Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሥነ ጥበብ ጠጋኝና ሠዓሊ ታደሰ ወልደ አረጋይ (1945 - 2012)

የሥነ ጥበብ ጠጋኝና ሠዓሊ ታደሰ ወልደ አረጋይ (1945 – 2012)

ቀን:

ኢትዮጵያ ለጥንታዊነቷ በአብነት ከሚቆሙት ቅርስና ውርሶቿ አንዱ ሥነ ሥዕል ነው፡፡ የሥዕል ጥበብ ከጥንታዊው የአክሱም ሥርወ መንግሥት ዘመን፣ በተለይ ከኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን በአመዛኙ የሚቀዳ ነው፡፡

ዘመናትን አቋርጦ የመጣው ትውፊታዊው ሥዕል ከ19ኛው ምዕት ዓመት ወዲህ ካቆጠቆጠው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥዕል ጋር መሳ ለመሳ መጓዙ አልቀረም፡፡ ዘመናዊው የሥዕል አስተምህሮት ጥንታዊው በብሉይነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ ጥንታውያን ሥዕሎች በዕድሜ ብዛት፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ የደረሰባቸውን አደጋ ወዘናቸውን ሳይለቁ እንዲጠገኑ በማድረግ ረገድ ጥቂት የማይባሉ ሥነ ሥዕል ጠጋኞችንና አዳሾችን አፍርቷል፡፡

ከእነዚህም መካከል በዘመናችን የሚወሳው ታደሰ ወልደ አረጋይ “አክሱማዊ” ነው፡፡ የአክሱምን ውርስና ቅርስ ጠብቆ ሲያስተላልፍ የኖረ ጠቢብ ነበር፡፡ ትውፊታዊውና ባህላዊው ሥዕል ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ ተጠቃሽም ነው፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ዘመናዊው ሙዚየም ሲደራጅ ሙያዊ ዕገዛ ማድረጉም ይነገርለታል፡፡ ከስድስት አሠርታት በፊት በመዲናዪቱ አዲስ አበባ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በተመሠረተው የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት (አሁን አለ የሥነ ጥበብ ዲዛይን ትምህርት ቤት) ትምህርቱን የቀሰመው ታደሰ ወልደ አረጋይ ዘመናዊ ሥነ ጥበብን ከእነ ጉተናዋ ያጠናው በእነ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ጠቢባዊ መምህርነት ነበር፡፡

በአክሱም ከየኔታ አለቃ ዮሐንስ ተክሉ የትውፊታዊ ሥዕል ወንበር ለሦስት ዓመታት የቀሰመውን ጥንታዊውን የአሣሣል ጥበብ ብሂልን ከባህል ማዛመድ በሚል ብሂል አልቆ ዘለቀበት፡፡ ቀፀለበት፡፡ ዝንባሌውና ርዕዩ ጥንታውያን ሥዕሎችን መጠገንና መንካባከብ ሆነና ለዚህ ይረዳው ዘንድ ስንቅ የሆነው በ1970ዎቹ መጀመርያ በዴንማርክ ያገኘው የሥዕል ጥገናና ክብካቤ ከፍተኛ የትምህርት ዕድል ነው፡፡ ‹‹ከባዕድ እየጎረስክ ወደ ዘመድ ዋጥ›› ሆነና በባህል ሚኒስቴር ከዕውቀትና ከሙያ ዘርፍ ባለሙያነት እስከ ዘርፍ ኃላፊነት ወደ አራት አሠርታት የሚጠጋ ዕድሜ ያህል ሠርቷል፡፡

ሠዓሊ ታደሰ ገጸ ታሪኩ እንደሚያስረዳው፣ በቀሰመው ጥልቅ ዕውቀት ከ50 በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ገዳማትና አድባራት ውስጥ የተሣሉ የግድግዳና የምሰሶ ሥዕሎች ጥገናና ክብካቤ አድርጎላቸዋል፡፡ ይህም የጥናትና ምርምር ቡድንን በመምራት በርካታ ሥራዎችንም አከናውኗል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ አክሱም ጽዮን፣ ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ፣ ጎርጎራ ደብረ ሲና ማርያም፣ አብርሃ ወአጽብሃ፣ ጨለቆት ሥላሴ፣ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም፣ ናርጋ ሥላሴ፣ እንዲሁም በሐረር የአርተር ራንቦ የቤት ውስጥ ጥንታዊ ሥዕሎች ይገኙበታል፡፡

ከጥገና ባሻገር በሠዓሊነቱም ትውታዊውን ሳይለቅ የራሱን ቱባ ሥዕሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በነኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ዴንማርክ፣ ቻይና፣ ጣሊያን ለዕይታ አብቅቷል፡፡ በአገር ውስጥ ሥራዎቹን ካሳየባቸው ቦታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ አዲስ አበባ ሙዚየም፣አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ፣ የጣሊያንና የጀርመን ባህል ማዕከላት፣ ሒልተን አዲስ አበባ ይገኙበታል፡፡

‹‹የምታውቀውን ሳታካፍል መሞት ቀድሞውንም አለመኖር ነው›› የሚል መርህ የነበረው ታደሰ፣ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በማስተማር ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

ከዘርዐ ክህነት ወገን የሆነው ታደሰ ከአባቱ ከአቦይ ወልደ አረጋይ ተፈሪና ከእናቱ ወ/ሮ ዘውዲቱ አሰጋኸኝ ጥር 29 ቀን 1945 ዓ.ም. በአክሱም ከተማ የተወለደ ሲሆን፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡

በቀድሞው የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብና ንድፍ ትምህርት ቤት በሥነ ሥዕል በዲፕሎማ ሲመረቅ፣ ከፍተኛ ትምህርቱን በዴንማርክ ዳኒሽ ሮያል አካዴሚ ኦቭ ፋይን አርትስ በሥዕል ጥገና (Art Conservation) የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በጣሊያን ሮም በኢንተርናሽናል ሄሪቴጅ ኮንሰርቬሽን ኤንድ ማኔጅመንት በግድግዳ ሥዕሎች ጥገናና ክብካቤ ዘርፍም ተመርቋል፡፡

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሥነ ጠቢቡ ታደሰ ወልደ አረጋይ ባደረበት ሕመም ምክንያት በተወለደ በ67 ዓመቱ አርፎ፣ ዓርብ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ፍሥሐ (ዶ/ር)፣ የቀድሞው የማስታወቂያና ባህል ሚኒስትር አቶ ወልደ ሚካኤል ጨሞ እና የቀድሞው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃራ ኃይለ ማርያም ተገኝተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...