Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገርን የማያከብር አክባሪ የለውም!

ሰላም! ሰላም! ይኼውላችሁ ባለፈው ክረምት በተወሰኑ ቀናት ሠፈራችን ዝናብ አልጥል ብሎ ጉድ ሲባል ሰነበተ። አንድም በኑሮ አንድም በሸረኞች ጫና ሰው ራሱን ሲጥል እየታዘብን ግን ጉድ አንልም። እናም ስንት የዘጋን ወዳጅ ዘመድ እያለ፣ ስንት ሥራ ያውጣችሁ ያለን ሹም ለተጠያቂነት ሳይጠራ፣ ለጥቂት ቀናት ዝናብ ዘጋን ተብሎ ስብሰባ ተጠራ። ግን አይገርማችሁም ለቡና መጠራራት እየተውን በረባ ባረባው ለስብሰባ ስንጠራራ? ኧረ የጉድ ነው ዘንድሮስ! ስንት የወደቀ ነገራችንን ሳናነሳና ሳናስተካክል በማያገባን ጉዳይ መንገዋለል ይቀናናል መቼም። አይገርማችሁም? ውሎ ሳያድር ደግሞ አዛውንቱ ባሻዬ ስብሰባውን እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ ተባለ። ‹እኔ በእግዜር ሥራ አልገባም› አሉ ተባለ። ገሚሱ ‹ደግ አደረጉ!› ሲላቸው ገሚሱ፣ ‹የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት አያሳስባቸውም?› ብሎ ተቀየማቸው ተባለ። ይኼ ለድጋፍና ለተቃውሞ መጣደፍ የሚለቀን ግን መቼ ይሆን? መጥኔ!

ስለስብሰባው የሰሙ ዲግሪ ጭነዋል የተባሉ ወጣቶች ደግሞ ሥራ ፈልግልን እያሉ አላስቆም አላስቀምጥ ብለውኛል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ ሕገወጥ ደላላ ሊሉኝ እኮ ነው፡፡ ‹ዝናብን እኮ አምላክ አያዘንበውም. . . ደመና ተንኖ ቅብጥርሶ. . .› ብለው ኧረ የት ሄደን ተግባር ላይ እናውለው እያሉ የሚንገዋለሉበትን የዕውቀት ጫና ባሻዬ ላይ ለማራገፍ መጣጣራቸው ተሰማ። ‘ዕውቀት ሲበዛ አመድ ገንፎ ነው ያስብላል’ ያለው ማን ነበር? ጠፋኝ ብቻ። ተብሎ ተብሎ የስብሰባውን ‘ሪፖርት’ በአጭሩ የባሻዬ ልጅ ሲያጫውተኝ ቧልተኞች ተናገሩት የተባለው ቀልቤን ስቦት ነበር። ምን አሉ አትሉም? ‹በየቦታው መንገድ የተዘጋበት ሰሞን ስለሆነ እስኪ ትንሽ እንታገስ? መንገድ ዘጊዎች ልቦና አግኝተው ሲሰክኑ ይሆናል. አሉ ብሎ አጫወተኝ።

ወዲያው የስብሰባው አጀንዳ ፖለቲካዊ ሆነ አሉ። ገሚሱ፣ ‹ተው እንጂ እናንተ! ደግሞ ፈረንጅም ደብተራ አለው ልትሉ ነው? ኧረ በሰላም እንኑርበት› እያለ ሲርበተበት ሌላው፣ ‹እኛ ሳንሰማ ሰማይም የመንግሥት ሆነ እንዴ?› እያለ ተንሾካሾከ። በበኩሌ ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝ ይኼ ‘አንዳንድ’ የሚባሉ ነዋሪዎች ትልም ነው። ሁል ጊዜ በዘዴ ይሰበሰቡና በጅልነት ይበተናሉ። ‘አልዘንብ አለ እኮ? የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ገላቸውን ታጥበው አይጨርሱም ወይ’ ብለው ተሰብስበው፣ ‘ኢሕአዴግ የሳሙና እጥረት ስለገጠመው ነው’ ዓይነት ወሬ አውርተው ይለያያሉ። በተቸገርንባቸው ነገሮች መፍትሔ የምንለውን ከማቅረብ ደግሞ ፎክሮና ተመፃድቆ የመለያየት አባዜያችን፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓይነት ‘ጂኒየስ’ በዝተውልን ችግራችንን ሊፈቱልን እንደሚችሉ አያወያየንም። መቼም ይኼ ምሳሌ ይገባችኋል፡፡ ወድጄ አይደለም የምሙለጨለጭባችሁ፡፡ ተግባባን?

ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል። አላዝልን እያለ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው። ‹‹በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰው. . .›› ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። ውዷ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር ‹‹ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ. . .›› እያለች ትሞዝቅላችኋለች። እኔ ደግሞ ‘መልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ። አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ። ስቀንስ ስደምር፣ የሆቴል፣ የምግብና የትራንስፖርት ሳባዛ ሳካፍል መዋል። ግን ለምንድነው ዘንድሮ ሽርሽር ለመጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው መዋዠቅ ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ። ኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?›› ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ ‹‹ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ሐዋሳ ላንጋኖ እያለች የምትዘፍነው። ሁሉም ነው፤›› አለኝ። እውነት ነው የሐዋሳ ሰዎችም እባካችሁ ኑልን እያሉ ነው!

አገር የምታድገው በወሬ አይደለም ሲባል በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ እኔ የዋሁ በቃ ነዳጅ ነው የሚያስፈልገን ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅን፣ ‹‹ታዲያ ምነው ነዳጃችንን በቶሎ አውጥተን በሀብት የማንንበሸበሸው?›› ስለው፣ ከነዳጅ በላይ ብዙ ሀብት አለን፡፡ ከሠራንበት በቱሪዝም ብቻ የትና የት መድረስ እንችላለን፡፡ ማዕድናቶቻችን ተዝቀው አያልቁም፡፡ ውኃ ብትል መሬት፣ ወጣት ብትል ታዳጊ ሞልቶናል፡፡ ‹‹የጎደለን አርቆ ማሰብ ነው!›› አይለኝ መሰላችሁ? ጉድ እኮ ነው እናንተ! ‹‹እኔ እኮ በነዳጅ ብቻ የምንከብር መስሎኝ ነው። እለዋለሁ፣ ‹‹ተው እንጂ አዕምሮህን አሠራው፤›› ብሎ ተቆጣኝ። ኧረ እንዴት ነው ነገሩ? ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ! እኔማ እጄ ላይ ያለውን ገንዘብ ስለመቆጠብ እንጂ፣ ሠርቼበት የበለጠ ለማትረፍና ሥራ ለመፍጠር አስቤበት አለማወቄ ቆጨኝ፡፡ እኛ ደግሞ ካጠፋን በኋላ ሲቆጨኝ እንጂ ሌሎች የፈጸሙትን ስህተት ላለመድገም አንጠነቀቅም፡፡ እኔም ራሴን እወቅሳለሁ፡፡ ራስን መውቀስ መልካም መሰለኝ!

ከሥራ የሚበልጥ የለም ብዬ ሁሉንም ነገር ትቼ እንደ ወትሮዬ ወደ ድለላዬ ሮጥኩ። አንድ ደንበኛዬ ያገለገለ ከባድ መኪና ከአውሮፓ ገዝቶ ከሚያስመጣ ሰው ጋር እንዳገናኘው ስለጠየቀኝ ወዲያው ደዋውዬ አገናኘኋቸው። ስለሚጫነው የመኪና ዓይነት በደንብ ተነጋገሩ። ያው ዘመኑ የሚሊዮኖች ነውና የምትሰሙዋቸው ቁጥሮች በጠቅላላ ባለሰባት ‘ዲጂት’ ናቸው። እኔን የሚገርመኝ ታዲያ ግለሰቦች ሰባት ‘ዲጂት’ እያገላበጡ ሥራ ሲሠሩ እያየንና እያመንን፣ አይኤምኤፍ ባለሁለት ‘ዲጂቱ’ን የኢኮኖሚ ዕድገት መጠራጠሩ ነው። እውነቴን እኮ ነው። አንድ ወዳጄን እንዲህ ስለው፣ ‹‹ፈረንጅ እሱ ባለህ መንገድ ብቻ ካልሄድክ መኖርህንም ይጠራጠራል፤›› አለኝ። ስለህልውናችን ለመፈላሰፍ ከተፈለገ እኮ እኛም እንብሳለን። በአንድ ወቅት አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ምንተስኖት በሚባለው ስምህ ብትታወቅም፣ ማንጠግቦሽ የምትባል ሚስት ብትኖርህም፣ ባሻዬ የሚባሉ ጎረቤትህ ቡና ቢያጣጡህም፣ ከምሁሩ ልጃቸው ጋር ቅርበትህ እስከ ግሮሰሪ ቢዘልቅም ለዓለም ኢምንት ነህ. . .›› ብሎ ጭር ካደረገኝ በኋላ በሰው ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡

ሌላው ወዳጄ የምለው ደግሞ የተለየ አባዜ ነው ያለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን ሰው ስታዘብ ይገርማችኋል ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ተነስቶ እየተወራ፣ ነገር ማብራራት የሚቀናው በሥጋና ምግብ ነክ በሆኑ ቅመማ ቅመሞች ነው። የአማልክት ስም ጠርቶ ምፅዋት ከሚጠይቀው የእኔ ብጤ ይልቅ ‘ከብቶቼ አልቀው በሬዎቼ ሞተው ተሰድጄ ነው’ ላለው ድፍን ሃምሳ ብር ይመፀውታል። አንዳንዴ የምናውቀውን ሰው በሌለበት ስንሸረድድ፣ ‹‹ቁርጥ አትቁረጡና ከሰው ተቆራረጡ፤›› ብሎ ያፌዝብናል። ግን መቆራረጥ ከአፈጣጠራችን ሳይሆን ከምናዘወትረው አመጋገብ የተነሳ ይሆን እንዴ? አለመተማመን፣ ለራስ ወገን ማድላት፣ አገርንና ሕዝብን በንብረቱና በጥቅሙ መበደል ምንጩ ከምንጎርሳት ጉርሻ አቀማመም ጋር ግንኙነት እንዳለውስ? በሚሊዮን እየተጫወትን ዝርዝር ሳንቲም ብቻ ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ችላ የምንልበት ምክንያቱም እኮ ከጉርሻችን ጋር አብሮ መጠናት አለበት። አይደለም እንዴ? ‘ኤግዛክትሊ!’ በሉ እንጂ! እንዲህም እንኖራለን ለማለት ነው!

እናላችሁ በቅርቡ ከባድ መኪናውን አስመጥቶ ከሚሸጠው ደንበኛዬ ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ እጄ እንደሚገባ እያሰብኩ ራሴን በተመለከተ አንዳንድ የ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ መተለም ጀመርኩ። ካፖርቴ ቅያሪ ያስፈልጋታል። የጫማዎቼ ሶሎች አልቀዋል። እግሬ እስኪቀጥን እየተጓዝኩ ዳሩ ቀድሞኝ የሚያልቀው ጫማዬ እየሆነ ተቸግሬያለሁ። ለሁሉም ‘ሾፒንግ’ ያስፈልገኛል። እናም አንድ የልብስና የጫማ ሱቅ ዘው ብዬ ገባሁ። ‹‹ይኼ ጫማ ስንት ነው?›› ብዬ ከመጠየቄ ደንበኛ ለማስተናገድ ሳይሆን ደመኛ ለማፍራት የተቀጠረች የምትመስል ቆንቋና ገጿን አጨፍግጋ “ስድስት ሺሕ” አለችኝ። “አቤት?” የምር አልሰማኋትም። አንዳንዴ እኮ አይሰማችሁም። “ስድስት ሺሕ አልኩህ!” ተነጫነጨች። የንጭንጯ ሰበቡ ገባኝ። በቀን ስድስት ሺሕ ጊዜ ይኼን ጥሪ እየጠራች አንድም ሰው ሳይገዛት ስለሚሄድ መሆን አለበት አልኩ። “ቅያሪ አለው ማለት ነው?” ታዲያ ምን ልበላት? ‹‹የምን ቅያሪ ጥንዱን ነው እንጂ፣ ከገዛህ መግዛት ነው፤›› ብላ ፊቷን አዞረችብኝ።

‹‹እሺ የስንት ዓመት ‘ጋራቲን’ አለው?›› ልላት ብዬ የስንትስ ዓመት ቢኖረው አሁን ይኼን ጫማ አድርጌ የሠፈር ሰው ቢያየኝ ሠርቶ ገዛው ብሎ ያምነኛል ብዬ ተውኩት። በቃ ባዶዬን ከምወጣ ካልሲ ምናምን ልግዛ ብዬ ካልሲ ስጠይቃት አንድ ካልሲ 350 ብር ገብቷል። እንዲህ የሚረባውም የማይረባውም እየጨመረማ እኛም ብልጠት ሳንጨምር ‘ጉድ እያሉ መኖር’ አያዋጣንም አልኩና ስከንፍ መርካቶ ሄጄ ክርና ኪሮሽ ገዛሁ። አንገቷ ላይ ያለቀች ካፖርቴን አስገልብጬ ለማሰፋት ወስኜ ለሰፊ አቀበልኳት። ክርና ኪሮሹን ደግሞ ለማንጠግቦሽ ወስጄ ሰጠሁና ጊዜ ስታገኝ ካልሲ እንድትሠራልኝ ነገርኳት። ታዲያ በዚህ ኑሮ ላይ ‘ኢምፖርትድ’ ዕቃዎች እየሸመትን ‘ኤክስፖርት’ ለመደረግ ሳንበቃ ‘ኤክስፓየርድ’ እንሁን እንዴ? ከዚህ የተሻለ የ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ ያለው ሐሳቡን ‘ሼር’ ማድረግ ነው። ‘ፌስቡክን’ም ስንሰዳደብበት ከምንውል ለ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅዳችን መሳካት ብንጠቀምበት ጥሩ ነው። የእናንተን ባላውቅም እኔን ግን መስሎኛል!

በሉ እንሰነባበት። የጥቅምት ብርድ እየጨመረ ነው። ‘መንገዱን ከፍተውት ነው ማለት ነው’ እያልኩ በውስጤ የመንገድ ዘጊዎች ነገር ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ባሻዬ መንገድ ላይ አገኙኝ። “አንተንም ጀመረህ?” አሉኝ ለሰላምታ እጃቸውን ዘርግተው። “ምኑ?” አልኳቸው። “ለብቻ መዋለሉ?” ብለው ተራቸውን ፈገግ አሉ። እንዳልገባኝ ስነግራቸው፣ ‹‹እስኪ ወደ ቤቴ እየሸኘኸኝ እነግርሃለሁ፤›› ብለውኝ መጓዝ ጀመርን። ‹‹እንዲያው ሕመሙና የጋራ ጥያቄው ሁሉ የወል፣ ማግኘቱና ማጣቱ፣ መታፈኑና መተንፈሱ፣ መጨነቅና መባዘኑ የሁላችን የሕይወት አካል ሆኖ ሰው ብቻውን ሲተክዝ ብቻውን ሲያወራ ብቻውን ሲያብድ ሆኗል የማየው። አንተም እንደዚያው የሆንክ ስለመሰለኝ እኮ ነው፤›› ሲሉኝ ያስፈገገኝን ነገር አጫወትኳቸው።

አዛውንቱ ባሻዬ ከወትሮው በተለየ ከትከሻቸው ጎብጠው በረጂሙ ተነፈሱና “አንበርብር?!” አሉኝ። “አቤት!” አልኳቸው። “ምን እንደሰለቸኝ ታውቃለህ?” ሲሉኝ፣ “ምን ይሆን ባሻዬ?” ስጓጓ እያዩኝ ጥቂት በሐሳብ ተጉዘው ቆይተው፣ ‹‹በማያንገዋልለው የሚንገዋለለው፣ በማይቸግረው የሚቸገረው ሰው ብዛት። እንዴ ምንድነው እንደዚህ ነገር ሰንጣቂው የበዛው? እንጨት እየሰነጠቁና እየላጉ ጎጆ የሚያጠብቅ ማገር መሥራት አይሻልም? በነፈሰው ሁሉ ሆ?! በየቀኑ ጭፈራ? በየቀኑ ስላቅ? በየቀኑ ቧልት? አይሰለችም እንዴ? ይህም አልዘልቅ ብሎ እርስ በርስ መጠማመድና መተናነቅ. . .›› ብለው ሳይጨርሱ ቤታቸው ደርሰን ነበር። ድንገት ቆም ብለው፣ ‹‹አደራ ለራስህም እያወቅክበት። ቁም ነገር ተረስቷል። ቢተች የማይሰለቸው፣ ቢዝት የማይደክመው ሰው በዝቷል። ሰውን ሰው ያደረገው ግን ሥራና ቁም ነገር ነው። ደህና እደር!›› ብለውኝ ቤታቸው ገቡ። እኔም ተለይቻቸው ስጓዝ ሰውን በእርግጥ ሰው ስለሚያስብለው ነገር እያሰብኩ ነበር። የማሰብ መብታችንን ሳንጠቀምበት ለምን ለአፍ ወለምታ እንደምንቸኩልም ማሰብ ስለፈለግኩ ቶሎ ብዬ ወደ ቤቴ ስገባ ማንጠግቦሽ ኪሮሿን ይዛ ተቀምጣለች። እንዲህ ነው እንጂ ‘ትራንስፎርሜሽን!” ስላት፣ ‹‹ገና ኤክስፖርት እናደርጋለን እባክህ! ይልቁንስ ሰው ለመሆን ከፈለግክ ሰውን ሰው ያደረገው ምን እንደሆነ ዕወቅ!›› ስትለኝ ግጥምጥሞሹ አስገረመኝ፡፡ ውኃ ልኩ ጠፋ እንጂ ይኼ መቼ ይጠፋናል? ከግጥምጥሞሹ ይልቅ እውነታው ላይ ብናተኩር ይበጀናል፡፡ እውነት ነፃ ያወጣል፣ ትውልድ ያንፃል፣ አገር ያሳድጋል፣ መግባባት ይፈጥራል፡፡ ከአገር በፊት ኖረው የማያውቁ እኛ ከሌለን አለቀላት ብለው ሲሳለቁ እረፉ መባል አለበት፡፡ ምክንያቱም ውሸታሞች ናቸውና፡፡ በባዕድ ፓስፖርት ወገንን የሚያምሱ የግጭት ነጋዴዎችንም ማስቆም የምንችለው እውነትን ይዘን ነው፡፡ አገር አዋራጅ ሐሰተኞችን የምናሳፍረው በእውነት ነው፡፡ አገርን የማያከብር አክባሪ የለውም እንዲሉ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት