Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየህዳሴ ግድቡን ውኃ አሞላል የኢትዮጵያን ጥቅም ሳይነካና ግብፅን ሳይጎዳ በማከናወን የፖለቲካ ስምምነት...

የህዳሴ ግድቡን ውኃ አሞላል የኢትዮጵያን ጥቅም ሳይነካና ግብፅን ሳይጎዳ በማከናወን የፖለቲካ ስምምነት መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ

ቀን:

ከማንኛውም ወገን ጋር ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ ኢትዮጵያ ችግር የለባትም ብለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሩሲያ – አፍሪካ ጉባዔ ስብሰባ ጎን ለጎን ከግብፅ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በመምከር፣ የግድቡ የውኃ አሞላል የኢትዮጵያን ጥቅም በማይነካና በግብፅ ላይም ጉዳት በማያደርስ መንገድ እንዲፈጸም የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡

የህዳሴ ግድቡ በምን ያህል ዓመት ውስጥ በውኃ እንደሚሞላ እስካሁን ስምምነት አለመደረጉ በግብፅ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ሥጋት መፍጠሩን የግብፅ ፕሬዚዳንት እንደገለጹላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ይኼንንም የግብፅ ሥጋት ለመቅረፍ ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን በእኩል የተወጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተመካክሮ የሚደርስበትን ሳይንሳዊ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ፣ የጀመረውን ውይይት እንዲቀጥል ሁለቱ መሪዎች እንደተስማሙም አስረድተዋል፡፡

 ግብፅ የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆንና ኢትዮጵያም በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ እንድትለቅ የተናጠል ጥያቄ የያዘ ሰነድ፣ በመስከረም ወር መጀመርያ ላይ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ የግድቡ 165 ሜትር መሆኑን በማረጋገጥ፣ የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ እንድትለቅ ባቀረበችው የተናጠል የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ሰነድ መጠየቋ አይዘነጋም፡፡

ከዚህ ባለፈም የህዳሴ ግድቡ የኃይል ማንጨት ተግባር፣ የግብፅ ባለሙያዎች በሚወከሉበት የጋራ ቡድን መመራት አለበት የሚል ሐሳብም ባቀረበችው ሰነድ ተካቷል፡፡

ኢትዮጵያ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ሉዓላዊነትን የሚዳፈርና በትብብር ላይ ተመሥርቶ ከተጀመረው ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ያፈነገጠ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡

ከሦስቱ አገሮች የተወጣጣው የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን አባላት በሱዳን ተገናኝተው ግብፅ ላቀረበችው ሐሳብ የኢትዮጵያና ሱዳን አማራጭ ሐሰቦች ቀርበው የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ በተወሰነው መሠረት፣ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ተገናኝተው ቢመክሩም ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ሪፖርተር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ውይይት ያለ መግባባት በመጠናቀቁ፣ የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ጣልቃ በመግባት ውይይቱን ለማስቀጠል ቢሞክሩም እነሱም መስማማት አልቻሉም፡፡ በዚህም ሳቢያ ግብፅ ሦስተኛ አደራዳሪ ወገን በተለይም የአሜሪካ መንግሥት እንዲገባ በይፋ ጠይቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበውን ጥያቄ እንደማትቀበለውና ያለ ሦስተኛ ወገን ልዩነቶች ላይ መስማማት እንደሚቻል፣ ነገር ግን ግብፅ ሳይንሳዊ አመክንዮዎችን ላለመቀበል ስትል የድርድሩን መንፈስ ማስተጓጎል የተለመደ ተግባሯ እንደሆነ በመግለጽ መተቸቷ ይታወሳል፡፡

ግብፅ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ባቀረበችው ሐሳብ ላይ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር ተወያይተው እንደሆነ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ትልልቅ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው አገሮች በመሆናቸው በሁለቱ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ቀጣናውን ይረብሻል የሚል ሥጋት ኃያላኖቹን አገሮች ሩሲያን ጨምሮ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሩሲያን ጨምሮ ሌሎች አገሮችም በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ያለውን ልዩነት ለማሸማገል ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ ከማንኛውም ወገን ጋር ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ ችግር እንደሌለባት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን አቋምና ፍላጎት የሚገልጽ መልዕክት ወደ ሩሲያ ከማቅናታቸው ከሁለት ቀናት በፊት፣ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት መላካቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...