Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዋልያዎቹ አሠልጣኝ የፋይናንስ እጥረት ለዝግጅት እንቅፋት እንደሆነባቸው ገለጹ

የዋልያዎቹ አሠልጣኝ የፋይናንስ እጥረት ለዝግጅት እንቅፋት እንደሆነባቸው ገለጹ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) እ.ኤ.አ. ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያ ከማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድን ጋር ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሜዳው ውጪ ለመጫወት እየተዘጋጀ ቢሆንም፣ ጠንካራና ደካማ ጎኑን ለመፈተሽ የሚረዱ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማካሄድ የአቅም ውስንነት ተጋርጦበታል፡፡ በገንዘብ እጥረት ጨዋታዎች እየታጠፉበት እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

በካሜሩን አስተናጋጅነት ከሚካሄደው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በሩዋንዳ ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራኅቱ እንደሚገልጹት፣ የቡድኑ አባላት በአብዛኛው ወጣቶች በመሆናቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን እንደሚፈለገው መጠን አላካሄዱም፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) የሚያወጣቸውን የወዳጅነት መርሐግብሮች ያማከለ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማካሄድ ሲጠበቅበት ቡድናቸው ግን በአቅም ውስንነት ይህንን ዕድል ማግኘት አልቻለም፡፡

ዋና አሠልጣኝ አብርሃም እንደሚሉት፣ ምንም እንኳ ከቻን ውድድር ውጪ ቢሆንም፣ ካደረገው እንቅስቃሴ አኳያ ውጤቱ ቡድኑን አይገልጸውም፡፡ ቡድኑ ከዚህም የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ከተፈለገና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቅሙ ከሌለው ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ችግሩን አስታውቆ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ቡድናቸው ከመደበኛው ምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በፊት ቢያንስ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ እንደሚኖርበት የገለጹት ዋና አሠልጣኙ፣ ምክንያቱን ሲናገሩም፣ አብዛኞቹ የቡድኑ ተጨዋቾች ወጣቶች በመሆናቸውና አቅማቸውን እንደልብ የሚፈትሹበት የውጭ ውድድር እንደሚፈለገው መጠን ባለማድረጋቸው ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮችን ያዘጋጀው አካል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያወጣቸው የጨዋታ ድልድሎች ቅሬታ እንዳሳደሩባቸው አሠልጣኝ አብርሃም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ፕሮግራሙ እንደገና መታየት ይኖርበታል፤›› ያሉት ዋና አሠልጣኙ፣ የዋልያዎቹ ቡድን ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያ በማከናወን ከማዳጋስካር ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ ግምት ውስጥ ሳይገባ፣ ኅዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በሜዳው ከኮትዲቯር አቻው ጋር በመቐለ አልያም በባህር ዳር ስታዲየም እንዲጫወት መመደቡ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ የጨዋታው ፕሮግራም እንዲስተካከል የጠየቁት አሠልጣኝ አብርሃም፣ የካፍ ውሳኔ እስካሁን ይፋ ባይደረግም ውይይት እየተደረገበት ስለመሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የወዳጅነት ጨዋታ ለቡድናቸው ውጤት ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመግለጽ፣ ይህ ባለመመቻቸቱና ቡድናቸውም ዕድሉን ባለማግኘቱ ቅሬታ እንዳደረባቸው ከንግግራቸው መረዳት ተችሏል፡፡

ቡድናቸው ውጤት እንደራቀው ለሚተቿቸው አካላት፣ የሩዋንዳውን ጨዋታ ጨምሮ ቡድናቸው እየተሻሻለ መምጣቱን፣ እሳቸው ከሚናገሩት በላይ በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ የተጻፉና የሚወጡ መረጃዎችን መመልከቱ በቂ ማሳያ እንደሆነ በመግለጽ ሞግተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ዕውቅና የተቸረው የወዳጅነት ጨዋታ ከማካሄድ ለረጅም ጊዜ ተቆራርጦ ቢቆይም፣ እሳቸው ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ማሳካታቸውን፣ ይህም የዕቅዳቸው አካል እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...