ቀጥታ ሥርጭትና የኦን ላይን ትኬት ሽያጭ አገልግሎት ይኖረዋል
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጥቅምት 22 እስከ ኅዳር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያከናውነውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የትኬት ሽያጩን በኦን ላይን ከማድረጉ ባሻገር፣ ውድድሩ የቴሌቪዥን ሽፋን እንደሚኖረው ገለጸ፡፡
አራት የክልል ቡድኖችን በተጋባዥነት የያዘው 14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ፣ አሸናፊው ቡድን ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት እንዲያገኝ በፌዴሬሽኑ በኩል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡
በመጪው ቅዳሜ በሚጀመረው የመዲናዪቱ ዋንጫ ስምንት ቡድኖች ይካፈሉበታል፡፡ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅጥር ግብ በይፋ ወጥቷል፡፡
በድልድሉ በምድብ “ሀ” ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ተጋባዦቹ ባህር ዳር ከተማና ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም መከላከያ ሲሆኑ፣ በምድብ “ለ” ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ተጋባዦቹ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሰበታ ከተማ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሁሉም ጨዋታ በአዲስ ቴሌቪዥንና በ96.3 ኤፍኤም የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው የተነገረለት የዘንድሮ ዋንጫ፣ አሸናፊዎች ከሚያገኙት ዋንጫ በላይ በተለይም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚኖረው ትርጉም ትልቅ እንደሚሆን በመግለጫው ተነግሯል፡፡
የቀጥታ ስርጭቱን አስመልክቶ፣ በአዲስ አበባ ሚዲያ ኔትዎርክና በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይለየሱስ ፍሥሐ (ኢንጂነር)፣ ውድድሩ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በአዲስ አበባ ሚዲያ ኔትዎርክ አማካይነት ሽፋን ማግኘት ለከተማዋ እግር ኳስ እንቅስቃሴና በተለይም ፌዴሬሽኑ ለሚያወዳድራቸው ዕድሜያቸው ከ15፣ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ታዳጊና ወጣቶች ትልቅ ተስፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ለአሸናፊ ቡድኖች ከሚሰጠው ዳጎስ ያለ የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ጎን ለጎን፣ ተመልካቾች የመግቢያ ትኬት ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜ ለማስቀረት የኦን ላይን ትኬት ሽያጩን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ከዳሸን ባንክ ጋር በመሆን የአሠራር ሥርዓቱን ለመዘርጋት ከሦስትና አራት ወራት በላይ ሲዘጋጅበት መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ጨዋታውን ለመከታተል የሚያስችለው ትኬት በሁሉም የዳሸን ባንክ ቅርንጫፎች እንደሚገኝ ያስረዱት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በኦን ላይን ሲስተሙ መጠቀም ለማይፈልጉ ተመልካቾች ጨዋታው ከሚጀመርበት ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ድንኳኖች እንደሚኖሩ፣ የገንዘቡ መጠን ከዋናው የኦን ላይን ዋጋ ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በወጣው መርሐ ግብር መሠረት የመክፈቻውን ጨዋታ የሚያደርጉት ከምድብ አንድ ተጋባዦቹ ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ሲሆን፣ ሰኞ ጥቅምት 24 ደግሞ በምድብ ሁለት የተደለደሉት ኢትዮጵያ ቡና ከተጋባዡ ሰበታ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እንደሚጋጠሙ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ተጋባዥ ክለቦች በሥራ አስኪያጆቻቸው አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይም በማዘውተሪያዎች አካባቢ እየተስተዋለ የሚገኘው አላስፈላጊ ውዝግብና ግርግር እየጎዳ ያለው እግር ኳሱን በመሆኑ ይህንኑ ሁኔታ ለማስቀረት፣ የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ላይ አርዓያነት ያለው ስፖርታዊ ጨዋነት እንደሚያሰፍኑ ተናግረዋል፡፡