Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበአክሱም ጫፍ አቁማዳ የታጀበው የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት

በአክሱም ጫፍ አቁማዳ የታጀበው የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት

ቀን:

በጋዜጣው ሪፖርተር

“እኔና ወንድሞቼ” አለ በለዘብታ፣
      ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፣

‹‹እኔና ወንድሞቼ ሁላችን…ሁላችን
      ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን

ይህ ነው አንድነታችን
      ይህ ነው ባህላችን
      ዘመን ማዛጋቱ በየአንደበታችን፡፡››

ይህ የሥነ ግጥም አንድ አንጓ የተገኘው፣ በሙዚቃዊ ቴአትር የተስተጋባው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ሦስተኛው የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲካሄድ ነበር፡፡ ከ45 ዓመታት በፊት ጠሊቁ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ “የአክሱም ጫፍ አቁማዳ” በሚል ርዕስ በዚያን ዘመኑ የኢትዮጵያ ገጽታ ከጠቅላይ ግዛትነት ወደ ክፍላተ ሀገር በተደረገው ሽግግር አጋጣሚ የጻፈው ግጥም፣ ከትግራይ ተነሥቶ በወሎ አድርጎ በስምንቱ አቅጣጫዎች (ሰሜንና ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ፣ መስዕና አዜብ፣ ባሕርና ሊባ) የሚገኙትን ጠቅላይ ግዛቶች እስከ ኤርትራ ድረስ እየጠራና እየተረከ አቁማዳዋ እህል ፍለጋን እየተሸከረከረች መጨረሻ ላይ ባዶዋን ከተነሳችበት አክሱም ትደርሳለች፡፡

ወገኖቹ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች እህል እንደቸገራቸው የተረዳው ትግራይም አቁማዳዋ የራሱ እንደሆነች አውቆ ረሃብ የሁሉም ወንድሞቹ ዕጣ መሆኑን ተገንዝቦ በትካዜ እንዲህ አንጎራጎረ ይላል ደበበ በተራኪ ግጥሙ፡፡

‹‹እንዳኖረው ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለ ሥፍራ

 መጥቆ እንደ ባንዲራ

ምንም ባዶ ቢሆን በውስጡ አይጠፋምና የታሪክ አዝመራ፡፡››

ይህንን የልሂቁ ገጣሚና የሥነ ጽሑፍ መምህር የነበረው ረዳት ፕሮፌሰር ደበበ ሰይፉ ተራኪ ግጥም፣ በሦስተኛው የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበው በመዝሙር፣ሙዚቃ፣ሰርከስናዳንስ ተዋሕዶ ነው፡፡

‹‹የአክሱም ጫፍ አቁማዳ›› ትዕይንት ሀገራዊ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት ሥራ መሆኑን ተከትሎ ተመልካቹም ለትዕይንቱ ከፍተኛ አድናቆት ችሮታል፡፡ ተራኪው ዕውቁ ተዋናይ ታምሩ ብርሃኑ፣ የሙዚቃዊ ቴአትሩን ያዘጋጀው አየሁ ሞላ ሲሆን፣ የትዕይንቱ አስተባባሪ ሄኖክ የእታገኝ ልጅ ነው፡፡

ለሥነ ጽሑፍ ለሥነ ጽሕፈት አዝመራ ይበልታን ይሁንታን የሚያጎናፅፍ ሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በዕለቱ በዘጠኝ ዘርፎች ሽልማት ሰጥቷል፡፡ የልጆች ንባብ ባለውለታ በመሆን ከሩብ ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን ለልጆች በማቅረብ፣ አጋዥ መጻሕፍትን በማሳተምና በማሰራጨት ኢትዮጵያ ሪድስ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የመጻሕፍት የውይይት መድረክ በመፍጠር ባለፉት 15 ዓመታት 450 በላይ መጻሕፍት ላይ ውይይት በማድረግ ደግሞ ሚዩዚክ ሜይዴይ የመጻሕፍት ውይይት የንባብ ባለውለታ በመሆን ተሸልሟል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው 10 ዓመት የጥናትና ምርምር መጻሕፍት ዘርፍ ሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ሥላሴ ተፈራ ‹‹ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀት›› መጽሐፋቸው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ብዝኃነትን እናክብር በሚል መርሕ የተካሄደው ሦስተኛው ሽልማት ከአማርኛ በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የትግርኛና የኦሮሞኛ የልጆች መጻሕፍትን አወዳድሮ፣ በትግርኛ አዶናይ ገብሩ ‹‹ስንዳዮ›› በተሰኘው ሥራው፣ ሂንሴኒ መኩሪያ ‹‹ጄዴለቻፊ ከንቢሮ›› በተባለው የኦሮምኛ መጽሐፉ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የሕይወት ዘመን የሥነ ጽሑፍ ባለውለታ ተሸላሚ የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ‹‹ቋሳ›› የተሰኘ ልብ ወለድ በማሳተም የመጀመሪያዋ ሴት ልብ ወለድ ደራሲ የሆነችው ፀሐይ መልዐኩ ናት፡፡

በአማርኛ የልጆች መጻሕፍት ዘርፍ በኃይሉ ብረ እግዚአብሔር የተጻፈው ‹‹ተረትን በግጥም›› መጽሐፍ፣ በግጥም ዘርፍ በመዘክር ግርማ የተጻፈው ‹‹ወደመንገድ ሰዎች›› መድበል፣ በረጅም ልብ ወለድ የውድድር ዘርፍ የአዳም ረታ ‹‹አፍ›› አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

አዳም ረታ 2009 .. በተካሄደው የመጀመሪያው የሆሄ ሥነ ጽሑፍ ሽልማት በ”የስንብት ቀለማትመጽሐፉ የዓመቱ ምርጥ የረጅም ልብወለድ ዘርፍ ማሸነፉ የሚታወስ ነው::

የሆሄ ሽልማት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት በእርሻ፣ ኢንዲስትሪና፣ ንግድ ትኩረት አድርጋ የምትሠራውን ያህል ጠንካራ ሰብእና ያለው ትውልድ መገንባት ላይም ትኩረት ማድረግ ያሻታል›› በማለት አንባቢ ትውልድ መፍጠር በጉልበት ሳይሆን በሐሳብ ልዕልና የሚያምን ዜጋንመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ሦስተኛው የሆሄ ሽልማት የተካሄደበት ቀን በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ከ55 ዓመት በፊት አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን የዓለም ሪከርድን በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀበት ታሪካዊ ቀን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ መሪ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እዚያው ቶኪዮ ላይ

‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፤
ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደ ቆሎ፤›› ብለውተቀኙትን ያስታውሷል፡፡

የሽልማቱ መድረክ አጋፋሪ ይህንን ታሪካዊ ዕለት የሐመልሚል (ኢሜራልድ) ኢዮቤልዩ ያስታወሰው የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ድምፃውያኑ እነ ተፈራ ካሳ፣ ጥላሁን ገሠሠ የዘፈኑትን ውዳሴ ግጥም እንዲህ በማቅረብ ነበር፡፡

      “በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ

      አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ

      በጥቅምት 11 በሩጫ ገበያ

      አቤ ይዞት መጣ የወርቁን ሜዳሊያ፡፡”

በአጋጣሚውም በመጪው ሐምሌ ቶኪዮ በምታዘጋጀው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአበበ ቢቂላን ድል  እንዲሰንቁ  ሆሄ ሽልማት ተመኝቶላቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...