መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ሲሰናዱ ከነበሩ ተጓዣች መካከል አንዱ ወዳጄ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከደረሰና ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ጣጣውን ጨርሶ ቢወጣም፣ በማግሥቱ ሳገኘው የጨዋታው አጀንዳ በጉዞው መጨረሻ ሰዓታት ማለትም በዱባይ የተመለከተውን ድባብ የሚያስቃኝ ነበር፡፡
የዱባይና የአቡ ዳቢ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች በዕለቱ በዲጅታል ቴክኖሎጂና በኤሌክትሮኒስ ቴክሎጂ የኢትዮጵያን ባንዲራ በምሽት ሲያሳዩ እንደነበር ትንግርቱን ከዚሁ ያልተጠበቀ ገጠመኝ መግለጽ ይጀምራል፡፡ በተለይ በአንደኛው ሕንፃ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ብቻም ሳይሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና (ዶ/ር) የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ ምሥልን በማፈራረቅ ሲያሳይ ነበር፡፡ ስለሚመለከተው ነገር ዓይኑን ማመን እንዳቃተው ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡
ይኸው ወዳጄ እንደገለጸው፣ የተለያዩ የንግድ ተቋማት በተለይም የነዳጅ ማደያዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ማየት የሚያስገርም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያዘወትሩባቸው የንግድ ድርጅቶችና የመዝናኛ ሥፍራዎች ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በቡድን እየሆኑ ደስታቸውን ሲገልጹም ተመልክቷል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በመጨረሻዎቹ የበረራ ሰዓታት ላይ በዱባይ የተመለከተው ልዩ ድባብም ስሜት እንደሚነካ በመግለጽ ትረካው ቀጥሏል፡፡ የበለጠ ትኩረቱን የሳበውን ድርጊት የተመለከተውም ዱባይ ኤርፖርት ለመሳፈር በደረሰ ጊዜ ነበር፡፡ በኤርፖርቱ ወደተለያዩ መዳረሻዎች የሚበሩትን ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን በጋራ ደስታቸውን ሲገልጹ ማየቱ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም በእልልታ የታጀበ የደስታ አገላለጽ ይታይ ነበር፡፡
ይህ ትዕይንትም የሌሎች መንገደኞችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ ባንዲራ ከየት እንዳመጡ ባይታወቅም፣ ባንዲራ የበለሱ ኢትዮጵያውያን ‹‹ይገባዋል፣ ይገባዋል፣…›› በማለት ድምፃቸውን እያጎሉ ይጨፍሩም ነበር፡፡ ይሁ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ከተሰማ በኋላ በዱባይና በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየፊናቸው ስሜታቸውን ሲገልጹባቸው ከነበሩ ትዕይንቶች መካከል የሚጎላውና የሚጠቀሰው ነው፡፡
ይህ በዱባይና በአካባቢው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥት ባሻገር የተለያዩ ተቋማትም ደስታቸውንና መልካም ምኞታቸውን የገለጹበት መንገድም ሊያስገርም ይችላል፡፡ በዱባይ እንደ ትንግርት የታየው ድባብ ሌላም መገለጫ እንደነበረው ሰምተናል፡፡ እንጀራ ፍለጋ በዱባይ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ በከተማዋ ግዙፍ ሕንፃዎች ላይ ጎልቶ እንዲታይ የተፈቀደለት የአገራቸው ባንዲራ እንደሆነ በኩራት ለቀጣሪዎቻቸው የተናገሩበትን ዕድል የፈጠረላቸው ነበር፡፡ ይህም ስሜቱ ምን ያህል እንደሆነና እንዴት መግለጽ እንደሚቻል ይቸግራል፡፡
እነዚህ ወገኖች ስለአገራቸው ለመግለጽ ዕድል ያገኙበትን አጋጣሚ በምን መልኩ ይናገሩት እንደነበር በቦታው ለሚመለከት የአገር ሰው ምን ያህል ጥልቅ ስሜት እንደነበረው መገመት ይችላል፡፡ ወዳጄ እንደሚለው በዱባይ ኤርፖርት ውስጥ የነበረው ትዕይንት አስገራሚ በሚል ብቻ የሚገልጽ አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለሽልማቱ ከበቁባቸው በርካታ ጉዳዮች ዋናው ‹‹ሞት አልባው ጦርነት›› ብለው የሚገልጹት የኢትዮጵያና ኤርትራ የረጅም ዓመታት ፍጥጫን በሰላም ለመቋጨት በመቻላቸው ነው፡፡ በዱባይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ደስታቸውን የገለጹትም ከዚህ አኳያ ሰላም በማውረዳቸው የተጎናፉት ያላሰቡት ትልቅ ክብር ሲሰጥ፣ ደስታቸውን ለመግለጽ ሲቃ ሲይዛቸው ማየት ልብ ይነካል፡፡
የዱባይ የተለየ በመሆኑና በዚያ የሚገኙ ዜጎችም ደስታቸው ምን ይመስል እንደነበር ለማመላከት ሞከርኩ እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማት ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ ያውም ስለሰላም ሲባል የተሰጠ በመሆኑ፡፡ የዓለም ሚዲያዎችም በሽልማቱ ዙሪያ ያስተጋቧቸው ዘገባዎች ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ መልካም አበርክቶ የነበረውና ወደፊትም ሊያበረክት የሚችለው አስተዋጽኦ በቀላሉ አይታይም፡፡
የፊት ለፊት ገጻቸውን በድህነት፣ በረሃብና በግጭት ገጠመኞቻቸን ሲያጭቁ የነበሩ ሚዲያዎች፣ ስለኢትዮጵያ በመልካም ዜና የተከሸኑ ወሬዎችን እየተቀባበሉ ማሠራጨታቸው አንገትን ቀና ያደርጋል፡፡ ለልብ ኩራት ያጎናፅፋል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡
በአንፃሩ ከእኛ በተሻለ እኚህን መሪ ዓለም የተገዘባቸውም ይመስላል፡፡ በአጭሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በፍቅርና በይቅርታ ላይ በሚያራምዱት የፀና አቋማቸው ያገኙት ውጤት ሲሆን፣ ለሽልማቱ ያበቃቸው ሥራ ብቻም ሳይሆን፣ እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሆ ብሎ የተቀበላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብም ጭምር እንደሆነ የሚያሳየን ይህ ሽልማት፣ እንደ አገር ኢትዮጵያን በመልካም ከፍ ከፍ ያደረገ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው፡፡
ሽልማቱን አሁን ካለው የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ስንመለከተው የዓብይ (ዶ/ር) ሽልማት ከባድ ኃላፊነትም ይዞ እንደሚመጣ መረዳትም ተገቢ ነው፡፡ የኖቤል ተሸላሚነታቸው ሲወሳ፣ ቁልጭ ባለ ንግግር ከሸላሚው ተቋም እንደተገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ይህ እውነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቀሪ ሥራዎችን በአግባቡ ለማካሄድ ግን ጤናማ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መኖርና መፈጠር አለበት፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት እንደታየው አደናቃፊና ሰዎችን ችግር ላይ ከሚጥሉ ተግባራት ራስን በማራቅ፣ በሰላምና በምክክር ሐሳብንና ልዩነትን መግለጽ የአዋቂዎች ግዴታና ኃላፊነት ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ሽልማት አገራዊ አጀንዳ ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል የሚጠቁም፣ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚያስተምር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ይህን አጋጣሚ እንደ ተጨማሪ ዕድል ተጠቅሞ ከአደንቃፊና ከክፉ ተግባራት ታቅቦ ወደ ሰላም መንገድ፣ ወደ ልማትና አምራችነት መገስገስ ዓለም የሚጠብቅንብን አጀንዳ ነው፡፡ የፖለቲከኛው አጀንዳ ሰላማዊ ትግል መሆን አለበት፡፡ በሌላ ዘርፍ ያለውም በተሰማራበት መስክ በጨዋነት በመሥራት አገርን፣ ሕዝብን ማገልገል ራስን ያስከብራል፡፡
የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መልካም ራዕይ ያለው ዜጋ ከመንደር ቡድንተኛነት ተላቆ ከፍ ባለ ደረጃ እያሰበ፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ነገር ስምን ማስጠራት እንደሚቻል፣ አመለካከትን ከዚህ አንፃር መቃኘት ቢቻል ውጤቱ ምን ያህል ዓለምን ባስደመመ ነበር፡፡
አገርን ወደ መልካም መንገድ ለማሻገር በሠለጠነ መንገድ መሞገት፣ ወደ ሥልጣን ለመምጣት በሕዝብ ተቀባይነት ላይ ብቻ እንደሚመሠረት አስቦ በመንቀሳቀስና ድል ማድረግ እንደሚቻል መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ሽልማት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሁሉም ለበጎ ተግባር ይትጋ!