Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ከአምስት ዓመታት በፊት በተመሠረተበት ክስ ታሰረ

የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ከአምስት ዓመታት በፊት በተመሠረተበት ክስ ታሰረ

ቀን:

ከአምስት ዓመታት በፊት ከግብር ጋር በተያያዘ ክስ ተመሥርቶበት የነበረውን የዕንቁ መጽሔት አሳታሚ ዓለማየሁ የኅትመትና ማስታወቂያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ወንጀል እንዲፈጸም በመርዳትና በማበረታታት ክስ ተመሥርቶበት የነበረውና በአሁኑ ጊዜ በመታተም ላይ የሚገኘው ግዮን መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ፍቃዱ ማኅተመ ወርቅ፣ ጥፋተኛ ተብሎ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ታሰረ፡፡

አቶ ፍቃዱ ክስ የተመሠረተበት በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ ፍቃዱ ላይ ክስ የመሠረተበት የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 268/94 አንቀጽ 101 ድንጋጌን ተላልፏል በማለት ነው፡፡ አንደኛ ተከሳሽ አድርጎ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰው ዓለማየሁ የኅትመትና ማስታወቂያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ማኅተመ ወርቅ፣ ለአቶ ፍቃዱ ውክልና ሰጥቶ እንደነበር ገልጿል፡፡ አቶ ዓለማየሁ ዕንቁ መጽሔትን ሲያሳትም ከመጽሔት ሽያጭና ከማስታወቂያ ገቢ ማግኘቱን በክሱ የጠቆመው ዓቃቤ ሕግ፣ ለባለሥልጣኑ አሳውቆ መክፈል የነበረበትን የገቢ ግብር አለመክፈሉንም አክሏል፡፡ ትክክለኛ የሽያጭ ገቢ አለማሳወቁን፣ ሽያጩንም መሰወሩንና አሳንሶ ማቅረቡን በማስታወቅ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. የግብር ዘመን ድረስ 629,140 ብር አለመክፈሉን ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም አቶ ፍቃዱ ከአቶ ዓለማየሁ በተሰጠው ውክልና መሠረት ድርጅቱን ሲመራ ከላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን እንዳይከፈል፣ የገቢ ግብር አለመክፈል ወንጀል እንዲፈጸም በመርዳቱና በማበረታታቱ ክሱን እንደመሠረተበት ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር አስፍሯል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያለውን የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ የተከራከረ ሲሆን፣ እንደ ክሱ ተከራክሯል በማለት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡

አቶ ፍቃዱ እንዲከላከል የተሰጠበትን ብይን አለመከላከሉና ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች አለማቅረቡም ታውቋል፡፡ በጽሑፍ የመከላከያ ማስረጃውን ለዓቃቤ ሕግ እንዳቀረበ ቢገልጽም፣ ፍርድ ቤቱ ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የመከላከያ ሰነዱን ውድቅ በማድረግ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ካለው ለሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያቀርብና አቶ ፍቃዱም የዓቃቤ ሕግን ማክበጃ ተመልክቶ የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ ካለው እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ቅጣት ለመወሰን፣ ለጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...