Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ መንግሥት መዘጋጀቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምርትና የአገልግሎት ሰነዶች በዚህ ወር ድርድር ይካሄድባቸዋል

ለዓመታት ሲጓተት የቆየው የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት የድርድር ሒደት እንደ አዲስ ተጀምሮ አራተኛው የሥራ ሒደት ስብሰባ በተያዘው ጥቅምት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት የድርድር ሒደቱን እንደ አዲስ ለማስጀመር ዝግጅቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ለ15 ዓመታት ሲጓተት የቆየው የአባልነት ሒደቱ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ መንግሥት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ፣ ይህ ግን በኢትዮጵያ ዝግጁነት ላይ ብቻ እንደማይወሰን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደትን እንዲያቀላጥፍ የተቋቋመውና ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ምሥጋኑ አረጋ (አምባሳደር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሸቀጦች የቀረጥ ጣሪያን ጨምሮ በአራት መስኮች የመደራደሪያ ሰነዶች ላይ የተጀመረው ዝግጅት በተያዘው ጥቅምት ወር ለድርድር እንደሚበቃ ይጠበቃል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪና ኢትዮጵያን በዋና ተደራዳሪነት የሚወክሉት አቶ ማሞ እስመለዓለም ምኅረቱ፣ አሥር አባላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራውን በይፋ እንደጀመረና የመጀመሪያውን ስብሰባም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዳካሄደ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም በዚህ ወር ድርድሩ እንደሚጀመር በሚጠበቀው ሒደት፣ ኢትዮጵያ በአገልግሎት መስክ ያደረገቻቸው ለውጦች ድርድሩን እንደሚያፋጥኑት ይታመናል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው ስብሰባ በዕቃዎች የቀረጥ ጣሪያ ወይም ‹‹ጉድስ ኦፈር››፣ ለውድድር ክፍት በሚደረጉ የአገልግሎት መስኮች ወይም ‹‹ሰርቪስ ኦፈር›› ላይ መወያየቱ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይም በሸቀጦች የታሪፍ ጣሪያ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ ማሞ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንን ተከትሎም አራተኛው የድርድር ሒደት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር፣ ለዚህም የድርድር ሰነዶችና የአገሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ከዓለም ንግድ ድርጅት ሕግጋትና አሠራሮች ጋር የማጣጣም ሥራዎች መካሄድ መጀመራቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ አራተኛ ዙር የድርድር ሒደት በመጪው ዓመት መጀመሪያ እንዲካሄድ ቀጠሮ መያዙን አቶ ማሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከፕላንና ልማት ኮሚሽን እንዲሁም ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ሥራውን ጀምሯል፡፡ ይህንን ያስታወቁት አቶ ማሞ፣ ለስድስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ድርድር ለማስጀመር ቴክኒካዊ ሥራዎች መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡  

እንደ አቶ ማሞ ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሦስት የድርድር ምዕራፎች የፖሊሲና የቴክኒክ ሰነዶች ለዓለም ንግድ ድርጅት ተደራዳሪዎች ቀርበዋል፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ድርድር ከሰባት ዓመታት በፊት ተካሂዶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሒደት ወቅት በተደራዳሪ አገሮች በኩል ሲነሱ የነበሩ የአገልግሎት መስኮችን ለውድድር ክፍት የማድረግ ክርክሮች ምላሽ ያገኙ ይመስላሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ ለሪፖርተር ያብራሩት አቶ ማሞ፣ ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሎጂስቲክስና የፋይናንስ ዘርፎች በከፊልም ቢሆን ክፍት እየተደረጉ ነው፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ ሁለት አዳዲስ ኩባንያዎች እንዲገቡ፣ ኢትዮ ቴሌኮምም 49 በመቶ ይዞታውን እንዲሸጥ፣ የሎጂስቲክ ዘርፉም 49 በመቶ ድርሻው ለውጭ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ክፍት እንዲደረግ፣ የባቡር ትራንስፖርትም ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፈት፣ የኢነርጂ ዘርፉም የውጭ አምራቾች እንዲገቡበትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ድርሻውን እንዲሸጥ ብሎም የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም የባንክ ኢንዱስትሪው ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉበትና የራሳቸውን ባንክ መመሥረት እንዲችሉ የሚፈቅድ አዋጅ መውጣቱ ሁሉ በአገልግሎት መስኩ ለድርድር ሒደቱ መቀላጠፍ በር የሚከፍቱ ዕርምጃዎች ተብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን የምትፈልገው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነትና ተዓማኒነት ለማጠናከር፣ የውጭ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ በሙሉ ልብ የሚተማመኑበት ማዕቀፍ ለመፍጠር የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት አቶ ማሞ ያብራራሉ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ የተጀመረው የድርድር ሒደት በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ በመንግሥት ካቢኔ በኩል ውሳኔ እንደተላለፈ የሚጠቁሙ መረጃዎች ይደመጣሉ፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴውም በሰኔ ወር በዝግ መወያየቱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በአራት መስኮች ማለትም በንግድና በአገልግሎት መስክ ከምትደራደርባቸው በተጨማሪ አዕምሯዊ ንብረቶችና ሌሎችም የንግድ መስኮች ላይ የድርድር ሒደቶችን እንደምትጀምር ይጠበቃል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ታዛቢ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ወቅት ድርጅቱ ሲመሠረት በአባልነት እንድትካተት የቀረበላትን ጥያቄ ወደ ጎን ማለቷን የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የሚደረገው ጉዞ ውስብስና ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ቢታይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኃያላኑ አገሮች መካከል እየተካረረ የመጣውና በታሪፍ ላይ የተመሠረተው የዓለም የንግድ ጦርነት የዓለም ንግድ ድርጅትን ሚና እየተፈታተነው ስለመምጣቱም ተንታኞች በየወቅቱ የሚገልጹት ነው፡፡ 

በአንድ ወቅት አቶ ገረመው አያሌው የተባሉና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ግንኙነትና የንግድ ድርድር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ስለ ዓለም ንግድ ድርጅት ለሪፖርተር እንዲህ አብራርተው ነበር፡፡ ‹‹የዓለም ንግድ ድርጅት ማለት አንድ የቆየ ትልቅ ዕድር ነው፡፡ አባላቱ ዕድሩን ሲመሠርቱ ምናልባት በአሥር ሳንቲም መዋጮ ጀምረውት ይሆናል፡፡ አሁን ግን የአባልነት መግቢያው አምስት ሺሕ ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ዕድሩ የሚገባው ሰው እናንተ በአሥር ሳንቲም ስለጀመራችሁት እኔም በአሥር ሳንቲም ልግባ ማለት አይችልም፡፡ አምስት ሺሕ ብር ከፍሎ ይገባና ባይሆን ሕጉ እንዲሻሻል ጥረት ያደርጋል፤ የዓለም ንግድ ድርጅትም ጠቅለል ተደርጎ ሲገለጽ እንዲህ ነው የሚመስለው፡፡››

እንደ አቶ ገረመው ሁሉ ይህን አባባል ይበልጥ ያብራሩት በወቅቱ የአቶ ገረመው ባልደረባና በሚኒስቴሩ የመልቲላተራል ንግድ ግንኙነትና ድርድር ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ልሳነውርቅ ጎርፉ የተባሉ ኃላፊ ናቸው፡፡ አባል የመሆን ጥቅሙን የሚያብራሩት አቶ ልሳነውርቅ፣ በድርድር ሒደቱ በተለይ የታሪፍ ጣርያን በመወሰን ረገድ ይህም ማለት፣ ኢትዮጵያ የገቢ ንግድ ዕቃዎች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ የመቀነስ፣ ባለበት እንዲጸና የማድረግና ካለበት ደረጃ እንዲጨምር የማድረግ አማራጭ ይዛ ለአባልነት እንደምትደራደር አብራርተው ነበር፡፡ የታሪፍ መጠኑ ከፍ ተደርጎ ድርድር እንደሚካሄድ፣ የታሪፉ መጠን ምን ያህል ይደረግ የሚለው ግን እንዳልተወሰነ አስታውቀው ነበር፡፡ እስካሁንም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግልጽ አልተደረገም፡፡   

ኢትዮጵያ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ማመልከቻ በማቅረብ ድርድር የጀመረችው በ1996 ዓ.ም. እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ድርጅቱ በሚቋቋምበት ወቅት (እ.ኤ.አ በ1948 ሲመሠረት) ጠቅላላ የንግድና የታሪፍ ስምምነት ወይም ‹‹ጄነራል አግሪመንት ኦን ታሪፍስ ኤንድ ትሬድ›› በሚል ስያሜ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 ጀምሮም አሁን የሚጠራበትን የዓለም ንግድ ድርጅት ሥያሜ አግኝቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች በዚህ ድርጅት እንዲሳተፉ የአባልነት ጥሪ ሲቀርብላቸው ኢትዮጵያ ምላሽ እንዳልሰጠች ይነገራል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ይህንኑ ስሙን ይዞ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ የታዛቢነት መንበር እንዲሰጣት ያመለከተች ብቸኛ አገር ስለመሆኗም የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህም ይባል እንጂ የታዛቢነቱ ወንበር ከኢትዮጵያ በኩል የተጠየቀው ከውጭ ሆኖ ጥቅምና ጉዳቱን ለመገምገምና የአባላቱን የንግድ እንቅስቃሴ ለመታዘብ በማሰብ እንደነበር ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

በ1996 ዓ.ም. አገሪቱ የውጭ ንግድ ሥርዓቷን ለድርጅቱ አባላት በማቅረብ ጥያቄዎቻቸውን ማስተናገድ ጀምራ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር ለቀረቡላት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቷን ከሦስት ዓመታት በፊት የነበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለቀረቡላት 134 ያህል ጥያቄዎች ምላሾቿን በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ላይ ስለመሆኗም ተዘግቦ ነበር፡፡ በመጀመርያው ዙር የተላኩላት ጥያቄዎች 197 የነበሩ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ከዓለም ንግድ ድርጅ ተደራዳሪ አባላት የተላኩት ጥያቄዎች ወደ 144 ዝቅ ብለው እንደነበረም ይታወሳል፡፡

የአባልነት ሒደቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የአባልነት መሥፈርቱ፣ የሚለዋወጡ ሕጎች፣ ለዝግጅት የሚጠይቀው ወጪ እንዲሁም አዳዲስ አባል አገሮች ሊያነሷቸው የሚችሏቸው ጥያቄዎች እየተበራከቱ ስለሚመጡ ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፍላሉ በሚለው ነጥብ ላይ የመንግሥት ኃላፊዎችም ባለሙያዎችም ይስማሙበታል፡፡

በቅርብ ጊዜ ሩስያ፣ ሞንቲኔግሮ፣ ሳሞኣና የላኦስ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተባሉት አራት የአውሮፓ አገሮች የዓለም ንግድ ድርጅትን በመቀላቀል ጠቅላላ የአባላቱን ቁጥር 157 አድርሰውት ነበር፡፡ ይህ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች በአባልነት ሒደት ላይ ለሚገኙ አገሮች ተጨማሪ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም ንግድ ድርጅት በአባልነት ያካተታቸው አገሮች ብዛት 164 እንደደረሱ መረጃዎች ሲጠቁሙ፣ የመጨረሻዋ ተመዝጋቢ አገር አፍጋኒስታን ነበረች፡፡ አውሮፓ ኅብረት ራሱን ችሎ እንደ አንድ አገር አባል ሲሆኑ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በተናጠል የድርጅቱ አባላት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 አገሮችም በታዛቢነት ይጠባበቃሉ፡፡

የመልቲላተራልና የሁለትዮሽ ድርድር ለመጀመር በቅድሚያ ‹‹ገበያን ክፍት የማድረግ›› ወይም ‹‹የማርኬት አክሰስ ኦፈር›› መደራደርያ ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ይህ ሳይቀርብ መደራደር የማይቻል በመሆኑ ይህንን መደራደርያ እያዘጋጀን ነው ያሉት አቶ ገረመው፣ ከቴክኒካዊ ዝግጅቱ አኳያ መጠናቀቁን፣ በብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው በኩልና በመንገሥት በኩል ግን ገና መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገበያው መደራደርያ ተቀባይነት ሲያገኝ ብቻ ደግሞ የሁለትዮሹ ድርድር ይጀመራል፡፡

ገበያን ክፍት የማድረግ ድርድር እንዴት ያለ ነው? ለሚለው ‹‹ብዙዎች ፍራቻ ውስጥ የሚገቡት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ከሆነች ገበያዋን ልትከፍት ነው፣ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው ሊጎዳ ነው በማለት ነው፡፡ እንደኛ ላሉ በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ አገሮች ማርኬት አክሰስ ኦፈር ማለት፣ አሁን ከምናስከፍለው የገቢ ንግድ ታሪፍ ላይ ወደ ፊት አንድ ደረጃ እንደምንለውጠው ገልጸን የምንደራደርበት ነው፡፡››

በዚህ መልኩ የሚያብራሩት አቶ ገረመው በምሳሌም ይገልጹታል፤ ‹‹ለምሳሌ አንድ እስክሪብቶ ከውጭ ሲገባ ዛሬ ላይ ሃያ በመቶ ታሪፍ ይከፈልበት ከሆነ፣ ወደፊት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪው ይህንን ቢያመርት፣ እንዳይጎዳ ለመጠበቅ ሲባል እስከ 40 በመቶ ከፍ አደርገዋለሁ ብሎ መንግሥት ቢያስብ፣ ለዓለም ንግድ ድርጅት የሚሰጠው መረጃ፣ እስክሪብቶ አሁን አገሬ የሚገባው በሃያ ከመቶ ታሪፍ ነው፣ ወደፊት ግን እስከ አርባ ከመቶ ድረስ ከፍ አደርገዋለሁ ብሎ ያሳውቃል፤›› ያሉት አቶ ገረመው፣ አባል አገሮች እንደሁኔታው ሊያነሱት በሚችሉት የታሪፍ ይቀነስ ጥያቄ ላይ ድርድር እንደሚደረግበት አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ማርኬት አክሰስ ኦፈር ማለት ገበያን መክፈት ሳይሆን አሁን ያለንን የገቢ ንግድ ታሪፍ በአንድ ደረጃ ከፍ አድርገን ከዚያ በላይ ላለመጨመር ቃል የምንገባበት ነው በማለት ገበያ ክፍት ማድረግ ለሚመስላቸው፣ ‹‹ያ ማለት ግን በአጠቃላይ ገበያን ከፋፍቶ መተው ማለት አይደለም፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

የታቀደው በወረቀት ቀረ እንጂ መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን፣ የአውሮፓ ኅብረት የነፃ ገበያ ድርድርን፣ የኮሜሳን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ድርድሮችን እንደምትቋጭ ዘርዝሮ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የድርድር ሒደት በጀመረችበት ወቅት የዓለም ንግድ ድርጅት አባላት ብዛት 157 ነበሩ፡፡ ለቀረቡላት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት በጀመረችበት ወቅት አራት አገሮች ድርጅቱን ተቀላቅለዋል፡፡ በተለይም እንደ ሩስያ ያለ ትልልቅ ገበያዎችን የሚፈልግ አገር በዚያን ወቅት ድርጅቱን ተቀላልቅሎ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ወደ አባልነት ለመግባት ተደራዳሪ የነበሩ አገሮች ድርድራቸውን በቶሎ ቋጭተው አባል ከሆኑ በኋላ ሌሎች በአባልነት ሒደት ላይ የሚገኙትን በጥያቄ የሚያፋጥጡ አገሮች እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ይህንን የአገልግሎት ዘርፍ ለውድድር ክፈቱልኝ፣ ይህንን ታሪፍ ወይም ኮታ ቀንሱልኝ በማለት ስለሚጠይቁ፣ ኢትዮጵያ በድርድር ሒደት ላይ ጊዜ ባጠፋችና በቆየች ጊዜ ሌሎች አገሮች ወደ አባልነት ቀድመዋት እየገቡ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ፍላጎት በሚኖራቸው ጊዜ ሁሉ ለመደራደር ይዘውት የሚመጡት ቅድመ ሁኔታ እየተበራከተ ስለሚመጣ ሒደቱን ፈታኝ እንደሚያደርገው ምሁራን ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ለድርድር አስቸጋሪ የነበሩ የኢትዮጵያ አቋሞች በአሁኑ ወቅት በመለወጣቸው፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ የአባልነት ሒደቱ እንደሚቋጭ መንግሥት ያምናል፡፡ ይህም ሆኖ የአባልነት ሒደቱ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ዝግጅት የሚያሳይ እንጂ በተደራዳሪዎቹ በኩል የሚኖረው ሒደት አባልነቱን ሊያፋጥነውም ሊያዘገየውም እንደሚችል አቶ ምሥጋኑ (አምባሳደር) አስረግጠው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አራተኛው ዙር ድርድር የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝባት በስዊዘርላንድ ከተማ ጄኔቫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች