Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወዴት እያመራ ነው?

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወዴት እያመራ ነው?

ቀን:

በዓለም ተፈቃሪ የሆነውን አትሌቲክስ በቴሌቪዥን መስኮት ሲመለከቱትና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲያሸንፉ በደስታ መጦዝ የበርካታ ኢትዮጵያውያን መገለጫ ነበር፡፡ የተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መመልከት በራሱ ትልቅ ደስታን ይፈጥራል፡፡ 

የአትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው በቆጂ ኦሊምፒክ ወይም ዓለም ሻምፒዮና ሲኖር ሕፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም ቴሌቪዥን ላይ ተደቅኖ ነው የሚውለው፡፡ በተለይ ኦሊምፒክና ሻምፒዮናዎች በሚኖሩበት ወቅት በየሠፈሩ በጠዋት ተነስቶ ዱብ ዱብ ማለት፣ ውድድር አዘጋጅቶ ከተማዋን ማድመቅ የተለመደ ድርጊት ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ለሙያው ቅርብ የሆኑ ሰዎች አሠልጣኞች፣ የቀድሞ አትሌቶች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የአትሌቲክሱ የቅርብ ሰዎች አትሌቲክስ ሱስ የመሆን አባዜ እንዳለው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

በዚህ መጠን ሊወደድ የቻለበት ሚስጥርም በጊዜው በዓለም አደባባይ የአገር ባንዲራን ማውለብለብ መቻል ከክብርም በላይ ትልቅ ዕድል ስለነበር ነው፡፡ የዚያ ዘመን አትሌቶችም ባንዲራውን በልባቸው አምቀው ወደ ውድድር መግባት ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር፡፡ በጊዜው ወርቅ ማምጣት ላይ ተግባብተው፣ ሰዓት ማሻሻሉ ላይ ብቻ እንደ ሚጨነቁ የቀድሞ አትሌቶች ይናገራሉ፡፡

በአንጋፋ አሠልጣኞች የሠለጠኑት የቀድሞ አትሌቶች በሥነ ምግባር የታደሉ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ እንደ አባትና ልጅ የሚተያዩት እነዚህ አይረሴ አትሌቶች ሥነ ምግባርን ተቀዳሚ በማድረጋቸው የማይረሳ አሻራ ጥለው ለአዲሱ ትውልድ አስረክበዋል፡፡

የቅርብ ጊዜ ትውስታ እንኳን ብናወሳ በአሠልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ዘመን ላይ የነበሩ ፈርጦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሴቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚ እንዲሁም በወንዶች ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ስለሺ ስህን፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም፣ አሰፋ መዝገቡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ እንደ ዛሬው ቀላል ባልሆነ ዘመን ውድድሮች ላይ መሳተፍ ቀላል አልነበረም፡፡ አንድ አትሌት ምንም እንኳን ችሎታው ድንቅ ቢሆንም ሥነ ምግባር ከሌለው የትኛውም ውድድር የመሳተፍም ሆነ የመመረጥ ዕድል አይኖረውም፡፡

ምክንያቱም ሥነ ምግባር ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ አትሌቶች ከአሠልጣኞቻቸው ጋር የተጋጩበት ጊዜም ነበር፡፡ አለመግባባታቸው ከአቅም በላይ ሆኖም ሽማግሌዎች ዘንድ የደረሰበት ወቅትም ነበር፡፡ ዳሩ ግን አንድ አትሌት ምንም እንደ ንፋስ መክነፍ ቢችል ሥነ ምግባርና አገርን ማስቀደም ድርድር የሌለው ነገር እንደሆነ የቀድሞ አትሌቶች ያስታውሳሉ፡፡

ጊዜ ጊዜን እየወለደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡ በርካታ አዳዲስ አትሌቶች በግላቸው እንዲሁም በማናጀሮቻቸው የሚወዳደሩበት ዘመን መጣ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ አዳዲስ አትሌቶች የተለያዩ ውድድሮች በግላቸው በመሳተፍ ለግላቸውም ሆነ አገርን ወክለው ሲወዳደሩ ቢያንስ አገሪቷ በረጅም ርቀቱ የምትታወቅበት ውድድሮች ድል ማስጠበቅ እየተሳናቸውም መምጣቱን የሚያነሱ አሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች አትሌቶቹ በዓመት ውስጥ በግላቸው ያደረጉትን ውጤት ተከትሎ፣ ለብሔራዊ ቡድን የሚመረጡት በተለይ የቡድን ሥራ ላይ ክፍተቶች እየታዩባቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

ቀድሞ በኢትዮጵያ ኬንያውያን መካከል ከፍተኛ ፉክክር መመልከት የተለመደ ነበር፡፡ እንዲሁም በተወሰኑ ርቀቶች ላይ ኢትዮጵያ የበላይነት እንደ ነበራት ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያውያን በ5,000 እና 10,000 ሜትሮች ወርቅ ማምጣት ብርቅ አልነበረም፡፡ በአንፃሩ አሁን ላይ ኬንያ የበላይነቱን እየወሰደች የመጣች ይመስላል፡፡ ለዚህም በአንድ ወር ውስጥ ሁለት ክብረ ወሰን ማስመዝገብ የቻሉ አትሌቶች ማሳያ ናቸው፡፡

በቪየና ማራቶን 1፡59፡40 ማጠናቀቅ የቻለው ኢልዩድ ኪፕቾጌ (በዓለም አቀፍ ተቋም መመዝገብ ባይችልም) የሰሞኑ መነጋጋሪያ ነበር፡፡ ሌላዋ ኬንያዊት ብሪጅድ ኮስጄይ ማራቶንን 2፡14.04 በመግባት ከ16 ዓመት በላይ ቆይቶ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር ችላለች፡፡ በ17ተኛው የደሃ የዓለም ሻምፒዮና ላይም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ያሳዩት ስኬት ከኬንያ አንፃር፣ ለወደፊቱ ከፍተኛ ዝግጅትና የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው አመላካች ነው፡፡

በሻምፒዮናው ኬንያ አምስት የወርቅ ሁለት ብር፣ አራት የነሐስና በድምሩ 11 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከአሜሪካ ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ በተወሰኑ ርቀቶች ላይ አስቆጪና የልምድ ማነስ ስህተቶች ተደምረው በሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ ነሐስ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች፡፡ ውጤቱን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ሲሰነዝሩበት የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ የሥልጠና አሰጣጡ ክፍተት እንዳለበት የቀድሞ አሠልጣኞች ይናገራሉ፡፡

‹‹የእኛ አትሌቶችና የኬንያ አትሌቶች አቅም ተመሳሳይ ነው፡፡ እነሱ ከእኛ አትሌቶች ቢያንሱ እንጂ አይበልጡም፡፡ በማለት የቀድሞ አትሌትና የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩት ቶሎሳ ቆቱ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

እንደ ባለሙያው አስተያየት ከሆነ የኢትዮጵያ አትሌቶች ትልቁ ችግር የሥልጠና አሰጣጥ ነው፡፡ አትሌቶች አቅም እንዳላቸው የሚያምኑት አሠልጣኙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ቢያጤነው ይላሉ፡፡

በነበረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሴት ማራቶን ተወዳዳሪዎች ውድድሩን ማቋረጣቸውን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ የተሰጠው ምክንያት ትክክል እንዳልሆነና ይልቁንም አትሌቶቹ ድካማቸውን ቀንሰው ለግል ውድድራቸው ራሳቸውን ለማመቻቸት እንደነበር ሻምበል ቶሎሳ ያብራራሉ፡፡

‹‹ልጆቹ አቅም አላቸው፡፡ አቅማቸውንም መጠቀም ይችሉ ነበር፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳ ቀድሞ በነበረው የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ወቅት ማንኛውም አትሌት በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተመርጦ በፌዴሬሽኑ በተዘጋጀለት አሠልጣኝ ብቻ እንዲሠለጥን ግዴታ ነበር፡፡ በአንፃሩ አሁን ላይ አትሌቶች በግል አሠልጣኞቻቸው መሠልጠን ካዘወተሩ በኋላ ግን በፌዴሬሽኑ የሚዘጋጅላቸውን አሠልጣኝ ሲጠቀሙ አይስተዋልም፡፡ ይሄን ተከትሎም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡

እንደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ አስተያየት፣ በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና ቡድን ውስጥ ሁለት አትሌቶች በግል አሠልጣኝ መሠልጠን በመፈለጋቸው በእዚያው መንገድ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ነበር፡፡

የብሔራዊ ቡድን ዝግጅትን ተከትለው የተለያዩ ቅሬታዎች የማያጣው ፌዴሬሽኑ የአሠልጣኞች አመራረጥ በራሱ ለውጤቱ ቀውስ በዋንኛነት ይጠቀሳል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአንፃሩ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ማሸነፍ የቻሉና ሚኒማ ማሟላት የቻሉ አትሌቶቻችን ያስመረጡ አሠልጣኞች ብቻ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሆን እንደሚችሉ አቶ ዱቤ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹አትሌት የሌለውን አሠልጣኝ አድርጎ ለብሔራዊ ቡድን መምረጥ አዳጋች ነው፤›› በማለት አቶ ዱቤ ስለሁኔታው ያስረዳሉ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዓለም አቀፉን ሕግና ደንብ ተከትሎ ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ እንደሚመረጥ የሚገልጸው ፌዴሬሽኑ፣ በግል አሠልጣኞቻቸውም መሠልጠን የሚፈልጉትን አትሌቶች ፍላጎት እንደሚያከብር አልሸሸገም፡፡

የሰባት ወራት ዕድሜ ለቀረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ዝግጅቱ የሚጀመረው፣ በዓለም ሻምፒዮና ላይ የታዩት ችግሮች ከተቀረፉ በኋላ መሆኑን አቶ ዱቤ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...