Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድር ልታስተናግድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

አሸናፊ ቡናዎች ለዓለም ገበያ በቀጥታ በሚካሄድ የኢንተርኔት ገበያ ይሸጣሉ

ከዓለም አገሮች በቡና አምራችነቷ በአምስተኛ ደረጃ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት መሰናዳቷን አስታወቀች፡፡ የቡና ጥራት የሚፈተሽበት ይህ ዓለም አቀፍ ውድድር ከጥር ወር ጀምሮ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

ምንም እንኳ የዓለምን የቡና ፍላጎት ከሰባት እስከ አሥር በመቶ በማሟላት ለገበያ ብታቀርብም፣ የሚገባትን ያህል ከቡና ንግድ ተጠቃሚ መሆን ያልቻለችው ኢትዮጵያ፣ ተጠቃሚነቷን ለማሻሻል በዚህ ዓመት ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድርን ማካሄድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ከዩኤስኤይዲ) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ይህንኑ ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡

ውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ መካሄዱ የአገር ገጽታን ለመገንባት፣ እስካሁን ያልተለዩና ለዓለም ገበያ ያልቀረቡ የቡና ዝርያዎች ጎልተው እንዲወጡ ለማስቻል፣ አርሶ አደሮች ከምርታቸው እንዲጠቀሙና የልዩ ጣዕም ቡናዎችን ለዓለም ገበያ በስፋት ከማስተዋወቅ አንፃር እንዲሁም የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከማሳደግ አኳያ ውድድሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ በውድድሩ ላይ በማንኛውም ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡና አምራቾች፣ ላኪዎች፣ አቀነባባሪዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች፣ አነስተኛና ትላልቅ የግልና የሕዝብ ድርጅቶች መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ‹‹ለውድድር የሚቀርቡ ናሙናዎች ዱካቸው የሚታወቅና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ተሳታፊዎች ከጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የቡና ናሙናዎችን ለውድድር ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከየካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለውድድር የገቡት ቡናዎች የቅድመ መረጣ ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ቡናዎችን ወደ መጋዘን የማስገባት ሥራ ከየካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን ሲገለጽ፣ ዋናው የውድድር ሥነ ሥርዓት ከመጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ይካሄዳል፡፡ አገር አቀፉን ውድድር ያሸነፉ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክም ከመጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ሲገለጽ፣ ለቡና ገዥዎችም ዓለም አቀፍ ጨረታ በግንቦት ወር እንደሚወጣ ታውቋል፡፡

አዱኛ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በውድድሩ የሚሳተፉት የአገር ውስጥ ቡናዎች ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ለውድድሩ ከሌላ አገር የሚመጣ ቡና የለም፡፡ ለውድድር የሚቀርቡት አገር ውስጥ ያሉ ቡናዎች ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ገዥዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በዚህም መሠረት ገዥዎች ውድድሩን በሚያካሂዱ አገሮች እየዞሩ ይገዛሉ፤›› ብለዋል፡፡

ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው የቡና ጥራት ውድድር በኢትዮጵያ ሲካሄድ የመጀመርያው በመሆኑና ኢትዮጵያም የቡና መገኛ እንደመሆኗ ቡናን ከቤቱ የሚገናኙበት ዓለም አቀፍ ታሪካዊ መድረክ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዋና ዋና ከሚባሉ ቡና አምራቾች አንዷ እንደመሆኗ፣ ይህንን ውድድር ከማዘጋጀት ለምን ዘገየች ተብለው ከሪፖርተር ለተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹በጣም ዘግይተናል፡፡ ስላልታሰበበት ነው፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ይህንን ውድድር እናካሂዳለን፡፡ የተሻለ ሥራ ሠርተን ከተገኘንም በዚያው እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡

ከ40 በላይ በዓለም ትልልቅ የሚባሉ ድርጅቶች ከወዲሁ ለውድድር ቀርበው ዕውቅና የሚያገኙ ቡናዎችን ለመግዛት ጥያቄዎች እንዳቀረቡ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› በአዘጋጁ አገር የተመረቱ በጥራታቸው የላቁ ቡናዎችን ለመምረጥና ለመሸለም የሚካሄድ የላቀ የቡና ጥራት ውድድር ነው፡፡ ተወዳዳሪዎች የወድድሩን ደንብና መመርያ በማክበር መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአርሶ አደሩ በየዞኑ በመሄድ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ያስታወቁት አዱኛ (ዶ/ር)፣ በጅማ፣ በሐዋሳና በድሬዳዋ የቡና ናሙናዎች መቀበያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች ርቀው የሚገኙ ቡናዎች በአዲስ አበባ የመቀበያ ማዕከል እንደተዘጋጀላቸው አክለዋል፡፡

የውድድሩ ነጥብ አሰጣጥ ሒደቶችን በተመለከተ እንደተገለጸው፣ ተወዳዳሪ ቡናዎች ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ የቅምሻ ውጤታቸው 86 እና ከዚያ በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከ86 በታች ያገኙ ቡናዎች ከውድድሩ ውጪ እንደሚደረጉ ተገልጿል፡፡

የውድድሩ ደረጃዎችን በተመለከተ ሲብራራ፣ የቅድመ መረጣ ዙር የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፡፡ የመጀመርያውን ዙር ያለፉ 150 ከፍተኛ ውጤት ያላቸውና 86 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ ቡናዎች ከቅድመ መረጣ ወደ አገር አቀፉ ውድድር ያልፋሉ፡፡

በዚህ ዙር ከመጀመርያዎቹ 150 ከፍተኛ ውጤት ካገኙ ማለትም 86 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ካላቸው ምርጥ ቡናዎች መካከል 90ዎቹ ወደ ሁለተኛው ዙር አገራዊ ውድድር ያልፋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 40 ቡናዎች ወደ ዓለም አቀፉ የቡና ውድድር መድረክ ያልፋሉ፡፡ በዓለም አቀፉ የቡና ውድድር መድረክ 86 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ያላቸው ሁሉም ቡናዎች ወደ ሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የቡና ውድድር መድረክ ያልፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ 87 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ያላቸው ምርጥ 30 ቡናዎች የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊዎች በመሆን በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. በሚካሄደው የቀጥታ የኢንተርኔት ጨረታ የግዥ ሒደት ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ይሁን እንጂ ፈቃደኛ ከሆኑ በዓለም አቀፉ የመጀመርያና ሁለተኛ ዙር የቡና ውድድር መድረክ ከ85 እስከ 87 ነጥብ ያገኙ ሁሉም ቡናዎች ጨረታው ላይ መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ሁሉ የላቀውና የመጨረሻው ዙር ዓለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድር የሚካሄድበት ሥነ ሥርዓት ላይ እስከ አሥረኛ ደረጃ ያገኙ ተወዳዳሪዎች የመጨረሻው የቡና ቅምሻ በሚካሄድበት ጊዜ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ዓለም አቀፍ ጨረታን ሒደት በቀጥታ የሚካሄድ የኢንተርኔት ጨረታ መድረክ ተከፍቶ ለአንድ ቀን እንዲቆይ ይደረግና በጨረታው ሁሉም የቡና መደቦች ቢያንስ አንድ ተጫራች ሲያገኙ ግዥው እንደሚጀመር ተብራርቷል፡፡ ጨረታው እንዳበቃ የሚቆጠረው አንድም ገዥ ለሦስት ደቂቃ አዲስ ዋጋ ሳያቀርብ ከቆየ ነው፡፡

የጨረታው መክፈቻ ዋጋን በተመለከተ እንደተገለጸው ለአንድ ፓውንድ (0.45 ኪሎ ግራም) ቡና የመሸጫ መነሻ ዋጋው 5.50 ዶላር ይሆናል፡፡ ከ85 እስከ 85.99 ነጥብ ያገኙ ቡናዎች የመነሻ ዋጋቸው በፓውንድ 3.5 ዶላር ሲሆን፣ 86 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ያገኙ ቡናዎች መነሻ ዋጋቸው በፓውንድ አራት ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የዚህ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ በቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሚመራ ሲሆን፣ ኮሚቴው አሥር አባላት አሉት፡፡ እያንዳንዱ ውድድርም አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ በተሰኘ ተቋም በሚመደብ ዋና ዳኛ መመርያና ክትትል ሥነ ሥርዓቱ ይከናወናል፡፡ 

ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በአዘጋጁ አገር በጥራታቸው የላቁ አሸናፊ ቡናዎችን በውድ ዋጋ በግልጽ ጨረታ ለመሸጥ የሚያስችል የጥራት ውድድር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1999 በብራዚል የተጀመረ ነው፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ 11 ቡና አምራች አገሮች ውድድሩን አካሂደዋል፡፡ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ፔሩ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ኮስታሪካ፣ ኒካራጓ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ሜክሲኮ፣ ቡሩንዲና ሩዋንዳ የውድድሩ አስተናጋጆች ነበሩ፡፡

ውድድሩን የሚመራው በአሜሪካ የሚገኘው አልያንስ ፎር ኮፊ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን፣ በጥራታቸው የላቁና የልዩ ጣዕም ቡናዎችን ለመምረጥ የሚያስችል አሠራር ለመፍጠር እንዳስቻለ ይነገርለታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች