Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክአዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

ቀን:

በመሐመድ አብደላ

የኢትዮጵያ የአሠሪና የሠራተኛ የሕግ ግንኙነት የ40 እና 50 ዓመታት ታሪክ ያለው ነው፡፡ ታሪኩን ትተን ሕጎቹ የወጡበትን ቅደም ተከተል በአጭሩ ስናይ በቅድሚያ የምናገኘው በነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር 1/1953 የወጣውና ከበርካታ ሕግጋት መሀል ስለሥራዎች አገልግሎት መስጠት ውል አንድ ክፍል የያዘው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በአዋጅ ደረጃ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ከሌሎች ሕጎች ተነጥሎ በአዋጅ ቁጥር 210/1956 በዘውዳዊው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ተደንግጎ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት በሶሻሊስት ቅኝት የታጀበው አዋጅ ቁጥር 64/1968 እስኪተካ ድረስ ሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ የወጣው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 42/1985 እሱንም የተካው አዋጅ ቁጥር 377/96 እንዲሁም የዚሁ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 በቅርቡ በአዲስ ሕግ  ተተክተዋል፡፡ ይህ አዲሱ ሕግ በስያሜ ደረጃ ከነባሩ ሕግ ጋር ምንም ልዩነት ሳይኖረው ስለአሠሪና ሠራተኛ የወጣ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 (1156/2019) በሚል በአዲሲቷ ፕሬዚዳንት በነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈርሞ በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ቀን (መስከረም እስከ ጥቅምት 2012) ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡

የሕጉ ማሻሻያ ዝግጅት ሒደትና ተሳትፎ

በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ከነማሻሻያዎቹ ለመተካት የወጣው ረቂቅ አዋጅ አጭር ምልከታ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ ሰነድ በተገኘ መረጃ መሠረት፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ሕጉን የማሻሻያ ቅድመ ዝግጅትና የአዋጅ ማሻሻያ ሰነድ ዝግጅት ጥረት ከአራት ዓመት በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጨማሪ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሐሳብ ያቀረቡና ሐሳባቸው እንዲካተት ከተደረጉ ተቋማት ውስጥ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ያካተተ ኮሚቴ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የተገኙ ሐሳቦች (የባለድርሻ አካላቱ ማንነታቸው በስም አልተጠቀሰም)፣ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አማካሪ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ በክልልና ፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ አስፈጻሚ አካላትና “ባለድርሻ አካላት” ጋር በተደረገ ውይይት የተገኙ ግብአቶች እንዲሁም አገራችን በአባልነት ከተመዘገበችበት የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) በተለያዩ ጊዜያት የተገኙ የአዋጁ የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች የተካተቱበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በሕጉ ውስጥ የተካተቱ የትኞቹ ነጥቦች ከውጭ ልምድ የተገኙ መሆኑ በግልጽ ባይጠቀስም፣ ከቬትናምና ከደቡብ ኮሪያ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም በረቂቅ ማሻሻያው ውስጥ እንዲገቡ መደረጉም ተገልጿል፡፡ ይህም ሆኖ “ባለድርሻ አካላት” በሚለው ጠቅላላ አገላለጽ ውስጥ ተካተዋል ካልተባለ በስተቀር፣ በሕጎቹ በመሥራትና የዕለት ተዕለት ችግሮችን ከማስተዋል አንፃር ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ዳኞችንና ጠበቆችን የሚወክሉት ተቋማት ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠበቆች ማኅበር በረቂቅ ሕጉ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ግልጽ አይደለም፡፡

በአዲሱ አዋጅ የተካተቱ ዋና ዋና አዲስ ነገሮች

በያዝነው 2012 ዓ.ም. ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ለ14 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ የተካ እንደመሆኑ፣ በረዥም ጊዜ ቆይታ ዕድገትና ለውጥ እንደሚያሳዩ የሚጠበቁ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮችን እንዲሁም ጊዜው ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር መራመድ የሚያስችል ሕግ ሊወጣ እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ በእርግጥ የተለወጠው ሕግ አገራችን ከደረሰችበት ዕድገትና በሁሉም ዘርፍ የታዩ ለውጦችን ያማከለ ነው ወይ የሚለው በሰፊው ሊያወያይ የሚችል በመሆኑ ለአንባቢያን እየተወዋለሁ፡፡ በመሆኑም ይህ ጽሑፍ የተለወጠው ምንድን ነው በሚለውና ዋና ዋና የተለወጡ ነጥቦችን ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 የሕጉ መለወጥ ወይም የሕጉን መውጣት አስፈላጊነት የሚዘረዝረው የሕጉ መግቢያ (Preamble) አስቀድሞ ከነበረው ሕግ ለየት ያሉ ጽንሰ ሐሳቦችና ዓላማዎች ሕጉ እንዳካተተ የሚጠቁሙ ነገሮች አሉት፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የመንግሥት ፖሊሲና አቅጣጫ ነፀብራቅ እንዲሁም የሕጉ ዓላማ መገለጫ እንደሚሆኑ ይታሰባሉ፡፡ የመጀመሪያው “አሠሪና ሠራተኛ የጋራ ራዕይ ኖሯቸው” ሕግን መሠረት ያደረገ “አስተማማኝ የኢንዱስትሪ ሰላም” በመጠቀም “ዘላቂ ምርታማነትና የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በመፍጠር አገራችን ለተያያዘችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማስመዝገብ ብሔራዊ ግብ በትብብርና በጋራ እንዲሠሩ” ማድረግ የሚል ሲሆን፣ በሁለተኛነት በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈታበት “የማኅበራዊ ምክክር ሥርዓት” (Social Dialogue) መዘርጋት የሚል አዲስ ጽንሰ ሐሳብ ተካቶበታል፡፡ በተጨማሪ ለኢንቨስትመንትና አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ግቦች መሳካት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሕግ መሠረት ሁኔታዎችን በማመጣጠን የሚሠራ አካል እንደሚያስፈልግና የዚህ አካል ሥልጣንና ተግባር በዝርዝር ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት በቀድሞው ሕግ ውስጥ የሌሉ አዳዲስ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሌላው እንዲካተት የተደረገው አዲስ ጉዳይ በአዋጁ ትርጓሜ በሚለው አንቀጽ 2(9) ላይ የሠፈረው “ማኅበራዊ ምክክር” ሲሆን፣ “በሁለትዮሽ ወይም በሦስትዮሽ መድረክ (አሠሪ-ሠራተኛ-መንግሥት) ማኅበራዊ አገልግሎት ስለሚስፋፋበት፣ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ስላሉ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጉዳዮች መረጃ በመለዋወጥና ምክክር ወይም ድርድር በማድረግ መግባት ላይ የሚደርሱበት ሒደት ነው፤” በሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ከላይ እንዳየነው ከዚህ በፊት በነበሩ ሕጎች ላይ ያልነበረና አዲስ ሲሆን፣ “ማኅበራዊ አገልግሎት” እንዲስፋፋ በጋራ እንሠራለን ተብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበራዊ አገልግሎት በዚህ ሕግ ላይ ምን እንደሚያካትት አልተቀመጠም፡፡ በተጨማሪ በእንግሊዝኛው የሕጉ ቅጂ ላይ በአማርኛው ክፍል ላይ የሌለ “Mutual Interests” የሚል የተጨመረበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል “ማኅበራዊ አገልግሎት” የሚለው በአማርኛው የሕጉ ክፍል ላይ የሚገኘው ደግሞ በእንግሊዝኛው ላይ ተዘሎዋል፡፡ ይህ የትርጉም ልዩነት አያመጣም ቢባል እንኳን ሕግን ያህል ነገር ሲወጣ ሊደረግ ከሚገባው ጥንቃቄ አኳያ ስህተቱ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ሌላው በትርጓሜ ክፍል ላይ የተጨመረው በርዕስ ደረጃ አዲስ ባይሆን እንኳን በቀድሞው ሕግ ላይ “የሥራ መሪ” ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ሳይተረጎም፣ በሕጉ ተፈጻሚነት ወሰን ላይ ሕጉ የሥራ መሪ ላይ የማይፈጸም መሆኑ በ‘Operational Definition’ ተቀምጦ ሲሠራበት የነበረው በአዲሱ አዋጅ ተሻሽሎ በትርጉም ክፍል ላይ ገብቶ እንዲተረጎም ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞው አዋጅ ላይ የሥራ መሪ ለመባል መሥፈርት ከነበሩት መካከል “የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ መውሰድ” (Taking Disciplinary Measure Against Employees) የሚለው በተግባር ክርክር የሚያስነሳና በትክክል የሥራ መሪ ለመባል በመሥፈርትነት ገላጭ ባለመሆኑ በአዲሱ አዋጅ ከመሥፈርትነት እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ሌላው በአዋጁ የትርጉም ክፍል እንዲካተቱ የተደረጉት ጣምራና ተያያዥ አዲስ ጽንሰ ሐሳብ “ወሲባዊ ትንኮሳ” እና “ወሲባዊ ጥቃት” የሚሉት ናቸው፡፡ “ወሲባዊ ትንኮሳ በንግግር፣ በምልክት ወይም በሌላ ማናቸውም አድራጎት አንዱ ሌላውን ከፈቃዱ ውጭ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባበል፣ መገፋፋት፣ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፤” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን፣ “ወሲባዊ ጥቃት” ደግሞ “ኃይል የተቀላቀለበት ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም የዚሁ ድርጊት ሙከራ ነው፤” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይህ አዲስ የተጨመረው ትርጉም በአሠሪ፣ የሥራ መሪ ቢፈጸም ወይም በማንኛውም ሠራተኛ ቢፈጸም እንኳን ለአሠሪው ወይም የሥራ መሪው ሪፖርት ተደርጎ፣ ለሠራተኛው የሥራ ቅጥር ውል ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ ምክንያት የሚሆን ሲሆን፣ አሠሪውም ድርጊቱን ማስቆም ወይም መከላከል ባለመቻሉ የሥራ ቅጥር ውል እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ካሳ እንዲከፍል የሚጠየቀበት ሁኔታ በአንቀጽ 39(1(መ)) ላይ ተካቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ከቅጥር በፊትም ሆነ በኋላ ሴት ሠራተኞች የሚፈተኑበትና የሥራ ደኅንነታቸው አደጋ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት በመሆኑ በአዲሱ ሕግ መካተቱ መልካም  ነው፡፡ ይህም ሆኖ ሪፖርት ማድረግ ማለት ምን ማለት እንደሆነና አሠሪው እስከምን ድረስ ኃላፊነት እንዳለበትና ማስረጃው የሚቀርብበትና የሚጣራበት ሁኔታ አለመጠቀሱ ሊፈጥረው የሚችለው ክፍተት በመኖሩ መታለፉ አግባብ አይደለም፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአዲሱ ሕግ በትርጉም ክፍል እንዲገቡ የተደረጉት “በሠራተኞች መካከል ልዩነት ማድረግ”፣ “የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ” እንዲሁም “የግል አገልግሎት ቅጥር” የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ የግል አገልግሎት ቅጥር በአዲሱ አዋጅ በትርጉም ክፍል ገብቶ እንዲተረጎምና አገልግሎቱ በቤት ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ሆኖ አሠሪው ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚቀጥራቸው እንደ ምግብ ዝግጅት፣ ጽዳት፣ ሞግዚትነት፣ የጥበቃ ሥራ፣ ሾፌርነት፣ አትክልተኝነትና የመሳሰሉት በአዋጁ እንደማይሸፈኑ በሕጉ ተፈጻሚነት ወሰን አንቀጽ 3 ላይ ተቀምጧል፡፡ ይሁንና የእነዚህን ሠራተኞች ሁኔታ አስመልክቶ እንዲሁም በአጠቃላይ የሠራተኞች አነስተኛ የደመወዝ መጠንን /Minimum wage/ በሚመለከት (አንቀጽ 55(2) እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማትና በጎ አድርጎት ድርጅቶች ጋር የሚመሠረት የሥራ ግንኙነት ላይ አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚያወጣ (ሊያወጣ እንደሚችል) ሕጉ አስቀምጧል፡፡

ሌሎች አዲስ ጉዳዮችና ማሻሻያዎች

በአዲሱ አዋጅ ቀድመው የነበሩ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችና አዳዲስ ጉዳዮች ውስጥ ከዚህ ቀጥሎ ዋና ዋናዎቹን እናያለን፡፡

የሙከራ ጊዜ ማለት አሠሪው ሠራተኛውን ሊመድበው ላሰበው የሥራ ዘርፍ ተስማሚ መሆኑን የሚሞክርበትና ሠራተኛውም የሚሠራውን ሥራና አሠሪውን ቋሚና ዘለቄታ ያለው ግዴታ ውስጥ ሳይገቡ በፊት የሚሞካከሩበት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ በጊዜ መገደብ በተለይም ከሠራተኞች ጥቅምና የሥራ ዋስትና አንፃር አስፈላጊ በመሆኑ፣ አስቀድሞ የነበረው ሕግ የሙከራ ጊዜ 45 ተከታታይ ቀናት እንደሆነ ደንግጎ ነበር፡፡ ሕጉ ከ45 ቀናት ውስጥ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ዕረፍት ነው ብለን ተቀናሽ ብናደርግ፣ አሠሪውና ሠራተኛው በሥራ የሚገናኙበት ትክክለኛ ቀናት ብዛት 39 ቀናት ብቻ በመሆኑ የተቀመጠው ጊዜ በትክክል የሕጉን ዓላማ ለመሳካት ያግዛል ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 11 የሙከራ ጊዜ መነሻ ጊዜውንም ግልጽ በማድረግ፣ “ሠራተኛው ሥራ ከጀመረበት ቀን አንስቶ” በዓላትና የሳምንት ዕረፍቶች ሳይታሰቡ 60 የሥራ ቀናት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም በበቂ ሁኔታ ለመሞካከር ዕድል የሚሰጥ፣ አላስፈላጊ ጥድፊያና ችኮላ እንዲሁም መሸዋወዶችን የሚያስቀር ነው፡፡

በቀደመው አዋጅ ላይ በግዴታ መልክ ያልተቀመጠ፣ ሠራተኛው የሠራተኞች ማኀበር አባል ሆኖ ከደመወዙ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ወደ ማኀበሩ ገቢ እንዲደረግለት ሲጠይቅ፣ አሠሪው ይህንን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉ ግዴታው እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 12(3) ላይ ተካቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 14(1) የሥራ መሪው ጥፋት የአሠሪው ጥፋት እንደሆነ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ስለሆነም በሥራ መሪ የተፈጸመ ሕገወጥ ተግባር በድርጅቱ ባለቤት እንደተፈጸመ ድርጊት እንደሚቆጠር ተቀምጧል፡፡

ከሥራ የሚያሰናብቱ ጥፋቶች

በተሻረው አዋጅ አንቀጽ 27 ላይ ሠራተኛ ከሥራ ያለማስጠንቀቂያ እንዲሰናበት ሊያደርጉ ከሚችሉ ተግባራት ነገር ግን በተግባር አወዛጋቢ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ “ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ከሥራ ማርፈድ” የሚለው ሲሆን፣ በቂና በቂ ያልሆነ ምክንያት ምንድነው እንዲሁም በተደጋጋሚ ማርፈድ የሚባለው ለምን ያህል ጊዜ ማርፈድ ነው የሚሉት ለዳኞች የህሊና ፍርድ የተተወ የነበሩ በመሆኑ ጉዳዮቹ አከራካሪ ነበሩ፡፡ በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 27(1(ሀ)) ላይ ግን የማርፈድ ምክንያት ወይም ሠራተኛው በሰዓቱ ሥራ ላይ መገኘት የማይችልባቸው ምክንያቶች በኅብረት ስምምነት፣ በሥራ ደንብ ወይም በቅጥር ውል ላይ ሊቀመጡ እንደሚችሉ ተገልጾ፣ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለስምንት ጊዜ ማርፈድ ከሥራ ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት በቂ ምክንያት እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ አከራካሪ ከነበሩና በተለይም በአሠሪዎች ቅሬታ ይቀርብባቸው ከነበሩ አንቀጾች ውስጥ አንድ ሠራተኛ በመደዳው ለአምስት የሥራ ቀናት ከሥራ ከቀረ ብቻ የሥራ ቅጥር ውል ይቋረጥበት የነበረው ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንድ ሠራተኞች ሕጉ ያለውን ክፍተት በመረዳት ለአራት ቀናት ቀርተው በአምስተኛው ቀን ወደ ሥራ በመመለስ ከቆይታ በኋላ ይህንኑ ተግባር በመድገም አሠሪዎችን ሕጋዊ የሆነ ዕርምጃ እንዳይወስዱ ሕግን ከለላ ያደረገ ጥፋት ይፈጽሙ የነበረበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 27(1(ለ)) ሥር ግን በማንኛውም ሁኔታ በሕግ ከተፈቀደ ዕረፍትና ፈቃድ ውጪ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በማንኛውም ቀን ተከታታይ መሆን ሳይጠበቅበት ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ለአምስት የሥራ ቀናት ከሥራ የቀረ ሠራተኛን ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ለማሰናበት ሕጉ ለአሠሪው  ፈቅዶለታል፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ የነበረ እሰጣገባና የሕግ ክፍተት እንዲሞላ ተደርጓል፡፡

ለሴት ሠራተኞችና ለቤተሰብ የተደረገ ጥበቃ

አስቀድሞ ሲሠራበት በነበረው አዋጅ በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ የቀጣሪ ድርጅት አገልግሎት ተፈላጊነት ሲቀንስና የሥራ እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት ሠራተኛ ሊቀነስ ይችላል፡፡ ሠራተኞች የሚቀነሱበት ቅደም ተከተል ላይ ግን ከግምት ውስጥ የሚገቡ ሁለት አካላት በአዲሱ አዋጅ ተጨምረዋል፡፡ እነዚህም ከመጨረሻው ረድፍ ሦስተኛ ላይ አስቀድሞ ሲቀጠር የአካል ጉዳተኛ የነበረ ሠራተኛ እንዲሁም ነፍሰጡር ሠራተኞች ወይም ከወለዱ ገና አራት ወር ብቻ የሆናቸው ሴት ሠራተኞች በአዲስ መልክ በሕጉ ላይ የተካተተ ብቻ ሳይሆን በስንብት ቅደም ተከተል በመጨረሻ ረድፍ ላይ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህም ሕጉ ለቤተሰብ የሰጠውን የተሻለ ዋጋ የሚያመላክት ነው፡፡

በሥራ ቦታ ላይ ከጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት ተጋላጭነት ረገድ ሴት ሠራተኞች ከወንዶች ይልቅ ተጠቂ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ይህን ለመከላከል በአዲሱ ሕግ አስቀድመን እንዳየነው ሥራን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥና የሥራ ስንብት ክፍያ ለመጠየቅ የጾታዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት በቂ ምክንያት ተደርጓል፡፡ ከዚህም አልፎ በዚህ ምክንያት ሠራተኛዋ ሥራዋን እንድታቋርጥ ከተገደደች የሥራ ስንብት ክፍያ ለመጠየቅ መብት የተሰጠ ሲሆን፣ የሦስት ወር ደመወዝ በካሳ መልክ አሠሪው እንዲከፍል ሕጉ ደንግጓል፡፡ ይህ ግን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስቀር አይለደም፡፡

አንዲት ሴት ሠራተኛ በቀድሞው ሕግ ታገኝ ከነበረው ድኅረ ወሊድ የ60 ቀናት ዕረፍት ላይ ማሻሻያ ተደርጎ፣ በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 88 ላይ ከወሊድ በኋላ ዕረፍቷ ለ90 ቀናት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሆኖም በሕጉ የመጀመሪያ ዕትም ላይ ከሕግ አውጪው እንዲሁም አርቃቂዎቹ ፍላጎት ውጪ በአጻጻፍና ሕትመት ላይ ተፈጠረ በተባለ ስህተት ቅድመ ወሊድ ዕረፍት “30 ተከታታይ ቀናት” እና “30 የሥራ ቀናት” በሚል በሚጋጭ መልኩ ተጽፏል፡፡ በቀጣይ ያሉ ሕትመቶች ላይ ስህተቱ የሚስተካከል መሆኑን ግምት በማድረግ፣ አስቀድሞ በነበረው ሕግም ቢሆን ቅድመ ወሊድ ዕረፍት 30 ተከታታይ ቀናት በመሆኑ፣ የጽሑፍ ግጭቱ 30 ተከታታይ ቀናት ተብሎ ታርሞ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አንዲት ሴት ጽንስ መቋረጥ (ማስወረድ) ቢገጥማት በሐኪም በሚሰጣት ፈቃድ መሠረት ከክፍያ ጋር ወይም ከተለመደው ሕመም ፈቃድ በተለየ መልኩ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይቀነስ ዕረፍት እንደምታገኝ በአዲሱ ሕግ ላይ ተደንግጓል (አንቀጽ 88(5)፡፡

በሕገ መንግሥት ጭምር የታገዘ ለሴቶች የሚደረግ ድጋፍ በአብዛኛው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶቸ ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለ ሲሆን፣ በአዲሱ አዋጅ ላይ አዋጁ በሚፈጸምበት የግል ድርጅቶች ሳይቀር እንዲተገብሩት የሚያደርግ አንቀጽ ተጨምሯል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 87(2) ወንድና ሴት ሠራተኞች በደረጃ ዕድገትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ተወዳድረው እኩል ውጤት ካመጡ ለሴቷ ቅድሚያ እንዲሰጣት ተደንግጓል፡፡  

አስቀድሞ በነበረው ሕግ የትዳር ጓደኛው የወለደች ሴት በተለምዶ ከዓመት ፈቃድ እንዲሞላ ተደርጎ ወይም ያለክፍያ ከሚሰጠው ፈቃድ ውጪ በሕጋዊነት ዕውቅና የተሰጠው ፈቃድ አልነበረውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ጥቂት ድርጅቶች በኅብረት ስምምነት ይህ ጉዳይ እንዲገባ አድርገው ፈቃዱን ሕጋዊ አድርገው ከሚሠሩበት ውጪ በሌሎች ድርጅቶች የሕግ ሽፋን አልነበረውም፡፡ ሆኖም በአዲሱ ሕግ አንቀጽ 87(2) ላይ የትዳር ጓደኛ ስትወለድ ለሠራተኛው ደመወዝ የሚከፈልበት የሦስት ተከታታይ ቀናት ፈቃድ እንዲሰጠው ሕጉ ግዴታ ጥሏል፡፡

የዓመት ፈቃድና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሥሌት

አስቀድሞ በነበረው ሕግ የዓመት ፈቃድ መነሻው 14 ቀን ሆኖ በየዓመቱ አንድ ቀን እየጨመረ ያለገደብ እየጨመረ የሚሄድ  ነበር፡፡ በአዲሱ አዋጅ የዓመት ፈቃድ መነሻው ለአንድ ዓመት አገልግሎት 16 ቀን ሆኖ እየጨመረ የሚሄደው ግን በየሁለት ዓመት አንድ የሥራ ቀን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ማሻሻያ የግል አሠሪዎችን ከክፍያ ጋር የሚሰጡት ፈቃድ ይበዛባቸዋል ከሚል መነሻ የተደረገ ማስተካከያ ነው፡፡ ይህም ሆኖ አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል የመሸጋገሪያ ድንጋጌ አንቀጽ 190 ውስጥ ያልተካተተ በመሆኑ፣ አስቀድመው ሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞችን የፈቃድ ስሌት አስመልክቶ ግራ መጋባት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በ2012 የአምስተኛ ዓመቱን ፈቃድ የሚወስድ ሠራተኛ አዲሱ ሕግ ተግባራዊ ስለሆነ አሠሪው ፈቃድ የምሰጠው በየሁለት ዓመት ስለሆነ በዚህ ዓመት ፈቃድ አትወጣም የማለት መብት አለውን፣ ፈቃዱንስ ሲሰጥ የስሌቱ መነሻ የደረሰበት የተጠራቀመ የፈቃድ ዓመት ነው ወይስ ወደኋላ ሄዶ የመጀመሪያውን ዓመት 16 የሥራ ቀን ዕረፍት በማለት ቆጥሮ በማስላት ነው ፈቃድ የሚሰጠው የሚለው ግልጽነት የሌለው ነው፡፡

በተሻረው አዋጅና በአዲሱ አዋጅ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ስሌት ንፅፅር

አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

ማጠቃለያ

አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከዚህ ቀደም ከነበሩት አሠሪና ሠራተኛ አዋጆች በተሻለ ለቤተሰብ ግንኙነትና ለሴቶች ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ኃላፊነቶች የተሻለ እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ የወሊድ ፈቃድ በድምሩ አራት ወር ከክፍያ ጋር እንዲሆን ሕጉ የሚያስገድድ መሆኑ፣ እንደአገርና ማኅበረሰብ ሲታይ ለውጥ መደረጉ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ አዋጁ አወዛጋቢና አከራካሪ ለሆኑ ጉዳዮች ከሥራ ማርፈድና መቅረት ግልጽ የሆነ መፍተሔ መስጠቱ ከመልካም ጎኖቹ መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

አዋጁ ከላይ የተገለጹት መልካም ጎኖች ቢኖሩትም በሕግ ማርቀቅና የሕግ ጥራት ጉዳይ ግን በድጋሚ መታየት ያለበት መሆኑን ለማመልከት በአንቀጽ 2(9) ላይ የታየው የአማርኛና እንግሊዝኛ ቅጂ የትርጉም አለመጣጣም እንዲሁም በአንቀጽ 68 እና አንቀጽ 88 የታዩት ተቃርኖዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ጭማሪ በተደረገባቸው ሰዓትና ቀናት ላይ በሰዓት 0.25 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ በተለይም የማይቋረጥ የሥራ ባህሪ ያላቸው ሆስፒታሎች፣ ተቋማትና አምራች ፋብሪካዎች ላይ በግዴታ ደመወዝ የመጨመር ዓይነት ውጤት የሚኖረው መሆኑ ከግምት ውስጥ የገባ አይመስልም፡፡ ይህ ሁኔታ የፍጆታ ዕቃዎችንና የአንዳንድ አገልግሎቶችን ዋጋ ሊያንር የሚችል መሆኑ በአግባቡ የታየ ስለመሆኑ እንኳን ጠቋሚ ነገር የለም፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በእ.ኤ.አ 2014 ባወጣው መረጃና ኤጀንሲው ባስቀመጠው ትርጉም መሠረት አንድ ሰው ሥራ አጥ (ያልተቀጠረ) የሚባለው በማምረት ተግባር ላይ ያልተሰማራ ማለትም ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ከሌለው፣ በራሱ ራሱን የቀጠረ ካልሆነ ወይም በቤተሰብ ሥራ በቅጥር ያልተሰማራ፣ የሥራ ዕድል ቢያገኝ በሚቀጥለው ወር ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ የሆነ ማንኛውም ሰው ያልተቀጠረ በተለምዶ ሥራ አጥ ከሚባለው ምድብ ውስጥ ይካተታል፡፡ ይህንን ትርጉም ከግምት ውስጥ በማስገባት የተባበሩት መንግሥታት የስታትስቲክስ ክፍል ባወጣው መረጃ መሠረት በእ.ኤ.አ 2014 ከአጠቃላዩ ሕዝብ 89.1 በመቶ ወንዶችና 76.9 በመቶ ሴቶች በዓመቱ ሥራ ነበራቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያለመቀጠር (ሥራ አጥነት) ሚዛን የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) ባወጣው መረጃ መሠረት ከአጠቃላዩ ሕዝብ አንፃር ቁጥሩ አሳሳቢ ነው፡፡ ችግሩ እጅግ የሚከፋው ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ላይ በሚኖሩ ሴቶችና ወጣቶች ላይ ነው፡፡ በዚሁ ዓመት 24 በመቶ የሚሆኑት የከተማው ቤተሰቦች ከቤተሰባቸው ቢያንስ አንድ ሰው ሥራ አጥ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ የሌሎች ከተሞችም የሥራ አጥነት አኃዝም ተቀራራቢ ነው፡፡ ከምንም በላይ እየጨመረ የመጣውንና ሕጉ በወጣበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር የሆነውን የሥራ አጥነት በፖሊስና አቅጣጫ ደረጃ እንኳን አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምንም ነገር ሳይል ማለፉ ሊታረም የሚገባውና ሕጉ ከግምት ውስጥ ሊያስገባው የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ የዘለለና የወቅቱን ጥያቄ አልመለሰም የሚያስብለው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...