Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ትራኮማን ለማጥፋት ረዥም መንገድ የሚቀራት ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› አቶ ዳዊት ሥዩም፣ የኦርቢስ...

‹‹ትራኮማን ለማጥፋት ረዥም መንገድ የሚቀራት ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› አቶ ዳዊት ሥዩም፣ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር

ቀን:

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የዓይን ጤና ችግሮች በርካታ ቢሆኑም፣ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ደግሞ ውስን ናቸው፡፡ ለዓይነ ስውርነት የሚዳርገውን የትራኮማ በሽታ ለማከም የሚያስችል ማዕከላት እንኳን የሌሉባቸው ክልሎች አሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሐኪሞችን ለማፍራት የሚፈጀው ጊዜ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በተቋቋሙት ማዕከላትም በአብዛኛው የዓይን ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በመካከለኛ ደረጃ ባሉ ባለሙያዎች እንጂ፣ በከፍተኛ ሐኪሞች አይደለም፡፡ ይህንን ችግር ከግንዛቤ በማስገባት በዓይን ጤና ላይ ትኩረት ባደረገው ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካይነት በገጠር የተቋቋሙት የሕክምና ማዕከላት ከሞላ ጎደል ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በጉራጌ ዞን እያካሄደ ያለው የዓይን ሕክምናና ክብካቤ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ከነዚህም በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በጉብርዬ ክፍለ ከተማ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መዛባት ወይም መቀነስ ችግር ላለባቸው ተማሪ ሕፃናት የሚሰጠው አገልግሎት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡

የዚህ ፕሮግራም ተቋዳሽ የሆኑ 30 ሕፃናት በአባ ፍራንሲስ ማርቆስ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚገኘው ቤተ መጻሕፍት ታድመዋል፡፡ ሁሉም በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መዛባት ወይም መቀነስ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህም ሕፃናት መካከል ከፊሉ የዕይታ ፍተሻ እና ምርምራ ተደርጎላቸው መነጽር ያደረጉ ሲሆን፣ እኩሉ ደግሞ አገልግሎቱን ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡

ከሁለት ወረዳዎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ችግሩ ያለባቸው ሕፃናት ተመርጠው እንደ ማዕከል ወደሚያገለግለው ቤተ መጻሕፍት የመጡት በዘርፉ አጫጭር ሥልጠና በወሰዱ መምህራን አማካይነት የማጣራት ሥራ ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡

ከዓይን ችግራቸው አንጻር ተስማሚ መነጽር ላልተገኘላቸው ሕፃናት ደግሞ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ በተቋቋመው የሁለተኛ ደረጃ የዓይን ክሊኒክ ሪፈር እንደሚደረግላቸው ክሊንኩም በስሩ ከሚገኘው የዓይን መነጽር ማምረቻ ክፍል የሚስማማቸውን መነጽር እንዲያገኙ በማድረግ እየሠራ መሆኑ የጤና ጣቢያው  ኦፕቶሜትሪስት አበባው በዛብህ አስረድተዋል፡፡

የዕይታ መዛባት/መቀነስ ችግር ያለባቸው ሕፃናት በዓመት ሁለት ጊዜ የሕክምና አገልግሎት በነፃ እንደሚያገኙ፣ የዕይታ መዛባት ወይም መቀነስ በዋናነት ወይም 80 ከመቶ ያህሉ መንስኤ ከቤተሰብ የሚወረስ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው መንስኤ አካባቢያዊ አቀማመጥ ሲሆን፣ አንድን ነገር ከቅርበት መሥራት ወይም ማንበብና መጻፍ ሦስተኛው መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት 12 ዓመት የሞላው ልጅ በቅርበት መጻፍና ማንበብ ካዘወተረ የበሽታው ተጠቂ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከአደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

መነጽር ከተሰጣቸውም መካከል አንድ የ15 ዓመት ታዳጊ፣ ጥቁር ሰሌዳ ላይ በቾክ የተጻፈውን እያነበበ ለመገልበጥ መቸገሩን፣ ጓደኞቹንም አስገልብጡኝ ማለቱ እንደሰለቸውና ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ‹‹ደደብ›› የሚል ቅጽል ስም እንዳተረፈለት ተናግሯል፡፡ ሕክምና ካገኘ በኋላ ያለምንም ችግር ማንበብና መጻፍ እንደቻለ አስረድቷል፡፡

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና ባለሙያና የክሊኒኩ ኃላፊ አቶ ደረጀ ኃይሉ ክሊኒኩ የዓይን ሞራ ግርዶሽና የትራኮማ ቀዶ ሕክምና፣ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ መዛባት ወይም ችግር ላለባቸው ወገኖች የመነጽርና የመድኃኒት አቅርቦት አቅምን ባገናዘበ ክፍያ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአቅሙ በላይ ለሆነው ችግር ደግሞ አዲስ አበባና ጅማ ከተሞች ለሚገኙ ተርሸሪ የዓይን ሕክምና ተቋማት ሪፈር እንደሚያደርግ ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጉራጌ ዞን ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ፍቅሩ ደሴ ቆትዬ እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፉ ድርጀት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማን ጨምሮ ከሚንቀሳቀስባቸው ስምንት ወረዳዎች መካከል እዣ፣ እንዳገኝና ሞርአክሊል ወረዳዎች ከትራኮማ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሲሆኑ፣ የዓይን ሽፋን ሽፍት ወደ ውስጥ የመቀልበሱ ችግርን የማጥፋቱ ሥራ ደግሞ በመገባደድ ላይ ነው፡፡

የተገኘው ውጤት እንዳይቀለበስ በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች እጅን በሳሙናና በውኃ የመታጠብ በመፀዳጃ ቤት በመጠቀም የግልና የአካባቢ ንጽሕና የመጠበቅ ልምዳቸውን፣ እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ከትምህርት በኋላ ወደየቤታቸው ሲመለሱ ወላጆቻቸውን እንዲያስተምሩ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊመጥን የሚችል ጠንካራ የዓይን ሕክምና ሆስፒታል፣ የዓይን ጤና ተቋማትና በቂ የዓይን ጤና ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል ያሉት የኦርቢስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሥዩም፣ ኢትዮጵያ ትራኮማን ካላጠፋች በስተቀር ዓለም ትራኮማን ሊያጠፋ አይችልም ብለዋል፡፡

ብዙ አገሮች ፈጣን የሆነ የትራኮማ ቅነሳ እንዳደረጉ ያወሱት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ትራኮማን ለማጥፋት ረዥም መንገድ የሚቀራት ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ፈጣን ለውጦች እንደታዩ፣ በእነዚህም ለውጦች በርካታ ወረዳዎች ከትራኮማ ነፃ ለመሆን እንደተቃረቡም ተናግረዋል፡፡

የዓይን ቀዶ ሕክምና እየተባለ ይጠራ እንጂ ሥራው ግን ቀለል ያለ ቀዶ ሕክምና መሆኑን ገልጸው፣ በአንድና በሁለት ወራት ሥልጠና ነርሶች ሊሠሩት የሚችሉት ሙያ እንደሆነ፣ በፕሮግራሙም ነርሶች እየሠለጠኑና ሕክምናውን እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሠለጠኑት ባለሙያዋችም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው የመጀመርያ ደረጃ የዓይን ሕክምና መስጫ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ አስረድተዋል፡፡

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የሰብ ስፔሻሊቲ የዓይን ሕክምና አይሰጥም ነበር፡፡ ለግላኮማ ወደ ኬንያ ወይም ህንድ መሄድ ግድ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ ድርጅት ከገባ በኋላ ግን ሰብ ስፔሻሊቲ ሐኪሞችን ማፍራት እንደተቻለ፣ በጣም ውድና ለዓይን ሕክምና ጠቃሚ የሆኑ መሣሪያዎችን በየዩኒቨርሲቲዎች ሆስፒታሎች እንዲገኙ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ አንድ የዓይን ቀዶ ሕክምና ለማከናወን በማይክሮስኮፕ መታገዝ ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን አንድ ማይክሮስኮፕ አንድ ወይም ሁለት ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪ የመግዛት ያህል ውድ ነው፡፡

ኦርቢስ በትኩረት ከሚተገብራቸው እንቅስቃሴዎች መካከል በአውሮፕላን የተለየ ሥልጠናና ሕክምና መስጠት ይገኝበታል፡፡ በየአምስት ዓመት የሚመጣው አውሮፕላን የሚያሠለጥነውም የዓይን ሕክምና ባለሙያዎችን መሆኑን፣ በዓለም ላይ ካሉት ታዋቂ ኦፕቶሞሎጂስቶች መካከል አብዛኞቹ ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ጋር አብረው የሚሠሩ ወይም የሠሩ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...