Friday, September 22, 2023

የአገር ውስጥ ደኅንነትና የውጭ ግንኙነት ንፅፅር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይቶች ዓውድ ውስጥ የማይታማውና የበርካታ ተዋናዮችን ቀልብ የሚስበው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በስኬታማነት ከሚነሱ መንግሥታዊ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የውጭ ግንኙነት፣ በፖለቲካዊ ፍላጎትና በሙያዊ ብቃት አስፈላጊነት የተወጠረበት ጊዜያት አሌ የሚባሉ ባይሆኑም፣ በዘርፉ የተመዘገቡ ድሎች አገሪቱ አሉኝ ከምትላቸው የተጠራቀሙ ወረቶች ቀዳሚውን ሥፍራ መያዝ የሚችል መሆኑ ይነገርለታል፡፡

በሰላም ማስከበር ከመካከለኛው አፍሪካ እስከ ኮሪያ የዘለቁ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ልምዶች በተለያዩ መድረኮች አገሪቱ ከምትሞገስባቸው ጉዳዮች መካከል ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫን አዲስ አበባ እንዲሆን ከማስቻል አንስቶ ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ትግል የወታደራዊ ሥልጠና ድጋፍ ማድረግ መቻሏ እውነትም በአፍሪካዊነት የምታምን አገር ናት ሊያስብላት የቻለ ድል እንደሆነም ብዙ ተብሎበታል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ጉዞዎች የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ስኬቶች እንዲመዘገቡ ያስቻሉ ባለሙያዎች የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት የፖለቲከ ጣልቃ ገብነትና ሥራውን ከባለሙያው ይልቅ ከፖለቲከኛው ጋር ማጣመር እየተያዘ በመምጣቱ ጉድለቶች መመዝገባቸውን በማንሳት የሚከራከሩም በርካቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት የሚመራበት ሁናቴ በደርግ ጊዜ የሕግ ቅርፅ ይዞ ለውስጥ አገልግሎት ብቻ እንዲውል በማድረግ ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ ሰነድ ተደርጎ የቆየ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ወዲህ የተቀረፀው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ከ17 ዓመታት በላይ ለሕዝብ ይፋ የሆነ ሰነድ ሆኖ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡

ለሁለት አሠርት ዓመታት ያገለገለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመሻሻል ላይ ነው፡፡ መንግሥት በእነዚህ ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በዓለም አቀፍ የኃይል አሠላለፍ ግንኙነቶች መለዋወጥ፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ሳቢያ እንዲሻሻል ማድረግ ማስፈለጉን በመጥቀስ እያሻሻለው ይገኛል፡፡

የፖለቲካውን መሻሻል ከግምት በማስገባት በርካታ ውይይቶች በጉዳይ ላዩ እየተደረጉ የሚገኝ ሲሆን፣ ከስድስት ተከታታይ የታቀዱ ውይይቶች አምስተኛው የሆነው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ኤፍኤስኤስ) ያዘጋጀውና በአዝማን ሆቴል ሐሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም. የተካሄደው መድረክ፣ ትኩረቱን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አድርጎ ነበረ፡፡

በመድረኩ የመጀመርያውን የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ተባባሪ ፕሮፌሰር አስናቀ ከፈለ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ከብዙ ሌሎች አዳጊ አገሮች በተለየ መልኩ የውጭ ፖሊሲ ባህል ያላት አገር ናት፤›› በማለት፣ የአገሪቱን የውጭ ግንኙነት አመጣጥ ገምግመዋል፡፡ ከእነዚህ የውጭ ጉዳይ ባህሎች መካከልም፣ ‹‹አንዱን ኃያል አገር በሌላው መመከት፣ የውጭ ወራሪ ሲመጣ በአንድነት መቆም፣ ዓለም አቀፍ ሕግና ተቋማትን ለውጭ ፖሊሲ ግብ መሳቢያ አድርጎ መጠቀም ሊጠቀስ ይገባል፤›› በማለት አውስተው፣ ከዚህ በተጓዳኝ ‹‹ለአገር ውስጥ የፖለቲካ ትግል የውጭ ኃይልን መጠቀም፣ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለው ባህል ሊጠቀስ ይገባል፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ሁለት መልክ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለችበትን የለውጥ ጉዞ አንስተው ለውጡ በርካታ ዕድሎችና ፈተናዎች ያቀፈ ነው በማለት የገለጹት አስናቀ (ዶ/ር)፣ እንደ ማንኛውም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሦስት ማጠንጠኛ ዓላማዎች እንዳሏቸው ያስረዳሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ወሳኝና ከአገር ህልውናና የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ጋር የተቆራኙ፣ በመካከለኛ ጊዜ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ዕድገቶች ጋር የተያያዙ ዓላማዎች እንዳሉ በመግለጽም፣ በረዥም ጊዜ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ከመመሥረት ጋር እንደሚያያዝ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በቀዳሚዎቹ ሁለት ዓላማዎች ላይ ያጠነጥናሉ ብለዋል፡፡

በእነዚህ ዓላማዎች ተመርቶ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስኬት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት፣ የመገንጠል መብት መፈቀድና ሥር የሰደደ ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነት የበላይነት ዕሳቤን በማምጣታቸው፣ ሳቢያ በውጭ ግንኙነቱ ላይ ፈተና ይደቅናሉ ይላሉ፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲ ቢፈቀድም በተግባር አምባገናዊነት በመኖሩ፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተደምሮ የውጭ ግንኙነት እንከን ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ የነበረው የፖለቲካ መረጋጋት ከኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር፣ አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ያለ ሚና መወጣት አስችሏት ነበርም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ቀንድ እጅግ የተሳሰረ ቀጣና ነው በማለት፣ ይኼ ትስስር ግን በልማትና በንግድ ሳይሆን የጦርነት መሆኑ፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ አፈጻጸም ከፍ ያለ አንድምታ እንዳለውም ይጠቀማሉ፡፡ ይኼም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚታየው የአገር ምሥረታ ግጭቶች አንፃር መታየት እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡

በዚሁ መድረክ ጽሑፍ ያቀረቡት ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰቡ አባል በመሆን እስከ አምባሳደርነት ያገለገሉትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ህሩይ አማኑኤል (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ በተለይ ከጎረቤት አገሮች አንፃር ስትታይ እነሱ ገና ሳሉ የኢትዮጵያ መሪዎች የውጭ ግንኙነት ያከናውኑ ነበር በማለት አስታውሰዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ መንግሥታት የመሪነት ዘመን የተለያዩ ድሎች መመዝገባቸውንም እንዲሁ፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደብ ባለቤት መሆኗና በኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ድርጅት እንዲቋቋም መደረጉ ስኬቶች ናቸው ያሉት ህሩይ (አምባሳደር)፣ ያኔ ግን ኢትዮጵያ ገለልተኛ የውጭ ግንኙነት ታካሂድ ነበር ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ በተለይ የአሜሪካ የጦር ሠፈር በኤርትራ እንዲቋቋም መወሰኑ፣ ኢትዮጵያን የቀድሞዋ የሶቪየት ኅብረት የጦርነት ዒላማ አድርጓት እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለነፃ አውጪ ታጋዮች ድጋፍ በመስጠት የሚታወቅ ነው በማለት፣ በኢሕዴግ ጊዜ ከአሜሪካና ከቻይና ጋር ግንኙነት የተጠናከረበት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሰላም ፍሬ ማፍራት በመጀመሩ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ መደረጉን፣ ከቱርክና ከህንድ ጋር በተፈጠረ ግንኙነትም የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እንዲጎለብት ተደርጓል ይላሉ፡፡

አሁን እየተረቀቀ ያለው አዲሱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰላም፣ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን ትኩረት ያደረገ እንደሆነና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ስደት፣ የሳይበር ደኅንነት፣ እንዲሁም የዜጎች ጥበቃ ላይ ትኩረት ቢያደርግም የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ሥጋቶች ያሉበት እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡

በአገሪቱ የሚታየው የደኅንነት ማጣትና ግጭት (ብጥብጥ)፣ የብሔርና የሃይማኖት አክራሪነት፣ ድህነትና የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ የባህር በር አለመኖር፣ እንዲሁም በአገራዊ አንድነት ረገድ ያሉ ጉድለቶችን እንደ ሥጋት በማንሳት የህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያሉ ፍላጎቶችና ያልተከለሉ ድንበሮችም ራሳቸውን የቻሉ ሥጋቶች እንደሚደቅኑ አመላክተዋል፡፡

እነዚህ ሥጋቶች ባሉበት ሁኔታ የሚከናወን የውጭ ግንኙነት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የምትተገብረው በፈጻሚው ተቋም የጎረቤት አገሮች ቋንቋ እምብዛም ዕውቀት አለመኖሩ፣ በድንበር አካባቢ ያሉትን አቅሞች እንደ ሀብት ወስዶ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ላይ አለማተኮር የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉድለቶች እንዲሆኑም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት አስናቀ (ዶ/ር)፣ ከኤርትራ ጋር የተፈጸመው ዕርቅ መልካም ነው ቢሉም የድንበሩ ሁኔታ አለመቋጨቱን፣ ኤርትራ በቀጣናው ምን ዓይነት ሚና መጫወት እንደምትፈልግ ግልጽ አለመሆኑ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነና ኤርትራን የሚያሳትፍ ይሁን አይሁን፣ የኢትዮጵያ ውስጣዊ አለመረጋጋት እንዴት የሁለቱን ግንኙነት እንደሚወስን፣ እንዲሁም የንግድ፣ የወደብና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ማዕቀፍ በምን ሁኔታ እንደሚዘጋጅ ግልጽ አለመሆናቸውን በመጥቀስ ይኼ በብልኃት ካልሆነ ወደ ግጭት አዙሪት ሊከት የሚችል እንደሆነ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት የተወሳሰበ እንደሆነ ያወሱት አስናቀ (ዶ/ር) ያልተፈታ የድንበር ጉዳይ መኖሩ፣ እንዲሁም ሱዳን በዓባይ ውኃ ላይ ያላት አቋም ምን እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁን በመጠቆም በተለይ የድንበሩ ጉዳይ የግጭት መንስዔ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ አክለውም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በእጅጉ የሚዋልል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት የጦርነት ጠባሳ ያለበት በመሆኑ በተለይ ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ ወደብ ድርሻ መግዛቷ የቅራኔ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል ዕሳቤ የማይገባትን ጥቅም ለማግኘት እየጠየቀች ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ ውጪ ግን፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና በፖለቲካ ኃይሎችና ክልሎች መካከል ያለው ሽኩቻ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ግንኙነት ላይ ከፍ ያለ ጎጂ አንድምታ አለው፤›› ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

በውይይቱ አስተያየታቸውን የለገሱት የቀድሞ የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አምባሳደርና የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል ሙሉጌታ አሰፋ (አምባሳደር)፣ ‹‹የአገራችን ደኅነነት ካልተረጋጋ ለአካባቢው ሥጋት ነው፤›› በማለት፣ ይኼ ሥጋት ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ አገሮችም ጭምር ነው ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይኼ ሥጋት በዋናነኛነት የኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሔር ማንነትን ማስታረቅ ላይ ባለው ጉድለት ሳቢያ የመጣ እንደሆነ የሚገልጹት ሙሉጌታ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያዊ የሚባል የአንድ ቡድን ማንነት ባለመኖሩ ብሔርና ኢትዮጵያዊ ማንነት ስለማይጋጭ ይኼንን በቅንነት በማስተማር መፍትሔ መሻት ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም ዘረኝነት በኢትዮጵያ እንደሌለና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጥቁር ዘር ነው ብለው በመከራከር፣ ‹‹ይኼንን መፍታት ከቻልን ነው ወደፊት መሄድ የሚያቻችለን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -