Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላኪዎች የሽያጭ ውላቸው በመንግሥት ካልፀደቀ በቀር መላክ አይችሉም ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁሉም ላኪዎች ከጥቅምት 17 ጀምሮ በኮንትራት አስተዳደር ሥርዓት ይስተናገዳሉ

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ሲያዛባ ነበር ያለውን የውል ማፍረስ የሚቆጣጠር የውል አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱን አስታወቀ፡፡ የመመርያው ዋና ዓላማ ዶላር ለማግኘት ሲሉ የወጪ ንግዱን የሚቀላቀሉ ላኪዎች በአገር ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ይህንኑ ለመቆጣጠር እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምሥጋኑ አረጋ (አምባሳደር)፣ ሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ላኪዎች በራሳቸው መንገድ የሚንቀሳቀሱ፣ የገቡትን ውል በሚጥሱበት ወቅትም መቆጣጠሪያ ሥልት ያልነበረበት በመሆኑ፣ የውል ጥሰትና የውል ማፍረስ ተግባር በተደጋጋሚ በላኪዎች በኩል እየተከሰተ በርካታ አቤቱታዎች ከውጭ ምርት ገዥዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን ተቀባይነት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር መፈጠሩን አውስተው፣ ለዚህ መነሻው የንግድ ሥርዓቱ በተለይም የወጪ ንግዱ የሚመራበት ሥርዓትና ላኪዎች ስለሚልኩት ምርት መጠንና ዋጋ ቁጥጥር የሚያደርግ አካል ባለመኖሩ ነበር፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚስተናገዱ ምርቶች የገዥና ሻጭ ውለታ ሰነዶች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈቃድ ተሰጧቸውና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፀድቀው ካልተረጋገጡ በቀር፣ ወደ ውጭ ምርት መላክ እንደማይቻል አቶ ምሥጋኑ (አምባሳደር) አረጋግጠዋል፡፡ ቡና ላኪዎችን በተመለከተም፣ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱን በውክልና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንዲያከናውን ኃላፊነት መውሰዱንም ገልጸዋል፡፡ 

መንግሥት የውል አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት የወጪ ንግዱን ለመቆጣጠር የተገደደበትን ምክንያት ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ጊዜያዊ ላኪዎች›› የፈጠሩትን ችግር ለመቅረፍ ብሎም ትክክለኛ ነባር ላኪዎች ከንግድ ሥራቸው እየከሰሩ እንዲወጡ የተገደደቡትን የንግድ አሠራር በማስተካከል በውድድር ሥርዓት ላይ የሚመራ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር በማስፈለጉ፣ ትክክለኛ ላኪዎችም ይህንኑ ሲጠይቁ በመቆየታቸው እንደሆነ አቶ ምሥጋኑ (አምባሳደር) አብራርተዋል፡፡

ዶላር አሳዳጆቹ ጊዜያዊ ላኪዎች ከአገር ውስጥ በተለይም ከምርት ገበያው በውድ ዋጋ እየገዙ ገበያውን ሲረብሹ ከመቆየታቸውም ባሻገር፣ ለውጭ ገዥዎች የሚሸጡትም በኪሣራ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታውም ይህንኑ ገልጸዋል፡፡ ዶላር አሳሾቹ ላኪዎች በአብዛኛው በአስመጪነት ንግድ መስክ የሚሳተፉ፣ ዶላሩን ለሚያስመጡት ሸቀጥ ሲሉ በኪሣራ ሸጠው፣ በምትኩ በሚያስመጡት ሸቀጥ ላይ ኪሣራቸውን እያቻቻሉ የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሱ መሆናቸው ተኮንኗል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ነጋዴዎች ከደህነኞቹ የሚለይ መመርያ ተዘጋጅቶ ከጥቅምጥ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባር ላይ እንደሚውል ይፋ ተደርጓል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ፍለጋ የወጪ ንግድ ዘርፉን በሚቀላቀሉ ነጋዴዎች የደረሰው ኪሣራ በዋጋ ንረትና በአገረቱ ገጽታ ላይ ብቻም ሳይወሰን፣ በገቢ ማጭበርበር ጭምር መንግሥት ሲታለል መቆየቱም ተወስቷል፡፡ ይህንን ሲያስረዱ፣ አብዛኞቹ ላኪዎች ‹‹በውድ ዋጋ ገዝተን የላክነው ምርት፣ በኪሣራ ተሸጠ›› በማለት፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር ሐሰተኛ የኪሣራ ሒሳብ ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደቆዩ አቶ ምሥጋኑ ገልጸዋል፡፡ የንግድ ማጭበርብሩ በዚህ ብቻ እንዳልተወሰነ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ተገቢው የወጪ ንግድ ቄራ ሳይኖራቸውና ለሥጋ ማቀነባበሪያ የተቀመጡ የጤናና ሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ፣ ሥጋ ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች መገኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ‹‹ዶላር ለማግኘት ዘው ብለው ወደ ላኪነት የገቡ ነጋዴዎች እየተጠኑ ነው፤›› ያሉት አቶ ምሥጋኑ (አምባሳደር)፣ በዋቢነት ከጠቀሷቸው መካከል በዓመት እስከ 300 ሺሕ ቶን ሰሊጥ ወደ ውጭ በሚላክበት አግባብ ከ1300 በላይ ላኪዎች ፈቃድ መውሰዳቸው ምርቱን ለመላክ ካላቸው ነተሳሽነት አለያም ሌላ ዓላማ ኖሯቸው ዘርፉን የተቀላቀሉ ስለመሆናቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ 

ይህንን ያስተካክላል የተባለው የኮንትራት አስተዳደር መመርያ፣ ከረቂቅ ዝግጅቱ እስከ መጨረሻው ደረጃ የሰነድ ዝግጅት ድረስ ሁሉም ላኪዎች ተወያይተውበት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ ባንክ፣ የምርት ገበያ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንና የሚመለከታቸው ተሳትፈውበት ለትግበራ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

መመርያው ፀረ ውድድር ተግባራትን ከመቆጣጠር ባሻገር፣ ተገቢውና ሕጋዊው ላኪ በተገቢው ሥርዓት እንዲስተናገድ ዕድል እንደሚሰጥ ያስታወቁት አቶ ምሥጋኑ (አምባሳደር)፣ ይህንን ተላልፈው በሚንቀሳቀሱ ላኪዎች ላይ እስከ ፈቃድ ስረዛ የሚያደርስ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡

የገቡትን ውል ሳይፈጽሙ ቅድመ ክፍያ ተቀብለው የጠፉ በርካቶች በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንደሚገኙና አንዳንዶቹም ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በተለይም ከገዙበት ዋጋ በታች አሳንሰው በመሸጣቸው በብሔራዊ ባንክ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ከ260 በላይ ነጋዴዎች እንደነበሩ በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከዋጋ በታች በመሸጥና የሽያጭ ስምምነትን ሲጥሱ በተደጋጋሚ የተገኙ ባላቸው ቡና ላኪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥሪም ማስጠንቀቂያም ቢሰጥም ሊቀርቡ አልቻሉም ያላቸውን 81 ነጋዴዎች ላልተወሰነ ጊዜ ከማገዱም ባሻገር፣ ከእነዚህ ውስጥ 26 ቡና ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ጋር በመሆን ከሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ባካሔደው ውይይት ወቅት፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ይፋ እንዳደረጉት እስካሁን ከ266 ያላነሱ ቡና ላኪዎች ለመሸጥ የገቡትን ኮንትራት ሲጥሱና ከዋጋ በታሽ ሲሸጡ በመገኘታቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የመጀመርያ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ባለሥልጣኑ በማስታወቂያ ጥሪ አቅርቦላቸዋል፡፡

መንግሥት ይህንን መመርያ እንደሚያወጣና እንደሚተገብር በተጋጋሚ ማስታወቁንና ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎም ከወዲሁ በምርት ገበያው የምርት ዋጋ እንቅስቃሴ ላይ መረጋጋት እየታየ መምጣቱን፣ የወጪ ንግዱም ዓምና በመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ካስመዘገበው ውጤት በ95 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ የመመርያውን አስፈላጊነት እንዳመላከተ አቶ ምሥጋኑ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ ከ790 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች