Wednesday, June 19, 2024

ሥርዓተ አልበኝነት አደብ መግዛት አለበት!

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር የተጠናወተው የሐሳብ ድርቅ ለሥርዓተ አልበኝነት ምቹ መደላድል ፈጥሯል፡፡ የረባ ሐሳብ ይዞ ከመሟገት ይልቅ፣ ጀሌ አሠልፎ ማፍረስና ማውደም የዘመኑ ፖለቲከኛ ነን ባዮች መታወቂያ ሆኗል፡፡ ጥራት ያለው ሐሳብ ይዞ ሕዝብ ዘንድ ቀርቦ መዳኘት የዴሞክራሲ ወግ መሆን ከተረሳ ቆይቷል፡፡ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት መሆኑ ተዘንግቶ ወደ ጎን እየተገፋ፣ ማንም ጉልበተኛ እየተነሳ አገር ሲያተራምስና የወጣቶችን ራዕይ ሲያጨልም ዝም ተብሏል፡፡ በአዳራሽ ውስጥ ክርክርና ድርድር ማለቅ ያለበት ጉዳይ በአደባባይ ነውጥ ሲደረግበት፣ ውጤቱ ትርምስና ቀውስ መሆኑን መገንዘብ አልተቻለም፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች እየተጨፈለቁ አገር የሚያፈርሱ ቅስቀሳዎች ሲለፈፉ፣ ከፊት እየመጣ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት መሆኑን መረዳት አዳግቷል፡፡ ተገዳዳሪዎቻቸውን በሐሳብ ተሟግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ የሚረዱ ነውጠኞች የሚቀናቸው፣ የጨዋታ ሕጉን ደርምሰው አገር ማበጣበጥና ሕዝብን ጭንቅ ውስጥ መክተት መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ምንም እንኳን የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት ሕግ ማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቢሆንም፣ በሆደ ሰፊነትም ይባል በትዕግሥት ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ አሁን ግን ከአገር ህልውና የሚቀድም ምንም ነገር ስለሌለ፣ ሕጋዊነት በሕገወጥነት ላይ የበላይ መሆኑ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን ያለነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የተሻለ ሐሳብ ይዞ የሚመጣ እንጂ፣ በሥርዓተ አልበኝነት አገር የሚያተራምሰውን አይደለም፡፡ ሕግ በፍጥነት ሥራውን ማከናወን አለበት፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የኢትዮጵያዊያን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚወዳደሩበት ዓውድ ሲኖር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ በእኩልነት ለማስተናገድ የሚያስችል መደላድል ሲፈጠር ነው፡፡ ለጭቆና፣ ለአድልኦና ለማግለል የሚረዱ ብልሹ አሠራሮች ሲወገዱ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ከማኅበረሰቡ ውስጥ ሲሸኙ፣ የመንግሥትም ሆነ የተለያዩ ተቋማት አሠራሮች ይዘምናሉ፡፡ የጉልበተኝነት መንገድን የሚያቀነቅኑ መሰሪዎችና ሴረኞች ተቀባይነት ስለሚያጡ፣ የተለያዩ ጠቃሚ ሐሳቦች አሉን የሚሉ ወገኖች በነፃነት ይፎካከራሉ፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ከአሻጥር፣ ከጥላቻ፣ ከመናናቅና እርስ በርስ ከመተናነቅ ወጥቶ የተሻለ ሐሳብ ወደ ማመንጨት ይሸጋገራል፡፡ አሁን እንደሚታየው ጎዳና ላይ ወጥቶ መንገድ መዝጋት፣ ተሽከርካሪዎችን መሰባበር፣ ተቃራኒ የሚባሉ ምልክቶችንና ዓርማዎችን ማበላሸትና ሕገወጥ ድርጊቶችን መፈጸም ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ጀርባ ያሉም ለአገር አይጠቅሙም፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትን እያራመዱ ለመብት እታገላለሁ ማለትም ቧልት ነው፡፡ ሕግ መከበር አለበት፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ከኢትዮጵያ ህልውና በላይ የሚቀድም ምንም ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ላይ ከመጣ ማንም ይሁን ማን በሕግ አደብ መግዛት አለበት፡፡ በተለይ የውጭ አገር ፓስፖርት ይዘው አገር እየበጠበጡ የከፋ ነገር ሲመጣ እብስ የሚሉትን፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ መቆጣጠር አስፈላጊ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ኢሕአዴግ ሳይወድ በግድ በሕዝባዊ እንቢተኝነት ተገዶ ለውጥ ከመጣ በኋላ፣ ከእስር ቤት የወጡም ሆኑ ከስደት የተመለሱ በርካቶች በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በታሪክ አጋጣሚ ተደማጭነት አግኝተናል የሚሉ ጥቂቶች ግን ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ወደ ነውጥ ቀይረውታል፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራሳቸውን ስሜት ብቻ እያዳመጡ ከፍተኛ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት በተደጋጋሚ ተወቅሷል፡፡ አሁን ግን ሕገወጥነት ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ከተባለ ዘንድ፣ የተግባራዊነቱ ጉዳይ ከቶም አጠራጣሪ ሊሆን አይገባም፡፡ ማንም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ በተግባር ሊረጋገጥ የግድ ይላልና፡፡

እዚህ ላይ አሁንም ልብ ሊባል የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ትናንት በነፃ አውጪነት ስም የተተከለ ስምና ዝና ለሥርዓተ አልበኝነት ማዋል እንደማይቻል መረጋገጥ አለበት፡፡ መንግሥት ሕግን ሲያስከብር ውስጡን መፈተሽ አለበት፡፡ ለሕገወጦች የተንበረከከ ቢሮክራሲና የፍትሕ አካል ይዞ ሕግ ማስከበር ከቶውንም አይቻለውም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ ሕገወጦች ሥር የሚርመጠመጥ ሹም ሕግ ማስከበር ዳገት ነው የሚሆንበት፡፡ መንግሥት ሕግ የማስከበር ቁርጠኝነት ሊኖረው የሚችለው፣ መንግሥት ሊኖሩት የሚገቡ ባህሪያትን መላበስ ሲችል ብቻ ነው፡፡ በአፋቸው መንግሥት የሚመስሉ ነገር ግን በልባቸው ከሥርዓተ አልበኞች ጋር የመሸጉ ሹማምንት ይዞ አገር መምራትም ከባድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በየቦታው በሥርዓተ አልበኞች ምክንያት ውይይት ማድረግም ሆነ መሰባሰብ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ምርጫ ማካሄድ፣ ወጥቶ መግባትም በጣም ከባድ ነው፡፡ በፀጥታ አስከባሪዎች ፊት መንገድ እየዘጉ አላንቀሳቅስ የሚሉ ነውጠኞች ባሉበት አገር ውስጥ ብዙ የሚከብዱ ነገሮች አሉ፡፡ ሕግ ጡንቻውን ማሳየት መቻል አለበት፡፡

አገር ከሥርዓተ አልበኝነት አታተርፍም፡፡ የሚያተርፉት በሰው ደም መነገድ የለመዱ ብቻ ናቸው፡፡ ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ዜጎችን መግደል፣ ማፈናቀል፣ መዝረፍና ሰብዓዊ ክብራቸውን ማዋረድ ማብቃት የሚችለው፣ መንግሥት በሙሉ አቅሙ ሕግ ማስከበር ሲችል ብቻ ነው፡፡ ሕግ ይከበራል ሲባል ‹‹እንተያያለን›› ዓይነት ፉከራ ውስጥ እየገቡ ያሉ ነውጠኞችን አደብ ማስገዛት ካልተቻለ፣ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ ይጠፋል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሲሆኑ ደግሞ፣ ሥርዓተ አልበኝነት የበላይነቱን ይይዛል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ ኢሕአዴግ ተዋሀደ አልተዋሀደ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በመብት ስም የተደራጁ ኃይሎች ክብርና ዝና አያሳስበውም፡፡ በብሔርተኝነት ስም እየበለፀጉ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ጉዳይ አያስጨንቀውም፡፡ ሕዝብ የሚያሳስበው የአገሩ ውሎና አዳር ብቻ ነው፡፡ አገሩ ሰላም ካልሆነች የልጆቹ ዕጣ ፈንታ ያሳስበዋል፡፡ አገሩ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በፍጥነት ካልገባችለት፣ ተረኛ ጉልበተኞች እንደሚደቁሱት ያውቃል፡፡ አገሩ ለምታ ብልፅግና ካልመጣ ከአስከፊው ድህነት ጋር እልህ አስጨራሹ ትግል እንደሚቀጥል ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ሕዝብ የኢትዮጵያ ኋላቀር ፖለቲካ እንዲለወጥ የሚፈልገው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስት ተብዬዎች ከብሽሽቅ ፖለቲካ ተላቀው ሐሳብ እንዲያመነጩና እንዲፎካከሩ የሚሻው፡፡ የሐሳብ ድርቅ የመታው የፖለቲካ ምኅዳር ጭራሽ የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ከሆነ፣ መጪው ጊዜ ጨለማ እንደሚሆን ለሕዝብ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ሲወገድና የተለያዩ ሐሳቦች መንሸራሸር ሲጀምሩ ሰላም ይሰፍናል፣ ዴሞክራሲ ያብባል፣ ብልፅግና ይመጣል፡፡ ለዚህም ነው ሥርዓተ አልበኝነት አደብ መግዛት ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...