውን ጥረት በማቀናጀት በመላ አገሪቱ የተሟላ ሰላም እንዲኖር ለማስቻል የምክክር መድረክ መዘጋጀታቸውን አወድሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለውን ዴሞክራሲ በሁሉም ለማስረፅ፣ ከአገር ሽማግሌዎች ኢትዮጵያዊ የሆነና መከባበር ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ቅብብሎች እንደሚያስልግ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡ የሐሳብ ብዝኃነት የዴሞክራሲ መሠረት እንደሆነና በምን መንገድ መቅረብ እንዳለበት ማሰብ ደግሞ የጥበብ አካል በመሆኑ፣ ይህንን የተጎናፀፈ የኅብረተሰብ አካል በሐሳብ ብዝኃነት እንደማይጋጭ ተናግረዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች የተጫወቱት ሚና ሲወሳ የሚኖር መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ በአገሪቱ ያሉ የሽምግልና አማራጮች ያሉትን ድልብ ማኅበራዊ እሴቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ዘላቂና መተኪያ የለሽ የሰላም መገንቢያ መሣሪያ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

አገር በአንድ ጊዜ ተገንብቶና ተቋጭቶ የሚያበቃ ሳይሆን፣ ከዘመን ዘመን በሒደት የሚገነባ የሕይወት ሰንሰለት መሆኑን ከአገር ሽማግሌዎች መማር የተቻለ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ትልልቅ እሴቶቻችን ቅኝ እንደተገዛ አገር በፍጥነት እየታጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ በአኅጉሪቱም ጎልቶ ከመታየቱ አንፃር መቋቋም ካቃተን ብዙ ነገር መላቅጡን ያጣል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ስብራትም ቢሆን ሊጠገን የሚችለው በአገር ሽማግሌዎችና በጥበበኞች በመሆኑ፣ ጠንክሮ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘንድሮ ሁሉም ሰው የታሪክ ልሂቅ ስለሆነ ያለፈውን ታሪክ ለባለሙያዎች ልተውና ከዘመናት በመሽቀንጠር ሃምሳ ዓመት ወደ ኋላ ብንሄድ፣ አገራችን ልጆቿ ይጠቅማል ብለው ባመጡባት የምሥራቅ ዕሳቤ (Ideology) አብዮት ቢመጣም፣ የደረሰው ዕልቂት ምናልባት ወደፊት ታሪክ ተገቢውን ቦታ ይሰጠዋል ብዬ እገምታለሁ፤›› ያሉት ደግሞ፣ የብሔራዊ የአገር ሽማግሌዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደገለጹት በዚህ ጊዜ፣ ዘመን የማይተካው የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር መሪዎችንና አፍላ ወጣቶችን አገሪቱ አጥታለች፡፡ ብዙ ወላጆችንም ጧሪና ቀባሪ አሳጥቷል ብለዋል፡፡

‹‹ያለፉት ጥቂት ዓመታትን ብንመለከት በመሠረተ፣ ልማትና በአካባቢ ሰላም ከፍተኛ ዕድገት ቢመዘገብም፣ ከሚያገናኙን ይልቅ በሚያለያዩን ላይ በርትተን በመሥራታችን አገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ጨምሯል፡፡ አስፈሪ የወጣቶች ሥራ አልባነት ጋር ተደማምሮና ጎሳን ያማከለ የፖለቲከኞች አመራር ተጨምሮበት፣ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ ድንጋይ ተኮልኩሎና አጥር ታጥሮ ወደ ሌላኛው ማዶ ማለፍ ብርቅ እየሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ተዋልደውና ተጋምደው ወደኋላ ከአንድ ትውልድ በላይ መቁጠር እስከሚያቅታቸው ድረስ ተሰናስለው የኖሩ ቤተሰቦች፣ ሆድና ጀርባ መሆናቸውንና ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በከፋ ሁኔታ ሕይወታቸው በማያውቁት ምክንያት መቀጠፉን ጠቁመው፣ አሁንም ላለመቀጠሉ ማረጋገጫ አለመኖሩን አክለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ ‹‹የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የት ሄደው ነበር?›› በማለት የጠየቁት መስፍን (ፕሮፌሰር) ‹‹አሉ›› በማለት ራሳቸው ምላሽ በመስጠት፣ የአገር ሽማግሌዎቹ በሶማሌና በኦሮሚያ፣ በጋሞ፣ በወልቃይት፣ በምዕራብ ወለጋና በሌሎችም በርካታ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን መፍታታቸውን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎች መንግሥት ያቋቋመው የሰላምና ዕርቅ ኮሚሽን አጋዥ ሆነው የሚሠሩና እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ለሁለት ቀናት በሚያደርጉት ምክክርና በየክልላቸው የሚፈጠረውን ግጭት፣ እንዴት እንደሚፈቱ ልምዳቸውን ከተለዋወጡና ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ጠቅላላ የትስስር መድረክ በመፍጠር፣ ለወደፊቱ መንግሥትንና ሕዝብን ለማገዝ ወይም ሲያስፈልግም ለመገሰጽ አቅም ያላቸውን የአገር ሽማግሌዎች የሚሰባስብ ተቋም እንደሚፈጥሩ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የምክክር መድረኩን በትብብር ያዘጋጀው ጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ዋና ኃላፊ ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች በትግራይ ክልልና አማራ ክልል መሪዎች መካከል የነበረውን ውጥረት ለማርገብ ያደረጉትን ጥረትና ያመጡትን ውጤት፣ እንዲሁም በኦዴፓና በኦነግ መካከል አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ያመጡትን ውጤት ጠቁመው፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የአገር ሽማግሌዎች በአገራችን ጉዳይ ያገባናል፤›› በማለት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...