Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የ2030 ግብን ለመምታት እጥፍ ሥራ የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ

የሴቶችና ሕፃናት ጤናና የሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት ወቅታዊ ሁኔታን የሚተነትነው ብሔራዊ ጥናት፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ አበረታች ለውጥ ማስመዝገቧን ይፋ አድርጓል፡፡ መልካም ውጤት አስመዝግባለች የተባለው በጤና፣ በሥርግተ ምግብ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ዘርፎች ነው፡፡ በየጊዜው የሚመዘገበው ለውጥ መልካም ነው ቢባልም፣ የሚሄድበት ፍጥነት ግን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግቡን መምታት አያስችለውም ተብሏል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ሪፖርቱ፣ አገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በጤና፣ በሥርዓተ ምግብ፣ በትምህርትና በሕፃናት ጥበቃ መስክ ያስመዘገበቻቸውን ለውጦች በዝርዝር ይዟል፡፡ ሻሂዳ ሁሴን እንደሚከተለው አጠናቅሯዋለች፡፡

የሕፃናት ጤና፡-

 ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሕፃናት በብዛት የሚሞቱበት አገር ነበረች፡፡ ወላጆች አንዱ ቢሞት አንዱ ያድጋል እያሉ ደጋግመው እንዲወልዱ ምክንያት እስኪሆን ድረስ ሕፃናት እንደዋዛ ይሞቱ ነበር፡፡ ይህንን አሳዛኝ እውነታ ለመቀየር መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ሲያስተገብር ቆይቷል፡፡ በዚህም ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ባለፉት ሁለት አሠርታት ውስጥ በሁለት ሦስተኛ ቀንሷል፡፡ አሁንም ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዓመቱ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በየዓመቱ 96,000 ሕፃናት ይሞታሉ፡፡ 872 ሺሕ ሕፃናት ከተለያዩ በሽታዎች የሚጠበቁባቸውን ክትባቶችም አያገኙም፡፡

ሥርዓተ ምግብ

ቅንጨራ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው የአመዛኙ ኢትዮጵያዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ አገራዊ ችግር ነበር፡፡ ችግሩ በምን ያህል ጥልቀትና ሥፋት እንደተንሰራፋ በጥናት ተለይቶ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ባለድርሻ አካላት እየተረባረቡበት ይገኛሉ፡፡ በተሠሩ ሥራዎችም ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ ይታዩ የነበሩ የሥርዓተ ምግብ መዛባት የሚያመጣቸው የጤና ችግሮች እንዲሁም ቅንጨራ እ.ኤ.አ. በ2,000 ከነበረበት 58 በመቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 37 በመቶ ወርዷል፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት የሚባል ቢሆንም፣ 5.4 ሚሊዮን ሕፃናት ለዕድሜያቸው የሚመጥን ቁመት የላቸውም፡፡ ዘላቂ የልማት ግቡን ለማሳካት የሚመዘገበው ውጤት በእጥፍ ሊጨምር ይገባል፡፡

ያለ ዕድሜ ጋብቻ

ዘለው ያልጠገቡ ሕፃናትና ሳይጎረምሱ ለትዳር የሚታጩበት ልማድ ብዙዎች በአጭሩ እንዲቀጩ ምክንያት ነው፡፡ በልጅነታቸው ወደ ትዳር ሲገቡ ትምህርታቸውን አቋርጠው ነው፡፡ ይህም ሴቶች በባሎቻቸው ላይ የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ገና በልጅነታቸው ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት እንዲወድቅባቸው ሲያደርግ ኖሯል፡፡ እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣው የጤና መዘዝም የበርካቶች ፈተና ነው፡፡ ይህንን ክፉ ባህል ለማጥፋት በተሠሩ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 በኢትዮጵያ 60 በመቶ የነበረው ያለዕድሜ ጋብቻ እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 40 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም መልካም ውጤት በሚል የተያዘ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ግን አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡ 15 ሚሊዮን ታዳጊ ሙሽሮች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት ከ15 ዓመታቸው በፊት ወደ ትዳር የገቡ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2030 ያለዕድሜ ጋብቻን ጨርሶ ለማስቆም የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም የተመዘገበው ውጤት በስድስት እጥፍ መጨመር ይኖርበታል፡፡

ትምህርት

የትምህርት ተደራሽነት ጉዳይ ለዘመናት አንገብጋቢ አገራዊ አጀንዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ተደራሽነቱ ከነበረው በብዙ እጥፍ እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል፡፡ ወደ አንደኛ ክፍል የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥርም በጥቅሉ አድጓል፡፡ ይሁንና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት የሚያጠናቅቁት ከአሥር ተማሪዎች ስድስቱ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉት የተወሰኑት እንደሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ልጆች በድህነት፣ በጋብቻ፣ በሰብዓዊ አደጋዎች፣ በትምህርት ጥራት ችግር፣ በግብዓቶች እጥረትና በመሳሰሉት ትምህርታቸውን ያቋርጥሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሰባት እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 2.6 ሚሊዮን ታዳጊዎች ትምህርት ቤት አልገቡም፡፡ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡

ንፁህ ውኃና ፅዳት

የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር መጠኑ ቢለያይም በገጠርም ሆነ በከተማ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ የንፁህ ውኃ ተደራሽነት ችግር ባለባቸው በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች ውኃ ለመቅዳት ሰዓታት በእግራቸው ይጓዛሉ፡፡ ከአሰልቺ ወረፋ በኋላ የጉድጓድ ውኃ በጀሪካን ቀድተው በጀርባቸው ተሸክመው አድካሚ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ውኃ ተዳርሷል በሚባልባቸው በከተሞችም የአቅርቦት ችግር አሳሳቢ ነው፡፡ በየጊዜው ከመጥፋቱ ባሻገር ንፁህ መሆኑም አጠራጣሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ፡፡

ነገር ግን በሒደት እየተስተካከለ፣ መስመር እየያዘ መሄዱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በአገሪቱ የንፁህ ውኃ አቅርቦ ያልነበራቸው ሰዎች ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2000፣ 75 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 31 በመቶ ዝቅ ማለቱን አሳይቷል፡፡ በፅዳት በኩልም እንዲሁ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000፣ 79 በመቶ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ፅዳት የተለየው ኑሮ ይገፉ ነበረ፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 22 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት 31 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የንፁሕ ውኃ አቅርቦት ቢኖራቸውም፣ 23 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ሜዳ ላይ የሚፀዳዱና አስከፊ የፅዳት ችግር ባለበት ሁኔታ የሚኖሩ ናቸው፡፡

በድህነት የሚኖሩ ሕፃናት

መዋለድን እንደ ፀጋ በሚቆጥር ማኅበረሰብ ውስጥ ወላጆች ደጋግመው ሲወልዱ ስለገቢያቸው ብዙም የሚጨነቁ አይመስልም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች አሥር ልጆች ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ በዚህም መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ወላጆች ይቸገራሉ፣ ሕፃናት ይራባሉ፣ የሚለብሱት ጥብቆ ሌላም ሌላም እስኪያጡ ችግሩ ይበረታል፡፡ ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ፣ ጥበቃ፣ መኖሪያ፣ ውኃ፣ ፅዳት ሁሉ ለሕፃናቱ ብርቅ ይሆናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 43 ሚሊዮን ልጆች መሠረታዊ ፍላጎታቸው በአግባቡ ሳይሟላ ይኖራሉ፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሠለፍና እ.ኤ.አ. በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሥራት አለባት፡፡ በዩኒሴፍ ትብብር የተሠራው ጥናትም፤ ግቡን ለመምታት ጫና በፈጠሩት የጨቅላ ሕፃናትን ሞት በመቀነስ፣ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን በማስፋፋት፣ ሜዳ ላይ መፀዳዳትን በማስቀረት፣ በማኅበራዊ ዋስትና፣ በትምህርት ጥራትና በመሳሰሉት ረገድ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...