Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹መደመር›› ምንድነው?

‹‹መደመር›› ምንድነው?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

‹‹መደመር›› በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዓሊ (ዶ/ር) ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በርካታ ሕዝብ በክብር እንግድነት በተጋበዘበትና በተገኘበት በሚሊኒየም አዳራሽ ተመርቋል፡፡ መጽሐፉ በ284 ገጾች የሰፈሩ አሥራ ስድስ ምዕራፎች አሉት፡፡ የመጽሐፍ ምረቃውን በዓል በሚመለከት የመንግሥት የፕሬስ ውጤት የሆነው አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በምረቃው ማግሥት በርዕሰ አንቀጹ፣ ‹‹የለውጥ አመራሩ ፈር ቀዳጅና የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድም እስካሁን የተከማቹ ችግሮችን ለመቅረፍና ለመጭው ትውልድ የተሻለች አገር ለማውረስ የሚያስችለውን መደመር የተባለ ፍልስፍና አዘል መጽሐፍ በትናንትናው ዕለት ለአገርና ለሕዝብ አበርክተዋል፤›› ብሏል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይስማሙበት አይስማሙበትም ‹‹የመደመር ዕሳቤ መነሻ ዓላማ ለአገር በቀል ችግር አገር በቀል መፍትሔ እንዲሆን ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መደመር የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንደ ማለት ነው፤›› በማለት ፍልስፍናውን በፍልስፍና ይተረጉመዋል፡፡ አንድ መጽሔትም ‹‹መደመር ወይስ መደርመስ?›› በሚል አስተያየት ሰጥቶበታል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ትኩረት የሚደረገው ‹‹መደመር›› በሚለው ዕሳቤ ላይ ብቻ ሲሆን፣ በዚህ ዕሳቤ ዙርያ ዳሰሳ ለማድረግ የተፈለገበት መሠረታዊ ምክንያትም  ‹‹መደመር ምንድነው?›› የሚለውን ጥያቄ በመጽሐፉ ውስጥ በቀጥታ ባለመመለሱ  ነው፡፡ አለመመለሱ ለአንዳንድ ሰዎች ፋይዳ የሌለው ሊመስል ይችላል፡፡ ለጭፍን ደጋፊ ደግሞ ‹‹ይበል! እንዴት ያለ መጽሐፍ ታተመ እባካችሁ?›› ካልተባለ ከምቀኝነት በመነሳት የሚቀርብ ሊመስል ይችላል፡፡ ለለዘብተኛ ደግሞ ምንም አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ዕሳቤ አገርን የሚያለማ ወይም የሚያጠፋ ሊሆን ስለሚችል፣ ግልጽልጽ ብሎ መቅረብ ስለሚገባው መታወቅ አለበትና በዚህ አስተያየት ሥር መደመር ‹‹በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት›› ማለት ነው? ‹‹መደመር›› ማለት በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ማለት ነው? ‹‹መደመር›› ማለት ቅንጅት ወይም መቀናጀት ማለት ነው? ‹‹መደመር›› ምናልባት መቀናጀት ማለትም ጥምር፣ ጥምርነት፣ መጣመር ማለት ይሆን? ‹‹መደመር›› አብሮ መሥራት ማለትም ሲነርጂ (Synergy) ማለት ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በማጠቃለያው ዝምብሎ መባዘን እንዳይሆን ‹‹የባህር ፈረስ ታሪክ›› በምሳሌነት ቀርቧል፡፡

‹‹መደመር›› ምንድነው?

እርግጥ ነው በምዕራፍ ሦስት በተለይም ‹‹የመደመር ብያኔ›› ከሚለው ርዕስ ሥር፣ ‹‹መደመር የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን ጨምሮ ሁሉንም ግላዊና ማኅበረሰባዊ የሕይወት ዘይቤ የሚነካ ዕሳቤ ነው፤›› (ገጽ 35) ብሎ፣ የዕሳቤው ምንጭ አገራዊ ተጨባጭና ዓውዳዊ ሁኔታዎች የሚመነጭ እንደሆነ በገጽ 36 አመልክቷል፡፡ በተጠቀሰው ገጽ በተለይም ‹‹መደመር ማለት›› የሚል ርዕስ ይሰጥና ምን ማለት እንደሆነ ሳያብራራ፣ ‹‹የመደመር ዋነኛ ዓላማ አገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎች ጠብቆ ማስፋት፣ የተሠሩት ስህተቶችን ማረም፣ እንዲሁም የመፃኢውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት ነው፡፡ በመሆኑም መደመር ከችግር ትንተና አንፃር አገር በቀል ነው፡፡ ከመፍትሔ ፍለጋ አንፃር ደግሞ ከአገር ውስጥም፣ ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው፤›› በማለት ንዑስ ርዕሱን ይደመድማል፡፡ ታዲያ ይህ የመደመር ዕሳቤ ትርጉም ይሆናል?

ምንም እንኳን በተለመደው መንገድ የመደመር ትርጉም በምዕራፍ አንድ ማለትም ለመደመር ዕሳቤ መነሻ ሐሳቦችው ከሚለው ቀድሞ መጀመር ቢኖርበትም፣ ከምዕራፍ ሁለት ማለትም ‹‹የሁለት ርዕዮቶች ተቃርኖ›› (ሊበራሊዝምና ሶሻሊዝም) ከሚለው ምዕራፍ ተከታይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሠረቱ በሥነ ጽሑፍ ሥራ አንድን ቀዳሚ ሐሳብ አግባብነት ካለው ተከታይ፣ ተከታይን ሐሳብ ደግሞ ቀዳሚ ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ለአገር ይጠቅማል ተብሎ የተጻፈ፣ ምናልባትም ለዓለም የሚጠቅም ዕሳቤ፣ በትርጉም ባለመጀመሩ ብዥታን የሚፈጥር ጉዳይ ይሆናል፡፡ የመጽሑፉ ጠቅላላ ትኩረትም በትርጉሙና ከላይ በቀረቡት አምስት ዓረፍተ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹መደመር›› ምንድነው?

መደመር ‹‹በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት›› ማለት ነው?

በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት የሚባለው ባለፉት 29 ዓመታት ስንሰማው እንደነበረውና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚመሠርቱት አንድ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የዚህም ፍልስፍና መሠረት ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት ሺሕ ዓመታት ስታራምደው የነበረው አሀዳዊነት አልጠቀማትምና እስቲ ብሔር ብሔረሰቦች እስከ መገንጠል ድረስ መብታቸው ተጠብቆላቸው በፌዴራል ሥርዓት ተሳስረው ይኑሩ፤›› ከሚል ፍልስፍና ይነሳል፡፡ ትክክል ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ቀስ ብለን የምናየው ይሆናል፡፡

የዚህ ጽሑፍ በተለይም የዚህ ንዑስ ርዕስ መሠረታዊ ዓላማ ‹‹የመደመር››ን ትርጉም ‹‹በልዩነት ከተመሠረተ አንድነት›› መፈለግ በመሆኑ ‹‹ነገርን ከሥሩ፣ ውኃውን ከጥሩ›› እንዲሉ ከዚህ አኳያ እንመልከተው፡፡ የዚህ ሐሳብ አመንጭ ነው የሚባለውና በ1915 (1907) የኖቤል ሽልማት ተጋሪ የሆነው ኧርኔስቶ ቴዎድሮ ሞኔታ (1933 1918) በሚላን የተወለደው ኢጣሊያዊ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ሰው በጁሴፔ ጋሪባልዲ ዘመን አገሩን ከኦስትሪያ የበላይነት ለማላቀቅ የታገለ፣ በኋላም ‹‹ኢል ስኮሎ›› የተሰኘ ጋዜጣ አዘጋጅ (አርታኢ) ሆኖ የሠራ ሲሆን፣ ‹‹ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለሰላም›› የተሰኘ ማኅበር አቋቁሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የእርሱም መፈክር ‹‹በልዩነት ውስጥ አንድነት›› ወይም ‹‹motto In Varietate Concordia/In Varietate Unitas›› የሚል ነበር፡፡ ታዲያ ኧርኔስቶ ቴዎድሮ ሞኔታ በዚህ ማኅበር ባደረገው ተሳትፎ ለኖቤል ሽልማት ይብቃ እንጂ፣ ኢጣሊያ ቱርክን ስትወጋና ኢምፔሪያሊዝም በዓለም የበላይነቱን ለማረጋገጥ ያደረገውን ጥረት ማክሸፏን አሞግሷል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ፣ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም የበላይነቱን በመላው ዓለም ለማስፈን በተነሳበት ጊዜ፣ አገሩ ኢጣሊያ ወደ ሊቢያና ኢትዮጵያ በወዳጅነት ገብታ ከዚህ አደጋ ለመታደግና አሠልጥና ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለማስቻል…›› በሚል ሰበብ የወሰደችውን ዕርምጃ አሞግሷል፡፡ በእርሱ እምነት መሠረት የኢጣሊያ መንግሥት የጦር ኃይሉን  በራሱ ‹‹መልካም ፈቃድና ቅን አሳቢነት›› ወደ ኢትዮጵያና ሊቢያ ያስገባው ለሁለቱ አገሮች ሕዝብ ጥቅም ሲል መሆኑ ነው፡፡

ሆነም ቀረ ከኧርኔስቶ ቴዎድሮ ሞኔታ በኋላም ‹‹በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት›› በሚመለከት በዓለማችን በሰፊው ተናፍሷል፡፡ መሠረታዊ ዓላማውም ያለ ልዩነት አንድነትን ከሚያራምድ አስተሳሰብ በተቃራኒ የተለያዩ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ሃይማኖቶችን፣ ዕሳቤዎችን፣ አመለካከቶችን፣ ሥነ ባህሪያዊ ልዩነቶችን ልዩነት ተቀብሎ በአንድ ላይ መጓዝ ነው፡፡

ነገሩን ትንሽ ጠጋ አድርገን ስንመለከተው የተለያየ ፍልስፍናን፣ ፖለቲካን፣ ሃይማኖትን፣ አስማምቶ፣ አስተባብሮ፣ አቀናጅቶ ሕዝብን ከመምራት ዕሳቤም ጋር አብሮ ሊሄድ ይችላል፡፡ በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት በሚያራምዱ ሰዎች ግንዛቤ መሠረት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተለያየን ብንሆንም ልዩነቶቻችንን አቻችለን፣ አዋደን፣ በሚያግባቡን ጉዳዩች ላይ ተግባብተን በፖለቲካው አስተባባሪነት ማለትም በፌደራሊዝምና በኅብረ ብሔርተኝነት አንድ መሆን እንችላለን፣ ወይም ለጋራ ዓላማ በአንድነት መሥራት እንችላለን፣ ወይም እንኖራለን እንደ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በሃይማኖት ረገድ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣ ዋቄ ፈታው፣ በሃኢው፣ ኦሪታዊው የተለያየ ቢሆንም አንድ በሚያደርገው ላይ ተስማምቶና ተባብሮ፣ የጋራ አመለካከት ፈጥሮና በሚያስማሙት ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚወሰንበት ዕሳቤ ነው፡፡ በዚህ ዕሳቤ መሠረት የአገር ውስጡን ልዩነት ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ምክንያት ከሚፈጠር ድንበር ተሻጋሪ ትስስር ጋርም  አብሮ ሊሄድ ይችላል፡፡

ሆኖም በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ላለፉት 29 ዓመታት በአገራችን ሲነገርና በተለያዩ መንገዶች ሲተገበር የነበረ ቢሆንም፣ ተፈጥሯዊ ወይም ተፈጥሯዊ ያልሆነ መሆኑን ወይም የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት (ገጽ 234) ‹‹ተናክኦታዊ ቁስ አካልነት›› (Mechanical Materialism) የሚለው ዓይነት እንደሆነ በፈላስፎቹ አልተገለጸልንም፣ አልተብራራልንም፡፡ በመጽሐፉ ላይ ፈላስፎች በመግቢያው ላይ ወይም በመቅድሙ ላይ መግለጫ ቢሰጡበት የተሻለ ይሆን ነበር? በጣም የሚገርመው ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን ዕሳቤውን በትክክል ይረዱትም አይረዱትም ሲያራምዱት መቆየታቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሚበጀን ‹‹በአንድነት ላይ የተመሠረተ ዕሳቤ ማራመድ ነው›› የሚል እንኳን ቢያዩ፣ ‹‹በልዩነት ላይ አንድነት›› የሚል ይመስላቸዋል፡፡  ነገር ግን ሁለቱ ዕሳቤዎች አንድ ሳይሆኑ ተቃራኒ ናቸው፡፡

ዳሩ ግን ‹‹መደመር›› በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ማለት ከሆነ ስሙን ለምን መለወጥ አስፈለገው? አመለካከቱኮ በብዙ አገሮች ይራመዳል፡፡ ገዥዎች የተለያዩ ባህሎችና እምነቶች አስተባብረው ለመግዛት ወይም ለማሠራት የሚጠቀሙበት ዕሳቤ ነው፡፡ ለምሳሌ ህንድ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተባብረው በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ ተጠቅማበታለች፡፡ ስለዚህ ‹‹መደመር›› ማለት በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ማለት ነው? ካልሆነ ምንድነው?

‹‹መደመር›› ማለት በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ማለት ነው?

በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ነገሮች የተለያዩ ቢሆኑም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸው ከሚል ዕሳቤ የሚመነጭና ‹‹በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት›› ከሚለው በተቃራኒ የሚቆም ዕሳቤ ነው፡፡ ይህ ዕሳቤ ተፈጥሯዊ ባህርይን የሚከተል ሲሆን፣ ‹‹ዓለም በመፈጠሯ በዓለም ላይ የሚገኙት ክስተቶች በአንድነት ወይም ቀስ በቀስ ተፈጠሩ እንጂ፣ ክስተቶቹ ተሰባስበው አንድነቱን አልመሠረቱትም፤›› ከሚል  ይነሳል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዛፍ ሥር ግንድ፣ ቅርንጫፍ፣ ቅጠል፣ አበባ፣ ፍሬ፣ ወዘተ የኖረው በአንድነቱ የተፈጠረ እንጂ የተጠቀሱት ነገሮች ተሰባስበው ዛፉን አልፈጠሩትም እንደ ማለት ነው፡፡ ይህንን በሰው ምሳሌነት ስንወስደውም እጅ፣ እግር ዓይን ወዘተ ከአንድ ሰውነት መገኘት ጋር አብረው ተገኙ እንጂ አካላት ተሰባስበው ሰውን አልፈጠሩትም ከሚል ይነሳል፡፡ በማኅበረሰብ አኳያም በኢትዮጵያዊነት ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን፣ ባህሎችን፣ አመለካከቶችን፣ ሃይማኖቶችን እናገኛለን እንጂ የተገለጡት ተሰባስበው አልፈጠሩትም ከሚልም ይነሳል፡፡ በዚህ ዕሳቤ መሠረት ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ መደብ፣ ወዘተ በተፈጥሮ ሕግ መሠረት ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል፣ ኢትዮጵያዊነት ግን አዲስ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ እየተቀበለ ይቀጥላል፡፡ የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የመደብ፣ ወዘተ ልዩነትን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን መሠረት አድርጎ ይሠራል፡፡ በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሲኖር ከሴል ጀምሮ ያለው አካል ማለትም ልብ፣ ጉበት፣ ሳምባ፣ ወዘተ ሁሉም ራሳቸውን ጨምረው ለአንድ ሰውነት እንደሚያገለግሉት ሁሉ ፖለቲካውም ዘር፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ያገለግላል፡፡

በመሆኑም በልዩነት ላይ የተመሠረተን አንድነት ገዥ መደቦች ያለውን ልዩነት ለራሳቸው እንደሚመቻቸውና እንደሚበጃቸው አድርገው ሊጠቀሙበት ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ፋይዳ የለውም፡፡ በታኝ ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም አያስገኝም በማለት በአንድነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ያጎላሉ፡፡ በእነዚህ ሰዎች እምነት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ስንመለከተው የምክር ቤት መቀመጫ የተያዘው ብሔር ብሔረሰቡ ባለው የሕዝብ ቁጥር መሠረት ነው፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ ውሳኔ ሲወስን ደግ ከሆነ ሐሳብን በሚገባ ካንሸራሸረ በኋላ በአብዛኛው ድምፅ ይወስናል፡፡ ደግ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ‹‹ህዳጣን አርፈሽ ተቀመጭ›› ይላል፡፡ በዚህ ሥርዓት ‹‹ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች›› እንዲሉ በመረጠው ምክር ቤት ላይ እንደፈለገ መናገር፣ መቆጣት፣ ሌላም ማለት ይችላል፡፡ በሌላ የተለሳለሰ አነጋገር በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት የአምባገነንነትን በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ‹‹የሚሻለው በአንድነት ላይ የተመሠረተው ልዩነት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ ‹‹መደመር›› በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነት ማለት ነው? ዶ/ር ዓብይስ በልዩነት ላይ የተመሠረተ ከሚያቀነቅነው የፖለቲካ ድርጅት ወጥተው ይህን አመለካከት ሊያራምዱ ይችላሉ? ካልሆነ ምንድነው?

‹‹መደመር›› ቅንጅት ወይም መቀናጀት ማለት ነው?

በአገራችን አብኛውን ጊዜ ‹‹ቀንጃ›› የሚለው ቃል የአንድ ጥንድ አካል የሆነ ብቻውን የማይቆም፣ ነገር ግን ካልተቀናጀ በስተቀር የተፈለገውን ያህል የማይሠራ፣ የማያመርት፣ የማያገለግል ከሚል ዕሳቤ ነው፡፡ ‹‹አንድ ሰው አስቦ፣ አንድ በሬ ስቦ›› የሚባለው አነጋገርም ከዚህ ጋር ይያዛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 29 ዓመታት ‹‹ቅንጅታዊነት›› በኋላ ላይ በራሱ ላይ በጠመጠመው ገመድ ተጠልፎ አይወድቁ ውድቀት ወደቀ እንጂ፣ ኢሕአዴግን የሚያህል ተራራ ያንቀጠቀጠ የፖለቲካ ድርጅት ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ‹‹መደመር››ን በራሱ ፍላጎትና ጊዜ የፈረሰውን ቅንጅት ለማለት ባይደፍርም፣ የመደመር ዕሳቤን ትርጉም ለማግኘት ግን ከቅንጅት ጋር የተያያዙ አቻ ቃላትን ለመፈለግ ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ትርጉም ዕሳቤ ቅንጅትን ከ “Cohesion” ብቻ ሳይሆን (Coalition, Synergism፣ Organizational Structure, Team and Team work) ከሚለው ዕሳቤ በመነሳትም ለማየት ጥረት ያደርጋል፡፡ በቅድሚያ “Cohesion” ከሚለው ትርጉም እንመልከተው፡፡

(ይህም ሆኖ፣ የ‹‹መደመር››ን ትርጉም ለመፈለግ በሚደረገው ዳሰሳ በዚህ በያዝነው ንዑስ ርዕስ ውስጥ ከቀረቡት ዕሳቤዎች ውስጥ ቅንጅት ሲባል የቀድሞው ቅንጅት ወይም ‹‹ቲም ለማ›› በመደመር ፍልስፍና ላይ አስተዋጽኦ አበርክቶ ይሆን እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሚያውቀው ከቶ የለምና አንባቢያን ወደዚህ እንዳያዘነብሉብኝ እጠይቃለሁ፡፡)

“Cohesion” ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ወይም የሁለቱ ጥምር ሊሆን ሲችል የተለያዩ፣ የተፈረካከሱ፣ የተበታተኑ፣ ማኅበረሰቦችንና ፖለቲካዊ ድርጅቶችን በሚያስተሳስራቸው አመለካከት ላይ በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት አስተባብሮ፣ አቀናጅቶ በሕግ መምራት ነው፡፡ የማቀናጀት ሥራ ሲከናወን የሚከፋፍለውን፣ ለአመፅ የሚያነሳሳውንና የሚያጋጨውን ሐሳብ አቀዝቅዞ ‹‹አንተም ይህን ተው፣ እኔም ይህን ልተው፣ እርሱም ያን ይተው›› ብሎ ጠንካራን ከደካማ በሬ አቀናጅቶ እንደሚታረሰው ሁሉ፣ የተለያየ አቅም ያላቸውን ለጋራ ዓላማና ግብ አሰማርቶ መምራት ነው፡፡ 

በዚህ ሒደት የተለያዩ አገሮች በቀጥታም ሆነ ደጋፊ ሆነው በመቅረብ፣ የራሳቸውን ዓላማ ሊያራምዱበት ማለት ‹‹ከረዳኸኝ እረዳሃለሁ›› ብለው ከበስተጀርባ ሊቆሙና ግልጽም ግልጽ ያልሆነ ድጋፍም ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በዓረብ አገሮች በተለይም በሊቢያ፣ በቱኒዚያ፣ በግብፅ፣ በሶሪያ የነበረውን የአንድ ፓርቲ አምባገነን አመራርን እንዲወገድና የቅንጅት መንግሥት እንዲቋቋም ምዕራባውያን አገሮች ተቃዋሚ ኃይሎችን በጦር መሣሪያ በመደገፍ ሳይወሰኑ፣ ራሳቸው በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን መንግሥታዊ ግልበጣ ዓይነት አካሂደዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የራሳቸውን ዓላማ የሚያራምዱላቸው አሻንጉሊት መንግሥታት ለማቋቋም ከበስተጀርባ ሆነው ድጋፋቸውን እየሰጧቸው ነው፡፡ ‹‹የዴሞክራሲ ምርጫ እንዲካሄድ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ወደ ምክር ቤት እንዲመጣ፣ ወዘተ የገንዘብና የዕውቀት ድጋፍ እያደረግን ነው፤›› ብለው ሲመሰክሩም ይሰማል፡፡ 

በመሠረቱ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ብቻ ሳይሆን በልፅገው ዴሞክራሲ የሚያራምዱ አገሮች ራሳቸውን ችለው ፖለቲካውን ለመምራት አቅም ሲያንሳቸው፣ ከእነሱ ደከም ከሚለው ጋር ተቀናጅተው ‹‹የጥምር መንግሥት›› አቋቁመው መንግሥትና እንደሚመሩና ሰላም እንደሚያሰፍኑ የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም ብዙ ጊዜ ከኢጣሊያ ምክር ቤት እንደሚታየው ዛሬ ተቀናጅቶ በማግሥቱ ቅንጅቱ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ‹‹ቅንጅት›› ሲባል በነበረው የአገራችን የፖለቲካ ድርጅት የተስተዋለውም ይኸው ነው፡፡ በሌላ በኩልም አቅምን እስኪያጎለብቱ ተቀናጅተው ከሠሩ በኋላ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ደካሞቹን አንሳፎ የሚተውበት የፖለቲካ መሣሪያ ሊሆን ይችላል፡፡

ነገሩ የበለጠ ግልጽ ይሆንልን ዘንድ ኢሕአዴግ የመሠረተውን የሽግግር መንግሥትን እንደ ተጨባጭ ምሳሌ እንመልከት፡፡ ኢሕአዴግ የተለያዩ አመለካከቶች የነበራቸውን ድርጅቶች ጠርቶ፣ እንደ ፍላጎቱ አልሆን ብሎ ሲገኝም የአገር ሽማግሌዎችን አሰባስቦና የፖለቲካ ድርጅት ካባ አልብሶ የሽግግር መንግሥት ካቋቋመ በኋላ በመጀመሪያ ቀንደኛ ተቀናቃኞቹን፣ ቀጥሎ የበሰሉ የአገር ሽማግሌዎችንና ምሁራንን፣ ቀጥሎ በራሱ ይሁንታ የተቋቋሙ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶችን በማዳከምና በኋላም በጠላትነት በመፈረጅ፣ የራሱን ጠንካራ ክንድ እንደ ዘረጋው ማለት ነው፡፡ በዚህ ሒደት የምናገኘው መሠረታዊ ቁምነገር፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በመጀመሪያ የቅንጅት መንግሥት ካቋቋመ በኋላ አገርን ወደ ብልፅግና የመምራት ፍላጎቱን የሚንፀባረቅበት መሆኑ ነው፡፡ ይህ እውነታ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከመግቢያው ጀምሮ የሚያንፀባርቀው ለመሆኑ አሌ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹‹መደመር›› ኮሂዥን ነው? ካልሆነ ምንድነው? ምናልባት ኮኦሊሽን ይሆን?

‹‹መደመር›› ምናልባት መጣመር ማለት ይሆን?

ጥምር ወይም ጥምረት የሚለው ቃል ለፖለቲካዊ አገልግሎት ሲውል ከመንግሥት ምሥረታ ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ (አግባብ) አለው፡፡ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ይህንን ዕሳቤ (ከገጽ 465-466) ሲገልጽ፣ ‹‹በቡርዧ ዴሞክራሲ ሥርዓት የአንድን መንግሥት አስተዳደር ሥልጣን ይዞ ለማቆየት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች የሚፈጥሩት የትብብር መንግሥት ነው፡፡

በጥምር መንግሥት የተለያየ የፖለቲካ መስመር ያላቸው ድርጅቶች ተባብረው፣ የአንዱን የበላይነት ቀንሰው አብረው የሚሠሩበት የፖለቲካ ሥልት ሲሆን፣ ይህም የጥምር መንግሥት ዕውን የሚሆነው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ አብዛኛውን መቀመጫ ሳይዝ ሲቀር ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የፖለቲካ ችግር ወይም ውጥረት ሲፈጠርም ጥምር መንግሥት የማቋቋም አስፈላጊነት ጎልቶ ሊመጣ ይችላል፡፡ የጥምረት መንግሥት በብዙ የአውሮፓና አገሮች የሚተገበር ሲሆን በአፍሪካ ኬንያ፣ በእስያ ጃፓን፣ በሰሜን አሜሪካ ካናዳና በአውስትራሊያ በሥራ የሚውል ዕሳቤ ነው፡፡ በስዊዘርላንድ እ.ኤ.አ. ከ1959 እስከ 2008 ድረስ አራት ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች በጥምረት እንደመሩ ሲታወቅ፣ ታላቋ ብሪታንያም ብዙ ጊዜ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲና ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በጥምረት ሲመሩ ይስተዋላል፡፡ ከአውሮፓ አገሮች ውስጥ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው ሁሉ የታላቋ ብሪታንያን የጥምረት ታሪክ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት እስከ ዛሬ እጅግ በአጭሩ ብንመለከት፣ እንደሚከተለው መልካም ምሳሌ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በመሠረቱ በዚች አገር የጥምረት መንግሥት (አንዳንድ ጊዜም ብሔራዊ መንግሥት ተብሎ ይጠራል) የሚቋቋመው ብሔራዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ቀውሶች አንዱ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1914 እስከ 1918፣ ቀጥሎም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1931 እስከ 1940 በነበረው ጊዜ ነው፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች ጥምረት በመፍጠር አገራቸውን ከገባችበት የቀውስ ማጥ በጋራ አውጥተዋል፡፡

በጀርመን ውስጥ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ ግዙፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ያፈጠጠ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር ሁለቱ አይጣመሩም፡፡ በምትኩም አንድ ጠንካራ ድርጅት ከአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት እንጂ፡፡ ለምሳሌ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ሔልሙት ኮል ፍሪ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከተባለ የፖለቲካ ድርጅት ጋር በመሆን እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 2005 ባለው ጊዜ መርተዋል፡፡ ነገር ግን የክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን መሪዋ አንጀላ ማርከስ ከፍሪ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጋር በመሆን ለመምራት የሚያስችል ድምፅ ስላላገኙ፣ ከሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ጋር በመሆን እየመሩ ነው፡፡ ስለዚህም ጀርመን የምትመራው በሁለቱ ኃያላን የፖለቲካ ድርጅቶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግ የገጠመውን የፖለቲካ ቀውስን ለመቋቋም በመደመር ፍስፍና የጥምረት መንግሥት፣ ወይም የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ማቋቋም እንደ አማራጭ ሊጠቀም ይችላል፡፡ ስለዚህ ‹‹መደመር›› ማለት ጥምረት ማለት ነው? ካልሆነ ምንድነው?

‹‹መደመር›› አብሮ መሥራት ማለትም ሲነርጂ (Synergy) ማለት ነው?

‹‹መደመር›› ማለት ሲነርጂ ከሆነ፣ ለብያኔ ይረዳናልና እንፈትሸው፡፡ በእርግጥም በምዕራፍ ሦስት ‹‹የመደመር ብያኔ›› በሚለው ርዕስ እንደሠፈረው ሁሉ፣ መደመር ‹‹ልዩነትን ተሻግሮ…›› በጋራ ግብ ላይ የተመሠረተ ነው (ገጽ 43 እስከ 47፡3.3 የመደመር መሠረታውያን)፡፡ ዳሩ ግን መደመር በጋራ መሥራት (ሲነርጂ) ከሆነ ልዩነት እንዳለ ሆኖ ማለትም ልዩነትን ሳይሻገር ለጋራ ዓላማና ግብ አብሮ መሥራት ማለት አይሆንም? ከሆነ ደግሞ ‹‹በልዩነት ላይ የተመሠረተ›› ከሚሉ ከኢሕአዴግ መሰል የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያራምዱት በምን ይለያል?

እርግጥ ነው መደመር በጋራ መሥራት ከሆነ ‹‹ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው…›› ከሚል ዕሳቤ ጋር አብሮ ሊሄድ ይችላል፡፡ ይህም ማለት ሁለት አቅማቸው የተለያዩ ሰዎች አንድ ከባድ ድንጋይ በአንድ ላይ ቢያንከባልሉ ሁለቱ የሚያፈሱት ጉልበት እኩል አይሆንም፡፡ ነገር ግን የኃይሉ ብቻውን የማያንከባልለውን በደካማው ድጋፍ ለማንከባለል ጠቅሟልና በጋራ መሥራት ሊባል ይችላል፡፡ በጋራ መሥራት ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ቁጥር ያላቸው በአንድ ላይ ተቀምጠው መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያየ ቦታና መስክ ሆነውም ለጋራ ዓላማ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ በውጤቱም በጋራ የሚያከናውኑት ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ጥቂት ክህሎት ያላቸው ብዙ ክህሎት ከሌላቸው የበለጠ ተግባር ሊያከባውኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት መደመር (ሲነርጂ) ከሆነ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከ2002 ዓ.ም.  ምርጫ በፊት በሲነርጂ ዕሳቤ ከደካሞች ጋር ለመሥራት ሞክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ሁሉንም አራግፎ ምክር ቤቱን ብቻ ለብቻ ተቆጣጠረው፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዕሳቤ መሠረት ደካሞችን አሰባስቦ መጓዝ ማለት ጊዜንና ሀብት ማባከን በመሆኑ፣ እነሱ ዕድገታቸውን እስኪጨርሱና ለውድድር እስኪበቁ ድረስ ኢሕአዴግ ሐሳብ አመንጪ፣ ኢሕአዴግ ዕቅድ አውጪ፣ ኢሕአዴግ አስፈጻሚ፣ ወዘተ አማራጭ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ዳሩ ግን ሕይወት የራሷ መንገድ አላትና የዚህ ዕሳቤ መሐንዲስ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በድንገት ስላረፉ ለብቻ መሥራት የሚችል ሰው ማስቀመጥ ሳይችል ቀረና በአራት ዓመት ውስጥ ግዙፉ የኢሕአዴግ ድርጅት ለውድቀት ተዳረገ፡፡

በዚህ ጽሑፍ አመለካከት ከፖለቲካው የሚመነጩ ጉዳዮችን ‹‹ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው›› ያለውን መርህ ተከትሎ በጋራ መሥራት አስፈላጊ የሚሆንበት ማኅበራዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮሚያዊ፣ ወዘተ ተግባራትን ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሲነርጂን (በጋራ መሥራት) በሚመለከት በጣም ሰፊ ተዛማጅ ሥነ ጽሑፍ ስላለ ዝርዝሩን ለአንባቢያን ለመተው ወደድኩ፡፡ እናም መደመር ሲነርጂ ማለት ነው? ካልሆነ ምንድነው? ምናልባት ‹‹መደመር›› ማለት በቡድን (በቲም) ማለትም በኮሚቴ ተቀናጅቶና ተጣምሮ መሥራት ማለት ይሆን?

ማጠቃለያ

ውድ አንባቢያን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመደመር ዕሳቤ ከቃሉ በመነሳት ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ ይህም የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ‹‹መደመር›› የሚለው ቃል በግልጽ ባለመተርጎሙ ምክንያት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፉ ፍልስፍናውን ከመተርጎም መነሳት ነበረበት፡፡ የፍልስፍና ሊቃውንቶቻችንም መቅድም ወይም ከዚህ ጋር የሚሄድ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባ ነበር፡፡ እንደተባለው አንድ ሚሊዮን ኮፒ ታትሞ ተሰራጭቶ እንደሆነ ይህን መጽሐፍ ሕዝብ አንብቦ አይረዳውም ይሆን የሚል ሥጋት ጸሐፊው አለው፡፡ ወደፊት የሚታተም ከሆነ በጉዳዩ ላይ ቢታሰብበት መልካም ነው ብሎም ያስባል፡፡ ካለበለዚያ የባህር ፈረስ ታሪክ ይከተላል፡፡

 

የባህር ፈረስ ታሪክ

በድሮ ጊዜ አንድ ጭንቅላቱ ፈረስ የመሰለ በባህር ውስጥ የሚገኝ ዓሳ፣ ከነበሩት ስምንት የወርቅ እንክብሎች ሰባቱን ያዘና ዕድሉን ለመሞከር ጉዞውን ቀጠለ:: በመንገዱም ላይ ‹‹ኢል›› የተባለ እባብ መሰል ዓሳ አገኘውና ‹‹ታዲያስ ጓደኛዬ በእንዲህ ያለ ችኮላ የት እየሄድክ ነው?›› በማለት ጠየቀው፡፡

የባህር ፈረስም ‹‹ዕድል የምትሰጠኝን መልካም አጋጣሚ ለመፈለግ!›› ሲል በኩራት መለሰለት፡፡

ኢልም ‹‹በእውነቱ ዕድለኛ ነህ፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹እንግዲያው በአራቱ የወርቅ እንክብሎችህ ይህንን በተሻለ ፍጥነት እንድትዋኝ የሚረዱህን ሁለት እርግብግቢቶች/ክንፎች ግዛ፤›› የሚል ጨመረበት፡፡

የባህር ፈረሱም ‹‹እንዴት ግሩም ነገር ነው!›› አለና አራቱን የወርቅ እንክብሎች ሰጠው፡፡ ኢልም በበኩሉ እርግብግቢቶቹን ተከለለት፡፡ በእርግጥም ፍጥነቱ በሁለት እጥፍ ጨመረለት፡፡ 

በአጭር ጊዜም የባህር ስፖንጅን አገኘውና ‹‹ወዳጄ ሆይ እንዲህ በፍጥነት የምተጓዘው ወዴት ነው?›› በማለት ጠየቀው፡፡

በልቡ ውስጥ ፍርኃት ያለነበረው የባህር ፈረስም ‹‹ዕድል የምትሰጠኝን መልካም አጋጣሚ ለመፈለግ!›› ሲል በኩራት መለሰለት፡፡

የባህር ስፖንጅም ‹‹በእውነቱ ዕድለኛ ነህ፤›› አለና ‹‹በቁራጭ ወርቅ ይህንን ጄትስኩተር (ተሸከርካሪ) ብትገዛ በበለጠ ፍጥነት ልትጓዝ ትችላለህ›› የሚል ሐሳብ አቀረበለት፡፡

የባህር ፈረሱም በቀረው ወርቅ ጄትስኩተሩን ገዛ፡፡ በዚያም ተሸከርካሪ ከቀዳሚው በአምስት እጥፍ ሲጓዘ አንድ ሻርክ አገኘውና ‹‹ታዲያስ ጓደኛዬ በእንዲህ ያለ ችኮላ የት እየሄድክ ነው?›› በማለት ጠየቀው፡፡

የባህር ፈረስም ‹‹ዕድል የምትሰጠኝን መልካም አጋጣሚ ለመፈለግ!›› ሲል በራስ መተማመን ስሜት መለሰለት፡፡

ሻርኩም ትልቁን አፉን ከፍቶ ‹‹ነገሩ እንዲያ ከሆነማ በዚች አቋራጭ መንገድ ብትጓዝ ብዙ ጊዜ ታድን ነበር፤›› በማለት ነገረው፡፡

የባህር ዓሳውም ምንም ሳይጠራጠር ‹‹አመሰግናለሁ!›› አለና ሰተት ብሎ ገባ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ስለዚያ የባህር ፈረስ እንደገና ተወርቶ አያውቅም፤›› ይባላል፡፡

በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚገኘው ቁልፍ ትምህርት ምንድነውመልሱ ‹‹ወዴት እንደምትሄድ የማታውቅ ከሆነ መሄድ ወደማትፈልግበት ትደርስና መክፈል የማይገባህን መስዋዕትነት ትከፍላለህ፤›› የሚል ሊሆን ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...