Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕገወጥ መንገድ እየተሰባሰቡ ግጭት የሚፈጥሩ ወጣቶች ሥጋት መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

በሕገወጥ መንገድ እየተሰባሰቡ ግጭት የሚፈጥሩ ወጣቶች ሥጋት መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ በመሰባሰብ በየሠፈሩ፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በሕዝብ ትራንስፖርት መተላለፊያ መንገዶች ላይ ግጭት እየፈጠሩ ያሉ ወጣቶች፣ ሥጋት እንደሆኑ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ በኮዬ ፈጬና በቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 አካባቢ ጥቅምት 9 እና 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰላማዊ ነዋሪዎችና በውይይት ላይ ይገኙ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ ሁከትና ብጥብጥ የፈጠሩ እነዚሁ ወጣቶች፣ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ገብሬ፣ ወ/ሮ ብርቄ ጉተማና  አቶ መስፍን ገብረ ሥላሴ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ እሑድ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ረብሻና ግጭት ተፈጥሯል፡፡

ምክንያቱን ሲገልጹ ጥቅምት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ኮዬ ፈጬ አካባቢ የአማራ ወጣቶች ማኅበር አባላት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ሲያደርጉ፣ ወጣቶቹ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል፡፡ የተለያዩ ስለቶች፣ ዱላና ድንጋይ ይዘው በመጮህ የምክክር መድረኩን አስተባብረዋል ባሉዋቸው ግለሰቦች ላይ ድብደባ በመፈጸም ጉዳት ማድረሳቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡

አንዲት ወጣት የለበሰችውን ዓርማ ያለበት ቲሸርት በማስወለቅ መቅደዳቸውንና እንደ ደበደቧት ነዋሪዎቹ ገልጸው፣ ሕገወጥ ስብስቦቹ የአካባቢውን ሰው በማስፈራራትና ነዋሪዎች ተረጋግተው ኑሮአቸውን እንዳይመሩ ሥጋት እንደሆኑባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ኮዬ ፈጬ አካባቢ የአማራ ወጣቶች ማኅበር አባላት ስብሰባቸውን እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ሆ ብለው ወደ ስብሰባው የሄዱት ወጣቶቹ፣ የአፀፋ ምላሽ ከተሰብሳቢዎቹ በኩል ሊገጥማቸው ሲል የፀጥታ ኃይሎች ደርሰው እንዳስቆሟቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በተወሰኑ ወጣቶች ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ለጊዜው ያንን ያህል የተጋነነ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የፀጥታ ሁኔታ መከታተልና መጠበቅ ያለበት የከተማው ፖሊሲ ቢሆንም፣ ቆሞ ከማየት የዘለለ ምንም ሲያደርግ አለመመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ውስጥ ተከስቶ የነበረው ግጭት በጠብመንጃ ተኩስ መበተን ባይቻል ኖሮ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ይሆን እንደነበር ተናግረው፣ ወደ ሌሎች ቅርብና አጎራባች ወረዳዎች የመዛመት ዕድል ይኖረው እንደነበር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ በተለይ አሁን ካለው የፀጥታ ችግር አንፃር ጥብቅ ክትትል በማድረግ፣ የነዋሪዎችንና የከተማውን ሰላም ማስጠበቅ ቢኖርበትም ችላ ያለው እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ነዋሪዎች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊያደርግበትና ሰላም እንዲሰፍን ተግቶ መሥራት እንዳበለት አሳስበዋል፡፡

የተለያዩ የአገሪቱ መውጫና መግቢያ መንገዶችን መዝጋትና መንገደኞች እንዳይተላለፉ የማገድ ሕገወጥ ባህሪ፣ በመዲና ከተማዋ ደግሞ በሕገወጥ ስብስቦች ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር ከቀጠለ ነገ የት ሊደረስ እንደሚችል መንግሥት ተረድቶ፣ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ያነሱትን ሥጋትና የሕገወጥ ስብስብ ቡድን ስለተባለው ጉዳይ ማብራርያ እንዲሰጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ሪፖርተር ለማነጋገር የሞከረ ቢሆንም፣ ‹‹በአጠቃላይ ስላለው ሁኔታ ማብራርያ እንሰጣለን ጠብቁ፤›› በመባሉ ምላሹን ማካተት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...