Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን አቋም የሚገልጽ መልዕክት ለፕሬዚዳንት ትራምፕ መላካቸው...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን አቋም የሚገልጽ መልዕክት ለፕሬዚዳንት ትራምፕ መላካቸው ተሰማ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ያሉ ጉዳዮችን ለማስረዳት የመንግሥታቸውን አቋም የሚገልጽ መልዕክት፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መላካቸውን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ለማድረስም በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የሚመራ ቡድን ወደ አሜሪካ መጓዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሚኒስትሩ ጋር አብረው ወደ ሥፍራው የተጓዙትም፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት  ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ መሆናውንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ካለፈው ወር ጀምሮ ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ላይ የኢትዮጵያ ኃላፊዎች የተለመዱ በማለት የሚገልጹትን ቅሬታ በአዲስ መልክ በማንሳት ድርድር ብትጀምርም፣ ድርድሩ ከሁለት ሳምንት በፊት በሱዳን ካርቱም ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም ምክንያት ግብፅ በግድቡ ግንባታ ሦስተኛ ወገን በተለይም አሜሪካ በአደራዳሪነት እንድትገባ ጥሪ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ ይህንን የግብፅ ፍላጎት ኢትዮጵያ ከትብብር ስምምነቱ ያፈነገጠ እንደሆነ በመግለጽ ውድቅ ማድረጓን በይፋ አስታውቃለች፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መንግሥት ዘንድሮ ሊያተኩርባቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት የመንግሥታቸውን አቋም ለማሳወቅ ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ግብፅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እያነሳችው የሚገኘውን ማስፈራሪያ አዘል ቅሬታና ግድቡ የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲያብራሩ ተጠይቀው ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በሚያስከብር፣ ምኞትና ፕሮፖጋንዳን በመለየትና የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች ሳይጎዳ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሱዳንና የግብፅን ሕዝቦች፣ እንዲሁም መንግሥታት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌለው ተናግረዋል። ‹‹ነገር ግን በህዳሴ ግድብ ላይ እየተነሳ ላለው ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ ችግር ፈጣሪዎቹ እኛ ነን፡፡ ባቀድነው ልክ ብንጨርሰው ኖሮ አጀንዳ አይሆንም ነበር፡፡ አሁንም ግንባታው ሲጠናቀቅ ልክ ጊቤ ሦስትን ጨምሮ በሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ላይ ሲነሱ እንደነበሩ ቅራኔዎች የህዳሴ ግድብ ጉዳይም መቆሙ አይቀርም፤›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የምትገነባው የማንንም ጥቅም ለመንካት ሳይሆን፣ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት የምታከናውነው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

በተለይም የግብፅ መንግሥትና ሕዝብ ቢችሉ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት በቀጥታ ቢደግፉ ጥቅሙ ለግብፅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ውጪ ግን በግብፅ በኩል ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል ተብሎ ለሚሰማው ውጊያ መፍትሔ አይሆንም፣ አስፈላጊ ከሆነ ግን ሁሉም ባለው አቅም ሊሰማራ ይችላል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ማንም ኃይል ኢትዮጵያን ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊያስቆማት እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

በቀድሞ መሪዎች የተጀመሩ ምርጥ ምርጥ ፕሮጀክቶችን መንግሥት እንደሚያስቀጥል፣ የህዳሴ ግድብም ምርጥ ፕሮጀክት በመሆኑ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶችን ያርማል እንጂ ግንባታውን እንደማያቋርጥ አስረግጠዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ ላይ በግብፅ በኩል የተነሳው ክርክር የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን የተመለከተ ሲሆን፣ በግብፅ በኩል የቀረበው ፕሮፖዛልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን የሚጋፋና ፍትሐዊ የመጠቀም መብትን የሚነካ እንደሆነ በመግለጽ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በሩሲያ እንደሚገናኙ ሪፖርተር በቅርቡ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ይህንኑ ለምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል፡፡ እሳቸውም ማክሰኞ ዕለት ወደ ሩሲያ ተጉዘዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...