በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች በተቀራራቢ ሰዓት ግድያ በተፈጸመባቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣት ጋር በተያያዘ፣ በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት አራት ወራት በእስር ላይ የቆዩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራሮችና አባላት በዋስ ተፈቱ፡፡
ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ከእስር ከተፈቱት ውስጥ የባልደራሱ አመራሮችና አባላት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አቶ መርከቡ ኃይሌና አቶ አዳሙ ውጅራ በመታወቂያ ዋስ ከፖሊስ ጣቢያ ተለቀዋል፡፡ አብረዋቸው በእስር ላይ የቆዩት የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አስፋ፣ የኢቶጲስ ጋዜጣ ዘጋቢ ጋዜጠኛ ምሥጋናው ጌታቸውና የአሥራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጌታቸው አምባቸውም በመታወቂያ ዋስ ተለቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችም፣ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ የአብን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አንተነህ ስለሺና የየካ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ይልቃል እያንዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
የአብን የቦሌ ክፍለ ከተማ ሰብሳቢ አቶ ዮናስ አሰፋ፣ የኮልፌ ክፍለ ከተማ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሽገዛ ሙሉጌታና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ በዕውቀቱ በላቸው፣ እያዳንዳቸው በ7,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በአብን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በለጠ ካሳ ላይ ዓቃቤ ሕግ በአምስት ቀናት ውስጥ ክስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡