Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየፓርቲና የሥርዓተ መንግሥት መለያየት የሁሉም ነፃነት ጉዳይ ነው

የፓርቲና የሥርዓተ መንግሥት መለያየት የሁሉም ነፃነት ጉዳይ ነው

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ስለአንድ ፓርቲ ለማወቅ ግድ አባል መሆን አይጠበቅም፡፡ ከደጅ ሆኖ ከተግባሩና ከሚለው የተወሰነ ነገር ማወቅ ይቻላል፡፡ የውስጥ አዋቂዎች ስለነበሩበትና ስላሉበት ፓርቲ ወደ ደጅ የሚያወጡት መረጃም የግንዛቤ ምንጭ ይሆናል፡፡ ከደጅና ከውስጥ የተገኙ መረጃዎችን በማገናዘብ ስለሕወሓት ኢሕአዴግ ምንነት ብዙ ማተት አይገድም፡፡ ሕወሓት ከኢሕአዴግ ጋር ግንባር ፈጠርኩ ብሎ የኢሕአዴግነት ካባ በመልበስ፣ ወደ አዲስ አበባ ካቀናበት ጊዜ ጀምሮ ስለሕወሓት ዕልቅናና በራሱ ዙሪያ ምኅዋር ስላስገባቸው ጨረቃ ድርጅቶች ብዙ ተብሏል፡፡

መባል ብቻ አይደለም ባለጨረቃነቱም፣ ጨረቃነቱም በተግባር ተኑሯል፡፡ የዚያ ዓይነቱ ኑሮ ዋንጫ ሞልቶ ጨረቃዎች ‹‹ሳተላይትነት›› በቃን ሲሉም ታይቷል፡፡ ከላይ የነበረው የድርጅታዊ እኩልነት፣ ቅጥፈትና ማስመሰያ ተቀዳዶ ከውስጥ የነበረው እኩልነት አልባ ግንኙነትና በዚህም ምክንያት የደረሱ በደሎች ሊገላለጡ በቅተዋል፡፡ ሕወሓት ከፌዴራላዊ ዋና ገዥነት ከተንሸራተተ በኋላ ሕወሓት ምን ያህል አፋኝ፣ ጣልቃ ገብና ቀጭን ትዕዛዝ ሰጪ እንደነበር ብዙ ተነግሯል፡፡ የለውጡ እንቅስቃሴ ራሱ ከሕወሓታዊ መዳፍ የመውጣትም ሒደት ነበር፡፡ ‹አባል›ም ‹አጋር›ም ከሚባሉት ድርጅቶች ውስጥ ከሕወሓት ጋር እኩልነት እንጂ፣ ተቀጥላነት አልነበረም ይሉ የነበሩ አድር ባይ ‹‹መሪዎች›› ተቀይረዋል፡፡ ስለሕወሓቶች በፊት ያልተጋለጡ ብዙ ነገሮች ተገልጠዋል፡፡

- Advertisement -

ይህ ሁሉ ሆኖም የሕወሓት መሪዎችና ለሕወሓትነት ታማኝ የሆኑ ሁሉ ዛሬም ድረስ ሕወሓታዊ የበላይነት በኢሕአዴግ ውስጥ አልነበረም ብሎ መሸምጠጡን ቀጥለውበታል፡፡ ፍንትው ብሎ የኖረና የተጋለጠ እውነትን በመሸምጠጥ የሚደርቁት ለምንድነው? የትግራይን ሕዝብና ወጣት ለማሞኘት ብንችል ብለው ይሆን? ከማለት በቀር የረባ ምክንያት ማቅረብ ይቸግራል፡፡ በሕወሓቶች ዓይን እንደ ከሀዲ መጠመድን ባለመፈለግ ወይም በሕወሓቶች መጠመድን በትግራይ ሕዝብ ከመጠመድ ጋር አሳክሮ በማየት እውነቱን እያወቁ የማይናገሩም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ አገር ያየውን እውነት ማየት ያልቻሉ የዋሆች ካሉ ሌላ የማሳመን ሐተታ ውስጥ ሳንገባ፣ ራሳቸውን በራሳቸው ለመሞገት የሚያግዙ ጥቂት ነገሮች እንወርውርላቸው፡፡

ብርሃነ ፅጋብ 2011 ዓ.ም. በጻፈው ‹የኢሕአዴግ ቁልቁለት ጉዞ› የሚል (ድርጅታዊ ስብሰባዎች ላይ ያተኮረ) መጸሐፍ ውስጥ እንደሰፈረው፣ በረከት ስምዖን አንዳንድ የትግራይ ተወላጀ የሆኑ ሌቦች እኛ ትግራይ የበላይ ነን ይላሉ… ሲል (ገጽ 234) የእውነቱን ሽራፊ አምኗል፡፡ የሚገርመው ግን ስለግለሰብ ትግራዊ ሌቦችና መንግሥት የግል ባለሀብቶች ምርኮኛ እስከ መሆን ስለመደረሱ የሚናገረው በረከት ስምዖን፣ የሕወሓት ፓርቲያዊ ኩባንያዎች መንግሥትን ምርኮኛ አድርጎ በመጠቀምና ሀብት በመጋፍ ተቀዳሚ ስለመሆናቸው ትንፍሽ አላለም፡፡ ደራሲው ሳይነግረን ቀርቶ ካልሆነ በቀርም በመጽሐፉ ውስጥ ሌላ ሰው ሲያምን አላጋጠመንም፡፡ አሁንም የሚገርመው በሕወሓትና በትግራይ ሕዝብ ላይ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር ሚና የተጫወቱ ኩባንያዎችን ጉዳይ ያልጠየቀ አዕምሮ፣ ኦሕዴድና ብአዴን ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› ባሉ ጊዜ ለመጠየቅና ለመንቀፍ ደፍሯል (የተጠቀሰው፣ 315-316)፡፡ ስብሐት ነጋ፣ እንኳን ተራውን ሰው ሹመኞችን ሳይቀር የሚያስፈራሩ ሰዎች በድርጅቱ ጥላ ሥር እንደሚገኙ፣ በአዲስ አበባ ከሕወሓት ሰዎች ጋር ማን ይሟገታል የሚል አስተሳሰብ እየሰፋ ስለመሆኑና የድርጀቱ ምሥል አደጋ ውስጥ ስለመውደቁ በመስከረም 2007 ዓ.ም. ስብሰባ ላይ መናገሩ ተዘግቧል (ገጽ 97)፡፡ ይህችም የእውነቱ ሌላ ሽራፊ ነች፡፡

ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመረጡ እንቅፋት የፈጠሩ የሕወሓት መሪዎች እንደነበሩ፣ የኦሕዴድ አመራር ላይ ቃለ ጉባዔ እስከ መመርመር ድረስ የተዳፈሩ እንደ ነበሩ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ተናግሯል (ገጽ 494)፡፡ ሥዩም መስፍንም፣ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በወ/ሮ አዜብ ምክንያት ለሁለት ወራት የሚሠሩበት ቢሮ ማጣታቸውን፣ ወ/ሮ አዜብ ከተቀመጥክበት የመለስ ወንበር ውረድ ማለቷን ተናግሯል፡፡ በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 494-5 ውስጥ፡፡ አንዳንድ የሕወሓት ሰዎች በኢሕአዴግ አባል ድርጅት ባልደረቦቻቸው ላይ ዘለፋ ስለመሰንዘራቸውም የሹክሹክታው ሐሜት ካወቀ ቆይቷል፡፡ የሐሜቱ ወሬና በስብሰባ የታመኑት ነጥቦች የሚያንፀባርቁት ከበላይነት ስሜት የሚመጣ ዕብሪትን ነው፡፡

ዕብሪትን ያንፀባረቁት ሰዎች ከሌላው በተለየ እዚህ ስሜት ውስጥ ገብቶ ለመታበይ/ለመዘባነን የበቁት ምንን ተማምነው ነበር? ዕብሪታዊ ድፍረቱ የተፈጸመባቸው ሰዎች (ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ) ትንፍሽ ያላሉት ለምን ነበር? በኢሕአዴግ ቁልቀለት ጉዞ ውስጥ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ የሕዝብ ምክር ቤቶች እንኳን ሊጠይቁን ከእኛ የበለጠ ሥልጣን እንዳላቸው አያምኑም ሲል ተናግሯል (ገጽ 118)፡፡ ለምን ሥልጣን እንዳላቸው ሳያምኑ ቀሩ? በሕወሓት መሰንጠቅ ጊዜ (1993 ዓ.ም. ግንቦት) የኦሕዴድን ግምገማ ወር ሙሉ መለስ ዜናዊ ሊመራ እንደምን ደፈረ? የእሱን አንጃ አልደገፉም የተባሉ የደኢሕዴንንና የኦሕዴድን መሪዎች ሕጋዊ በመሰለ ሕገወጥነትና በፍርደ ገምደል ውንጀላ ከሥልጣን ፈንቅሎ ለማሰር እንደምን ቻለ? አባዱላ ገመዳን ከመከላከያ አሰናብቶ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እንዲሆን ያዘዘው መለስ ዜናዊ እንደሆነም በነጋሶ መንገድ መጽሐፍ ውስጥ ሠፍሯል (263)፡፡ ኦሕዴዶችን ትዕዛዝ ተቀባይ ያደረጋቸው ምን ኃይል ገንዟቸው ነው? የኦሕዴድ መሪዎችን ብቻ ሳይሆኑ የብአዴን፣ የሃብሊና የአጋር ድርጅት መሪዎችን ሁሉ የሕወሓት አጫፋሪነት ገንዞ ለምን አቆያቸው? ማሰብና እውነታን መረዳት የፈለገ የዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ፣ እውነተኛ ሥልጣንና ኃይል በማን እጅ እንደነበር ከማወቅ ጋር የተያያዘ መሆኑን አይስትም፡፡

‹‹ቲም ለማ›› የሚባለው ቡድን የሽፈራው ሽጉጤን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዕጩነት በአብላጫ ድምፅ ከመዘረር አንስቶ ያካሄዱትን ውስጣዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ‹‹ነፍስን ሸጦ›› የተካሄደ ስለመሆኑ ሲናገሩ፣ ወንበር ላይ መቀመጥ ማለት እውነተኛ ሥልጣንን መጨበጥ አለመሆኑን ስላወቁ ነበር፡፡ የደኅንነትና የታጠቀ ኃይሉን አውታር ከፖለቲካ ታማኝነት ለማፅዳት የፈጠኑትም ከተንሳፋፊነት ለመውጣት ነበር፡፡ በተንሳፋፊነታቸው ጊዜም አሻንጉሊት ታዛዥ ከመሆን ወይም ከመፈንቀል ለማምለጥ የቻሉትም ኅብረተሰቡን ያጥለቀለቀና ተቀናቃኞቻቸውን ያደነዘዘ ፈጣን የሕዝብ ድጋፍ አጅቧቸው ስለነበር ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተነገረው ከበላይነት ልዩነት በቀር ሕወሓትና ጭፍሮቹ የነበሩት ድርጅቶች ከፌዴራል እስከ ክልላት ድረስ ገዥና የቢሮክራሲ መረብ መሆን ችለው ነበር፡፡ ገዥ ፓርቲም ቢሮክራሲም በአንድ ጊዜ መሆን ምን ዓይነት ባህርይ ውስጥ እንደሚከት ለማሳየትም የብርሃነ ፅጋብን የኢሕአዴግ ቁልቁለት ጉዞ (ራሱ የተሳተፋባቸውን ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. የተካሄዱ የስብሰባዎች ትረካ) ምርኩዝ አድርጌያሁ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙዚቃ ውስጥ የሚመላለስ አዝማችን የመሰሉ ረቺ መከራከሪያዎች ላይ ያልተቋቋሙ ባዶ ‹‹ድምዳሜዎች›› ይሰጣል፡፡ በየደረጃው የታዩ የቁልቁለት ጉዞዎችን ሳይፈለቅቅ ‹‹የኢሕአዴግ  የቁልቁለት ጉዞ ቀጠለ›› ይለናል፡፡ ያንን ትተን የሚወሳልን የአምስት ዓመታት የስብሰባዎች ሐተታ ባለበት የሚረገጥና አታካች ቢሆንም፣ አውታረ መንግሥትነትና ፓርቲነት ሲቀላቀሉ ምን ዓይነት ትብትብ እንደሚፈጠር ለመረዳት ያስችላል፡፡ 

በየስብሰባዎች ከተባለውና ከተወሳው፣ ሥልጣን የጥቅም መረብን ለመፍጠርና ለመጠበቅ እንደዋለ፣ ሥልጣን ለመክበሪያና ለመንደላቀቂያ እንዳገለገለ ማስተዋል ችለናል፡፡ ሥልጣን አሽከር መፍጠሪያ (ያጨበጨበን መጥቀሚያ፣ የተዳፈረን ማጥቂያ) ሆኖ ሠርቷል፡፡ ሂስና ግለ ሂስ ሳይቀር መተራረሚያ ከመሆን ፈንታ ያጠቃ ማጥቂያ፣ ጥፋት አግንኖና አቀናብሮ ሳይቀድመኝ ልቅደም የሚባልበት የሾኬ ግጥሚያ ሲሆንም ዓይተናል፡፡ ለዓመታት እንደ ውኃ የተወቀጡት ችግሮች ፀረ ዴሞክራሲ ተስፋፍቷል፣ ኔትወርክ ተፈጥሯል፣ ሥልጣን መክበሪያ ሆኗል፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ችግር ነውና ንብረት ይመርመር በማለት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ ሥርዓተ መንግሥትና ፓርቲ ምን ያህል እንደተደበላለቁ እነዚህ ጉዳዮች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሥርዓተ መንግሥትና ፓርቲ ተለያይተው ቢሆን ኖሮ ሥልጣንን ለመክበሪያ፣ ለመመሳጠሪያ፣ ተቀናቃኝን ለማጥቂያና ሸሪክን ለመጥቀሚያ መገልገልን ሁሉ መከላከል፣ መከታተልና ማፅዳት የሥርዓተ መንግሥቱ ሥራ በሆነ ነበር፡፡ የፓርቲ ውይይቶችም በመስመርና በፖሊሲዎች ላይ ያተኮሩ በሆኑ ነበር፡፡ ፓርቲ ስለሙስና/በሥልጣን ስለመባለግና ስለአስተዳደር ብልሽቶች አንስቶ ቢወያይ እንኳ ስለችግሮቹና ስለመፍትሔዎቹ ይወያያል እንጂ፣ ጥፋተኛ ግለሰቦችን በሂስና ግለ ሂስ ‹‹አበጣሪ›› አይሆንም፡፡ በኅብረተሰቡ በፖለቲከኞችና በጋዜጠኝነት የታሙ፣ የተጋለጡ ራሱም የሚጠረጥራቸው አባላት ካሉት የፓርቲው ተቀባይነት በእነሱ ምክንያት እንደይበላሽ ተወያይቶ በሕገ ፓርቲው መሠረት ለስሙ የሚበጅ ዕርምጃ ቢወስድ አግባብ ነው፡፡

ፓርቲም፣ የመንግሥት ገዥም፣ የመንግሥት ቢሮክራሲም ተሁኖም በሦስቱም መስክ ፍሬ የሚሰጥ (ለመራመድ የሚያስችል) ማስተካከያ ቢደረግ ኖሮ አንድ ነገር ነበር፡፡ ይሠሩት የነበረው ግን የይስሙላ መሳይ ነበር፡፡ የስለላና የመረጃ ተቋሙና ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ሁሉ በእጃቸው ውስጥ እንደመሆኑ የማያወላውል መረጃ አጠናቅሮ ተገቢ የሚሉትን ዕርምጃ በመውሰድ ፈንታ፣ ግለሰቦች በግለ ሂስና በሂስ ተፈትተው ኃጢያታቻቸውን እንዲናዘዙና በዚህም ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ለመስጠት ነበር የሚሞከረው፡፡ ሂስና ግለ ሂስ ሊሸወድ ከማይችል መረጃ ጋር ካልተገናኘ ጉንጭ ከማልፋት በምን ይለያል! ከጊዜ ጊዜ በሚደረግ ግምገማ የእያንዳንዳችን ሀብትና ንብረት ይመርመርና ይውጣ ይባላል፡፡ ግን የሀብት ምርመራው ተግባራዊ አይደረግም፡፡ በጥቅም መረብ የተካሄዱ የዘረፋና የበደል ሥራዎችን አንጠርጥሮ በመረጃ ለማውጣት ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ ከነበረ በኢትዮጵያ ይህን ማድረግ አዳጋች አልነበረም፡፡ በረከት ስምዖን ሥርዓቱ የዘረፋና የአፈና ምርኮኛ ስለመሆኑና ራሱን መፈወስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለመድረሱ መናገሩና በተስፋ መቁረጥ ራሱን እስከ ማግለል መወራጨቱ፣ የንቅዘቱን ሥር መስደድና የድርጅቱን መፍትሔ አልባነት በማስተዋል ነበር፡፡ የእሱ ትችትም ቢሆን ሥርዓቱ እንደ ሥርዓተ ነፍስ አለው፣ ምርኮኛ አልሆነም፣ ምርኮኛነቱ ግለሰባዊ ነው ተብሎ ተነቅፏል፡፡

ነፍስ ያለውና እየተራመደ ነው የተባለው ሥርዓት  ግን የነቀዙ ግለሰቦችን ከውስጡ ለማበጠር እንኳ አልተጋም፡፡ ለምን አልተጋም? ምን ቀሰፈው? ይህን ጥያቄ ደፍሮ የተጋፈጠና ዕውናዊ መልስ ሊሰጠው የደፈረ አልነበረም፡፡ ‹‹በስብሰናል›› ባነት ከይስሙላ ያለፈ ትርጉም ኖሮት ከነበር፣ ተራማጅነታችን ተሰልቧል ፓርቲያችንም ፓርቲያዊ የመንግሥት ቢሮክራሲያችንም የአፈናና የዘረፋ መረብ ሆኗል ማለት መሆኑን ማየት ከባድ አይሆንም ነበር፡፡ ሀብት ሰርቆ የሸሸገንና በሽፍንፍንም ሆነ በግልጽ ሕንፃ የገተረን ሰው ጥፋት ሠርተህ ከሆነ በግለ ሂስ ተናገር ማለት የለበጣ ሥራ ይሆናል፡፡ በብሔረተኛ የአስተሳሰብና የቡድን ሠልፍ ውስጥ ተነጣጥሎ፣ በብሔር ወገናዊነት ያልታጠረ የጭቁን ሕዝቦችን ዝምድና እናስበልጥ ማለት ቅዠት ይሆናል፡፡ ልክ እንደዚያው፣ የዘረፋና የአምባገነንነት ባህርይን በፓርቲና በአገዛዝ ደረጃ ተጋሪ ሆኖ እየኖሩ ባህሪይን የሚቀይር ለውጥ በግምገማ ለማምጣት መሞከር ከንቱ ሥራ ነው፡፡

ሕወሓት ኢሕአዴግ በፖለቲካ ድርጅትነቱም በፌዴራላዊ የመንግሥት አውታርነቱም ከላይ እስከ ታች በጥቅሉ የአፈናና የዘረፋ ጎሬ እንደነበር አንድ ሁለት የለውም፡፡ ጭምልቅልቃቸው የወጣ ሰዎች በአሥር ሺዎች እየተነሱና ሌሎች እየተተኩ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳላሳየ ዓይተናል፡፡ የሕዝብ ቅዋሜ በአገሪቱ ውስጥ እየበረታ በሄደ ጊዜ፣ ሲመለስ ሲቀለስ የቆየው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሂስና ግለ ሂስ ጨክኖ በካድሬ ጉባዔ ፊት ሊካሄድ ሲል፣ ጉባዔተኞቹ በድምፅ ብልጫ እዚያው እናንተው ለብቻ አካሂዱት ብለው እንቢ ማለታቸው (የተጠቀሰው፣ ገጽ 270) ንፁህ ጠፍቶ ፓርቲው ይንኮታኮታል ከሚል ፍርኃት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ግንባሩ በአጠቃላይና አባል/አጋር ድርጅቶቹ በየርስታቸው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የመውደቅ ሥጋት የሌለባቸው ጌታና የመንግሥት ቢሮክራሲ መሆናቸውም፣ ራሳቸውን ከማፅዳት እንዲሰንፉ ሁነኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱም አከራካሪ አይደለም፡፡ ብልሽት ሥርዓተ መንግሥታዊና ድርጅታዊ ከሆነ፣ ፈውሱ የግድ በአስተሳሰብም በመፍትሔም ቀፎ ሰብሮ መውጣትን ይጠይቃል፡፡ የአብዮትን መንገድ ያልተከተለ ቀፎን ሰብሮ የመውጣት ዕርምጃ እንዳለ ልሙጡን በፓርቲና በአገዛዝ ደረጃ ሊካሄድ አይችልም፡፡ የሚጀምረው በጥቂት ግለሰቦች/ቡድን ነው፡፡ ጀማሪዎቹ ደግሞ ብልህ ዕቅድና የአካሄድ ጥበብ ከሌላቸው፣ በተንሰራፋው የአገዛዝ ሥርዓት መቀንጠስ ወይም ተመልሶ መሾር ዕጣቸው መሆኑ አይቀርም፡፡

ተቃውሞ እየበረታ በመጣበት ጊዜ እንኳ ግምገማ ከዱለታ ግብ ፀድቶ ጥፋተኞችን ተጠያቂ በማድረግ ላይ ማትኮር አልቻለም ነበር፣ በተለይ በሕወሓት ውስጥ፡፡ የነገር ውል ለመያዝ እንዲቀል ወደኋላ መለስ እንበል፡፡ መለስ ዜናዊ ከማረፉ በፊት የአንጋፎቹ መሪዎች በሌሎች የመተካት ጉዳይ ስምምነት የተደረሰበትና በዕቅድ የተቀመጠ ነበር፡፡ ከመለስ ሞት በኋላ የመተካካት ዕቅዱ የሚመለከታቸው የሕወሓት አንጋፋዎች፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ መቆየት አለብን ትግሉን ለማጠናከር የሚል አቋም ያዙ፡፡ ሆኖም ከመተካት አልዳኑም፡፡ መተካትን በፅናት ከደገፉት ውስጥ ዓባይ ወልዱ፣ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ አዜብ መስፍን፣ በየነ መክሩ ነበሩበት (የተጠቀሰው 9፣14)፡፡ በመተካካቱ ውጤትም ዓባይ ወልዱና በየነ መክሩ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ተሿሚዎች ለመሆን መቻላቸው ይታወሳል፡፡ ሕወሓት አንጋፋ መሪዎችን በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ሲተካ ብአዴን ደግሞ አቆይቶ ነበር (አዲሱ ለገሠን፣ በረከት ስምዖንን፣ ህላዌ ዮሴፍን፣ ታደሰ ካሳን)፡፡ በዚህም ምክንያት የሕወሓት አንጋፎች ከሞላ ጎደል የሕወሓትን ድርጊት መራራ ጥፋት አድርገውት ነበር፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር ዓባይ ወልዱ ደግሞ የብአዴንን ውሳኔ ማዕከላዊነትን የጣሰ ብሎ ተከፍቶበታል (26)፡፡ አንጋፋዎቹን በመተካት ላይ ተመሳሳይ አቋም የነበራቸው ዓባይ ወልዱና በየነ መክሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በሒደት ሽኩቻ ውስጥ በመግባትና የየራሳቸውን ቡድን በመፍጠር ይታሙ ነበር፡፡ እነ አዜብ መስፍንንና እነ ስብሃት ነጋም እንደዚሁ (44-5)፡፡

በ2010 ዓ.ም. ግምገማ አንድ ደረጃ ላይ ተወራራሽ ችግሮችን (ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋልን፣ ፀረ ዴሞክራሲነትን፣ ቡድን ፈጠራን፣ የአመራር ድክመትን፣ ወዘተ) እንደተለመደው ከመደርደር ፈንታ፣ የድርጅታችን ዋናው ችግር ኪራይ ሰብሳቢነትና ዘረፋ ሳይሆን ፀረ ዴሞክራሲነት ነው የሚሉ ሰዎች ብቅ አሉ፡፡ ብርሀነ ፅጋብ እንደሚያወሳን፣ አንድ የችግር ግንጣይ ላይ ያተኮረው ይህ ትችት ሥርዓቱን ሳይከተል ከመጣና ‹‹ኮንትሮባንድ›› ከተባለ ሰነድ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ‹‹ኮንትሮባንድ›› የተባለው ሰነድ ዝግጅት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከአቶ ዓባይ ወልዱ ጋር ተሻኳቾቹ በየነ መክሩ፣ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድና ተፈነቀልን የሚል ቅሬታ ያላቸው አንጋፋዎቹ አሉበት፡፡ ይህ ሰነድ ሥነ ሥርዓት ያልተከተለ ተብሎ ውድቅ እንዳይደረግ የታገሉ የሰነዱ ደጋፊዎችም እነሱና ሌሎች በእነ ዓባይ ወልዱ ላይ ቅሬታ የቋጠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ በአቶ ዓባይ ወልዱ ላይ የተሰነዘሩ ሂሶች ስትራቴጂካዊ አመራር አለመስጠት፣ የፀረ ዴሞክራሲ ምልክቶች፣ የአመራር አንድነት መዳከም፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በበቂ አለመታገል የሚሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በየነ መክሩ በሙስና ባይታሙም ለሥልጣናቸው ሥጋት ካዩ ድምፅ አልባ ጥቃት በመፈጸም የተካኑና እንደ አመቺነቱ ‹ኔትወርክ› ቀያያሪ ተብለዋል፡፡ ዓለም ገብረ ዋህድ ደግሞ ሀብት የሚያነፈንፉ አምስት ፎቅ የሠሩ ተብለዋል (ከአምስቱ አራቱን አምነዋል)፡፡ አሜሪካ ሄደው በሁለት ሳምንት ጊዜ ለሞባይል ስልክ ወጪ 12,000 ብር ማወራረዳቸው ተገልጦባቸዋል፣ ወዘተ፡፡ እንዲህ የተባሉት ዓለም ገብረ ዋህድና በየነ መክሩ ከእነ ስብሃት ነጋ፣ ሥዩም መስፍን፣ ዘርዓይ አስግዶም፣ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ጋር አንድ ላይ ገጥመዋል፡፡ ‹‹ዋናው ጠላት ፀረ ዴሞክራሲ ነው›› የሚል መከራከሪያ የእነ አቶ ዓለምን ሀብት አካባችነት ከልሎ በዓባይ ወልዱ ላይ ለማነጣጠር እንዲስማማ ተደርጎ የተነደፈ መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡

ግምገማውን ተከትሎ በመጣ ድርጅታዊ ዕርምጃ ዓባይ ወልዱ ከሕወሓት ሊቀመንበርነት ተነስተው የማዕከላዊ ኮሚቴ ተራ አባል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በየነ መክሩም ከሥራ አስፈጻሚነት ኮሚቴ ወጥተው ተራ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከመሆን ባይተርፉም፣ እነ ስብሃት ነጋና አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በሥራ አስፈጻሚነት ውስጥ እንዲቀጥሉ ተከራክረውላቸዋል፡፡ የፎቅ ቤቶች ጌታውና ሌላ ሌላ የሙስና ሂስ የቀረበባቸው ዓለም ገብረ ዋህድ ግን በማስጠንቀቂያ ታልፈው በሥራ አስፈጻሚነት መቀጠል ችለዋል፡፡ በዚህ ውጤትም ዓባይ ወልዱን ለመፈንቀል የተዋደቁት ደስተኛ ሆነዋል (በየነ መክሩን ጨምሮ)፡፡ ከዚያም ባለፈ በለውጥ ወገንና በፀረ ለውጥ መሀል ትግል ተካሂዶ ‹‹የለውጥ ወገን ያሸነፈበት››፣ ‹‹የተዋጣ ጥልቅ ተሃድሶ›› እያሉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች ባሉበት ስብሰባ ላይ ተመፃድቀውበታል (የተጠቀሰውን መጽሐፍ ከምዕራፍ ስምንት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ያለውን ክፍል መመልከት ዝርዝሩን በሰፊው ለመጨበጥ ይጠቅማል)፡፡ በአጠቃላይ ግን ከላይ እንዳየነው ግምገማ ቢግልም ቢበርድም፣ በቃላት ቢሞኳሽም ባይሞካሽም፣ በተበላሸ ቀፎ ውስጥ የብልሽት አካል ሆኖ በተለመዳው የመጠላለፍ ሥልት፣ ቂም ከማወራረድና አንዱን ብልሹ በመፈንቀል ከመርካት አልወጣም ነበር፡፡ ቀፎን የሰበረ ዕይታ በኢሕአዴግና በአስተዳደሩ ውስጥ የተከሰተው በዓብይ መንግሥት መምጣት በኩል ነው፡፡

የዓብይ መንግሥት ብሔረሰባዊ ማንነቶችን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አስማምቶ፣ ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ትልምን መርጦ፣ የአገሪቱን የሥልጣን ዓምዶች ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ማሻሻያን የማካሄድ ሒደት ውስጥ መግባቱ፣ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ያልነበረ አዲስ ውጤት (ሕዝቦች በድምፃቸው ሿሚና ሻሪ የሚሆኑበትን ሥርዓተ መንግሥት) የሚያመጣ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት መቋቋም፣ ፓርቲዎች መንግሥታዊ ዙፋንንና ቢሮክራሲን በፍላጎታቸው ቀርፀው ከመንፈላሰስ (በልሽቀትና በንቅዘት ከመብከት) ነፃ ይወጣሉ፡፡ ሥልጣን      ማግኘት አለማግኘታቸውም ሆነ የሥልጣን ቆይታቸው በሕግና በሕዝብ ይሁንታ ሥርዓት ውስጥ መውደቁ፣ ሕዝብ የሚማርክ ነገር ይዞ ለመምጣትና ለመሥራት ያተጋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የነፃነት ዋስትና ተስማምቷቸው የሚኖሩበት ምዕራፍ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ምክንያቱም የመብቶቻቸው ህልውና በዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሪፐብሊካዊ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የተካተተ ስለሚሆን፣ እንዲሁም በምርጫ መጥቶ ከአናት የሚቀመጠው ፓርቲያዊ አስተዳዳሪነት መብቶቹንም ሆነ ፌዴራላዊውንና ሪፐብሊካዊውን ሥርዓት  እንዳሻው መገነዝና መቆልመም ስለማይቀለው ነው፡፡ ሊገንዝና ሊቆለምም ቢቃጣው ሕግና ሥርዓቱ ከግለሰብና ከፓርቲ በላይ ነውና ይታገለዋል፣ ይቆነጥጠዋል፡፡ ሕግና ሥርዓቱ ጊዜያዊ መንፈዝ ቢደርስበት፣ ሕዝቦች ነፃነታቸው ከሥርዓተ መንግሥቱ ነፃነት ጋር ሲሰለብ ዝም አይሉም፡፡ መሪ እስከ ማውረድና በአዲስ ምርጫ መሪና እንደራሴዎች እስከ መቀየር ሊሄዱ ይችላሉ፡፡

ይህ ሥርዓት ሕዝቦችን በብሔረሰብ ማንነት/በጎጥ ለማንጓለል ወይም መጤና ባይተዋር አድርጎ ለመጨቆን አይመችምና፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ለዚህ ሥርዓት የሚስማማ ሁሉን በእኩል የሚያይ፣ ሁሉን ወገኔ/እኔነቴ የሚልና የትኛውንም ዓይነት ጭቆና የሚታገል አስተሳሰብ ውስጥ መግባት ግዳቸው ነው፡፡ በየብሔርተኛ ጎጆ ውስጥ ተወሽቆ፣ ጎጆ ድርጅቶችን በግንባር ቢያያይዙ የአገር ልጆችን ሁሉ እኔነቱ ያደረገ አመለካከት አይገኝም፡፡ ምክንያቱም በግንባሩ ውስጥ ክፍልፋይና አንጓላይ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ድርጅታዊ ቅንብሮች ፈጥረው ተኮልኩለዋልና፡፡ እስከተኮለኮሉ ድረስም አገራዊ ፍላጎትና ጎጇዊ ሩጫዎች እየተሻሙ መቋሰል፣ መጠራጠር፣ መተማማትና መርኮምኮም መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ መፍትሔ ካላገኙም በሒደት የእኩልነት እምነትን ፍትሕንና ዴሞክራሲን መሸርሸራቸው አይቀርም፡፡ ፓርቲያዊ ዕይታና አስተሰሰብ መስፋት የሚጀምረው ከአንጓላይ አደረጃጀት ወደ ተዋሀደ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ከመግባት ነው፡፡

ልዩ ልዩ ቀለማት ያሏቸው ብርሃኖች ሲቀላቀሉ አንዱ ቀለም ለብቻው አይገኝም፡፡ እያንዳንዱ ቀለም የብርሃን ወሰኑ ተለይቶ አይታይም፡፡ የትኛውም ቀለም በሌሎች ላይ ልግነን አይልም፡፡ ሁሉም በአንድ ላይ ቀለም የለሽ የብርሃኖች ኅብር ይፈጥራሉ፡፡ በቀለም የለሹ ኅብር ውስጥ ሁሉም አሉ፡፡ የሚቀነሱ አይኖሩም፡፡ ቀለም አልባው ‹‹ነጩ›› ብርሃን አረንጓዴ ቦታ ላይ ሲያርፍ አረንጓዴነት ይፈካል፡፡ ዳለቻ ላይ ሲያርፍ ዳለቻ፣ ቀይ ዳማ ላይ ቀይ ዳማ፡፡ የትኛውም ቀለም ላይ ሲያርፍ የነገርየውን ዓይነተኛ ቅልመት ይገልጻል፡፡ እያንዳንዱ ቅልመት ላይ የሚታይ ከለር የኅብሩ ብርሃን ዝርዝርና ቅንስናሽ ቅንብር ነው፡፡

በውህድ ዕይታም ውስጥ እንደዚያው የሁሉም ሕዝብ  ቀለም ተዘማምዶና የሁሉም ኅብራዊ እኔነት ሆኖ ይወጣል፡፡ በፌዴሬሽኑ ማዕከላዊ ስብስብ ደረጃ፣ በፌዴራል አባል አካባቢዎች ደረጃ፣ በአውራጃም ሆነ በወረዳ ደረጃ የብሔረሰባዊ ብዝኃነት ክምችት ከመጉላት እስከ መሳሳት ልዩነት ቢኖርም፣ የዚህ ዓይነት ልዩነት የፓርቲ ኅብራዊ አተያይን አያሰናክልም፡፡ ከላይ እስከ ታች የትኩረት ሥፍራ ልዩነት እንጂ የዕይታ ባህርይ ልዩነት የለም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም፣ በትንሿ ሠፈር ደረጃም፣ በአባል ግለሰብ ደረጃም እንዲሠራ የሚደረገው ፓርቲያዊ ዕይታ ቀለም የለሽ ኅብራዊነት (በአጠገቡና ካጠገቡ በራቁ የአገር ልጆች ዘንድ ያሉ ከለሮችን/ዥንጉርጉርነቶችን ሁሉ) እኔነቴ ብሎ ያዘለ ነው፡፡ የሚሠራውም የሁሉም ዥንጉርጉርነት የእያንዳንዱ ዜጋ እኔነት ሆኖ እንዲታይና እንዲበለፅግ ይሆናል፡፡ ይህንን ኅብራዊነት ዕይታቸውና የመሰባሰቢያቸው ውል ያደረጉ የአካባቢ ፓርቲዎች ከውህደት በመለስ ግንባር ሆነው ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን ለመምራት ቢንቀሳቀሱ፣ አገር አስማምቶ ለመምራት የሚያደነቃቅፍ የአተያይ ግጭት አይኖርባቸውም፡፡ በየብሔር ማንነት መሥፈሪያ የተደራጁ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ግን፣ ግንባር ቢፈጥሩ እንኳ እዚህ ከሚወራለት ኅብራዊነት ባህርያዊ ልዩነት አላቸው፡፡ ሰማኒያ የብሔር ፓርቲዎች ቢኖሩ ሰማንያ ዓይነት ዕይታና እኔነት ነው የሚኖረው፡፡ የእያንዳንዱም እኔነት ሌላውን ከራሱ ውጪ ያደረገ ነው፡፡ እነዚህ እኔነቶችና ዕይታዎች ተኮልኩለው ግንባር ቢሠሩ ከእርስ በርሳቸው ጋርና ከወል ህልውናቸው ጋር መሻኮት አይቀርላቸውም፡፡

የሁሉን ቀለም ኅብራዊ እኔነቱ ያደረገ አተያይ፣ በፌዴራላዊ አገርነት ውስጥ የሚገኝ የእያንዳንዱን አካባቢያዊ ‹‹አሀድ›› ግስጋሴና የአጠቃላዩን የጋራ ግስጋሴ አጣጥሞ ለማየትና ለማስኬድ የሚስማማ ነው፡፡ እየተጠቃለለ ባለው የዓለም፣ የአኅጉርና የክፍለ አኅጉር ዳንቴል ውስጥ ኢትዮጵያን ለማራመድ ይመቻል፡፡ ኅብራዊ ቀለም የለሽ አተያይ ባለው ፓርቲ ውስጥ ማንኛውንም ችግር መርምሮ ለመፍታትና ሐሳቦችን አፋትጎ ለማንጠር፣ ብሎም በተማመነ መስማማት ለመወሰንና ሥራን ለማስኬድ በየትኛውም ደረጃ ከፍተኛ ዕድል አለ፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ማንነትና የሁሉም አካባቢ መልማትም ሆነ መጎዳት በኅብራዊ እኔነት ዕይታ ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ የአንዱ ስኬት የራስ ስኬት ሆኖ ሁሉን ያስፈነድቃል፡፡ የአንዱ መጎዳትና ለድንገተኛ አደጋ መጋለጥ ከይስሙላ ያለፈ ርብርብ የሚወልድ የሁሉ ሕመም ይሆናል፡፡

የቀለም ብርሃኖች ቅልቅል ለፓርቲና ለፓርቲ ዘለል ኅብራዊ አመለካከት ያለው ሥዕላዊ ገላጭነት ግን ሁለመናዊ አይደለም፡፡ ብርሃኖች ሲቀላቀሉ ሁሉን ያዘለ ቀለም አልባ ቅንብራቸውን በዚያው ቅፅበት ይቀዳጃሉ፡፡ በኅብረ ብሔራዊ ውህደት ውስጥ የኅብራዊነት ሒደት ወደ ውህደት ከተጓዙበት ጊዜ ቢጀምርም ያኔውኑ አይጠናቀቅም፡፡ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ለ28 ዓመታት ደርቶ የቆየውን የአተያይና የአስተሳሰብ ብጥስጣሽነትን በፓርቲውም ውስጥ ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ የማሸነፍ ተግባር ገና ያንገላታል፡፡ ሥልጣንን መክበሪያ ማድረግ የጣማቸውና ያጓጓቸው ጥቅመኞች፣ ጥቅማቸውን የሕዝብ  አስመስለው እንደሚንፈራፈሩም አያከራክርም፡፡ ምርጫ ሲመጣ ውህድ ፓርቲን የራስ አስተዳደር ፀር አስመስሎ ሕዝብን በማወናበድ ድምፅ ሸምተው ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚዘጋጁ እንዳሉም ዕውቅ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ቅጥፈቶችን እየገላለጡ ለማምከን በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ዝግጅቱ እስከተሟላ ድረስ፣ ኅብራዊ አመለካከት ውዝግቦችን ጥርጣሬዎችን ቅያሜዎችንና መሸካከሮችን በማቃለልና የተማመነ መስማማትን በማጎልበት ረገድ አቻ የለውምና በየደረጃው የሚያስገኛቸው ውጤቶች እያጎለመሱ በፖለቲካችንና በኅብረተሰባችን ውስጥ መስፋፋቱ አንድና ሁለት የለውም፡፡ አሁን የሚወራለት ውህደት የኢሕአዴግና አጋር የሚባሉት ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ ላይ በመድረክ ውስጥ የተሰባሰቡ ኃይሎች ወደ ውህደት መምጣትም ለኅብረተሰባችን የፖለቲካ ሰላም መዳበር የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ ሌሎች ቁርጥራጭ ድርጅቶችም አዝማሚያውን ተከትለው ወደ ውህደት ካልመጡ ለመረሳት የመረጡ መሆናቸውን ከወዲሁ ቢገነዘቡ ማለፊያ ነው፡፡

ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓት በተግባር እንዲሠራ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት በአግባቡ መቋቋም ግድ ነው፡፡ በዚህ አባባል ውስጥ የሥርዓተ መንግሥት ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለያየት፣ የፓርቲዎች ከባለጠመንጃነት መሰነባበት፣ የፓርቲዎች ከአግላይነት መውጣትና ከዴሞክራሲ አሠራርና እሴቶች ጋር መግባባት ታዝለዋል፡፡ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን የሚደርሱበት ብቸኛ ሕጋዊ መንገድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸውን በነፃነት አወዳድረው፣ በተዓማኒ የምርጫ ሒደት በሚገኝ የድምፅ ውጤት መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደዚህ ሥርዓት ለመግባት ጉዞው ተጀምሯል፡፡ በግርግሮች ድንበር ገተር ማለት ቢኖርም፣ የለውጡ አሠረጫጨት ጥሬ የበዛበት ቢሆንም፣ ‹‹ለውጡ በትምክተኞች ተጠልፏል የለም በፅንፈኛ ብሔርተኞች ተጠልፏል›› በሚሉ የንጭንጭ ወስፌዎች ከሁለት በኩል የሚጨቀጨቅ ቢሆንም እንደ ምንም ወደፊት እየተጓዝን ነው፡፡

‹‹የፌዴራላዊ ሥርዓቱን እናድን አሃዳዊነት እየመጣ ነው›› የሚል ጩኸት ዋና ማዕከል ሆኖ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ትግራይን በሚገዛው ሕወሓት ነው፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የማትረፍም ሆነ ሕይወት የመስጠት ተግባር ቀደም ብሎ እንደ ተጠቆመው፣ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ውስጥ የመግባትና መንግሥታይ አዕማድን ከፓርቲ የማላቀቅ ጉዞ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ከተገተረባቸውና የፓርቲና የመንግሥት ቢሮክራሲ መደበላለቅ ከጠናባቸው ሥፍራዎች አንዱና ዋናው ትግራይ ነው፡፡ ‹‹ፌደራላዊነትን እናድን›› እያሉ የሚጮሁት ሕወሓቶችና ሌሎች ሸሪኮቻቸው ጉዳያቸው ፓርቲና ሥርዓተ መንግሥትን ከሚያለያይ ለውጥ ጋር ሳይሆን፣ ከብሔር ፓርቲነት ወደ ውህድ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነት መሸጋገርን በመቃወም ላይ ነው፡፡

በብሔር መሥፈርት ሌላውን አግልሎ ከተደራጀ ፓርቲ ይልቅ ሁሉን አካታች የሆነ ፓርቲ ከዴሞክራሲ የእኩልነትና የፍተሐዊነት መርህ ጋር እንደሚጣጣም አላጡትም፡፡ ፌዴራላዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሠመረላቸው አገሮች ሁሉን አካታች አተያይና አደረጃጀት ባላቸው አካባቢያዊና አገር አቀፍ ፓርቲዎች እንደሚሠሩም ያውቃሉ፡፡ የአካባቢዎች ራስ በራስ አስተዳደርም ኢውህዳዊ የፓርቲ አደረጃጀት ላይ የማይንጠለጠል፣ በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥቱ ተግባራዊ አቋቋም የሚጠበቅ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ህያው በሆነበት ሥፍራ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ በበርካታ ‹‹ክልሎች›› ውስጥ የሥልጣን ወንበር የሚያሸንፈው በየክልሎቹ ባሉት የፓርቲ ማዕከላቱ አማካይነት ለየአካባቢዎቹ የሚስማማ መርሐ ግብር ይዞ፣ ከዚያው አካባቢ በወጡ አባላቱ አማካይነት ተፎካክሮና የየአካባቢዎቹ ሕዝቦች  ከሌሎቹ ፓርቲዎች በበለጠ ከመረጡት ብቻ እንደሆነም የታወቀ ነው፡፡

ይህ እውነት ሳይጠፋቸው ራሳቸውም ኢሕአዴግ እንዲዋሀድ አብሮ መካሪ የነበሩ ሆነው፣ ዛሬ ስለምን የውህድ ፓርቲ መፈጠርን የፌዴራላዊ ሥርዓት መጥፋትና የአሀዳዊ አገዛዝ ተመልሶ መምጣት አድርገው ሕዝብ ለማጭበርበር ይለፋሉ? የአጭበርባሪና የሸር ፖለቲካ ልማደኞቹ የሕወሓት የፖለቲካ መሐንዲሶች በዚህ ፕሮፓጋንዳዊ ሰም ውስጥ ያላቸው ወርቃዊ ፍላጎት ምንድነው? የፖለቲካ ስንጥቅም ሆነ ቅሬታና የማፈንገጥ ጥያቄ ባለበት አነፍንፈው በግልጽም ሆነ በሥውር የመብት ተቆርቋሪ እየመሰሉ ስንጥቅና መከፋፈል እንዲበራከት የሚሠሩት ምን ፈልገው ነው? ያለ ጥርጥር ትናንትና እነሱና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው የበላይ የሆነበት ገዥነት ለማዋቀር ጨረቃዎች እንደመለመሉ፣ ዛሬም የዓላማ ማስፈጸሚያ ጭፍሮች ማሰባሰብ ይሻሉ፡፡ ጭፍራ እያነፈነፈ ያለው ድብቁ ዓላማቸው ምንድነው? እንደገና መንገሥ? ወይስ የዚህ ምዕራፍ ፋይል ተጠናቆ፣ አሁን ደግሞ ሳጥን ውስጥ የቆየ ሌላ ፋይል ወጥቶ ይሆን? በ2012 ዓ.ም. ጥቅምት የመጀመርያ ቀናት ውስጥ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሰጠውን መግለጫ የፖለቲካ ጠበብቶቻቸው ሲያብራሩልን፣ ከኤርትራ ጋር ያለ ዝምድናን ‹‹ስትራጂካዊ››፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያለ ቆይታን ፌዴራሊዝም ተነካ ብለው ሲያምኑ የሚበጥሱት አድርገው ስለምን አቀለሉት? የትግራይ ገዥዎች መነጠልን በኪሳቸው ለያዙ ቡድኖች መድረክ ሰጥተው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያስቡ ትግራዊ ቡድኖችን በከሃዲ ዓይን የሚያዩትና የሚያፍኑት ለምንድነው? የትግራይ ሕዝብን የፖለቲካ ዕጣ የመወሰኑ ጉዳይ ከእነሱና ከመሰሎቻቸው ፍላጎት እንዳይወጣ? ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የራስ በራስ አስተዳደር፣ ሰላምና ግስጋሴ የቆሙ ፖለቲከኞች ሁሉ ዛሬ በደንብ ሊመረምሩት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...